ደጋግመው ለሚጠየቁ የኮቪድ-19 ጥያቄዎች መልሶች

ጤና

Script

ባለፉት ጥቂት ሳምንታት የራዲዮ አጋሮቻችን ስለ ኮቪድ -19 አንገብጋቢ ያሏቸውን ጥያቄዎች ሲልኩልን ነበር፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ያሉ የታወቁ ባለስልጣናት እና የተረጋገጡ ምንጮችን ተጠቅመን መልሶቻቸውን አዘጋጀን፡፡

ደጋግመው ለሚያገጥሟችሁ አንዳንድ የኮቪድ-19 ጥያቄዎች የሚሆኑ መልሶች ከዚህ በታች አሉ፡-

ማሳሰቢያ፡- ይህ መረጃ የባለሙያ ምክርን አይተካም፡፡ ስለደህንነታችሁ ጥያቄ ካላችሁ በአካባቢችሁ ያሉ የጤና አካላትን ባስቸኳይ አነጋግሩ፡፡.

ጥያቄና መልሶቹ ከዚህ በታች ባሉት መደቦች ተከፋፍለዋል፡-

ስለኮቪድ-19 መሰረታዊ መረጃ

 
ኮቪድ-19 ምንድን ነው?
በዓለም ጤና ድርጅት መረጃ መሰረት ኮቪድ-19 አዲስ በተገኘ ቫይረስ አማካኝነት የሚነሳ ተላላፊ በሽታ ነው፡፡ ዘሩ ጉንፋንን ከሚጨምረው ከኮረናቫይረስ ስብስብ ውስጥ ነው፡፡

ለምን ኮቪድ-19 ነባለ?
ኮቪድ-19 የሚለው ስያሜ የመጣው “ኮሮናቫይረስ” እና “በሽታ/disease” የሚሉት ቃሎች አጥረው ከተቀላቀሉ በኋላ ነው፡፡ አስራ ዘጠኝ (19) የሚለው ቁጥር የተጨመረ አዲሱ ቫይረስ በ2019 ዓ.ም. እ.አ.አ. መገኘቱን ለማሳየት ነው፡፡ ኮቪድ-19 በተጨማሪ ኮሮናቫይረስ፣ አዲሱ (አዲስ የተገኘው) ኮሮናቫይረስ እና በሳይንሳዊ ስያሜው ሳርስ-ኮቭ-2 ተብሎ ይጠራል፡፡

ኮቪድ-19 የመጣው ከየት ነው?
ኮቪድ-19 መጀመርያ የተገኘው ዉሃን ቻይና ሲሆን ምንጩ ምናልባት ከእንስሳት ሊሆን ይችላል ተብሎ ይገመታል፡፡ ከተገኘ በኋላ ሳይንቲስቶች ባደረጉት ጥናት ቫይረሱ በላብራቶሪ የተፈጠረ ሳይሆን በተፈጥሮ የነበረ መሆኑ አረጋግጠዋል፡፡

የአሁኑ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ አለም አቀፍ ወረርሽኝ/ፓንዴሚክ የተባለው ለምንድን ነው?
ቫይረሱ በአለማችን በአብዛኛው ክፍል የሚገኙ እጅግ በጣም ብዙ ሰዎችን እየጎዳ ስለነበር የዓለም ጤና ድርጅት በመጋቢት 2012 ዓ.ም. ኮቪድ-19 አለም አቀፍ ወረርሽኝ መሆኑን አወጀ፡፡

ሁሉም ሃገሮች በኮቪድ-19 ተጠቅተዋል?
ከ40 በላይ የአፍሪካ ሃገራትን ጨም ከ200 በሚበልጡ የአለም ሃገራት ሰዎች በኮቪድ-19 ምክንያት ሞተዋል፡፡ በእያንዳንዱ ሃገር ያለውን ትኩስ የኮቪድ-19 መረጃ ለማግኘት የሚከተለውን ድረ-ገጽ ተመልከቱ፡- https://www.worldometers.info/coronavirus/#countries.

ኮቪድ-19 አደገኛ የሆነው ለምንድን ነው?
ቫይረሱ በጣም በቀላሉ ስለሚሰራጭ እና ከባድ የጤና ቀውስ ስለሚያስከትል አደገኛ ነው፡፡

በኮቪድ-19 እና በሳርስ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?
ከባድ እና አጣዳፊ የመተንፈሻ አካል ችግር/Severe Acute Respiratory Syndrome (ሳርስ/SARS) የሚመጣው ልክ እንደ ኮቪድ-19 በኮሮናቫይረስ ነው፡፡ ግን ሳርስን የሚያመጣው የኮሮናቫይረስ ዓይነት በቀላሉ አይሰራጭም፣ በሽታው ግን ከኮቪድ-19 ይከፋል፡፡

የበሽታው ስርጭት እና የአደጋ ተጋላጭነት ምክንያቶች

 
ኮቪድ-19 እንዴት ይሰራጫል?
ኮቪድ-19 ቫይረሱ ያለበት ሰው ሲያስነጥሰው፣ ሲያስለው ወይም ወደ ውጭ ሲተነፍስ ወደ አየር በሚለቀቁ ፍንጣቂዎች አማካኝነት ይሰራጫል፡፡ ሰዎች አየር ላይ ያሉ እነዚህ ፍንጣቂዎች ሲያርፉባቸው ወይም እነዚህ ፍንጣቂዎች ያረፉባቸውን እቃዎች በጃቸው ሲነኩ ቫይረሱ ወደነሱ ሊገባ ይችላል፡፡ ዋነኛው የኮቪድ-19 መተላለፊያ ግን በቀጥታ ከሰው ወደ ሰው ነው፡፡

ኮቪድ-19ን የሚያመጡት ፍንጣቂዎች የተለያዩ አካላት ላይ ምን ይህል ጊዜ መቆየት ይችላሉ?
ተመራማሪዎች ኮቪድ-19ን የሚየመጡት ፍንጣቂዎች ካርቶን ላይ ከ24 ሰዓት ያነሰ ጊዜ እና ፕላስቲክ ወይም ብረት ላይ ደግሞ እስከ ሁለት ወይም ሦስት ቀን ድረስ ሊቆዩ ይችላሉ ብለው ያስባሉ፡፡ ደጋግመው ከሚነኩ ዕቃዎች ላይ ሊያጋጥም የሚችል ስርጭትን ለመከላከል እነዚህን አካላት በውሃና በሳሙና ወይም ሳሙናነት ባለው ማጽጃ አጽዱ፡፡

ለኮቪድ-19 ይበልጥ ተጋላጭ የሆነ ማነው?
አረጋውያን እና ስኳር በሽታ፣ የደም ግፊት፣ የልብ ሕመም እና ካንሰር ያለባቸው ሰዎች በሽታ የመቋቋም አቅማቸው ዝቅተኛ ስለሆነ ለኮቪድ-19 በጣም ተጋላጭ ናቸው፡፡እንደ ድህነት ያሉ የማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችም ለጽዳት አስፈላጊ የሆኑ እቃዎች አቅርቦት ዝቅተኛ ስለሆነ ሰዎች ለበሽታው እንዲጋለጡ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ሴቶችም የታመሙ ሰዎችን የመንከባከብ ሃላፊነት ስለሚጣልባቸው እና አብዛኛው የጤና ባለሙያዎች ሴቶች ከመሆናቸው የተነሳ ከወንዶች የጎላ ተጋላጭነት አላቸው፡፡

ለኮቪድ-19 ይበልጥ ተጋላጭ የሆነ የደም ዓይነት አለ?
በዚህ ዙርያ ጥናት እያደረጉ ያሉ ተመራማሪዎች በደም ዓይነት እና በኮቪድ-19 በሽታ መካከል ግልጽ ግንኙነት አላገኙም፡፡

ኮቪድ-19 አረጋውያንን ብቻ ይገድላል የሚባለው እውነት ነው?
አረጋውያን ኮቪድ-19 ከያዛቸው በበሽታው በጣም ለመጎዳት እና ለመሞት ያላቸው ዕድል ከፍተኛ ነው፡፡ ነገር ግን በሁሉም እድሜ ያሉ ሰዎች ወጣቶችን ጨምሮ በበሽታው ሊያዙ፣ በጠና ሊታመሙ እና ሊሞቱ ይችላሉ፡፡ ሴቶች እና ሌሎች ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ሐኪም ቤት ለመሄድ የመወሰን እና የገንዘብ አቅም ችግር ሊኖራቸው ስለሚችል ለጉዳት ተጋላጭነተቻው ይጨምራል፡፡

የበሽታው ስርጭት፡- አሉባልታ እና መረጃ

 
የቤት እንስሳት በበሽታው መያዝ እና ማስተላለፍ ይችላሉ?
ቁጥራቸው በጣም ጥቂት የሆኑ የቤት እንስሳት በከቪድ-19 መያዛቸው በምርመራ ተረጋግጧል፡፡ ኮቪድ-19 ግን ከእንስሳት ወደ ሰው ሊተላለፍ እንደሚችል ማስረጃ የለም፡፡

ቢምቢ ቢነድፈኝ ኮቪድ-19 ሊይዘኝ ይችላል?
አይይዝህም፡፡ ቢምቢዎች ኮቪድ-19 ያስተላልፋሉ የሚል መረጃ የለም፡፡

ኮቪድ-19 በግብረ ስጋ ግንኙነት ሊይዘኝ ይችላል?
እንደማንኛውም አካላዊ ንክኪ ኮቪድ-19 ካለበት ሰው ጋር ከአንድ ሜትር ያነሰ ቅርርብ ካለዎት ለበሽታው ተጋላጭነት ይጨምራል፡፡

ፋይቭ-ጂ (5G) ቴክኖሎጂ በመጠቀም ሊይዘኝ ይችላል?
አይይዝህም፡፡ ቫይረሱ በኔትዎርክ፣ በራዲዮ ወይም በቴሌቪዥን የሚሰራጭ አይደለም፡፡ ኮቪድ-19 የሚተላለፈው ቫይረሱ ካለበት ሰው ወደ ሌላ ሰው ነው፡፡

የበሽታውን ምልክቶች መገንዘብ

 
የኮቪድ-19 ምልክቶች ምንድን ናቸው?
ዋና ዋናዎቹ ምልክቶች ትኩሳት፣ ሳል፣ ድካም እና የመተንፈስ ችግር ናቸው፡፡

የመተንፈስ ችግር ምንድን ነው?
የመተንፈስ ችግር ማለት ያልተጠበቅ ትንፋሽ ማጠር ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ትንፋሽ ማጠር ከምልክቶቹ አንዱ መሆኑን ማስታወስ ይገባል፡፡ ሌሎቹ የኮቪድ-19 ምልክቶች ሳይታዩባችሁ የመተንፈስ ችግር ብቻ ቢያጋጥማችሁ ችግሩ ከሌላ የጤና ሁኔታ ጋር ሊያያዝ ይችላል፡፡ የመተንፈስ ችግሩ ከቀጠለ ባካባቢያችሁ ወዳሉ የጤና አካላት ደውሉ፡፡

የጤነኛ ሰው የሰውነቱ ሙቀት ስንት ነው?
የጤናማ ሰው ሰውነት ሙቀት ከ36-37 ድግሪ ሴንቲግሬድ ነው፡፡

ኮቪድ-19 ያለባቸው ሰዎች ምልክት ማሳየት የሚጀምሩት መቼ ነው?
የበሽታው ምልክቶች ከአምስት እሰከ ሰባት ቀን ባለው ጊዜ መታየት ይጀምራሉ፡፡ በጣም በጥቂት ሰዎች እስከ 14 ቀን ሊቆይ ይችላል፡፡ ቁጥራቸው ጥቂት የሆነ ሰዎች ምንም ምልክት አያሳዩም፡፡

የያዘኝ ኮቪድ-19 ሳይሆን ጉንፋን ወይም ፍሉ እንደሆነ እንዴት ማወቅ እችላለሁ?
ብቸኛው እርግጠኛ መሆኛ መንገድ የህክምና ምርመራ ነው፡፡ ነገር ግን የኮቪድ-19 ምልክት የሆኑት ትኩሳት፣ ሳል፣ ድካም እና ትንፋሽ ማጠር ካለባችሁ እራሳችሁን ለ14 ቀን መለየት አለባችሁ፡፡

ምልክቶች ካሉብኝ ሆስፒታል ልሂድ ወይስ መጀመርያ ስልክ ልደውል?
ሁልጊዜ ወደ ሆስፒታል ከመሄዳችሁ በፊት ስልክ ደውሉ፡፡ የኮቪድ-19 ምልክቶች ያሉባቸው ሰዎች ለማስተናገድ የሚደረጉት ዝግጅቶች እና የአካባቢው የጤና ሥርኣት አቅም ከሃገር ሃገር እና በሃገሮች መካከል ይለያያል፡፡

ደህና እና ጤነኛ ሆኖ ለመቆየት የሚጠቅሙ ምክረ ሃሳቦች

 
እራሴን ከኮቪድ-19 አንዴት መጠበቅ እችላለሁ?
እጃችሁን በውሃና በሳሙና ቶሎ ቶሎ ታጠቡ ወይም በሳኒታይዘር አጽዱ፤ ከቤተሰባችሁ ውጭ ከሆኑ ሰዎች ቢያንስ ባንድ ሜትር ራቁ፤ አፍንጫ፣ አፍ፣ አይንና ጆሯችሁን አትንኩ፡፡

እጅን በውሃና በሳሙና መታጠብ ለምን ይጠቅማል?
ኮሮናቫይረስን ለመግደል ሳሙና ያስፈልጋል፡፡ ቢያንስ 60% አልኮል ያለው ሳኒታይዘርም እጅ ላይ ያለውን ኮሮናቫይረስ ይገድላል፡፡

ወሸባ (እራስን መለየት) ምንድን ነው?
ሰዎች የኮቪድ-19 ምልክት ከታየባቸው፣ ኮቪድ-19 ካለበት ወይም ሊኖርበት ከሚችል ሰው ጋር ከተገናኙ ወይም በሕዝብ ጤና ባለሙያ ራሳቸውን እንዲለዩ ከተነገራቸው ለ14 ቀናት ራሳቸውን እንዲለዩ የዓለም ጤና ድርጅት ይመክራል፡፡ ራስን መለየት ማለት ሌሎች ሰዎች በሽታው እንዳይተላለፍባቸው ቤት መቆየት እና ሕዝብ ወደሚሰበሰብባቸው ቦታዎች አለመሄድ ማለት ነው፡፡

እራሴን እንዴት ልለይ?
ራሳቸውን የለዩ ሰዎች ቤት ውስጥ መቆየት እና በራሳቸው እና በሌሎች ሰዎች መካከል የቤተሰብ አባሎቻቸውን ጨምሮ የአንድ ሜትር እርቀት ጠብቀው የበሽታውን ምልክት እድገት መከታተል አለባቸው፡፡ የራሳቸው ክፍል እና መጸዳጃ ቤት ሊኖራቸው ካልቻለ አልጋቸውን ቢያንስ በአንድ ሜትር እርቀት ማስቀመጥ አለባቸው፡፡ ደጋግመው የሚነኳቸውን እቃዎች በውሃ እና በሳሙና ማጽዳት አለባቸው፡፡ የጥርስ ቡርሽ፣ የመመገቢያ እቃዎችን እና ፎጣዎችን ከሌሎች ሰዎች ጋር ተጋርተው መጠቀም የለባቸውም፡፡

ደህና እና ጤነኛ ሆናችሁ ለመቆየት የዓለም ጤና ድርጅትን ምክረ ሃሳብ ተከተሉ፡፡ እጃችሁን በውሃ እና በሳሙና ወይም በሳኒታይዘር ቶሎ ቶሎ አጽዱ፡፡ ሲያስላችሁ እና ሲያስነጥሳችሁ አፍንጫና አፍን በክንዳችሁ ሸፍኑ፡፡

ህክምና፡- አሉባልታ እና መረጃ

 
ለኮቪድ-19 ሕክምና ወይም ፈውስ አለው?
የለውም፡፡ ኮቪድ-19ን የሚያድን ሕክምና ወይም ፈውስ የለም፡፡ ምልክቶች የታዩባቸው ሰዎች ሌሎች ሰዎች በበሽታው እንዳይጠቁ ራሳቸውን መለየት አለባቸው፡፡ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ሁሉ ኮቪድ-19ን ሊያክሙ፣ ሊያድኑ ወይም ሊከላከሉ አንደሚችሉ ማስረጃ የለም:-

  • የፍሉ መርፌ
  • አልኮል
  • የበርበሬ ወጥ
  • ቫታሚን ሲ
  • ጨው፣ ነጭ ሽንኩርት ወይም ሎሚ
  • ሻይ እና ሌሎች ትኩስ መጠጦች
  • የሚሞቅ ልብስ
  • ሞቃት የአየር ሁኔታ ወይም ጸሐይ መሞቅ
  • በሙቅ ውሃ ሰውነትን መታጠብ
  • ሃይድሮክሲክሎሮኩዊን
  • ሰውነት ላይ አልኮል ወይም ክሎሪን መርጨት
  • ጀርም ማጥፊያ ኬሚካል መጠጣት
  • በአፍንጫ እና በአፍ እንፋሎት መሳብ
  • የእጅ ማድረቂያ ማሽኖች
  • በአልትራቫዮሌት አምፑሎች ጀርሞችን ማጥፋት
  • ፀረ-ተሃዋሲያን
  • የሳምባ ምች ክትባት

የፊት መሸፈኛ ጭንብል እና የእጅ ጓንቶች

 
የፊት መሸፈኛ ጭንብል መልበስ ያለብኝ መቼ ነው?
የኮቪድ-19 በሽታ ምልክቶች ያለበት ወይም ተመርምሮ ቫይረሱ የተገኘበት ሰው ሁሉ ቫይረሱ ወደ ሌሎች ሰዎች እንዳይተላለፍ ጭንብል መልበስ እንደሚችል የዓለም ጤና ድርጅት ይመክራል፡፡ ኮቪድ-19 ያለባቸውን ሰዎች የሚንከባከቡ ጤነኛ ሰዎችም ራሳቸውን ለመከላከል ጭንብል መልበስ ይችላሉ፡፡

ምን ዓይነት ጭንብል መልበስ አለብኝ?
N-95 የተባሉት የሕክምና ጭንብሎች ለሐኪሞች መተው አለባቸው፡፡ ሌላው ሰው አንዴ ብቻ የሚያገለግሉ የሕክምና ጭንብሎች ወይም ከጨርቅ የተሠሩ ደጋግመው አግልግሎት ላይ መዋል የሚችሉ ጭንብሎችን መጠቀም ይችላል፡፡

ጭንብልን በትክክል መጠቀም የምችለው እንዴት ነው?
ጭንብል ከመልበሳችሁ በፊት እጆቻችሁን ቢያንስ ለ20 ሰከንድ በውሃ እና በሳሙና ታጠቡ፡፡ ጭንብሉ አፍና አፍንጫችሁን ሙሉ በሙሉ እንዲሸፍን አድርጋችሁ ከጆሯችሁ ወይም ከጭንቅላታችሁ ጀርባ እሰሩት፡፡ ጭንብሉ በጎን በኩል ከፊታችሁ ጋር ግጥም ማለት አለበት፡፡ ጭንብሉን ከለበሳችሁ በኋላ በእጃችሁ በፍጹም አትንኩ፣ ለአንዴ ብቻ የሚያገለግሉ ጭንብሎችን ደግማችሁ አትጠቀሙ፡፡

አንዴ ብቻ የሚያገለግል ጭንብል ሲረጥብ ወይም ሲቆሽሽ ፌስታል ውስጥ አድርጋችሁ ፌስታሉን በማሰር አስወግዱ፡፡ ደረቅና ንጹህ ጭንብል ከመልበሳችሁ በፊት እጃችሁን በውሃና በሳሙና ቢያንስ ለ20 ሰከንድ ታጠቡ፡፡

ጭንብል የሚለብሱ ሰዎች እጃቸውን በውሃ እና በሳሙና ቶሎ ቶሎ መታጠብ፣ ከሌሎች ሰዎች ቢያንስ በአንድ ሜትር መራቅ እና አፍንጫ፣ አፍ፣ አይኖቻቸውን እና ጆሯቸውን አለመንካት አለባቸው፡፡

የፊት መሸፈኛ ጭንብልን አጥቤ መጠቀም እችላለሁ?
N-95 ጭንብሎች እና ተጠቅመው የሚጣሉ ጭንብሎች ድጋሚ ማገልገል አይችሉም፡፡ የጨርቅ ጭንብሎች ደጋግመው አገልግሎት ላይ መዋል ስለሚችሉ ቶሎ ቶሎ በውሃ እና በሳሙና እየታጠቡ ደርቀው ድጋሚ ጥቅም ላይ መዋል ይችላሉ፡፡

ጓንት ማድረግ አለብኝ?
የዓለም ጤና ድርጅት ማንም ሰው ጓንት እንዲያደርግ አይመክርም፡፡ ደጋግመው ከሚነኩ እቃዎች ላይ ጀርሞች እንዳይተላለፉ እጆችን ቶሎ ቶሎ ለ20 ሰከንድ ያህል በውሃ እና በሳሙና መታጠብ ወይም አልኮል ባለው ሳኒታይዘር ማጽዳት በቂ ነው፡፡

ጓንት ማድረግ ከመረጣችሁ እጆቻችሁን ቶሎ ቶሎ በውሃ እና በሳሙና መታጠባችሁን ቀጥሉ አፍንጫ፣ አፍ፣ አይኖች እና ጆሮዎቻችሁን ከመንካት ታቀቡ፡፡

የፊት ጭንብል እና ጓንት ከኮቪድ-19 ሊጠብቁኝ ይችላሉ?
የፊት ጭንብል እና ጓንት መጠቀም ከበሽታ የመከላከል ዋስትና አይሰጡም፡፡ እነዚህ የራስ መጠበቂያ ቁሶች ውጤታማ የሚሆኑት እጅን እንደ መታጠብ እና እርቀትን እንደመጠበቅ ያሉ ሌሎች መካለከያ መንገዶች ሲከበሩ ነው፡፡

ከበሽታ ማገገምን መገንዘብ

 
አንድ ሰው ለምን ያል ጊዜ ነው በኮቪድ-19 በሽታ የሚያዘው?
ኮቪድ-19 ያለባቸው ሰዎች ምልክት ከማሳየታቸው በፊት ጀምሮ በሽታውን ሊያስተላልፉ ይችላሉ፡፡ የኮቪድ-19 ምልክቶችን ማሳየት ካቆሙ በኋላም ማስተላለፍ ሊቀጥሉ ይችላሉ፡፡ በሽታው የሚተላለፍበት ጊዜ ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ ሳይንቲስቶች ገና ጥናት ላይ ናቸው፡፡ ከወሸባ (ራሳችሁን ከማግለል) ከመውጣታችሁ በፊት በአካባቢያችሁ ያሉ የጤና ባለስልጣናትን አማክሩ፡፡

ከወሸባ ከወጣችሁ በኋላ ደህንነታችሁን እና ጤንነታችሁን ለመጠበቅ የዓለም ጤና ድርጅትን ምክረ ሃሳብ መከተል ያስፈልጋችኋል፡፡ እጃችሁን በውሃ እና በሳሙና ታጠቡ ወይም ሳኒታይዘር ተጠቀሙ፣ ከቤተሰቦቻችሁ ውጭ የሆኑ ሰዎች ጋር ስትገናኙ ቢያንስ የአንድ ሜትር እርቀት ይኑራችሁ፤ እፍንጫ፣ አፍ፣ አይንና ጆሯችሁን አትንኩ፡፡

ከኮቪድ-19 ለማገገም ምን ያህል ጊዜ ይወስዳል?
መካከለኛ የሆነ ኮቪድ-19 ያለባቸው ሰዎች ከሁለት እስከ ሦስት ሳምንት ባለ ጊዜ ውስጥ ይሻላቸዋል፡፡ በጣም የታመሙት እስከ ስድስት ሳምንት እና ከዚያም በላይ ሊቆዩ ይችላሉ፡፡

ከኮቪድ-19 ያገገመ ሰው ለበሽታው ቢጋለጥ በድጋሚ ሊያመው ይችላል?
ሳይንቲስቶች በዚህ ዙርያ ጥናት እያካሄዱ ነው፣ አንድ ሰው ድጋሚ ሊታመም ይችላል ወይስ አይችልም የሚለው ጉዳይ ላይ የደረሱበት ድምዳሜ ገና የለም፡፡

የኮቪድ-19 ምልክት የሌለበት ሰው በሽታው ሊኖርበት ይችላል?
አዎ፣ የበሽታው ምልክት የሌለበት ሰው የኮቪድ-19 ተሸካሚ ሊሆን ይችላል፡፡

እርግዝና፣ ወባ እና ነባር የጤና ችግሮች

 
ነፍሰ ጡር ሴቶች ኮቪድ-19ን ወደ ጽንሳቸው ማስተላለፍ ይችላሉ?
ሳይንቲስቶች ይህንን ጥያቄ ገና እያጠኑት ነው፡፡ እስካሁን ግን ከነፍሰ ጡር እናት ወደ ጽንስ ሊተላለፍ እንደሚችል ማስረጃ አልተገኘም፡፡

ኮቪድ-19 ያለባቸው አራስ እናቶች ልጆቻቸውን ጡት ማጥባት አለባቸው?
እስካሁን ኮቪድ-19 ጡት በማጥባት ሊተላለፍ እንደሚችል የሚያሳይ ማስረጃ የለም፡፡ ግን ልክ እንደማንኛውም አካላዊ ንክኪ የምታጠባ እናት እና ልጇ ቅርብ ንክኪ ስላላቸው ጡት ማጥባት በሽታው ካለባት እናት ወደ ልጇ የመተላፍ ዕድሉ አለው፡፡ ኮቪድ-19 ያለባቸው እናቶች ከማጥባታቸው በፊት እጃቸውን በውሃ እና በሳሙና እንዲታጠቡ እና አፍና አፍንጫቸውን በጭንብል እንዲሸፍኑ ሳይንቲስቶች ይመክራሉ፡፡ ይህን ማድረግ ካልቻሉ በሽታው የሌለበት ሌላ ሰው ልጁን እንዲመግብ ይሁን፡፡

ነፍሰ ጡር እናቶች ለቅድመ ወሊድ ክትትል ወደ ጤና ተቋም የሚያደርጉትን ጉብኝት መቀጠል አለባቸው?
የእናቶችን እና የጽንሱን ጤንነት ለማረጋገጥ የቅድመ ወሊድ ክትትል በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ነገር ግን በኮቪድ-19 የተነሳ ብዙ የማህጸን ሐኪሞች የጉብኝቱን ጊዜ እያራዘሙት ወይም እናቶች በመምጣት ፋንታ ወደ ሆስፒታል ስልክ እንዲደውሉ እያደረጉ ነው፡፡የእናንተ ወይም የልጃችሁ ጤንነት ካሳሰባችሁ በአካባቢያችሁ ወዳለ የጤና ተቋም ደውሉ፡፡

የወባ ወይም የኤችአይቪ መድሃኒት ለመቀበል ወደ ጤና ተቋም መሄድ መቀጠል እችላለሁ?
በዚህ ሰዓት ከመሄዳችሁ በፊት ስልክ አስቀድማችሁ ብትደውሉ የተሻለ ነው፡፡ የተለያዩ የጤና ችግሮቻችሁን በተመለከት ምን ማድረግ እንዳለባችሁ በአካባቢያችሁ ያሉ የጤና ባለሙያዎችን አማክሩ፡፡

የኮቪድ-19 ዘርፈ ብዙ ተጽእኖዎች

 
ወደ ሥራ መሄድ እችላለሁ?
የዓለም ጤና ድርጅት በበሽታው የመያዝ እድልን ለመቀነስ በተቻለ መጠን ቤት መቆየትን ይመክራል፡፡ ከሃገራችሁ ጋር የተያያዘ መረጃን ለማግኘት በአካባቢያችሁ ባሉ የጤና በላስልጣናት የተለቀቁ መመርያዎችን ተመልከቱ፡፡

ኮቪድ-19 ግብርና ላይ ምን ዓይነት ተጽእኖ ይኖረዋል?
ኮቪድ-19 የተለያዩ ዓይነት ሰዎች እና የግብርና እንቅስቃሴዎች ላይ ከባድ ተጽእኖ ሊኖረው ይችላል፡፡ ከሁሉም በፊት ከቤት ለመውጣት የተደረገው እግድ የሚመረተው እና የሚሸጠው ምግብ መጠን እና ዓይነት ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል፡፡ ግብርና ሥራ ላይ በተሰማሩ ጊዜ ደህንነታቸውን ለመጠበቅ አርሶ አደሮች በመካከላቸው ቢያንስ የአንድ ሜትር እርቀት መጠበቅ አለባቸው፣ እጆቻቸውን በመታጠብ እና በሌሎች መንገዶች የግል ንጽሕናቸውን መጠበቅ አለባቸው፡፡ ኮቪድ-19ን ለመከላከል ተብለው የተጣሉት እግዶች በምግብ አቅርቦት ሰንሰለት ላይ ያሉትን አምራቾች፣ ነጋዴዎችና ሌሎችንም በተለያየ መጠን ተጽእኖ ያሳድሩባቸለዋል፡፡

በግብርና እና ምግብ አቅርቦት ላይ ያለው ተጽእኖ በጊዜ ግልጽ እየሆነ ሲሔድ አርሶ አደሮች እና ሌሎችም አሠራራቸውን መቀየር ሊያስፈልጋው ይችላል፡፡ ከዓለም ጤና ድርጅት መመርያዎች በተጨማሪ በሃገር ደረጃ የሚሰጡ ምክረ ሃሳቦችን በመከተል ደህንነታችሁን እና ጤንነታችሁን ጠብቁ፡፡

ኮቪድ-19 ሴቶች ላይ የተለየ ተጽእኖ አለው?

 
በቤት ውስጥ እና በማሕበረሰብ ውስጥ የታመሙ ሰዎችን የመንከባከብ ሃላፊነት ብዙውን ጊዜ የሴቶች ስለሆነ እና ከጤና ባሙያዎችም ውስጥ አብዛናዎቹ ሴቶች ስለሆኑ ሴቶች በኮቪድ-19 የመጠቃት እድላቸው ከፍ ያለ ነው፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታዎች በሚኖሩ ጊዜ የሴቶች የሥራ ጫና ይበዛል፡፡ ትምህርት ቤቶች እና የሕጻናት ማቆያ ቦታዎች ዝግ ሆነው በሚቆዩበት ጊዜ እነዚህን ልጆች መንከባከብ የሴቶች ሥራ ይሆናል፡፡ የታመሙ ሶችንም ጎን ለጎን መንከባከብ የሴቶች ሥራ ነው፡፡ የጤና ባለሙያዎች ሲሆኑ ደግሞ በቤት ያለው ሃላፊነታቸው እንዳለ ሆኖ በሥራ ቦታ ላይ ረጅም ሰዓት ሊሠሩ ይችላሉ፡፡

በቀውስ ጊዜ ጾታዊ ጥቃቶች እና የቤት ውስጥ ጥቃቶች ይጨምራሉ፤ እነዚህን ጥቃቶች ለመከላከል የሚሰጡ አገልግሎቶች ደግሞ ሊቀንሱ ይችላሉ፡፡ አንቅስቃሴ ላይ ገደብ ሲጣል እና ቤት የመቆየት መመርያዎች ሲወጡ ለቤት ውስጥ ጥቃት ተጋላጭ ለሆኑ ሴቶች የቤታቸው አካባቢ አደገኛ ይሆናል፡፡

ኮቪድ-19 ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖዎች ሴቶች ላይ ይበረታሉ፡፡ ለምሳሌ ሥራ ቢጠፋ ሴቶች ከትምህርት ቤት ሊቀሩ ወይም ያለ እድሜያቸው ሊዳሩ ይችላሉ፡፡

ለሴቶች የሚደረጉ ወሳኝ የስነ ተዋልዶ እና ሌሎች የሕክምና አገልግሎቶች በቀውሱ ሊጎዱ ይችላሉ፣ በዚህም ሴቶች አሉታዊ የጤና ችግሮች እና በወሊድ ጊዜ የሞት አደጋ ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡

ለተጨማሪ መረጃ

 
ስለ ኮቪድ-19 ተጨማሪ መረጃ የት ማግኘት እችላለሁ?
አስተማማኝ እና ወቅታዊ መረጃ ከዓለም ጤና ድርጅት ድረ ገጽ ማግኘት ትችላላችሁ፡- https://www.who.int/health-topics/coronavirus.

ስለ ኮቪድ-19 የሚለቀቁ የሐሰት ዜናዎች እና አሳሳች መረጃዎች እንዴት ማስወገድ እችላለሁ?
ስለ ኮቪድ-19 መረጃ ስትሰበስቡ እና ስትዘግቡ እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ካሉ አስተማማኝ ድርጅቶች የምታገኙትን መረጃ ተጠቀሙ፡፡ መረጃው ወቅታዊ መሆኑን ለማረጋገጥ የመረጃው ምንጭ ላይ የተጻፈውን ቀን እዩ፡፡ መረጃው ካጠራጠራችሁ ከሌላ ምንጭ አረጋግጡ፡፡ መረጃን ስለማረጋገጥ እና በተለይም የኮቪድ-19 መረጃዎችን ለማረጋገጥ የሚከተለውን ድረ-ገጽ ጎብኙ፡- https://africacheck.org/reports/live-guide-all-our-coronavirus-fact-checks-in-one-place/.

Acknowledgements

This resource is undertaken with the financial support of the Government of Canada provided through Global Affairs Canada.