Script
መግቢያ
ኢትዮጵያውያን ከማንኛውም አዝርዕት በበለጠ (በቆሎን ሳይጨምር) ጤፍ ይዘራሉ፣ ያመርታሉ፣ እንዲሁም ይመገባሉ፡፡ ወደ አምስት ሚልዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን አባወራዎች ወደ ሶስት ሚልዮን ሄክታር የሚጠጋ መሬት ላይ ጤፍ ይዘራሉ፡፡ የጤፍ ሳይንሳዊ ስሙ ኤራግሮስቲስ ጤፍ ሲሆን የተገኘውም ከኢትዮጵያ እደሆነ ይታመናል፡፡
በኢትዮጵያ ወደ 15 በመቶ የሚጠጋው ካሎሪ ከጤፍ የሚገኝ ነው፡፡ ከጤፍ የሚሰራው እንጀራ የአብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን የየዕለት ምግብ ነው፡፡
ይህ ጉዳይ ለአድማጮች አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው
በብዙ ምክንያቶች ጤፍ በኢትዮጵያ አስፈላጊ አዝርዕት ነው፡-
- አነስተኛ እርጥበት ባለበት እና የውሃ መጥለቅለቅ ባለበት ሁኔታ ጤፍ ከሌሎች አዝርዕቶች በተሻለ ምርት ይሰጣል፡፡ በብዙ አይነት የግብርና ከባቢዎች (አየር ንብረት ዞኖች) እና በልዩ ልዩ የአፈር ዓይነቶች ላይ (ከአሲዳማ አፈር ጀምሮ እስከ አልካላይን እና ጥቁርና ቀይ አፈሮች ድረስ) መብቀል ይችላል፡፡
- ጤፍ ከተመረተ በኋላ በክምችት ጊዜ በሚመጣ ተባይ ሳይጠቃ ለረጅም ጊዜ መቀመጥ ይችላል፡፡
- ጤፍ ያን ያክል በበሽታ ተጠቅቶ አየውቅም፡፡
- የጤፍ ተረፈ ምርት (ጭድ) በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል ለከብት መኖነት ዋነኛ ጥቅም ይሰጣል፡፡ ጭድ እጅግ ጠቃሚ ንጥረ-ነገር ያለው የከብት መኖ ሲሆን በጭቃ ተለውሶ ለቤት መምረጊያነትም ያገለግላል፡፡
- የጤፍ ምርትም ይሁን ተረፈ-ምርቱ (ጭዱ) ትልቅ ዋጋ የሚያወጡ ሲሆን ለውጪ ገበያም ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡
- ጤፍ በአንፃሩ ጤናማ እና ብዙ ገንቢ የሆነ አዝርዕት ነው፡፡ ከግሉተን ነፃ የሆነ እና አይረን፣ ካልሺየም እና ኮፐርን ከሌሎች አዝርዕቶች በላይ የያዘ ነው፡፡
ጥቂት ዋና ዋና እውነታዎች ምንድን ናቸው
- ጤፍ ለአብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ቋሚ ምግብ (የዕለት ተዕለት ምግብ) ነው፡፡
- አርሶአደሮች ጤፍን በዋናነት ለገበያ ብለው ያመርታሉ፡፡ ይህም የሆነው ገበያው አስተማማኝ ስለሆነና ዋጋውም ከሌሎች አዝርዕቶች አንፃር የማይለዋወጥና በየጊዜው የሚጨምር በመሆኑ ነው፡፡
- ጤፍ ቡሉም የአፈር አይነቶች ላይ የሚበቅል ሲሆን አንዱና ዋነኛው የጤፍ ጥቅም የውሃ መጥለቅለቅን መቋቋም በመቻሉ ውሃ በሚመበዛባቸው አፈሮች ላይም መብቀል ይችላል፡፡ እንዲሁም በበሽታ ያንያክል የማይጠቃና በክምችት ወቅት በሚከሰት ተባይ ጨርሶ የማይጠቃ አዝርዕት ነው፡፡
ጤፍን የማብቀል ዋና ዋና ተግዳሮቶች ምን ምን ናቸው
- ጤፍ ከስንዴና በቆሎ ያነሰ ምርት ነው የሚሰጠው፡፡ አማካይ ሀገራዊ ምርቱ 1.5 ቶን በሄክታር ነው፡፡ ነገርግን በአመቺ ማብቀያ ቦታዎች ሊገኝ የሚችለው ምርት ወደ 3 ቶን በሄክታር ነው፡፡
- በብዛት የሚዘሩት የአንድ አካባቢ የጤፍ አይነቶች አነስተኛ ምርታማነት ያላቸው መሆኑ፡፡
- ለተለያዩ የግብርና ከባቢዎች (የአየር ንብረት ዞኖች) የሚስማሙ የተለያዩ ዘሮች አለመኖራቸው፡፡
- የመጋሸብ ባህሪ፣ በዚህ ምክንያት የሚደርስ ከ20 እስከ 25 ከመቶ የሚደርስ የምርት ብክነት
- ትክክለኛ የሆኑ የመስመር መዝሪያና ሌሎች የተሻሻሉ የማምረቻ መሳሪያዎች አለመኖር፡፡
- የጤፍ ዘርን በመበተን መዝራት ለአነስተኛ ምርት ይዳርጋል፡፡
- አረምን ማረም ጉልበት የሚጠይቅ ሲሆን ሁልጊዜ ውጤታማ አይደለም፡፡
- የመሬትና የአካባቢ መሸርሸር፣ የአፈር ለምነት መቀነስ እና ከፍተኛ የግብዓት ዋጋ ምርታማነትን መቀነሳቸው
- ዘግይቶ ምርትን መሰብሰብና ደካማ የሆነ አያያዝ ለምርት ብክነት ይዳርጋል፡፡
- ከምርት መሰብሰብ በኋላ ላለው ስራ የሚያገለግሉ አመቺና የተሻሻሉ መሳሪያዎች እና ዕቃዎች አለመኖራቸው፡፡
- ሰብልን ከብቅለት መከላከያ ዘዴ አለመኖሩ፤ ይህም ማለት ምርቱ ከደረሰና ከደረቀ በኋላ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ከመጣ ሰብሉ ከተሰበሰበም በኋላም ቢሆን ያጎነቁላል፡፡
- በእጅም ይሁን እንስሳትን በመጠቀም መሬት ላይ የሚደረጉ የተለመዱ የመውቂያ መንገዶች የምርት ብክነትን እና የእህል ጥራትን ይጨምራል፡፡
- የተገደበ የብድር አገልግሎት መኖሩ፣ ማስያዣ አለመኖር፣ እና በአነስተኛ የብድርና ቁጠባ ተቋማት የሚጠየቀው ከፍተኛ የሆነ ወለድ፡፡
በዚህ ርዕሰ-ጉዳይ ላይ ማንሳት ያለብኝ የተሳሳተ መረጃ አለ
ጤፍ በኢትዮጵያ ሁለተኛው ታዋቂ አዝርዕት ቢሆንም ከሌሎች ለቋሚ ምግብነት ከሚውሉ ሰብሎች አንፃር በታሪክም የተዘነጋ ነው፡፡ በጤፍ ውስጥ ያሉት ንጥረ-ነገሮች ደረጃ ከሌሎች አዝርዕቶች ጋር ተመሳሳይ ሲሆን በአይረን፣ ካልሺየም፣ እና ኮፐር ይዘቱ ከሌሎች አዝርዕቶች ይበልጣል፡፡ ነገርግን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ጤፍ አነስተኛ ንጥረ-ነገሮችን የያዘ ነው የሚል የተሳሳተ አረዳድ ነበር፡፡
ጤፍን በማምረት ሂደት ያለው የፆታ ሁኔታ
- በኢትዮጵያ ወደ 15 ከመቶ የሚገመተው ቤተሰብ በሴቶች ነው የሚመራው፡፡ ያገቡ ሴት አርሶአደሮችም በሁሉም የማምረት ሂደት (ከማሳ ዝግጅት፣ መዝራት፣ አረም ማረም፣ ሰብልን መቆጣጠር እና ሰብልን ሰብስቦ እስከ መውቃት እና ማከማቸት) ይሳተፋሉ፡፡
- ጤፍ በተፈጥሮው የሰው ኃይል የሚፈልግ ሲሆን አርሶአደሮች አሁን አሁን ከሌሎች ሰብሎች በላይ ደጋግመው ያርሳሉ፡፡ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን እና ጥሩ የግብርና ልምዶችን መጠቀም ምርትን ይጨምራል እንዲሁም ጤፍ ማምረት የሚጠይቀውን የሰው ኃይል ይቀንሳል፣ ይህም የሴቶችን የስራ ጫና ይቀንሳል፡፡ የጤፍ ምርትን መጨመር እና የሰው ኃይልን መቀነስ ሴቶች የሚመሯቸውን ቤተሰቦች ደረጃ ከፍ የሚያደርግ ሲሆን ይህም የስራ ጫናቸውን ይቀንሳል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ በምርት ላይ የሚያሳድረው የተተነበየ ተፅዕኖ
- በኢትዮጵያ እየተለወጠ ያለውን የአየር ንብረት የሚላመዱ የተለያዩ የጤፍ አይነቶች አሉ፡፡ ስለዚህ አርሶ አደሮች በተተነበየው የአየር ንብረት መሰረት የባለሙያ ምክርን እና ጥናትን ሲተገብሩ ያነሰ አደጋ ነው የሚያጋጥማቸው፡፡
- አርሶአደሮች በእርጥበት እጦት ምክንያት ሙሉ ለሙሉ የሰብል ብልሽት በሚያጋጥማቸው በአንዳንድ አካባቢዎች ጤፍ ጥሩ ምትክ ሆኖ ምርት ይሰጣል፡፡ እንደ በቆሎና ማሽላ ያሉ የረጅም-ወቅት ሰብሎች በድርቅ፣ ተባይ ወይም በሽታ ምክንያት ምርት ሳይሰጡ ሲቀር የኢትዮጵያ አርሶአደሮች ብዙ ጊዜ ጤፍ ደግመው ይዘራሉ፡፡
ጤፍ ማምረትን የተመለከቱ ዋና ዋና መረጃዎች
1. አመቺ ማሳ እና የማሳ ዝግጅት፡-
- ጤፍ ከባህር ወለል በላይ ከ1800-2100 ሜትር ከፍታ ላይ ከ750-850 ሚሊሜትር ዓመታዊ ዝናብ ባለበት እና ከ10-27 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በሆነ ሙቀት የተሻለ ይበቅላል፡፡ ነገርግን ባህር ወለል በላይ ከ2400 ሜትር በላይ የሆነ ከፍታ እና እስከ 1200 ሚሊሜትር የሚደርስ አመታዊ ዝናብ ባለበት አካባቢም ይበቅላል፡፡
- ጤፍ በብዙ የአፈር አይነቶች ላይ ይበቅላል፤ እነዚህም ለሌሎች አዝርዕቶች በጣም መጥፎ የሆኑ ጥቁር የጥጥ አፈሮች እና የፒኤች (pH)* ይዘታቸው ከ5 በታች የሆኑ አሲዳማ አፈሮች ናቸው፡፡
- ጤፍ ምናልባትም ከሌሎች በተሸለ ደረጃ እርጥበታማ ሁኔታዎችን መቋቋም ይችላል፡፡
- የጤፍ ማሳዎች በባህላዊ መንገድ በበሬ በአንድ ወቅት ከሁለት እስከ ሶስት ጊዜ ይታረሳሉ፤ ይህም እንደ አፈሩ አይነት፣ የአረም ብዛት፣ እና የአፈሩ የውሃ መጠን ይወሰናል፡፡ ደጋግሞ የሚታረስበት ምክንያትም የጤፍ ዘሮች በጣም ትንንሽ ስለሆኑ ባልደቀቀ እና ከባድ በሆነ አፈር ውስጥ መብቀል ስለሚያስቸግር ነው፡፡ ደጋግሞ ማረስ የአረምን መጠንም ይቀንሳል፡፡
- ከባድ የሸክላ አፈሮች እና ከፍተኛ የሆነ የአረም ብዛት ከአሸዋማ እና ሎም አፈሮች በበለጠ በተደጋጋሚ ማረስን ይጠይቃል፡፡
- በውሃ በሚጥለቀለቅ አካባቢ ያለ መረሬ* አፈርም ፍሳሽ ለመክፈት ተደጋጋሚ ማረስን ይፈልጋል፡፡ ቢቢኤም (ሰፊ አልጋ ማዘጋጃ) የተሰኘ የግብርና ዘዴን መጠቀም ይመከራል፡፡ ይህ በሌለበት በአማርኛ ዝቆሽ ወይም ሹሩቤ በትግርኛ ደግሞ ምፅንፋፍ የተሰኘውን ባህላዊ የቦይ መስሪያ ዜዴ መጠቀም፡፡
- ባለፉት 10 ዓመታት አንዳንድ አርሶአደሮች የጤፍ ማሳን ሳያርሱ የመጠቀም ዘዴን በመተግበር ስኬታማ ሆነዋል፡፡ ስለዚህ ደጋግሞ ማረስ ከግብርና ሳይንስ ይልቅ ባህላዊነቱ ያመዝናል፡፡
2. ዘር፣ አይነቶች እና መዝራት፡-
- አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን አርሶአደሮች ባህላዊ/አካባቢያዊ የጤፍ ዘር አይነቶችን ነው የሚጠቀሙት፡፡ እነዚህ ዘሮች በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ሲሆን እ.ኤ.አ.ከ1970 ወዲህ ከ40 በላይ የተሻሻሉ የጤፍ ዘር አይነቶች በልፅገው ለአርሶአደሮች ተሰራጭተዋል፡፡
- ሁለቱ አስፈላጊ የጤፍ ዘር ምንጮች መደበኛው የንግድ ዘር ስርዓት እና ኢመደበኛው ስርዓት – አርሶአደሮች የሚያስቀምጧቸው ዘሮች እና በአካባቢው ባለው ገበያ የሚሸጡ ናቸው፡፡ በቅርቡ ሶስተኛ አማካይ የዘር ምንጭ የሰለጠኑ የዘር አምራቾችን በማደራጀት ተጀምሯል፡፡ እነዚህ የተደራጁ ቡድኖች ከግብርና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች እና አጥኚዎች ጋር እና ከቁጥጥር አካላት ጋር በቅርበት በመስራት እና ከልማት ድርጅቶች ጋር በመተባበር እውቅና ያላቸውን ዘሮች ያመርታሉ፡፡ የተሻሻሉት እና በሀገሪቱ በብዛት የሚዘሩትና ተቀባይነት ያላቸው የምርጥ ዘር አይነቶች ቁንጮ፣ ክሮስ37 (ፀደይ) እና ዲዜድ196 (ማኛ) በመባል ይታወቃሉ፡፡ በቅርቡ የተመረቱ፣ ከፍተኛ ዝናብ ላለባቸው አካባቢዎች የሚሆኑና ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የጤፍ ዘር አይነቶች ኮራ፣ ፍላጎት፣ ተስፋ፣ እና ንጉስ ናቸው፡፡ አነስተኛ ዝናብ ላለባቸው አካባቢዎች ደግሞ ቦሰት፣ ስማዳ (በጣም ቆላማ ለሆነ) እና ፀደይ (ክሮስ-37) የተባሉት ዘሮች ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ ቀዝቃዛማ ለሆኑ ከፍታማ ቦታዎች ደግሞ ጊምቢቹ እና ደጋ ጤፍ የየተቫሉ ዘሮች ይሆናሉ፡፡
- የኢትዮጵያ ገበሬዎች የጤፍ ዘርን በመበተን ይዘራሉ፡፡ ይህ የሆነውም በጣም አነስተኛ የሆነ የዘር መጠን በመስመር ለመዝራት በቂ ስለማይሆን ነው፡፡ አርሶአደሮች ለአንድ ሄክታር መሬት ከ20-25 ኪሎግራም ዘር ይጠቀማሉ፡፡
- ዘርን በመበተን ከመዝራት ይልቅ በመስመር መዝራት የተለያዩ ጥቆሞች አሉት፡- እንደየ አፈሩ አይነት አረም ማረምን ያቀላል እንዲሁም የዘር መጠን ከ10-15 ኪሎግራም በሄክታር ዝቅ እንዲል ያደርጋል፡፡ እስከ 15 ኪሎግራም በሄክታር የሚደርስ ያነሰ የዘር መጠንን በቀላል አፈሮች ላይ መዝራት እና ብዙ የዘር መጠን በከባድ መረሬያማ አፈሮች ላይ መዝራት ማዳበሪያን በአግባቡ ለመጠቀምና ግሽበትን ለመከላከል ይረዳል፡፡
- ትክክለኛ መትከያ መሳሪያዎችን በመጠቀም ከ3-5 ኪሎግራም ዘር በአንድ ሄክታር ማሳላይ መጠቀም ይቻላል፡፡
- ምንም እንካን ጥናት ባይመክርም አርሶአደሮች በባህላዊ መንገድ መካከለኛ የሆነ የአፈር እመቃን በመጠቀም ብቅለትን ይጨምራሉ አረምን ይቀንሳሉ፡፡ ይህም ብዙ ጊዜ የቤት እንስሳትን በመጠቀም አልፎ አልፎ ደግሞ በሰዎች የሚሰራ ነው፡፡
- ጤፍ በመስመሮች መካከል 20 ሴንቲሜትር ክፍተት ላይ እንዲሁም ወደ መሬት ውስጥ ከሁለት እስከ ሶስት ሴንቲሜትር ጥልቀት ላይ ይዘራል፡፡ እንዲሁም በመስመሮች መካከል 20 ሴንቲሜትር ክፍተት በመተው እና በተክሎች መካከል ከ10 እስከ 15 ሴንቲሜትር በሚደርስ ክፍተት ተነቅሎ ሊተከል ይችላል፡፡ ከሁለት አስከ ሶስት ችግኞች በእያንዳንዱ ከፍታ ላይ ከሁለት እስከ ሶስት ሴንቲሜትር በሚደርስ ጥልቀት ይተከላሉ፡፡
- ችግኞች ከ3-4 ሳምንት ውስጥ ይተከላሉ ወይም ችግኞች ሲተከሉ ከ3-4 ቅጠሎች ሲኖራቸው ይተከላሉ፡፡ ከ20-21 ቀን ባለው ጊዜ ተነቅለው ሲተከሉ የተሻለ እድገት እና ጥሩ ምርት ይኖራቸዋል፡፡
- የነቅሎ-መትከል ጥቅሞች፡-
- ምርት በመበተን ወይም በመቅበር ከሚዘራበት መንገድ አንፃር ከ3-4 ሳምንት ቀድሞ ለመሰብሰብ ይደርሳል፡፡ እንዲሁም በዘር ወቅት የሚያጋጥምን ያልተጠበቀ የዝናብ እጥረትን ያልፋል፡፡
- የተሻሻለ፣ አንድ አይነት፣ የቀደመ እና ጠንካራ እድገት
- የዘር መጠንን ይቀንሳል፡- ከ250-400 ግራም ዘር በአንድ ሄክታር በቂ ይሆናል፡፡
- በእያንዳንዱ ተክል ላይ የሚኖረው የጉንቁል መጠን ይጨምራል
- የጭድ መጠንን ይጨምራል
- በሬም ሆነ ማረሻ ለሌላቸው አርሶአደሮች አመቺ ነው፡፡
- የአረም መጠንን ይቀንሳል፡፡
- ለኩትኳቶና ማዳበሪያ ለመጠቀም አመቺ መሆኑ
- የንቅለ-ተከላ ጉዳት የሰው ኃይል የሚፈልግ መሆኑና ትልቅ የእርሻ መሬት ላይ መተግበር አለመቻሉ ነው፡፡
- የጤፍ ሰብል እንደየ ከፍታውና የዘሩ አይነት ከ45-160 ቀናት ባለው ጊዜ ይደርሳል፡፡ በጣም በቶሎ የሚደርሱ ዘሮች ከ45-60 ቀናት ባለው ጊዜ ለመሰብሰብ ይደርሳሉ፡፡ ቶሎ የሚደርሱ አይነቶች ከ60-120 ቀናት ባለው ጊዜ ሲደርሱ የሚዘገዩ ዘሮች ደግሞ ከ120-160 ባሉት ቀናት ይደርሳሉ፡፡
3. የማምረት ልምዶች፡-
- በአብዛኞቹ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ጤፍ በዋናው የዝናብ ወቅት (መኸር) ነው የሚመረተው፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ግን በአጭሩ የዝናብ ወቅት (በልግ) ነው የሚዘራው፡፡
- ጤፍ ጠቃሚ የሰብል አይነት ሲሆን ለአርሶአደሮች አነስተኛ አደጋ ያለው አስተማማኝ ሰብል ነው፡፡
- ጤፍ በአብዛኛው እንደ ብቸኛ ሰብል ከአመት አመት የሚዘራ ሰብል ነው፡፡ በዝናብ ሰብል በሚበቅልበት የአየር ሁኔታ ጤፍ ለተለያዩ የሰብል ማምረቻ ዘዴዎች (እንደ ብቸኛ ሰብል፣ አከታትሎ መዝራት፣ አሰባጥሮ መዝራት፣ ሁለት ሰብል በአንድ ማሳ ላይ መዝራትና ቀላቅሎ መዝራት ላሉ) የተመቸ ነው፡፡
- ብዙ አርሶአደሮች በተለይ በከፍተኛና መካከለኛ ከፍታ ባለቸው የሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ጤፍን ከቅባት እህሎች እና ጥራጥሬዎች (እንደ ሰሊጥ፣ ሱፍ፣ እና ባቄላ) ጋር ቀላቅለው ይዘራሉ፡፡
4. የአፈር ለምነት፡-
- በኢትዮጵያ ባለው የጤፍ ምርት ዋናው ተግዳሮት አነስተኛ የአፈር ለምነት ነው፡፡
- ባህላዊ የአፈር ለምነትን መጠበቂያ ዘዴዎች የሰብል ተረፈ ምርት፣ ፍግ፣ እና አፈራርቆ ወይም ቀላቅሎ መዝራትን ይጨምራሉ፡፡
- በገበያ የሚቀርቡ ማዳበሪያዎች ኤንፒኤስ፣ ኤንፒኤስቢ፣ ኤንፒኤስዜድ፣ ኤንፒኤስቢዜድ እና ዩሪያ ናቸው፡፡
- ለጤፍ ምርት የሚመከረው የማዳበሪያ አጠቃቀም፡-
- ለቀላል ቀይ አፈር 40 ኪሎግራም ኤን በሄክታር እና 60 ኪሎግራም ፒ2ኦ5 (ፎስፈረስ ፔንቶክሳይድ) በሄክታር
- ለመረሬ አፈር 60 ኪሎግራም ኤን በሄክታር እና 60 ኪሎግራም ፒ2ኦ5 በሄክታር
በእነዚህ ምክረሀሳቦች መሰረት ጥቅም ላይ የሚውለው የዩሪያ መጠን በሚመከረው እና በአካባቢው በሚገኘው የፒ2ኦ5 ማዳበሪያ መጠን ይወሰናል፡፡
- ኤንፒኤስ ባለባቸው አካባቢዎች፡-
- ለመረሬ አፈር 157.89 ኪሎግራም ኤንፒኤስ በሄክታር እና 89.13 ኪሎግራም ዩሪያ በሄክታር ሲሆን
- ለቀላል ቀይ አፈር 157.89 ኤንፒኤስ በሄክታር እና 45.65 ኪሎገራም ዩሪያ በሄክታር ነው፡፡
- ኤንፒኤስቢ ባለባቸው አካባቢዎች፡-
- ለመረሬ አፈር 159.15 ኪሎግራም ኤንፒኤስቢ በሄክታር እና 89.35 ኪሎግራም ዩሪያ በሄክታር ሲሆን
- ለቀላል ቀይ አፈር 159.15 ኪሎግራም ኤንፒኤስቢ በሄክታር እና 45.86 ኪሎግራም ዩሪያ በሄክታር ነው፡፡
- ኤንፒኤስዜድ ባለባቸው አካባቢዎች፡-
- ለመረሬ አፈር 172.41 ኪሎግራም ኤንፒኤስዜድ በሄክታር እና 92.6 ኪሎግራም ዩሪያ በሄክታር ሲሆን
- ለቀላል ቀይ አፈር 172.41 ኪሎግራም ኤንፒኤስዜድ በሄክታር እና 49.13 ኪሎግራም ዩሪያ በሄክታር ነው፡፡
- ኤንፒኤስቢዜድ ባለባቸው አካባቢዎች፡-
- ለመረሬ አፈር 173.9 ኪሎግራም ኤንፒኤስቢዜድ በሄክታር እና 92.8 ኪሎግራም ዩሪያ በሄክታር ሲሆን
- ለቀላል ቀይ አፈር 173.9 ኪሎግራም ኤንፒኤስቢዜድ በሄክታር እና 49.34 ኪሎግራም ዩሪያ በሄክታር ነው፡፡
5. አረም፡-
- ጤፍ በብዙ የአየር ንብረት አይነቶች ውስጥ እና የተለያዩ የአፈር አይነቶች ላይ መብቀል ስለሚችል ምርትን እና ምርታማነትን ለሚጎዱ የተለያዩ የአረም አይነቶች የተጋለጠ ነው፡፡
- በጤፍ ማምረት ሂደት ውስጥ የሚመጡ የአረም አይነቶች ሲፔረስ ሮቱንዱስ፣ ፋላሪስ ፓራዶክሳ ኤል (በአማርኛ አሰንዳቦ የሚባለው) እና ኮንቮልቩለስ ኤል. እንደ ስትሪጋ ሄርሞኒቲካ እና ፓርቴኒየም ያሉ የአረም ዝርያዎች ምርትንበከፍተኛ ሁኔታ ሊቀንሱ ይችላሉ፡፡ በአረም ምክንያት የሚከሰት የምርት እጦት ከ23 እስከ 65 በመቶ ይሆናል፡፡
- አረምን መቆጣጠር የሰው ኃይል የሚጠይቅ ቢሆንም ጥሩ ምርት ለማግኘት ግን እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ አረምን በእጅ መንቀል በስፋት የሚተገበር ዘዴ ነው፡፡
- የአረሙ ብዛት አነስተኛ ከሆነ ሰብሉ ከማጎንቆሉ በፊት አንድ ጊዜ በእጅ መንቀል (ሰብሉ ከወጣ ከ15-18 ቀናት ውስጥ) በቂ ነው፡፡ የአረም ብዛት ከፍተኛ ከሆነ የሰብሉ ግንድ በሚረዝምበት ወቅት (ሰብሉ ከወጣ ከ25-30 ቀናት ውስጥ) ለሁለተኛ ጊዜ አረም ነቀላ መካሔድ አለበት፡፡
- በቂ የሰው ኃይል በማይኖር ጊዜ ማንኛውም አይነት አረም ለመቆጣጠር በጥናት የሚመከረው የአረም ማጥፊያ ኬሚካል መጠን መደረግ አለበት፡፡
6. ተባይ እና በሽታን መቆጣጠር፡-
- የጤፍ ዋግ እና የአናት መበስበስ ዋናዎቹ የጤፍ በሽታዎች ናቸው፡፡ ነገርግን በሽታዎች ያንያክል አንገብጋቢ ችግር አይደሉም፡፡
- ሰብልን አፈራርቆ መዝራት ንፁህ እና ጤናማ ዘርን መጠቀም፣ በጊዜ መዝራት፣ እና ቶሎ የሚደርሱ የጤፍ ዘር አይነቶችን መጠቀም የበሽታ ተጠቂነትን ይቀንሳል፡፡
- ደገዛ (ወሎ ቡሽ-ክሪኬት) ዋናው ጤፍ ላይ የሚከሰት ተባይ ነው፡፡ አርሶአደሮች ሰብሎች ከማፍራታቸው በፊት አረምን መንቀል ይችላሉ፣ ይህም ተባዮቹ ምግብ እንዳያገኙ እና በሰብሉ ላይ ያላቸው ብዛት እዲቀንስ ያደርጋል፡፡ ጤፍን በጊዜ መዝራት የተባዮች የምግብ ምንጭ ሳያድግ ጤፉ ቀድሞ እንዲደርስ ያደርጋል፡፡ ይህም የተባዮችን ብዛት በመቀነስ ጉዳትን ይቀንሳል፡፡
7. መሰብሰብ፡-
- ጤፍ የሚሰበሰበው ቅጠሉና ግንዱ ወደ ቢጫነት ሲቀየሩ ሲሆን ይህም በመርገፍ ምክንያት የሚደርሰውን ብክነት ይቀንሳል፡፡
- ምርት መሰብሰብ በተለያዩ መንገዶች ሊሰራ ይችላል፡፡ በአነስተኛ የመሰብሰቢያ መሳሪያ ወይም በባህላዊ ማጨጃ ሊሰበሰብ ይችላል፡፡
- የጤፍ ዘር መጠን አነስተኛ መሆን እና የጤፍ ግንድ የመጋሸብ (የመተኛት) ባህሪ በምርት መሰብሰብ ወቅት ዋና ችግሮች ናቸው፡፡ ይህም የሆነው በማሽንም ሆነ በእጅ መሰብሰብ አስቸጋሪ ስለሚሆን ነው፡፡
- ንፁህ እና ነጭ ጤፍ ከፍተኛ የሆነ ዋጋ ያወጣል፡፡ ስለዚህ ንፁህ ዘር ማምረት የአርሶአደሮችን ገቢ ይጨምራል፡፡
- አርሶአደሮች ጤፍን በባህላዊ መንገድ በእበት በተለቀለቀ አውድማ ላይ ይወቃሉ፡፡ የተሰበሰበው ጤፍ አውድማው ላይ ይበተን እና ምርቱን ከግርዱ ለመለየት ከብቶች ወይም ሌሎች የጋማ ከብቶች እንዲያበራዩት ይደረጋል፡፡ ይህም ምርቱ ከአፈር ጋር እና የከብቶች እበት ጋር እዲነካካ በማድረግ የምርት ጥራትን ይቀንሳል፡፡ ጤፍን በንፋስ አማካኝነት ምርቱን እና ግርዱን ለመለየት መበተን የጤፍ ፍሬዎች እዲባክኑ በማድረግ የጤፍን የገበያ ዋጋ ይቀንሳል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ሌሎች ዋቢዎችን ከየት ማግኘት እችላለሁ
ማስታወሻ፡- ጤፍን ማምረት በተመለከተ ሙያዊ የሆኑ ከባድ ቃላት የሌሉባቸው ተዛማጅ ፅሁፎች በኢንተርኔት ላይ የሚገኙት በጥቂቱ ነው፡፡
ኢንተርኔት ላይ የሚገኙ ዋቢዎች፡-
- The National Academies Press, 1996. Lost Crops of Africa, Volume 1: Grains. Chapter 12: Tef. Pages 213-236. http://www.nap.edu/read/2305/chapter/15#227
- Alemayehu Refera, 2001. Tef: Post-harvest operations. Institute of Agricultural Research Organization, Holetta Agricultural Research Center. http://www.fao.org/3/a-ax445e.pdf
- Hailu Tefera, Getachew Belay, & M. Sorrels (eds.), Narrowing the Rift: Teff Research and Development. Ethiopian Agricultural Research Organization (EARO). Addis Ababa, Ethiopia. Note: This document is the proceedings of a workshop on tef production and contains a lot of very useful information. But it is generally written in technical language. You might want to read the abstracts of the different workshop papers before reading the papers themselves.
- 4. Bay, Kaleab. (2014). Teff: Nutrient Composition and Health Benefits. Ethiopian Development Research Institute and International Food Policy Research Institute, Ethiopian Strategy Support Program, Working Paper #7. https://ebrary.ifpri.org/digital/collection/p15738coll2/id/128334
ቁልፍ ትርጉሞች፡-
- ግሽበት (መተኛት)፡- ተክል በተለይ አዝርዕት በመቅጠኑ ወይም በአየር ሁኔታ በመጎዳቱ ምክንያት ቀጥ ብሎ መቆም ሳይችል፣ ወይም የሰብሉ አገዳ ተክሉን መደገፍ ሳይችል ሲቀር
- ፒኤች (pH):- የአፈርን አሶዳማነትና አልካላይንነት የሚወክል ቁጥር ነው፡፡ 7 ገለልተኝነትን፣ እንዲሁም ከዚህ ያነሱ ቁጥሮች አሲዳማነትን እና ከፍ ያሉ ቁጥሮች አልካላይንነትን ይወክላሉ፡፡
- መርገፍ (መሰባበር)፡- የጤፍ ፍሬዎች ከደረሱ በኋላ መርገፋቸው ወይም መበተናቸው፡፡ ብዙ የጤፍ ዘር አይነቶች ከሌሎች ያልተላመዱ ተክሎች በላይ ዘርን ለዘጅም ጊዜ ይዞ የመቆየት አቅም አላቸው፡፡ ይህም ሰብል መሰብሰብን በጣም ቀላል እና ውጤታማ ያደርጋል፡፡
- መረሬ አፈር፡- ሸክላማ የሆነ እና በደረቅ ወቅት የሚሰነጣጠቅ አፈር ነው፡፡
Acknowledgements
ምስጋና፡-
አዘጋጅ፡- ዶ/ር አበበ አጥላው፣ በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲቲዩት ዋና መስሪያ ቤት የቴክኖሎጂ ማስፋፋት ዳይሬክተር እዲሁም ተጨማሪ ግብአት በወ/ሮ ፅዮን ፍቅሬ፣ በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲቲዩት ስር ባለው የደብረዘይት የግብርና ምርምር ማዕከል የጤፍ ተመራማሪ
በአቶ መለሰ ልይህ፣ በሳሳካዋ ግሎባል 2000 ኢትዮጵያ የሰብል ምርታማነት ማበልፀጊያ ቡድን መሪ በጁላይ 2019 የተከለሰ እና እንዲስማማ የተደረገ
ይህ ማጣቀሻ ሰነድ በፓርትነርሺፕ ፎር ኢንክሉሲቭ አግሪካልቸራል ትራንስፎርሜሸን ኢን አፍሪካ/PIATA/ አጋርነት ከአላያንስ ፎር ግሪን ሪቭሉሽን ኢን አፍሪካ/AGRA/ በተገኘ ድጋፍ ተዘጋጀ