የኔዲ ታሪክ፡ የማህበረሰብ እንስሣት ጤና ባለሙያው የአንድ መንደር ነዋሪዎች የኒውካስል በሽታን መቆጣጠር እንዲችሉ ረዳ

የእንስሳት እርባታ እና ንብ ማነብ

Notes to broadcasters

Save and edit this resource as a Word document.

Save and edit this resource in Oromo.

Save and edit this resource in Sidama.

ማስታወሻ ለአዘጋጁ
ዶሮዎች ያገኙትን ምግብ ጭረው ሰለሚመገቡ ለማሳደግ ቀላል የሆኑ የቁም እንሥሣት ናቸው፡፡በተጨማሪም ዶሮዎቸ በቀላሉ ይራባሉ፡፡ ነገር ግን ኒውካስል በተባለ መድሃኒት በሌለው ዋነኛ በሽታ በቀላሉ ይጠቃሉ፡፡ በሽታው ፈዋሽ መድሃኒት ባይኖረውም ክትባት ግን አለው፡፡ አርሶ አደሮች ከእውቀት ማነስ ወይም ክትባቱ ውድ ስለሆነ ዶሮዎቻቸውን በየጊዜው አያስከትቡም፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ክትባቱ ለብዙ መቶ ዶሮዎች በሚበቃ ትልቅ ጠርሙስ ይሸጣል፡፡ ጥቂት ዶሮዎች ብቻ ላሏቸው አርሶአደሮች በጣም ውድ ነው፡፡ ስለዚህ በማህበረሰብ የጤና ባለሙያ በመጠቀም የማህበረሰቡን ዶሮዎች አንድ ላይ እንዲከተቡ ማድረግ ጥሩ ሃሳብ ነው፡፡

በብዙ አካባቢዎች የእንስሣት ሃኪም እጥረት አለ፡፡ የእንስሣት ሃኪም በሌለበት አካባቢ ረዳት ሃኪሞች፣ የማህብረሰብ እንስሣት ጤና ሃኪሞች ወይም በጎ ፈቃደኛ ሃኪሞች እገዛ ያደርጋሉ፡፡ እነዚህ ደሞዝ የማይከፈላቸው ነገር ግን ለልፋታቸው መጠነኛ ሂሳብ በማስከፈል አገልግሎት የሚሰጡ በጎ ፈቃደኞች ናቸው፡፡ ብዙ የእንስሣት በሽታዎችን ለይተው እንዲያክሙ እና ሌሎች በሽታዎችን ለሃኪም እንዲልኩ ስልጠና ይሰጣቸዋል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ አርሶ አደሮቸ መድሃኒት እራሳቸው ገዝተው ለማህብረሰብ ጤና ባለሙያው ደርሶ መልስ ትራንስፖርት ያቀርባሉ፡፡

በዚህ ጽሁፍ ውስጥ የማህበረሰብ ጤና ባለሙያው መንደርተኞቹን የኒውካስል በሽታ መድሃኒት 300 ወይም ከዚያ በላይ ዶሮዎችን ማስተናገድ በሚችል መጠን ብቻ እንዳለ ይነግራቸዋል፡፡ ባንዳንድ የአፍሪካ ሃገሮች አነስተኛ መጠን ያላቸው ክትባቶች ሊገዙ ይችላሉ፡፡ እንደ ዛምቢያ፣ ሞዛምቢክ እና ጋና በመሳሰሉ ሃገሮች ደግሞ ማቀዝቀዣ የማያስፈልጋቸው ክትባቶች ገበያ ላይ አሉ፡፡ በሃገራችሁ ያለውን ሁኔታ ለማወቅ ጥናት አድርጉ፡፡

Script

ተራኪ:
ማላዊን ጨምሮ በብዙ የአፍሪካ ሃገሮች አብዛኛዎቹ አርሶ አደሮች ቢያንስ አንድ ዶሮ አላቸው፡፡ እነዚህ ዶሮዎች ጭረው የሚበሉ የአካባቢው ዝርያዎች ናቸው፡፡ የኒውካስል በሽታ ወረርሽኝ ቢፈጠር እነዚህ ዶሮዎች በቀላሉ ያልቃሉ፡፡ ኒውካስልን በክትባት መከላከል ይቻላል፡፡ ታዲያ ለምንድን ነው ብዙ አርሶ አደሮች ለዶሮዎቻቸው ክትባት የማይገዙተ ለምንድን ነው? አብራችሁን ቆዩና መረጃ ታገኛላችሁ፡፡
የድምጽ ኢፌክት፦
ብረት በትንሽ መዶሻ ሲመታ ድምጽ
ሚስት:
ባለቤቴ ኔዲ ለምንድን ነው አሁን ሳይክልህን የምትጠግነው? የት መሄድ ፈልገህ ነው?
ኔዲ፦
ዛሬ የትም አልሄድም ሚስቴ። ለነገ እየተዘጋጀሁ ነው፡፡ በጋው ወቅት እየመጣ እንደሆነ ታውቂያልሽ።
ሚስት:
(ፈገግ ብላ) ደሞ ሌላ ላም የታመመች መስሎኝ ነው። የማህበረሰብ የእንስሣ ጤና ሰራተኛ ከሆንክ ወዲህ ሁል ጊዜ እንደሄድክ ነው።
ኔዲ:
እንዴት ነው አሁን ደስተኛ ነሽ ሚስቴ?
ሚስት:
በጣም። እንዴት አልደሰትም?
ኔዲ:
የማህበረሰብ የእንስሣ ጤና ሰራተኛ መሆን ማለት እንደዚያ ነው። ገቢያችንንስ ከሱ አይደለም የምናገኘው?
ሚስት:
አውቃለሁ። ቢሆንም ሰዎች ትንሽ ፋታ ሊስጡህ ይገባል። ያለማቋረጥ ነው እኮ የሚጠሩህ። እኩለ ሌሊት ሳይቀር! ና እዚህ! ይቺ ላም እንደዚህ አደረገች፣ ያቺ አሳማ ይሄ ችግር አለባት … ምንም ማረፊያ ጊዜ የለም።
ኔዲ:
ያን ያክል ትጨነቂልኛለሽ ማለት ነው?
ሚስት:
አዎ ውዴ።

ሁለቱም ይስቃሉ።.

ሚስት:
ግን ኔዲ፣ በጋ እየመጣ ነው እያልክ ነበር። በጋ ቢደርስ አንተ ነገ ወደ ከተማ ከመሄድህ ጋር ምን ያገናኘዋል?
ኔዲ:
ያው በጋ ደረቅ መሆኑን ታውቂያልሽ። በክረምት ያራባናቸውን ዶሮዎች በጋ ላይ እንደሆነ ታውቂያልሽ ኒውካስል በሽታ መጥቶ የሚጠራርግብን?
ሚስት:
አዎ አውቃለሁ።
ኔዲ:
አሁን ኒውካስል በሽታ ሳይመጣ ዶሮዎቻችንን ለመከተብ ጥሩ ጊዜ ነው። እዚህ መንደር እና በዙረያው ያሉት ዶሮዎች ከተከተቡ ሶስት ወር አልፏቸዋል።
ሚስት:
እና ለዶሮዎቻችን ክትባት መግዛት ትፈልጋለህ?
ኔዲ:
አይ ለኛ ዶሮዎች ብቻ አይደለም …
ሚስት:
(በቁጣ ታቋርጠዋለች) እና ለማን? ከዚህ በፊት እንደተዋረድከው አሁንም መዋረድ ትፈልጋለህ? የሰፈሩ ሰው ገንዘባቸውን ለመብላት ብለህ ዶሮ እንደምትከትብ የተናገሩትን ረሳኸው?
ኔዲ:
በሚገባ ትዝ ይለኛል ግን አየሽ …
ሚስት:
(ታቋርጠዋለች) ምንድን ነው የማየው? በቃህ አትከራከር። ነገ ገበያ ስትሄድ ለራሳችን አስር ዶሮዎች ብቻ የሚበቃ ክትባት ግዛ። አለቀ!
ኔዲ:
አይሆንም። ለአስር ዶሮ ብቻ የሚሆን ብልቃጥ የለም። ለአንድ ሺ ዶሮ የሚሆን ነው ያለው እሱንም አንድ ሱቅ 50 ብር ነው የሚሽጠው። ለ300 ዶሮዎች የሚሆነውን ደሞ ሌላ ሱቅ 30 ብር ይሸጠዋል። ስለዚህ …
ሚስት:
(ታቋርጠዋለች) በቃ ለ300 የሚሆነውን ገዝተህ ለአስሩ ተጠቅመህ ቀሪውን ትጥለዋለህ።
ኔዲ:
እንደዚያማ ገንዘብ እንከስራለን። ላንድ ዶሮ 50 ሳንቲም መክፈል ስንችል 3 ብር ልንከፍል ማለት ነው።
ሚስት:
ሰው የሚያወራው ውነቱን ነዋ – ለገንዘብ ብለህ ነው የምታደርገው ማለት ነው?
ኔዲ:
ሚስቴ መጀመርያም የእንስሣት ህክምና ክሂሎት ለመማር ለምን እንደፈለኩ አስታውሺ። እዚህ መንደር ውስጥ ያለውን የእንስሣት በሽታ ለማጥፋት አልነበረም? ህልማችን መንደራችንን መከላከል ከምንችላቸው የቁም እንስሣት በሽታዎችና ችግሮች ለማዳን መስሎኝ ነበር?
ሚስት:
ልክ ነሕ። እሺ ለዚህ ምክንያት እንዳቀድከው እንድታደርግ ፈቅጄልሃልሁ።
ኔዲ:
እሰይ የኔ ሚስት እንዲህ ነው።

ሁለቱም ይስቃሉ።

ትይንት ይቀየራል። ሙዚቃ ይመጣል፣ ከዚያ ቀስ ብሎ ይቀጥላል።

ተራኪ:
ኔዲ ለጥቂት ዶሮዎቸ ብሎ አንድ ትልቅ ጠርሙስ ክትባት መግዛት ገንዘብ መክሰር እንደሆነ ያውቀዋል። ዶሮዎቻችሁን ለማስከተብ ጎረቤቶቻችሁን ለማሳተፍ ሞክራችሁ ታውቃላችሁ? ውስብስብ ነው! መንደርተኛውን ሁሉስ በትንሽ ገንዘብ ማሳተፍ? ኒውካስል በሽታን ለመከላከል ማህበረሰቡን ሁሉ ለማሳተፍ ሞክራችሁ ታውቃላችሁ?

የትእይንት ሙዚቃ ድምጹ ይጨምርና ቀንሶ ከጀርባ ይቀጥላል።

ተራኪ:
ኔዲ ከሶስት ወራት በፊት ዶሮዎችን ካስከተባቸው በኋላ የኒውካስል በሽታ ወሬ ባላስከተቡት መንደሮች እንኳን ሳይቀር ወሬው እንደሌለ ያውቃል። አሁንስ የመንደሩ ሰዎች ዶሮዎቻቸውን እንዲከትብላቸው ይፈቅዱለት ይሆን? ሰዎቹ ወደ መንደሩ አለቃ ችሎት ተጠርተው የተጠሩበትን ምክንያት ለመስማት እየተጠባበቁ ነው።
የድምጽ ኢፌክት:
ከመንደር አለቃው ችሎት ውስጥ የተሰበሰበው ሰው ድምጽ
የመንደር አለቃው:
ሰዎች። ጸጥታ እባካችሁ። ጸጠታ እባካችሁ።
ምዋሌ:
(ሰክሯል። ቀስ ብሎ እየዘፈነ እና እየደነሰ ወደ ችሎቱ ድምጽ ማጉያ ይጥጋል።) አዮ! አዮ! አዮ! ሙሉ ብርጭቆ ቢራ ስጡ!
የድምጽ ኢፌክት:
ሰዎች ይስቃሉ
ሚስት:
(በሹክሹክታ) ወንድሜ ምዋሌ ያሳፍረኛል። ሁሌ እንደሰከረ! ሚስቱን ከዚህ በላይ እንዴት ያሳፍራት?
ወይዘሮ ክዌንዳ:
አዎ ያንቺ ወንድም ሁልጊዜ እንደሰከረ ነው። ግን ደሞ ወንድምሽ ጠንካራ ሰራተኛ ነው። የሚጠጣውን አልኮል ቢቀንስ ሃብታም ይሆን ነበር።
ሚስት:
ልክ ነሽ።
የመንደሩ አለቃ:
አቶ ምዋሌ! አቶ ምዋሌ!
ምዋሌ:
አለቃ!
የመንደሩ አለቃ:
ጸጥታ ብያለሁ!
ምዋሌ:
(በለሆሳሰ) እሺ አለቃ። ከአማቼ ኔዲ አጠገብ እቀመጣለሁ። መጀመርያ ግን ለምን እንደጠራኸን ንገረን። ወደ ቤት መሄድ እንፈልጋለን። ሌላ ጠቃሚ ስራ አለን። እንጠጣለን።

አንዳንድ ሰዎች ይስቃሉ። አንዳንዶች በድጋፍ አንዳንዶች በመቃወም ያጉረመርማሉ።

የመንደሩ አለቃ:
ምዋሌ! ጸጥታ። በኔ ችሎት ከረበሽክ ቅጣት ትከፍላለህ።
ምዋሌ:
ይቅርታ አለቃ። ይቅርታ አለቃ።
የመንደሩ አለቃ:
(በእፎይታ ይተነፍስና ራሱን ይቀይራል።) ይህ ስብሰባ የተጠራው የራሳችን ልጅ በሆነው በአስማት እጁ በሰው ሰራሽ መንገድ እያዳቀለ ግሩም የሆኑ የወተት ላም ዲቃላዎች እንዲኖሩን ባደረገልን በአካባቢያችን የእንስሣት ጤና በጎ ፍቃድ ሰራተኛ ነው። መድረኩን ለኔዲ እለቃለሁ።
ህዝቡ:
(እየጮሁ እና እያፏጩ) ኔዲ! ኔዲ!
ኔዲ:
(ሰዉ እየተንጫጫ እያለ ይናገራል) አለቃ ስላከበሩኝ አመሰግናለሁ።
ምዋሌ:
ቀጥታ ወደጉዳዩ ግባ እዚህ እንዳትጎልተን።
ወይዘሮ ክዌንዳ:
(ድምጿን ከፍ አድርጋ) ጸጠታ! ጸጥታ! (ሁሉም ጸጥ ይላል) የማህበረሰባችን እንስሣ ጤና ሰራተኛ ለምን እንደጠራን እንስማ። (ጸጥታ)
ኔዲ:
(ጉሮሮዉን እየጠረገ።) እንደምታውቁት ዶሮዎቻችንን ካስከተብን ሶስት ወር አልፎናል። አደገኛው በጋ እየደረሰ ነው፣ ኒወካስል በሽታ ዶሮዎቻችንን እንደገና ሊያጠቃ ይችላል።
ሁሉም:
አዎ።
ኔዲ:
አሁን ዶሮዎቻችንን ድጋሚ ማስከተብ አለብን።
አቶ ክዌንዳ:
ዶሮዎቻችንን መቼ ነው እንደገና መከተብ የምትፈልገው?
ኔዲ:
ዛሬ ቅዳሜ ነው። ገንዘብ ለመሰብሰብ ጊዜ እንዲኖርህ መቼ ብናደርገው ይሻላል አቶ ክዌንዳ?
አቶ ክዌንዳ:
በሚቀጥለው ሳምንት ማክሰኞ ጥዋት።
ኔዲ:
ሁላችሁም ትስማማላችሁ? በሚቀጥለው ማክሰኞ!
ሁሉም:
አዎ።
ኔዲ:
ማክሰኞ ዶሮዎቻችሁ ሳይከተቡ እንዳትለቋቸው።
ሁሉም:
እሺ።
ምዋሌ:
አሁን ደሞ ለአንድ ዶሮ ስንት ልታስከፍለን ነው?
ኔዲ:
እዚህ ሰፈር ብዙ ሰዎች ዶሮ ስላላቸው እናንተን ህዝቦቼን ለማገልገል ስል ሂሳቡን ለእያንዳንዱ ከ50 ሳንቲም ወደ 25 ሳንቲም ቀንሼዋለሁ። 50% ቅናሽ ማለት ነው።
የድምጽ ኢፌክት፡
(ሁሉም ሰው በደስታ ይጮሃል) ኔዲ! ኔዲ!
ምዋሌ፡
(ይቃወማል) ውድ ነው፣ በጣም ውድ ነው።
ኔዲ:
25 ሳንቲም እርካሽ ነው። ለቢራ ስንት ታወጣለህ? በሌሎች ሰፈሮች ለአንድ ዶሮ 50 ሳንቲም ነው።
ወይዘሮ ክዌንዳ፡
አንተ ለምን የተለየ ታስከፍላለሁ? ለዚያ ሁሉ ዶሮ ለምን ዝቅተኛ ታስከፍላለህ?
ኔዲ:
አመሰግናለሁ ለጥያቄሽ ወይዘሮ ክዌንዳ። ክትባቱን ከኪሴ ገዝቼ ገንዘቤን እና ላቤን ብቻ ለመተካት የሚበቃ ሂሳብ እንደማስከፍላችሁ ስነግርሽ ትዝ ይልሻል? የሚከተቡት ዶሮዎች ጥቂት ከሆኑ ያወጣሁትን መልሼ ለማግኘት ዋጋውን ከፍ ማድረግ አለብኝ።
ምዋሌ፡
ውሽትህን ነው። ቀሪውን መዳኒት አስቀምጠህ ለሌላ መንደር አትጠቀምበትም?
ኔዲ:
አልችልም! አንዴ ጠርሙሱ ከተከፈተ በኋላ ከሁለት እስከ አራት ሰአት ውስጥ ተጠቅሜ መጨረስ አለብኝ አለበለዚያ ተበላሽቶ ከጥቅም ውጭ ይሆናል።
ምዋሌ፡
ወደኔ ቤት እንዳትመጣ።
ኔዲ:
ሁልጊዜ እንደነገርኳችሁ ገንዘቡ ካላችሁ ለ300 ዶሮ የሚሆን መዳኒት በውድ ዋጋ መግዛት ትችላላችሁ። እንደ አቶ ምዋሌ – እሱ ለራሱ መግዛት ያሰበ ይመስለኛል።
ወይዘሮ ክዌንዳ፡
ተረድተንሃል። ማክሰኞ ና፣ ክትባት የማይፈልጉትን ተዋቸው። እኛ ጥቂት ዶሮዎች አሉን። አምሳ ሳንቲም መክፈል እየቻልን ለምን ያን ሁሉ ብር እንከፍላለን?
ኔዲ:
ሰለዚህ ሁላችሁም ማክሰኞ እንገናኝ።
ሁኡም፡
አዎ።
ምዋሌ:
አማቼ ኔዲ ቤቴ እንዳትምጣ ብየሃለሁ። ውሻ ነው የምለቅብህ።
የመንደር አለቃ:
(እየጮኸ) ወደቤታችሁ መሄድ ትችላላችሁ። ማክሰኞ ጠዋት ግን እንዳትረሱ። ለአንድ ዶሮ 25 ሳንቲም።
ሁሉም:
(ከማይክሮፎን እየራቀ) አዎ።
ምዋሌ:
ኔዲ፣ ኔዲ ወደ ቤቴ እንዳትመጣ። እደግመዋልሁ። ወደኔ ቤት እንዳትመጣ።
ኔዲ:
እስኪ አታሳፍረኝ አቶ ምዋሌ። እየሄድን እናውራ እስኪ። (ወደ መንደሩ አለቃ) አመሰግናለሁ፣ አለቃ። ማክሰኞ ጠዋት አገኝሃለሁ።
የመንደሩ አለቃ፡
(ከማይክሮፎን እየራቀ) የኔን ዶሮዎች እንዳትረሳ፣ ኔዲ። ስብሰባ ስላለኝ ቤት አልኖርም ግን እንዳትቀር። ሁሉም ነገር ተስተካክሎ ታገኘዋለሕ። ያጎትህ ልጆች እና እናታቸው ይረዱሃል።
ኔዲ:
አታስብ አለቃ። እኔ አለሁ። (ጸጥታ፣ ከዚያ ለምዋሌ) አንተስ ምዋሌ። አማቼ ሁል ጊዜ የምታስቸግረኝ ሰው የሆንክ ለምንድን ነው?
ምዋሌ፡
አንተ ታጭበረብረናለሕ?
ኔዲ፡
እንደሱ ነው የምታስበው?? ክትባት ከተጀመረ በኋላ እዚህ ሰፈር የኒውካስል በሽታ አይተህ ታውቃለህ?
ምዋሌ:
ላለፉት ስምንት ወራት ቢራ ልጠጣ የሄድኩባቸው መንደሮች ሁሉ ውስጥም አላየሁም። ዶሮዋቻቸውን እንዳትከትባቸው የከለከሉህ መንደሮችም ውስጥ አላየሁም።
ኔዲ፡
አሁን ግን እንድከትብላቸው ጠይቀውልኛል።
ምዋሌ:
(እየሳቀ) ሃሃሃሃ! አማቼ እነሱንም አታለልካቸው?
ኔዲ፡
ምዋሌ እባክህ አዳምጠኝ። በጋው እየቀረበ ስለሆነ ዶሮዎቻችንን ለመከተብ አሁን ጥሩ ጊዜ ነው።
ምዋሌ፡
በገንዘባቸው የሚያደርጉበት የተሻለ ነገር የሌላቸውን ሰዎች አታልል። እኔን አትችልም።
ኔዲ:
(በንዴት እና በስልችት) እሺ! ሰዉ ሁሉ ደንቆሮ አንተ ግን ብልጥ የሆንክ ይመስልሃል? ተስማምቻለሁ! አንተ ቤት ዶሮ ለመከተብ አልመጣም። ደና ሁን።
ምዋሌ:
(ከማይክሮፎን እየራቀ) አሁን አማቼ እየተናገረ ነው። እባክህ እንዳትመጣ ኔዲ።
ሙዚቃ። ድምጹ ቀንሶ ይቀጥላል።
ተራኪ:
ማከሰኞ ደረሰ። የምዋሌ ዶሮዎች ሲቀሩ ኔዲ የሁሉንም ሰው ዶሮዎች ከተበ። አቅራቢያ መንደሮች ውስጥ ያሉ አንዳንድ ሰዎችም ዶሯቸውን እንዲከትብላቸው ፈቀዱለት፣ አንዳንዶች ግን አልፈቀዱም። የኒውካስል በሽታ ወሬ ሳይሰማ አንድ ወር አለፈ። ዶሮዋቸውን ያላስከተቡ ሰዎች ልክ ነበሩ ማለት ነው?

ሙዚቃ። የድምጽ ኢፌክት ሲገባ ሙዚቃው ይቀንሳል።

የድምጽ ኢፌክት:
የአውራ ዶሮ ጩኸት በማለዳ።
የድምጽ ኢፌክት:
ከባድ የበር ማንኳኳት። ድምጹ ቀንሶ ማንኳኳቱ ይቀጥላል።
ሚስት፡
(ባሏን እየቀሰቀሰች) ኔዲ! ኔዲ! ተነስ። በር የሚያንኳኳ ሰው አለ።
ኔዲ:
(ተነስቶ እየጮኸ) ማነው በሌሊት የመጣ?
ምዋሌ:
እኔ ነኝ አማችህ። ክፈት እባክህ። (የታመመች ዶሮ ድምጽ)
ኔዲ:
ምን ፈለክ ዶሮ ይዘህ የመጣህ?
ሚስት:
ኔዲ ዝምብለህ ተነስ። ወንድሜ እንደሆን አትሰማም? (ለምዋሌ) ቆይ ወንድሜ፣ እየመጣ ነው።

በር ሲከፈትና ሲዘጋ።

ኔዲ:
(በንዴት) የታመሙ ዶሮዎችህን ይዘህ በሌሊት ቤቴ ምን ትሰራለህ? ዶሮዎቼን መበከል ትፈልጋለህ?
ምዋሌ:
ወይ አማቼ ድምጻቸውን ብቻ ሰምተህ መታመማቸውን አወክ?
ኔዲ:
አረንጓዴ ቢጫ የሆነ ተቅማጣቸውን ታያለህ? ጭንቅላታቸውም አብጧል። ኒውካስል በሽታ ይዟቸዋል።
ምዋሌ:
እየሞቱ ነው። አማቼ እባክህ እርዳኝ። መዳኒት ስጣቸው።
ኔዲ፡
ምን?
ምዋሌ:
ኔዲ ይቅርታ ዶሮዎቼ ሁሉም ታመዋል፣ እየሞቱ ነው።
ኔዲ:
እኔም ይቅርታ። ልረዳህ አልችልም።
ምዋሌ:
(በሚያባብል ድምጽ) ለምን ወንድሜ ለምን…?
ኔዲ:
በሰፈሩ ሰው ሁሉ ፊት እንዴት እንዳሳፈርከኝ ረሳኸው?
ምዋሌ:
(ተንበርክኮ እየለመነ) ይቅርታ አርግልኝ፣ ይቅርታ አርግልኝ አባቴ (የኤዲተሩ ማስታወሻ፡ ምዋሌ ኔዲን አባቴ እያለ በማክበር የፈለገውን ለማግኘት እየሞከረ ነው) እህቴ እርጅኝ። ባልሽን እንደተጸጸትኩ ንገሪው። ልንበርከክ?
ኔዲ:
ተነስ! ተነስ! አትንበርከክ። ልረዳህ አልችልም።
ምዋሊ፡
(ሊያለቅስ እያለ) አይቻልም? ኔዲ እባክህ እርዳኝ። ያለኝ ሰራ ይሄ ብቻ ነው። እባክህ እርዳኝ።
ኔዲ:
ዶሮዎችን እየከተብኩ የነበርኩ ጊዜ ለምን እንደዚህ አላሰብክም?
ምዋሌ:
ምን እንደጋረደብኝ አላውቅም።
ኔዲ:
(በሃዘን ይስቃል) ዉነቴን ነው ምዋሌ ኒውካስል በሽታ መድሃኒት ቢኖረው ኖሮ እረዳህ ነበር። ነገር ግን መድሃኒት የለውም፣ ክትባት ብቻ ነው ያለው።
ምዋሌ:
በቃ ከትብልኛ።
ኔዲ:
አሁንማ አይሆንም። ማቀዝቀዣ ቤቴ ስለሌለኝ ክትባት አላስቀምጥም።
ምዋሌ:
ውሸትህን ነው። ማቀዝቀዣ እንደሌለህ እናውቃለን። ለሌሎች ሰዎች የሰጠኸውን ክትባት እንዴት ነው ያስቀመጥከው?
ኔዲ:
ከክትባቱ ቀን በፊት አሰቀድሜ እንደምመዘግብ ታስታውሳለህ?
ምዋሌ:
አዎ፣ ለምን?
ኔዲ:
ክትባቱን ከክትባቱ ቀን አንድ ቀን አስቀድሜ ነው የምቀበለው። በረዶ የሚይዝ ማቀዝቀዣ ሳጥን እዋሳለሁ።
ምዋሌ:
ክትባቱን ለምን ቀዝቃዛ ቦታ ውስጥ ታስቀምታለህ?
ኔዲ፡
ሞቃት ቦታ ላይ ካስቀመጥከው ይበላሻል። ስለዚህ የተረፈውን በሙሉ እንጥለዋለን።
ምዋሌ፡
በከባድ ሁኔታ ተምሪያለሁ። ሁለተኛ አይለመደኝም።
ኔዲ፡
ባትደግመው ነው የሚሻልህ አማቼ።
ምዋሌ፡
ከዚህ በኋላ ዶሮዎቼን ወቅቱ ሆነም አልሆነም ሁል ጊዜ አስከትባለሁ።
ኔዲ፡
ጎሽ የኔ አማች። አዲስ ዶሮዎች ለመግዛት የምታወጣውን ወጭ አስብ።
ምዋሌ፡
ልክ ነህ። ሌሎች ዶሮዎች ለመግዛት ገንዘብ ለማውጣት እገደዳለሁ።
ኔዲ:
እሺ የክትባት ጥቅም ከገባህ ለክትባት ልታወጣው የነበረውን 40 ብር ስጥኝና ሶስት ስድስት ሳምንት የሞላቸው የሚኮሎንግዌ ጫጩቶች እሰጥሃለሁ። (የኤዲተሩ ማስታወሻ፡ ይህ ዝርያ በሌላ ስሙ ጥቁር አውስትራሎርፕ ይባላል። ጥሩ የእንቁላል እና ስጋ ምርት ሲኖረው ከመጤ ዝርያዎች በላይ በሽታ ይቋቋማል። የራዲዮ ጋዜጠኞች እነዚህ ተመሳሳይ ባህሪዎች ያሏቸው ሌሎች ዝርያዎችን መጠቀም ይችላሉ።)
ምዋሌ፡
የእነዚያ ትላልቅ ዲቃላ አውራ ዶሮዎችህ ልጆች?
ኔዲ፡
አዎ።
ምዋሌ፡
አመሰግንሃለሁ። አሁን ግን ገንዘብ የለኝም። የሰው እርሻ ላይ ተቀጥሬ እሰራለሁ። እነዚያን ጫጩቶቸ እስክገዛ ድረስ ቢራ መጠጣት አቆማለሁ።
ኔዲ፡
(እየሳቀ) ሃሃ! አማቼ እነዚያንም ጫጩቶ እንዳትገላቸው።
ምዋሌ፡
(ከማይክ እየራቀ) አውቃለሁ። የኔ መልካም አማቼ እንደገና አልገላቸውም። ስለመልካም ባህሪህ ናና ሁለተኛ እህቴን አግባ። (የኤዲተሩ ማስታወሻ፡ ይሄ ቀልድ ነው። በቀድሞ ጊዜ ማላዊ ውስጥ ሰዎች አማቾቻቸው መልካም ባህሪ ካሳዩ ሁለተኛ ሴት ልጆቻቸውን ይድሩላቸው ነበር። አሁን ግን ሰዎች በዚህ ያለፈ ልማድ ይቀልዳሉ።)
ኔዲ:
(እየሳቀ) ሃሃ!
ተራኪ፡
የማህበረሰብ እንስሣ ጤና ሰራተኛውን የኔዲን ታሪከ ስታዳምጡ ቆይታችኋል። ያሏችሁ ዶሮዎች ጥቂት ከሆኑ ከጓደኞቻችሁ ጋር በመተጋገዝ የኒውካስል በሽታ ክትባት ወጭን መጋራት እንድምትችሉ አስታውሱ። ሌላው ማስታወስ ያለባችሁ ነገር ደግሞ ክትባቱ ማቀዝቀዣ ውስጥ መቀመጥ እንዳለበት ነው። ጠርሙሱ አንዴ ከተከፈተ በኋላ ለሌላ ቀን ልትጠቀሙበት አትችሉም። በመጨረሻም ኒውካስል በሽታ መድሃኒት እንደሌለው አስታውሱ። ዶሮዎቹን ማስከትብ የምትችሉት በበሽታው ከመያዛቸው በፊት ብቻ ነው።

ይህን ፕሮግራም ባዘጋጀው ዘ ስቶሪ ወርክሾፕ ስም እኔ ግላድሰን ማኮዋ ነኝ። በሚቀጥለው ሳምንት በተመሳሳይ ሰኣት እንገናኝ።

Acknowledgements

ምስጋና
የጽሁፉ አዘጋጅ፦ ግላድሰን ማኮዋ፣ ዘ ስቶሪ ወርክሾፕ፣ብላንታየር፣ ማላዊ፣ የፋርም ራዲዮ ኢንተርናሽናል የራዲዮ አጋር።
የጽሁፉ ገምጋሚ፦ ዲሊፕ ብሃንዳሪ፣ የእንሣት ሃኪም፣ ሄይፈር ኢንተርናሽናል።

ይህ ጽሁፍ የዶሮ እርባታ ራዲዮ ፕሮግራምን በኢትዮጵያ ለማስፋፋት የሚደረገው ጥረት አካል ሆኖ ከአይኤፍሲ በተገኘ የገንዘብ ደጋፍ ተዘጋጀ።