ከጋብቻ በፊት የሚደረግ የግብረ ሥጋ ግንኙነት

Notes to broadcasters

ለስርጭት ባለሙያዎች ማስታወሻ

ከጋብቻ በፊት የሚደረግ የግብረ ሥጋ ግንኙነት በሁለት ሰዎች መካከል ከመጋባታቸው በፊት የሚደረግ ነው። ወጣቶች ከጋብቻ በፊት የፆታ ስሜቶቻቸውን የማወቅ ጉጉት አላቸው። ነገር ግን ምክር ለማግኘት የወሲብ እና የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎቶችን እምብዛም አይጠቅሱም። ይህም በግብረ ሥጋ ግንኙነት ለሚተላለፉ በሽታዎች እና ላልተፈለገ እርግዝና ያጋልጣቸዋል።

ይህ የሬዲዮ ስክሪፕት ከአምስት ሰዎችን እንደ መረጃ ምንጭ ይጠቀማል። በመጀመሪያ አንዲት ወጣት ሴት ልጅ እና አንድ ወጣት ወንድ በጉዳዩ ላይ ስላላቸው ልምድ ይናገራሉ። ከዚያም ሁለት ወላጆች ተስፋ የሚያደርጉትን እና ልምዶቻቸውን ያጋራሉ። በመጨረሻም አንድ የጤና ባለሙያ ደህንነቱ የተጠበቀ የግብረ ሥጋ ግንኙነትን ለማረጋገጥ መደረግ ያለበትን ጥንቃቄ ያብራራሉ።

ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነትን በተመለከተ ተመሳሳይ ፕሮግራም ለማዘጋጀት ይህን ስክሪፕት እንደ መመሪያ ሊጠቀሙት ይችላሉ። እንደ መደበኛ ፕሮግራምዎ አካል ለማቅረብ ከወሰኑ፣ ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸውን ሰዎች የሚወክሉ የድምጽ ተዋናዮችን ወይም የፕሮግራም መሪዎችን መምረጥ ይችላሉ። ይህን የሚያረጉ ከሆነ እባክዎን በፕሮግራሙ መጀመሪያ ላይ ለአድማጮችዎ የሚሰሙት የድምጽ ተዋናዮች ወይም የፕሮግራም መሪዎቹ እንጂ ትክክለኛ ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው ሰወች እንዳልሆኑ ያሳውቋቸው።

ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነትን የሚመለከቱ ፕሮግራሞችን ማዘጋጀት ከፈለጉ ልምድ ካላቸው ሰዎች እና የጾታዊ እና የስነ ተዋልዶ ጤና ባለሙያዎችን ያነጋግሩ። ለምሳሌ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ሊጠይቋቸው ይችላሉ፦

  • ከጋብቻ በፊት የግብረ ስጋ ግንኙነት መፈጸም የሚያስገኘው ጥቅም ምንድን ነው?
  • ከጋብቻ በፊት የግብረ ስጋ ግንኙነት የሚፈጽሙ የትዳር ጓደኞችን ጤንነት ለመጠበቅ ምን እርምጃዎች ሊወሰዱ ይችላሉ?
  • ሴቶች እና ወንዶች ሳይገለሉ ወይም በድብቅ አገልግሎት ማግኘት ሳያስፈልጋቸው የጾታዊ እና የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎቶችን እንዴት ማግኘት ይችላሉ?

የስችሪፕቱ ርዝማኔ የሙዚቃ ግብዣ፣ መግቢያ እና መውጫን አካትቶ በግምት 20 ደቂቃ ይፈጃል

Script

ማጀቢያ የመሳሪያ ሙዚቃ፤ ድምጹ አየደበዘዘ የሚወጣ

የፕሮግራም መሪ፦
ሰላም ጤና ይስጥልን የዛሬው ፕሮግራማችን ከጋብቻ በፊት ግብረስጋ ግንኙነትን የሚመለከት ነው።

ይህ በዋነኛነት በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶችን ኣና ያልተጋቡ ጥንዶችን የሚመለከት ርዕሰ ጉዳይ ነው፣ ምክንያቱም አብዛኛውን ጊዜ ስለ ጾታዊ ግንኙነት እና ከጋብቻ በፊት የግብረ ሥጋ ግንኙነት ስለመፈጸም የማወቅ ጉጉት ያላቸው ስለሆነ ነው።

ጥያቄዎቻችንን ለመመለስ አምስት እንግዶች ይኖሩናል። እነርሱም፡ አቡባካር ትራኦሬ እና ማርያም ኮኔ፣ ሁለቱም ወጣት ጋዜጠኞች ናቸው፣ ጥንዶቹ ሬቸል እና ድሪሳ ኮሊባሊ፣ እንዲሁም የጾታዊ እና የስነ ተዋልዶ ጤና ኤክስፐርታችን ዶ/ር ማማዱ ኮሊባሊ ናቸው። መልካም ቆይታ!

ማጀቢያ የመሳሪያ ሙዚቃ ፤ድምጹ አየደበዘዘ የሚወጣ

የፕሮግራም መሪ፦
ሰላም ማርያም፤ ጥሪያችንን ተቀበልሽ ስለተገኘሽ እናመሰግናለን። የ19 አመት ወጣት ጋዜጠኛ ነሽ። በማሊ ሰላምን የሚያበረታታው ዴንሚሰንው ኩንካን የአማርኛ ትርጉሙ ወጣቶችን እናውራ የተሰኘ ፕሮግራምም መሪ ነሽ። ከጋብቻ በፊት ግብረስጋ ግንኙነትን በሚመለከት ምን ልትይን ትችያለሽ?

ማሪያም ኮኔ፦
በእኔ አስተያየት ከጋብቻ በፊት የሚደረግ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ጠቃሚ ነው ምክንያቱም የወደፊት አጋሮች በግብረ ሥጋ ግንኙነት አማካኝነትም እንዲተዋወቁ ያስችላቸዋል። ህጋዊ ጋብቻ ከመፈጸማቸው በፊት እያንዳንዳቸውን የትዳር ጓደኞቻቸው የሚወዷቸውን ወይም በጾታዊ ግንኙነት እስከ ምን ድረስ መግፋት አንደሚችሉ ያሳውቃቸዋል። ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም የሚያስገኛቸው ጥቅሞች አዲስ ተጋቢዎች እርስ በርስ እንዲተዋወቁና የመቀራረብ ስሜት እንዲፈጥሩ ማስቻል ነው።

የፕሮግራም መሪ፦
በከጋብቻ በፊት ወሲብ ምክንያት ሊፈጠሩ የሚችሉ አንዳንድ መዘዞች ምንድን ናቸው?

ማሪያም ኮኔ፦
አንዳንድ ጊዜ ከጋብቻ በፊት የሚደረግ የፆታ ግንኙነት ጋብቻን ሊያፈርስ ይችላል። በቅድመ አያቶች ልምዶች ላይ የተመሰረተው የማሊ ባህል እንደሚለው፤ የሠርግ ምሽት ለሁለቱም ቤተሰቦች አስፈላጊ ጊዜ ነው። አዲስ ተጋቢዎች አንድነታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የአልጋቸውን ነጭ ሽፋን ደም እንዲታይበት ባህሉ ይጠይቃል። እንደሚጠበቀው ከታየ የሙሽራዋ ቤተሰቦች ከሠርጉ ድግስ በክብር ይወጣሉ። አንሶላ ላይ ደም ካልታየ ለሙሽሪት እና ለቤተሰቧ እንደ ውርደት ይቆጠራል። ዛሬ ከሃይማኖት ወይም ከባህል ጋር ላለመጣረስ ከጋብቻ በፊት ስለሚደረግ ግብረ ስጋ ግንኙነት በግልፅ ማውራት በጣም ከባድ ነው።

የፕሮግራም መሪ፦
በማሊ ከጋብቻ በፊት የሚደረግ የግብረ ስጋ ግንኙነትን በርካታ ሰወች እንደ ታላቅ ነውር የዩታል። ለምንድነው?

ማሪያም ኮኔ፦
ይህ የተከለከለው ከቅድመ አያቶቻችን ጊዜ አንስቶ ነው። በዚያን ጊዜ ወሲብ የተቀደሰ ስለነበር ሃሳቡ መጀመሪያ ሳይነሳ ስለሱ ለማውራት ግፊት ካልተደረገ አይወራም ነበር። ወጣቶች ስለዚህ ጉዳይ መጠየቅ አልቻሉም። ይህ የነበረው ወላጆቻቸው ወይም አያቶቻቸው እንደ ግርዛት ባሉ ልማዶች ስለ ወሲብ መነጋገር እስኪጀምሩ ድረስ ነው። በጥንት ጊዜ እነዚህ ልማዳዊ ድርጊቶች የሚፈጸሙት ልጆች ወደ ጉርምስና ዕድሜ ሲቃረቡ ነው

የፕሮግራም መሪ፦
ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነትን በተመለከተ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እምነቶች ምን ይላሉ?

ማሪያም ኮኔ፦
በባህላዊ እና በሃይማኖታዊ እምነታችን መሰረት የግብረ ሥጋ ግንኙነት ከጋብቻ በፊት የተከለከለ ነው። ይህ ክልከላ የመጣው ማንኛውም ወጣት ሴት ያገባች ድንግል ናት ከሚለው ወግ ነው። ሆኖም ይህ ክልከላ በሙሽራው ላይ አይተገበርም።

የፕሮግራም መሪ፦
ወጣት ሴት እንደመሆንሽ መጠን ስለ ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነትን በሚመለከት ስላረግሽው ውሳኔ ባሕላዊና ሃይማኖታዊ እምነቶች ተጽዕኖ አሳድረዋል?

ማሪያም ኮኔ፦
አዎን፣ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ እምነቶች ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነትን በሚመለከት ስለነበረኝ ውሳኔ ላይ ተጽዕኖ አሳድረዋል። ወላጆቼን እንዳላሳፍር በመፍራት ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት ከመፈጸም መቆጠቡ አስፈላጊ ነበር። ነገር ግን ወንድና ሴት ጓደኞቼ ስለ ጉዳዩ በሚናገሩት ነገር የተነሳ የማወቅ ጉጉት ሰረጸብኝ። በጣም አስቸጋሪው ነገር ደግሞ የወንድ ጓደኛዬም ለወሲብ አዲስ ነበር። እርግዝና እንዳይከሰት ወይም ተላላፊ በሽታ እንዳይኖር ምን ማድረግ እንዳለብን የሚነግረን ማንም አልነበረም። የግብረ ሥጋ ግንኙነት ማድረጋችንን ለመቀጠል እንፈልግ ነበር ነገር ግን ከእያንዳንዱ የግብረ ሥጋ ግንኙነት በኋላ ሰቀቀናችን የማያቋርጥ ነበር።

የፕሮግራም መሪ፦
ሴቶች እና ወንዶች ሳይገለሉ ወይም በድብቅ አገልግሎት ማግኘት ሳያስፈልጋቸው የጾታ እና የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎትን በቀላሉ ማግኘት የሚችሉት እንዴት ይመስልሻል?

ማሪያም ኮኔ፦
ከጋብቻ በፊት ጾታዊ ግንኙነትን ለማወቅ የሚደፍሩ ልጃገረዶች ላይ የሚደርሰውን መገለል ማቆም አለብን። በሀገራችን ታዋቂ በሆኑ የሬዲዮ ጣቢያዎች ላይም ለወላጆች የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞችን ማዘጋጀት አለብን። ወጣቶች የሚያስፈልጋቸውን እውቀት እንዲያገኙም የጾታዊ ጤና ትምህርት በትምህርት ቤቶች ሊሰጥ ይገባል።

የፕሮግራም መሪ፦
አመሰግናለሁ ማርያም። ስቱዲዮ ውስጥ አብሮን የ21 አመቱ አቡባካር ትራኦሬ አለ። በባማኮ በሚገኘው በኤኮል ሱፕሪዩር ደ ጆርናሊዝም ዴ ሳይንስ ደ ላ ኮሚኒኬሲዮ የጋዜጠኝነት ተማሪ እና የአሶሲዬሲዮን ዴ ዡኔ ኤንጌዠኤ ፖር ላ ፔይ ፕሬዝዳንት ነህ። በማሊ ውስጥ ሰዎች ከጋብቻ በፊት ፆታዊ ግንኙነት ይፈጽማሉ?

አቡበከር ትራኦሬ፦
በማሊ ብዙ ሰዎች ከጋብቻ በፊት የግብረስጋ ግንኙነት ይፈጽማሉ። ማናችንም በትዳር ውስጥ ባንሆንም ከጓደኞቼ መካከል በጣም ጥቂቶቹ ናቸው ወሲብ ፈጽመው ስላለማወቃቸው በዕርግጠኝነት የሚናገሩት።

የፕሮግራም መሪ፦
ታዲያ ድንግልናን መጠበቅ እስከ ጋብቻ ድረስ ያለው እምነት ከየት የመጣ ነው?

አቡበከር ትራኦሬ፦
ይህ እምነት በወላጆቻችን ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ ቆይቷል። ሃይማኖት የመጣው ይህንን እምነት ለማጠናከር ነው። ነገር ግን ይህ የተደነገገው በዋነኝነት ለወጣት ልጃገረዶች ነው። ዛሬ ላይ ግን ይህ እምነት ባላገቡ ሴቶችም ሆነ ወንዶች እየተከበረ እንዳልሆነ በግልፅ እንገነዘባለን። ይህንን እምነት ለመለወጥ መጣር መጀመር አለብን።

የፕሮግራም መሪ፦
እንዳላገባ ሰው፤ ከጋብቻ በፊት ጾታዊ ግንኙነት መፈጸምን በሚመለከት ባደረግከው ውሳኔ ላይ ባሕላዊና ሃይማኖታዊ እምነቶች ተጽዕኖ አሳድረዋል?

አቡበከር ትራኦሬ፦
አይ አላሳደረብኝም። ከወሲብ በመቆጠብ ወላጆቻችንን ማክበር እንደምንፈልግ እውነታ ነው። ነገር ግን የወሲብ ስሜቴ መቀስቀስ ሲጀምር፣ እራሴን ለማርካት ከመሞከር ይልቅ ወጣት ሴት ጋር መሄድን እመርጥ ነበር።

የፕሮግራም መሪ፦
የጾታዊ ግንኙነትን በሚመለከት ጤና አገልግሎቶችን ማግኘት ትችላለህ?

አቡበከር ትራኦሬ፦
በዋና ከተማው ውስጥ የጾታዊ ግንኙነትን በሚመለከት ጤና አገልግሎቶች እንዳሉ አውቃለሁ ነገር ግን አንድም ሄጄ አላውቅም። በእድሜዬ ወጣትነት ሳቢያ ሰው ሲያፈጥብኝ ወይም ደግሞ በጾታ እና በስነ-ተዋልዶ ጤና አማካሪዎች መሰደቡ ያሳፍረኝ ነበር።

የፕሮግራም መሪ፦
ወንዶች በተለይም ወጣት ወንዶች ሳይገለሉ ወይም በድብቅ አገልግሎት ማግኘት ሳያስፈልጋቸው የጾታ እና የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎትን በቀላሉ ማግኘት የሚችሉበትን መንገድ ምን መለወጥ አለበት ብለህ ታስባለህ?

አቡበከር ትራኦሬ፦
የመረጃ እና የግንዛቤ ክፍለ ጊዜዎችን ልናዘጋጅላቸው ይገባል። በዚህ መንገድ፣ የጤና አገልግሎት እነሱን ለመርዳት እና ደህንነታቸውን ለመጠበቅ እንደሚገኝ ይገነዘባሉ።

ማጀቢያ ሙዚቃ፦
አጠር ያለ ማጀቢያ ሙዚቃ፣ ከዚያ ፕሮግራም መሪ ድምጽ ስር እየደበዘዘ የሚሄድ

የፕሮግራም መሪ፦
በስቱዲዮ ውስጥ ለብዙ ዓመታት በትዳር የቆዩ እና ሁለት ልጆች አንድ የስምንት ዓመት ወንድ እና የአምስት ዓመት ሴት ልጅ ያሏቸው ወይዘሮ ሬቸል እና አቶ ድሪሳ ኮሊባሊ የተባሉ ጥንዶች ይገኛሉ። ጥንዶቹ ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነትን በተመለከተ ተሞክሮዎች ያካፍሉናል።

ወይዘሮ ሬቸል ኮሊባሊ፣ ምን ይመስልሻል፡- ወንዶች ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነትን በሚመለከቱ ውሳኔዎች ውስጥ ይሳተፋሉ ብለሽ ታምኛለሽ? ካልሆነ ለምን?

ሬቸል ኮሊባሊ፦
ብዙውን ጊዜ ወንዶች ከጋብቻ በፊት ወሲብን በሚመለከት ውሳኔዎች ውስጥ አይሳተፉም። ምክንያቱም በተለምዶ ከጋብቻ በፊት ወንዶች ድንግል እንዲሆኑ አይጠመጠበቅ ነበር። በዚህ ረገድ በህብረተሰቡ ዘንድ ምንም ዓይነት የሞራል ግዴታ አልነበራቸውም። ነገር ግን ዛሬ ባለው ህብረተሰብ ውስጥ የግብረ ስጋ ግንኙነት ደህንነቱ የተጠበቀ፣ የጋራ ስምምነት እና ሁለቱንም አጋሮች የሚያከብር መሆኑን ማረጋገጥ የሁለቱም አጋሮች ውሳኔ ነው።

የፕሮግራም መሪ፦
አቶ ድሪሳ ኮሊባልይ፣ ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት ለመፈጸም በሚደረጉ ውሳኔዎች ላይ ወንዶችም መሳተፍ አለባቸው ብለው ያስባሉ? መልስዎ አዎ ወይም አይ ከሆነ ለምን እንደሆነ ያብራሩልን።

ድሪሳ ኮሊባሊ፦
በፍጹም! ከጋብቻ በፊት ድንግል መሆን አይጠበቅባቸውም። እንደውም በባህላችን ወንዶች እንደ “ዋና ጾታ” ተደርገው ይወሰዳሉ። ስለዚህ ወንድ ሚስቱን በጾታዊ ግንኙነት ለማርካት ልምድ ቢኖረው ይመረጣል። አሁን አሁን አንዳንድ ጥንዶች ከጋብቻ በፊት የፆታዊ ግንኙነት ቢፈጽሙም ያንን የማያደርጉም አሉ።

የፕሮግራም መሪ፦
ሬቸል እንዳለችው ሴቶች ከጋብቻ በፊት የግብረ ሥጋ ግንኙነት በመፈጽሙ መገለል ሊደርስባቸው እንደሚችል ጠቁማለች፣ ወንዶች ግን አይገለሉም። ይህ የሆነው ለምን ይመስልሃል?

ድሪሳኮሊባሊ፦
በባህላችን እና ሀይማኖታችን መሰረት ሴት ጋብቻ ወደ ጋብቻ በምትገባበት ጊዜ ድንግል ሆና መገኘት አለባት። ሰወች ይህንን የሚያዩት ወላጆቿ በትክክል እንዳሳደጓት የሚያመላክት ነው ብለው ነው። አንዲት ሴት ከጋብቻ በፊት ስለ ወሲብ የምታውቅ ከሆነ ሴሰኛ እንደሆነች ትቆጠራለች። በማህበረሰቧ እንቅስቃሴዎች ከመሳተፍ ትገለላለች፣ አንዳንዴም ስድብ ይደርስባታል። ዛሬ ላይ ይህን የምናየው በሴቶች ላይ እንደሚፈጸም ኢፍትሃዊነት ነው።

የፕሮግራም መሪ፦
ከራስሽ ልጆች ጋር ስለ ጾታዊ ግንኙነት እና ጤንነት ለማውራት ዝግጁ ነሽ? ለምን ወይም ለምን አይሆንም? ምላሽሽ አዎ ወይም አይ ከሆነ አብራሪልን።

ሬቸል ኮሊባሊ፦
አዎን። ስለ ወሲባዊ ጤንነታቸው ለደህንነታቸው እና ለእድገታቸው መነጋገር አስፈላጊ ነው። እኛ ወላጆቻችን የሠሩትን ተመሳሳይ ስህተት መሥራት አንፈልግም። እውነት ነው እኛን እየተንከባከቡን መስሏቸው ስለ ጉዳዩ በግልጽ አላወሩንም። ዛሬ ግን አለማወቅ እንክብካቤ እንዳልሆነ እናውቃለን። ይህንን ከልጆቻችን ጋር መወያየቱን እንመርጣለን።

የፕሮግራም መሪ፦
እናመሰግናለን አቶ እና ወ/ሮ ኮሊባሊ። በመቀጠል ያለን የጾታዊ ግንኙነት እና የስነ ተዋልዶ ጤናን የሚከታተል ዶክተር ነው። በአሁኑ ወቅት በባንካስ ሪፈራል ጤና ጣቢያ እየሰራ ሲሆን ወጣት ልጃገረዶችን እና ሴቶችን በወሲባዊ ሕይወታቸው ላይ የጤና አገልግሎት የመስጠት ሃላፊነት አለበት። ዶ/ር ማማዱ ኮሊባሊ ይባላል። እስቲ ንገረን ዶ/ር ኮሊባሊ ከህጋዊ እድሜ በፊት የሚደረግ የፆታ ግንኙነት እና ከጋብቻ በፊት የሚደረግ የፆታ ግንኙነትን መካከል ያለው ልዩነት ምንድነው?

ዶ/ር ማማዶ ኮሊባሊ፦
ከህጋዊ እድሜ በፊት የሚደረግ ጾታዊ ግንኙነት ከ18 አመት በታች በሆኑ ሁለት ግለሰቦች መካከል የሚደረግ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ነው። ከጋብቻ በፊት የሚደረግ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ደግሞ ከሕጋዊ ጋብቻቸው በፊት የጾታ ግንኙነት የፈጸሙ ሁለት ሰዎችን ያመለክታል።

የፕሮግራም መሪ፦
ከጋብቻ በፊት ወሲብ አዲስ ክስተት ነው? ከጋብቻ በፊት የሚደረግ የግብረ ሥጋ ግንኙነት የጤና ጥቅሞች አሉት?

ዶ/ር ማማዶ ኮሊባሊ፦
ከጋብቻ በፊት የሚደረግ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ምድር ሲፈጠር ጀምሮ የነበረ ክስተት ነው። እኔ እስከማውቀው ድረስ ከጋብቻ በፊት የሚደረግ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ምንም ዓይነት የጤና ጥቅም የለውም።

የፕሮግራም መሪ፦
ሰዎች ከጋብቻ በፊት የግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈጸማቸው ይታወቃል፤ ታዲያ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ጤናቸውን እንዴት ሊጠብቁ ይችላሉ? ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት ለያስከትላቸው የሚችለን መዘዝ ለመከላከል ወይም ለመቋቋም ያላገቡ ሰዎች ምን ዓይነት ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው?

ዶ/ር ማማዶ ኮሊባሊ፦
ከጋብቻ በፊት የግብረ ሥጋ ግንኙነት ለመፈጸም ሲፈለግ የአባላዘር በሽታዎችን እና ኤችአይቪን ለመከላከል ኮንዶም መጠቀም ይገባል። ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከላከል የእርግዝና መከላከያ ዘዴን መጠቀም ያስፈልጋል። ለምክር አገልግሎት ለሚመጡ ወጣት ሴቶች በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ ኢንፌክሽኖችን ወይም የእርግዝና ምርመራ እና እንደፍላጎታቸው ሌሎች አገልግሎቶችን እንሰጣቸዋለን። የልጅቷ ሁኔታ ከታወቀ በኋላ ተገቢውን ህክምና እንሰጣለን። ጤንነቱን ለማረጋገጥ አጋሯን እንድታመጣም እንጠይቃታለን።

የፕሮግራም መሪ፦
በእርስዎ ልምድ፣ ላላገቡ ሰዎች የጾታዊ ግንኙነትን በሚመለከት የሚሰጡ የጤና አገልግሎቶች ተደራሽ ናቸው? ለምሳሌ፤ ስለ የወሊድ መከላከያ ጥቅም ላይ ማዋል ውሳኔዎች ወይም የጤና አገልግሎቶች ለአባላዘር በሽታ ምርመራ የሚሰጡ ክሊኒኮች?

ዶ/ር ማማዶ ኮሊባሊ፦
ያላገቡ ሰዎች ሁሉንም የጾታዊ ግንኙነትን በሚመለከት የሚሰጡ የጤና አገልግሎቶች እና የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎቶችን በማሊ ባሉ የጤና ተቋማት ሊያገኙ ይችላሉ። እነዚህ አገልግሎቶች በመንግሥት ወይም ዓለም አቀፍ ኤጀንሲዎች በቀጥታ ድጎማ ስለሚደርጉላቸው ይገኛሉ።

የፕሮግራም መሪ፦
የጾታዊ ግንኙነትን በሚመለከት ጤና አገልግሎቶችን ለማግኘት በሚመጡ ያላገቡ ሰዎች ላይ በማህበረሰቡ ዘንድ የሚደርስባቸው መገለል አለ?

ዶ/ር ማማዶ ኮሊባሊ፦
በጤና ጣቢያችን የሚሰጠውን አገልግሎት በሚመለከት በፆታ በማህበራዊ ሁኔታ ላይ ወይም የጋብቻ ሁኔታ ላይ የተመሰረተ መድልዎ የለም። ለምሳሌ፣ በባንካስ ሪፈራል ጤና ጣቢያ፣ ለታዳጊ ወጣቶች ፍላጎት የተቀረጸ አገልግሎቶች አዘጋጅተናል። ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት ለመፈጸም ለሚያስከትላቸው መዘዞች በበለጠ የተጋለጡ ናቸው። ተቀብለን ካዳመጥናቸው በኋላ ሳንታዘባቸው የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎቶችን ስለመጠቀም በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ እንዲወስኑ እናግዛቸዋለን። ዋናው አላማችን ለእነዚህ ወጣቶች እና ያላገቡ ጥንዶች እንደየፍላጎታቸው አገልግሎት መስጠት ነው።

የፕሮግራም መሪ፦
በእርስዎ አስተያየት፣ ያላገቡ ጥንዶች በማህበረሰቡ መገለል አለባቸው?

ዶ ር ማማዶ ኮሊባሊ፦
አንዳንድ ጊዜ ከጋብቻ ውጭ ያረገዙ ወጣት ሴቶች የሚደርስባቸውን መገለል በሚመለከት ቅሬታዎች ይደርሱናል። ቅሬታዎቹን የሚያደርሱን እኩዮቻቸው፣ የቤተሰባቸው አባላት ወይም የሃይማኖታዊ ማህበረሰብ ውስጥ ያሉ ናቸው።

የፕሮግራም መሪ፦
መገለልን ለመቀነስ እንዲሁም የጾታዊ ግንኙነትን በሚመለከት የሚሰጡ የጤና አገልግሎቶች እና የግብረስጋ ግንኙነት ላይ የሚሰጡ የጤና ትምህርቶችን ለማሻሻል ምን ለውጦች መኖር አለባቸው?

ዶ/ር ማማዶ ኮሊባሊ፦
መገለልን እና መድልዎ ለመቀነስ የሚያስፈልገው ሁሉም ሰው መብት እንዳለው እና እነዚህ መብቶች መከበር እንዳለባቸው መረዳት ነው። እነዚህ መብቶች ያሚያካትቱት ደግሞ የጤና፣ የትምህርት እና ለራስ የመወሰን መብቶች ናቸው። ዛሬ በሀገራችን ሁሉም ሰው መሰረታዊ ማህበራዊ አገልግሎቶች ተጠቃሚ ለማድረግ እና ተመሳሳይ እድል እንዲያገኝ በክልሉ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው።

የፕሮግራም መሪ፦
ለጥያቄዎቻችን መልስ ለመስጠት ጊዜያቸውን ሰውተው እዚህ የተገኙትን ወጣቶች እናመሰግናለን። እንዲሁም በጉዳዩ ላይ የቤተሰብ እይታን የሚዳስስ አመለካከት ያጋሩንን የኮሊባሊ የትዳር ጥንዶችን እናመሰግናለን። የሥነ ተዋልዶና የጾታዊ ግንኙነት ጤና አገልግሎትን ማጣቀስ አስፈላጊ መሆኑን ያሳወቁንን የጾታዊ እና ሥነ ተዋልዶ ጤና ባለሙያም ሳናመሰግን አናልፍም።

በመጨረሻም፣ ጾታዊ ግንኙነት ከጋብቻ በፊትም ሆነ በኋላ ሊመጣ የሚችል የአባላዘር በሽታን ወይም ያልተፈለገ እርግዝናን የሚያስከትልበት ሁኔታ ይኖራል። ለዚህ ደግሞ የሚመከረው መፍትሔ በጾታዊ ግንኙነት ትምህርትን ነውር አርጎ መቁጠር በመተው ከወጣቶች ጋር ከጉርምስና ጊዜ ጀምሮ ስለ ጾታዊ ጤና በግልጽ ማውራት መድፈር ነው። ይህም የጾታዊ ጤና አገልግሎቶችን በቀላሉ እንዲያገኙ እና የወደፊት ህይወታቸው ጥሩ እንዲሆንም ዋስትና ይሆናል። ቀደም ብለው ያገቡ ጥንዶች የጾታዊ ግንኙነት እና የስነ ተዋልዶ ጤንነታቸውን በተሻለ ሁኔታ ለመቆጣጠር እነዚህን አገልግሎቶች ማግኘት ይችላሉ።

አድማጮቻችን ስላዳመጣችሁን እናመሰግናለን። በሌላ ፕሮግራም እንመለሳለን። እስከዛው፣ ቸር እንሰንብት።

አጃቢ ሙዚቃ፦
እየደበዘዘ የሚሄድ ማጀቢያ ሙዚቃ

Acknowledgements

ምስጋና
አዘጋጅ፦ አሲባቪ ሲካ ኢዛቤል አግቦግቤ፣ ፍሪላንስ ጋዜጠኛ
ገምጋሚ፦ ማይሞናቶው ቱሬ፣ በማሪ ስቶፕስ ማሊ የሥርዓተ-ፆታ ባለሙያ

ውስጥ በስርዓተ-ፆታ ላይ የተመሰረቱ ጥቃቶችን መከላከል እና ምላሽን ለማጠናከር በማሊው “እዚህ – የሴቶች ደህንነት በማሊ” ፕሮግራም የተዘጋጀ። ፕሮጀክቱ የሚተገበረው በእዚህ – ኤመኤሰይ ማሊ ጥምረት ከፋርም ሬዲዮ ኢንተርናሽናል እና በአፍሪካ ሴቶች በህግ እና በልማት ከግሎባል ጉዳዮች ካናዳ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ነው።

Information sources

ቃለ መጠይቆች፦

ማሪያም ኮኔ፣ እድሜ 19፣ ከዴንሚስንው ኩንካን ሬዲዮ ፕሮግራም ጋር ወጣት ጋዜጠኛ። ቃለ መጠይቁ የተከናወነው ነሃሴ 3 ቀን 2014 ዓ.ም. ነው።

አቡበከር ትራኦሬ፣ እድሜ 21፣ በባማኮ በሚገኘው በኤኮል ሱፕሪዩር ደ ጆርናሊዝም ዴ ሳይንስ ደ ላ ኮሚኒኬሲዮ የጋዜጠኝነት ተማሪ ነው። ቃለ መጠይቁ የተከናወነው ነሃሴ 3 ቀን 2014 ዓ.ም. ነው።

 

አቶ ድሪሳ ኮሊባሊ እና ወ/ሮ ሬቸል ኮሊባሊ ለ10 አመታት በትዳር የቆዩ ጥንዶች ሲሆኑ የስምንት አመት ወንድ ልጅ እና የአምስት አመት ሴት ልጅ ወላጆች ናቸው። ቃለ መጠይቁ የተከናወነው ነሃሴ 4 ቀን 2014 ዓ.ም. ነው።

ዶክተር ማማዱ ኮሊባሊ፣ በባንካስ ሪፈራል ጤና ጣቢያ የፆታዊ ግንኙነት ጤና ሀላፊ ሐኪም። ቃለ መጠይቁ የተከናወነው ነሃሴ 4 ቀን 2014 ዓ.ም. ነው።