Farming wisdom: የእርሻ ጥበብ እርሻ አቀባ ለተሻለ ኑሮ

Notes to broadcasters

Download and edit this resource as a Word document.

ለአዘጋጁ ማስታወሻ

አንድ ሶስተኛ የሚሆን የኢትዮጵያ የእርሻ መሬት በከፋ ወይም እጅግ በከፋ ሁኔታ ተሸርሽሯል፡፡

በመጀመሪያ በሰሜን አሜሪካ የተተገበረው የእርሻ ዕቀባ ዘዴ ባለፉት ሀምሳ አመታት በፍጥነት በመላው አለም ተግባራዊ ሆኖ በዛቢያ መቆፈር የእርሻ ዕቀባ ዋና ክፍል ሲሆን የአፈር መሸርሸርን የሚቀንስና በአጠቃላይ የአፈሩን ጤንነት የሚጨምር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ግን ብዙ የልማት ፕሮጀክቶች የሚመክሩት በተደጋጋሚ ማረስ ለተባይ ማጥፊያነትና ሌሎች አላማዎች እንዲጠቅም ነው፡፡

ይህ ድራማ ደጎች ተብሎ በሚጠራ ምናባዊ የኢትዮጵያ የገጠር ቀበሌ ስላሉ አርሶ አደሮች ነው:: ደጎች ወረዳ በመባል የሚታወቀው የገጠር ወረዳ የአየር ፀባዩ ፀሃያማ ሲሆን ለእርሻ የሚጠቀሙበት መሬት የአሸዋማነት ባህርይ አለው፡፡ እናም በወረዳው የሚገኙ የገነቱና የሰላሙ ቀበሌ አርሶ አደሮች የሚከተሉት ልማዳዊ የአስተራረስ ዘዴ መሬቱን ለንፋስና ለጎርፍ ያጋልጠዋል፡፡ ደጋግመው ቢያርሱም ምርታቸው አነስተኛ ነው፡፡

እናም አንዳንድ የሰላሙና የገነቱ ቀበሌ አርሶ አደሮች በአካባቢያቸው የሚንቀሳቀሱ የግብረሰናይ ድርጅቶች በእርሻ አቀባ ታቅፈው ማሳቸውን በተደጋጋሚ በማረስ ለንፋስና ለጎርፍ ከመጋለጥ ይልቅ በዛቢያ ቆፍረው በማሳ ሽፋን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ እንዲዘሩ ያሰለጠንዋቸውን ስልጠና ተግባራዊ ማድረግ ጀምረዋል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ስለተጠራጠሩ ለመተግበር ተቸግረዋል፡፡ ዛሬ በእርሻ አቀባ ባለሞያው አባቡ በኩል የገነቱ ቀበሌ ነዋሪዎች ወደ ሰላሙ ቀበሌ ሄደው- ተሞክሮውን እንዲያዩ ጥሪ እየተላለፈ ነው፡፡ የአቶ ንጉስ ባለቤት መሰሉም በትግበራው ደስተኛ ናቸው፡፡ ልጃቸው ፈለቁም ብትሆን በማሳ ሽፋን በዘሩት የጎመን ምርት ሽያጭ የኮሌጅ ትምህርትዋን መከታተል ጀምራለች፡፡ ባለሙያው አባቡ ታዲያ በገነቱ ቀበሌ ያሉት ነዋሪዎች ይህንን ተሞክሮ እንዲያዩ በአንድ ወጣት አማካኝነት ጥሪ እያስተላለፈ ነው፡፡

ድራማው የሚጀምረው ለአርሶ አደሮች በሚደረገው ጥሪ ነው፡፡ ይህንን ድራማ የአፈርን ለምነት መቀነስ፣ የምርት ማነስ ችግርን እና የአፈር መሸርሸርን መቅረፍ የሚያስችሉ የእርሻ እቀባ ዘዴዎች የሆኑትን በዛቢያ መቆፈር፣ አፈራርቆ መዝራት፣ ቀላቅሎ መዝራት፣ እና ማሳን መሸፈን የመሳሰሉ ዘዴዎችን በተመለከተ ተመሳሳይ ፕሮግራም ለመስራት እንደመነሻ መጠቀም ይቻላል፡፡ ወይም ተናጋሪዎቹን የሚወክሉ የድምፅ ተዋናዮችን በመጠቀም የመደበኛው የአርሶ አደሮች ፕሮግራም አካል በማድረግ ሊዘጋጁ ይችላል፡፡

ድራማው አስራ ሁለት ትዕይንቶች አሉት፡፡ በፕሮግራም መልክ ለማዘጋጀት ከፈለጉ አንዱ አማራጭ በቀን አንድ ወይም ሁለት ትዕይነት ለተከታታይ ቀናት ማቅረብ ነው፡፡ ትዕይንቶቹ በርዝመታቸው ይለያያሉ፡፡ ከሶስት እስከ አራት ወይም ከሰባት እስከ ስምንት ደቂቃ ይረዝማሉ፡፡
ከድራማው ቀጥሎ አርሶ አደሮችን ወይም ሌሎች ባለሙያዎችን ስለ እርሻ እቀባ ጥቅሞች እና ተግዳሮቶች ቃለ-መጠይቅ ማድረግና ማቅረብ ይቻላል፡፡ አርሶ አደሮቹን የትኞቹን ዘዴዎች እንደተጠቀሙና ምን ተግዳሮት እንዳጋጠማቸው መጠየቁን ያረጋግጡ፡፡ አድማጮች እንዲደውሉ ወይም ጥያቄዎችን እና አስተያየቶች በፅሁፍ መልዕክት እንዲልኩ ይጋብዙ፡፡

የውይይት እርዕስቶች፡-
ባዩ የእርሻ እቀባን መተግበሩ ትክክለኛ ውሳኔ ነው ብለው ያስባሉ?
አርሶ አደሮች ማሳቸውን ለመሸፈን በቂ ሽፋን ማግኘት ቢፈልጉ በዚህ አካባቢ ምን ምን አማራጮች አላቸው?
በዚህ አካባቢ የእርሻ እቀባን መተግበር ምን ምን ተግዳሮች አሉት?አርሶ አደሮችስ እነዚህን ተግዳሮቶች እንዴት ማለፍ ይችላሉ?

Script

ገፀ ባህሪዎች፡-

ባዩ አባተ፡-
ዕድሜ 50፣ የወይኒቱ ባለቤት፣ የተከበረ እና ሀብታም ገበሬ፣ በዘልማድ የሚያርስና ጥሩ የእርሻ ምርት የሌለው ነገር ግን በእንስሳት እርባታ የሚተዳደርና ጥሩ ኑሮ ያለው፡፡

ወይኒቱ ተሻለ፡-
ዕድሜ 36፣ የአቶ ባዩ ባለቤት እና የአራት ልጆች እናት፣ ተመስገን የራሱ መሬት እንዲኖረው የምትፈልግና ባለቤቷ እንዲሰጠው ሁሌም የምትጠይቅ፡፡

ተመስገን ባዩ፡-
ዕድሜ 20፣ የአቶ ባዩ እና የወይኒቱ ልጅ አስራ ሁለተኛ ክፍል የጨረሰ ነገር ግን መሬትም ሆነ ስራ የሌለው እናት እና አባቱን በከብት እርባታ የሚያግዝ ከፈለቁ ጋር በአንድ ክፍል የተማረና ፈለቁን የሚያፈቅር፡፡

ደመቁ ደጀኔ፡-
ዕድሜ 40፣ የገነቱ ቀበሌ ነዋሪ እና የአቶ ዘለቀ አባት ባለቤት፡፡ በእቴነሽ የእርሻ ስራ ስኬት እና ከባለሙያ ጋር ባላት ጓደኝነት የምትቀና እንደ እቴነሽ ጥሩ ገቢ እንዲኖራት የምትፈልግ፡፡

አባቡ ኃይሉ፡-
ዕድሜ 32፣ የእርሻ ዕቀባ ባለሙያ እና ጥሩ የመግባባት ችሎታ ያለው፡፡

እቴነሽ እጅቱ፡-
ዕድሜ 30፣ ባለቤቷ የሞተባትና የደመቁ ጎረቤት ሁለት ልጆች ያሏት፡፡ አንድ በሬ ያላት፣ የቤት ባለቤትና ሞዴል አርሶ አደር

ንጉስ አበበ፡-
ዕድሜ 49፣ የሰላሙ ቀበሌ ነዋሪ እና ጠንካራ ሞዴል እርሶ አደር፡፡ የመሰሉ ባለቤትና በእርሻ ዕቀባ የሚሳተፍ አንድ በሬ ያለው፡፡

መሰሉ አዳነ፡-
ዕድሜ 38፣ የንጉስ አበበ ባለቤት እና የአራት ልጆች እናት በአዲስ የአስተራረስ ዘዴ የምታምን

ፈለቁ፡-
የንጉስ እና መሰሉ ልጅ እና የኮሌጅ ተማሪ፡፡ እናትና እና አባቷን በእርሻ ዕቀባ ስራ የምታግዝ፡፡ ከተመስገን ጋር በአንድ ክፍል የተማረች እና ተመስገንን የምታፈቅር፡፡

 

ትእይንት 1.

ቦታ፡-
በገነቱ ቀበሌ

ተዋናዮች፡-
ባዩ፣ ወይኒቱ፣ ተመስገን፣ ደነቁ፣ አንድ ወጣት

 

የገጠር ባህላዊ ሙዚቃ ይሰማል፤

የከብቶችና የበጎች ድምፅም ይሰማል፤

አንድ ወጣት በርቀት ይጣራል፤ ተመስገን፡ ተመስገን፡ እየሰማከኝ ነው?

 

ተመስገን፡-
እየሰማሁ ነው

ወጣቱ፡-
በደጎች ወረዳ ሰላሙ ቀበሌ እነ አቶ ንጉሱ ጋር ዛሬ በእርሻ እቀባ በሽፋን እና በመስመር የተዘራው ማሳ ዛሬ አርሶ አደሮች ወደ እዛ ሂዱ እየተባለ ነው፡፡

ተመስገን፡-
ጮክ ብሎ/ደግነው፡፡ እኔና እናቴ እንሄዳለን፡፡

አቶ ባዩ፡-
በርቀት እየተጣሩ ይመጣሉ፡ ተመስገን?

ተመስገን፡-
አቤት አባዬ

ባዩ፡-
ከብቶቹን መኖ ሰጠሀቸው ወይ?

ተመስገን፡-
አዎ አሁን ነው የሰጠኋቸው አሁን ግን መሄዴ ነው፡፡

ባዩ፡- በቅርበት ጮክ ብለው እኮ ወዴት ነው የምትሄደው?

ተመስገን፡-
ሰላሙ ቀበሌ

ባዩ፡-
በግርምት ወቸ ጉድ መቼም ያችን ልጅ ካላየህ አይመሽልህም አይደል፡፡ ወደ ሰላሙ ልሂድ ያልከው ለማመሀኘት ነው፡፡

ተመስገን፡-
የምን ማማሀኘት ነው? እኔ አንድ ነገር ለመማር ነው የምሄደው አልኩህ አኮ፡፡

ወይኒቱ፡-
እኔም ስለምሄድ ልጆቹ ምሳ ያቀርቡልዎታል፡፡

ባዩ፡-
በንዴት/አንቺ ደግሞ ወዴት ነሽ?

ወይኒቱ፡-
ጥሪውን አልሰሙም?

ባዩ፡-
በንዴት/እኮ መቼነው ባል ሲገባ ሚስት ወደ ውጪ መውጣት የተጀመረው? ወቸ ጉድ

ተመስገን፡-
ለዙረት እኮ አይደለም የምንሄደው ሲሆን ሲሆን አንተም ከእኛ ጋር ና እንሂድ? ባዩ፡- የእኔ መሄድ ይቅርና እናንተም አትሄዱም ብያለሁ፡፡

ወይኒቱ፡-
እስኪ ይስሙኝ ለወትሮ ማዳመጥ ላይ የተካኑ ነበሩ፡፡ ስለሰላሙ ቀበሌ ስለ አቶ ንጉሱ ቤተሰብ አልሰሙም? በእርሻ እቀባ ታቅፈው ማሳውን በተረፈ ምርት ሸፍነው የተሻለ ምርት አገኙ አሉ፡፡

ባዩ፡-
ባለመደነቅ/ ሰምቼአለሁ፡፡

ተመስገን፡-
አባየ ከሰማህማ ጥሩ ነው፡፡

ባዩ፡-
ይሄውላችሁ፤ እኔ የሰማሁት ለከብቶች የሚሆነው መኖ ተጠቅመው እሱን ለማሳ ሽፋን እየተጠቀሙ ማሳውን ከንፋስና ከጎርፍ እየተከላከሉ ሽፋኑ ሲሰበሰብ ማሳውን እያዳበረ ለምነቱን ጠብቀው የተሻለ ምርት ማግኘታቸውን አቶ ንጉሱ ነግሮኛል፡፡

ተመስገን፡-
ጥሩ ሰምተሃል ማየት ደግሞ ማመን ነው፡፡ ከብቶችና በጎች አሉኝ፡፡ እነሱን አርብቼ ሲደርሱ ወደ ገበያ አውርጄ ሸጬ ጥሩ ገቢ እያገኘሁ ነው፡፡ ታዲያ የከብቶቹን ቀለብ ለማሳ ሽፋን ካዋልኩት ከከብት እርባታ ወጣሁ ማለት አይደል፡፡

ባየ ፈለቁ እንደነገረችኝ ከሆነ……

ባዩ፡-
ልጃቸውን ያቋርጡታል/በንዴት/አንተ ልጅ ተወኝ፡፡ ደግሞ እኔን ስለ እርሻ ታስተምረኝ፡፡

ወይኒቱ፡-
እኔስየ አቶ ንጉስ ባለቡት መሰሉ በእርሻ አቀባ ማሳቸውን ሽፍና በመጀመሪያው አመት በቆሎ ሰብስበው ከበቆሎ ጋር የተዘራው የእርግብ አተር አመቱን ሙሉ እያገኙ መሆኑን ነግረውኝ ነው ማየት የፈለግኩት፡፡ በሁለተኛው አመት ደግሞ 10በ 10 በሆነ ተጨማሪ ማሳ ጎመን ዘርተው ልጃቸው ፈለቁን እያስተማሩበት መሆኑን ነግረውኛል፡፡

ተመስገን፡-
በብስጭት ከፈለቁ ጋር አብረን አንድ ክፍል ላይ ተምረን አስዋየ ኮሌጅ ትምህርትዋን እየቀጠለች ያለችው እኮ ከጎመን ሽያጭ ከምታገኘው ገቢ ነው፡፡ ይኸው አሁን አንድ አመት ቀደመችኝ፡፡ እንደውም ካልፈለጋችሁ የድርሻየን መሬት ስጡኝና እራሴ መሬት ላይ በሽፋን መዘራትን ልተግብር፡፡ በዛውም በሬ ስለሌለኝ በዛቢያ ቁፈራው ለእኔ ግልግል ይሆንልኛል፡፡

ወይኒቱ፡-
እስኪ ጎረቤት ከሚሰማ ቀስ ብለን እንነጋገር፡፡

ባዩ፡-
ቆጣ ብለው/ እኔ እያልኩ ያለሁት ለማሳ ሽፋን የሰብል ቅሪት እንዲሁም ሳሩን ተጠቅሜማሳዬን የምሸፍና ከብቶቼን አስርቤ ነው?

ተመስገን፡-
ለከብቶቹ መኖ እንገዛለን፡፡

ባዩ፡-
የባሰ መጣ ከብት ሸጩ መኖ ልግዛ? እህህም

ተመስገን፡-
ከብትህን ሽጥ አላልኩም፡፡ ማሳውን በመሸፈን የተሻለ ምርት ስታገኝ ከዛ ሸጠን ተጨማሪ መኖ እንገዛለን፡፡ በዋናነት ግን ከማሳው ሳር ለከብት መኖ የሚሆን መሬት እናስቀራለን፡፡

ባዩ፡-
ልጄ የአንድ ከብት ዋጋ ከ12ሺ እስከ 14ሺ በሆነበት ልስማማ አልችልም፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ በአንድ ነገር አምን ነበር፡፡ አንድ ነገር ሞክሬ ካልተሳካልኝ ሌላ መወጣጫ እፈልጋለሁ፡፡ ስለዚህ በእርሻ ብዙ ምርት ማግኘት ቢያቀተን ወደ እንስሳት እርባታ ገባሁ፡፡ በዛወስም ጥሩ ነገር እያገኘሁ ነው፡፡

ተመስገን፡-
በቃ ለእኔ ድርሻየን መሬት ስጠኝ፡፡ በማሳ ሽፋን ተጠቅሜ በማገኘው ምርት ኮሌጅ እማራለሁ፡፡ በእንስሳት እርባታ እንድትሰማራ ፈልጌ እንጂ መክፈል አቅቶኝ አይደለም፡፡

ወይኒቱ፡-
ትደሰታለች? በቃ ልጄ እንኩዋን ትምህርት ፈቀደልህ እልልልልል

ደመቁ፡-
ከጎረቤት ምን ተገኘ? ወይኒቱ ውይይ

ተመስገን፡-
ይቺ ደመቁ ግን ወሬ አያመልጣትም አይደል?

ደመቀ፡-
ጉሮሮዋን እየጠረገች ተመስገን ደግሞ ምን ማለትህ ነው ወይኒቱ እልል ስትል ደስ አለኝ

ተመስገን፡-
ኮሌጅ ልቀጥል ነው ያው ፈለቁ አንድ አመት ቀድማኛለች፡፡

ወይኒቱ፡-
ያው ሁለተኛ ክፍል እያለህ እኮ ደርበህ አልፈህ ነበር ልጄ ታዲያ አሁንም ኮሌጁን ደርበህ ታልፈውና ትደርስባታለህ፡፡

ባዩ፡-
ይስቃሉ/ኮሌጅ ደርቦ አይታለፍም ወይኒቱ

ተመስገን፡-
ይስቃሉ/እማ ምኞትሽ ብቻ ይበቃኛል፤ ኮሌጅ እኮ ደርቦ ማለፍ አይቻልም፡፡ የስልክ ጥሪ ድምፅ

ደመቁ፡-
በማፈር ተመስገን ያንተ ስልክ ነው

ወይኒቱ፡-
ተይው ደመቁ ያነሳዋል

ባዩ፡-
ይኸው ስልኩን ይዞ ወጣ እኛ እንዳንሰማ እኮ ነው፡፡

ተመስገን፡-
(ከርቀት) ሄሎ ሄሎ ፈለቁ……. ዛሬ.. ወደ ቀበሌአችሁ እመጣለሁ

ደመቁ፡-
እሄሄሄ አንድ ሰው ደወለ ማለት ነው፡፡

ወይኒቱ፡-
(ቆጣ ብላ) ደመቁ ነውርም አይደል ምነው

ባዩ፡-
የወንድ ወግ ነው ይሂድ እንግዲህ

ወይኒቱ፡-
ይሂድ ይተውት ልጅቷም አይደለች ደዋይዋ…. ይሂድ ደርሶ ይምጣ እኔ እንደሆንኩ ቀርቻለሁ፤ የቡና እቃ ላቀራርብ፡፡

 

 

የመሸጋገሪያ ሙዚቃ

ትእይንት 2.

ቦታ፡- በገነቱ ቀበሌ

ተዋናዮች፡- አባቡ፣ እቴነሽ፣ ደነቁ

 

የልጆች ጨዋታ የሰማል/

አባቡ፡-
ልጆች አቴነሽ አለች?

እቴነሽ፡-
አለሁ አባቡ ደህና ነህ ግባ እባክህ፡፡

አባቡ፡-
አልተዘጋጀሽም እንሂድ እንጂ ሰላሙ ቀበሌ፡፡

እቴነሽ፡-
አረ ተዘጋጅቼአለሁ እንሄዳለን ግን ቤት ግባ እና ቤት ያፈራውን ቀምሰህ ትሄዳለህ…. በሞቴ ግባ፡፡

አባቡ፡-
ግድ የለም ሰዓት እየደረሰ ነው እንሂድ ውጪ፡፡

እቴነሽ፡-
አልገባም ካልክማ በል እንሂድ….

አባቡ፡-
አረ ነጠላሽ በዚህ በኩል ወደቀ ቆይ ላንሳልሽ፡፡

እቴነሽ፡-
ውይ በሞቴ አይ የኔ ነገር አለፋሁህ /ትስቃለች/

ደመቁ፡-
ከርቀት/ጉድ እይልኝ ወይኒቱ….. አይ ነጠላዋን ሲያለብሳት…. አባቡ እኮ ነው ያ ባለሙያው ውይ ሴቱ ደግሞ እኮ ቤት ግባ እያለችው ነበር፡፡ ደፋር

ወይኒቱ፡-
አይ ደመቁ ሁሉም ብርቅሽ ቤት ግባ ብትለው ታዲያ ምን አለበት ልጆችዋ አሉ….. ምን ችግር አለው ደግሞ….

ደመቁ፡-
ወይኒቱ ደግሞ የዋህ ነሽ… የሆነ ነገርማ አለ….በይ ወደ ቤቴ ልሂድ

አባቡ፡-
ዛሬ መቸም የሰላሙ ቀበሌ ተሞክሮ ደስ ይልሻል ብየ አስባለሁ፡፡

እቴነሽ፡-
ምን መሰለህ አባቡ በበሬ በአመት 5 እና 6 ጊዜ አለስልሰንም ጥሩ ወይም የተሻለ ምርት አላገኘንም፡፡ አሁን ደግሞ በዛቢያ ዘሩን ብቻ የሚያርፍበት ጉድጓድ ተቆፍሮ ጠባብና ጥልቅ ቦይ በማበጀት ዘር ተዘርቶ፡፡ የበለጠ ምርት ይገኛል ብየ አላመንኩም፡፡ ግን እየተጠራጠርኩም ቢሆን ሄጄ ማየት እፈልጋለሁ፡፡

አባቡ፡-
ልክ ብለሻል እቴነሽ ማየት ማመን ነው፡፡

እቴነሽ፡-
/ትስቃለች/ ልታሳምኝ ቆርጠህ ተነስተሀል፡፡

አባቡ፡-
ምነው ወደ ሃላ ቀረሽ?

እቴነሽ፡-
አሯሯጥከኝ እኮ፡፡

አባቡ፡-
ይስቃል/ ሮጥኩብሽ የኔ ነገር መቸኮሌ እኮ ነው በይቀስ ብለሽ ውረጂ ቁልቁለቱ ቆይ ልደግፍሽ

ደመቁ፡-
እህህም ወይኒቱ የሚላት ሴት አልስማም አለች እንጂ እኔማ ምን እየሆነ እንደሆነ ገብቶኛል አሁን ጎረምሳውን ይመስሉ ተደጋግፈው ጉድ ጉድ ይልቅስ ደረሱብኝ ቤቴ ልግባ

አባቡ፡-
ይጠራታል ወይዘሮ ደመቁ

ደመቁ፡-
በድንጋጤ ውይ እናንተ ናቸሁ እንዴ አቤት ደህና ዋላችሁ?

አባቡና እቴነሽ /በጋራ/፡-
ደህና ነሽ ደመቀ?

አባቡ፡-
ደመቁ እንሂድ እንጂ ወደ ሰላሙ ቀበሌ አቶ ንጉስ እርሻ ጋር ተሞክሮ እናያለን እኮ ብየሻለሁ፡፡

ደመቁ፡-
ባለቤቴ የለም ራቅ ወዳለ ከተማ ዘመድ ጥየቃ ሄደ እኮ

አባቡ፡-
ጋሽ ዘለቀ የለም እንዴ?

ደመቁ፡-
የለም

አባቡ፡-
እንግድያውስ ቤት ምን ትሰርያለሽ?…. አብረን እንሂድ……. ህይወትን የሚያሻሽል ልምድ ተምረሽ ትመጫለሽ

ደመቁ፡-
እሺእመጣለሁ ቀድማችሁ ሂዱ

አባቡ፡-
ምን ማለትሽ ነው? አብረን ነው የምንሄደው ነይ

እቴነሽ፡-
ደመቁ ከሰው ጋር ብትሄጂ ነው ጥሩ ነይ

ደመቁ፡-
ወሬ ይዛችሁ እንዳትሆኑ /ትስቃለች/

አባቡ፡-
የጋራ ወሬነው ይልቅ እንሂድ

ደመቁ፡-
በሉ ካላችሁ ልሂድ……. ልምዱን ማየትማ እፈልጋለሁ…. የአቶ ንጉስ ሚስት ከጎመን ከእርግብ አተር ከበቆሎ ጥሩ ምርት አገኘች ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡ ያስቀናል፡፡

አባቡ፡-
በአይንሽ ታይዋለሽ እንሂድ ብቻ

እቴነሽ፡-
ፈጥነን እንሂድ…ሌሎቹ ቀድመውን ሄደዋል፡፡

ደመቁ፡-
በርቀት/ጎረቤት ትጣራለች/ አዳኑ አዳኑ….. ልጆቹ ሲመጡ የቤት ቁልፍ እዛ የምናውቀው ቦታ ነው ያለው በያቸው፡፡

 

 

የመሸጋገሪያ ሙዚቃ

ትእይንት 3.

ቦታ፡- በሰላሙ ቀበሌ

ተዋናዮች፡- ንጉስ፣ መሰሉ፣ እቴነሽ፣ ተመስገን፣ ደመቁ

 

አባቡ፡
እንደማመጥ ሁላችንም እንደማመጥ አሁን የምንገኘው በደጎች ቀረዳ ሰላሙ ቀበሌ በአቶ ንጉስ አበበ ማሳ ነው፡፡ ነገር ግን መጀመርያ ማሳውን ከማየታችሁ በፊት ስለ እርሻ እቀባ አጭር መግለጫ እሰጣለሁ፡፡ እቀባ እርሻ ማለት የአፈርን ለምነትና ምርታማነት በጠበቀ መልኩ እህል ማብቀል ማለት ነው፡፡

ይህ ማለት ደግሞ በተለምዶ አስተራረስ 5 እና 6 ጊዜ የማረስ የምናደርገው አድካሚ ይቀንስልናል፡፡ አሁን አሁን አንዳድ ሰዎች በርከን በተባለው ማረሻ በቀላሉ ዘር የሚያርፍበትን የመሬት ክፍል በመስመር በ80 ሳ.ሜ ትክክለኛውን ርቀት ጠብቆ በጥልቀት ዘሩ የሚያርፍበት ጉድጓድ የሚያበጅ ዘመናዊ ማረሻም እየተጠቀሙ ነው፡፡

ሌላው የዕቀባ እርሻን ልዩ የሚያደርገው ነገር በሬ ለሌላቸውና ቤተሰብ ለሚመሩ እማወራዎች ባህላዊ መዶሻ በሺባጎ መስመር ተወጥሮ ቆፍረው በመዝራት የተሻለ ምርት እንዲያገኙ ያደርጋል፡፡

ሌላው በእርሻ እቀባ በአጨዳ ጊዜ የበቆሎም ይሁን የሌላ ሰብል ተረፈ ምርት ማሳው ላይ በመተው በሌላው ትይዩ መስመር ማለትም ባልታረሰው ማሳ ላይ ተረፈምርቱ እንዲሁም ሌሎች የሳር ዝርያዎች እናለብሰዋለን፡፡

ይህም፡-

1ኛ. እርጥበት በፀሐይ ሙቀት እንዳይተን በማድረግ አፈሩ እርጥብ ሆኖ እንዲቆይ ያደርጋል፡፡

2ኛ. መሬቱ በንፋስና በጎርፍ እንዳይወሰድ ያግዛል፡፡

3ኛ. ማሳው ላይ የሚሸፈነው ተረፈ ምርት በስብሶ የአፈር ለምነት ይጨምራል በዚህም አፈራችን አመቱን ሙሉ እርጥብ ሆኖ ይቆያል፡፡ እንደ እነ እርግብ አተር ጎመን፣ እንሰት፣ ላቭ ላቭ የመሰሉ ሰብሎች አመቱን ሙሉ እንድናበቅል ያስችለናል፡፡ በተጨማሪም በተግባር እንዳየነው በዘልማድ ከሚዘራው ይልቅ አፈርን በተረፈ ምርት እና በሳር በመሸፈን እና በማበስበስ የሚዘራው ምርቱ ይጨምራል፡፡ ለአሁን ይህን ብየ ወደ አቶ ንጉስ ልለፍ፡፡

አቶ ንጉስ፡-
ጎሮሮውን ይጠርጋል/ ወዳጆቼና ወገኖቼ ይህንን መልካም ስራየን ፈጣሪ ባርኮልኝ ለዚህ በመብቃቴ ፈጣሪ ይመስገን፡፡ /በቡድን የተሰበሰቡት ሰዎች/…. አሜን አሜን

ንጉስ፡-
እንግዲህ እዚህ ማሳ ላይ በመጀመሪያ አመት፣ ላይ የዛሬ ሁለት አመት መሆኑ ነው፣ ስልጠና እንደወሰድኩኝ 25 በ25 ግማሽ ጥማድ መሬት ላይ እቅድ አውጥቼ ማሳየን ሸፈንኩ፡፡ ኋላም በአቀባ እርሻ በበርከን ማረሻ መስመሬን ለይቼ በቆሎና የእርግብ አተር ዘራሁ፡፡

ተመስገን፡-
ጥያቄ አለኝ

አባቡ፡-
እሺ ተመስገን

ንጉስ፡-
በሰለጠንሁት መሰረት 20 ሳ.ሜ ጥልቀት በኮምፖስ ማለትም ቤት ሰራሽ ባህላዊ ማዳበሪያ ካልሆነ 15 ሳ.ሜ ማዳበሪያ በዘመናዊ ማዳበሪያ ዩርያ ከሆነ ደግሞ በ8 ሳ.ሜ ይቆፈራል፡፡ ለእንሰት ሲሆን ደግሞ ይጨምራል፡፡

እቴነሽ፡-
እኔም ጥያቄ አለኝ

አባቡ፡-
እቴነሽ ቀጥይ

እቴነሽ፡-
የዛሬ ሁለት አመት በግማሽ ጥማድ መሬት ስንት በቆሎ አገኙ?

ንጉስ፡-
3 ኩንታል በቆሎ አገኘሁ፡፡ ይግረማችሁ፤ በልማዳዊ መንገድ ሳርስ 75 ኪሎ በላይ ማግኘት አልችልም ነበር

ደመቁ፡-
እኔም ጥያቄ አለኝ…. እርግብ አተርና ጎመንስ?

ንጉስ፡-
ይህንን መሰሉ ትመልሰው…/ይስቃሉ/ እስዋ ናት የምታስተዳድረው

መሰሉ፡-
እሺ እንግዲህ እርግብ አተር በማፈራረቅ በመዝራታችን በየጊዜው 50 ኪሎ እያደረግን ገበያ እንወስድ ነበር፡፡ ጎመንማ አመት ይቀነጠሳል፡፡ በየሁለት ሳምንት ገበያ እንወስዳለን አሁን 100 ኪሎ ተቀንጥሶ አዘጋጅተናል፡፡ ጎመን ሸጠን ባገኘነው ብር ልጃችን ፈለቁን ኮሌጅ እናስተምርበታለን፡፡ ጎመን ሸጠን ባገኘነው ብር ልጃችን ፈለቁን ኮሌጅ እናስተምርበታለን፡፡ የእርግብ አተር ሸጠን አስቤዛ እገዛለሁ፡፡ በቆሎውን ለራሳችን ቀለብ እናውለዋለን፡፡

አባቡ፡-
አቶ ንጉስ ዘንድሮ ሰፋ ባለ መሬት ነው የዘራው፡፡ የአምናውን ብቻ ሳይሆን በበሬ ሲያርሰው የነበረውን መሬት ጭምር ዘንድሮ በማሳ ሽፋን በእርሻ እቀባ ዘርተዋል?

ንጉስ፡-
መሰሉ ጨርሳለች?

አባቡ፡-
ምን?

ንጉስ፡-
የባለቤቴ መጠይቅ አለቀ ወይ ወደ እኔ ቀጠላችሁ፡፡

– ሁሉም ሰዎች ይስቃሉ

አባቡ፡-
/እየሳቀ/ አንድናችሁ ብለን ነው ዘንድሮ ስንት ማሳ ሸፈናችሁ አቶ ንጉስ?

ንጉስ፡-
ዘንድሮ 40 ሜትር በ60 ሜትር ሸፍነን ዘርተናል፡፡ ማሳ ላይ ሰብል ማፈራረቅም ጀምረናል አምና በቆሎ የነበረውን ዘንድሮ ሽምብራ፣ ላቭ ላቭ እና ካሳቫ እዛን ቀን ዘርተናል፡፡ ያው እያያችሁት ነው፡፡ እየደረሰ ነው፡፡

አባቡ፡-
ሌላስ ጥያቄ ያለው አለ?

ተመስገን፡-
ጎመን ዘርታችኋል ዘንድሮም? በግማሽ ጥማድ መሬት ለብቻ ጎመን ብቻውን ዘርተናል፡፡ ለልጃችን ፈለቁ ማስተማርያ የሚውል ነው፡፡ ቅድም ስልጠና ላይ አባቡ እንዳለው የማሳው ሽፋን መሬቱ አመቱን ሙሉ እርጥበት እንዲኖረው ያደርጋል፡፡ እና ጎመን አመቱን ሙሉ ይቀነጠሳል፡፡ መድረቅ አይታሰብም፡ አይደለም እንዴ መሰለ? /ይስቃሉ/

መሰሉ፡
ተመስገን ነው ከወንዶች ብር መጠየቅ አቁመናል፡፡ አሁን እኛ ዘንድሮ እኔና ፈለቁ ጎመኑን በዛቢያ ቆፍረን ነው የዘራነው ለሴቶች ምቹ ነው፡፡

እቴነሽ፡-
ግሩም ነው፡፡ በሁለተኛው አመት 40 በ60 ማሳ ሸፍናችሁ ምን ያህል ምርት አገኛችሁ?

ንጉስ፡-
ወደ አምስት ኩንታል

ተመስገን፡-
ላቭ ላቭ ነው?

ንጉስ፡-
በቆሎ ነው፡፡ ላቭ ላቭ ዘንድሮ ነው የዘራነው ገና ነው፡፡

እቴነሽ፡-
ለከብቶች መኖ ግን ምን ትጠቀማላችሁ?

ንጉስ፡-
ከማሳው ወሰን ሳር እናበቅላለን፡፡ እሱን በጥበቃ እንዲበሉ ይደረጋል፡፡ ደግሞ የበቆሎ አገዳም እሸቱ ካለበት በላይ ለከብቶች እናጭደዋለን፡፡ የተቀረው ላማሳ ሽፋን ይሆናል፡፡

ደመቀ፡-
ታዲያ በዘልማድ የምታርሱት ሌላው መሬታችሁን ለምን በማሳ ሽፋን አትዘሩም

መሰሉ፡-
እንፈልግ ነበር

ደመቁ፡-
ታዲያ?

መሰሉ፡-
ችግሩ በቂ መሸፈኛ ቅጠላቅጠልና ተረፈ ምርት ይኖራል ወይ ነው እንጂ ሁሉንም መሸፈን ይቻላል፡፡

ደመቁ፡-
የሽፋን ችግር ስትይ ምን ማለትሽ ነው?

መሰሉ፡-
አኩሪ አተር የእርግብ አተር ላቭ ላቭ እና ካሳቫ ለሽፋን እየተጠቀምን አልበቃንም፡፡ እንደገና ጫካ ሄደን ከባህር ዛፍና ማንጎ ውጪ ያሉ ሁሉንም አይነት ቅጠሎች ለሽፋን እንጠቀማለን፡፡ እንሰትና ሙዝም ጥሩ ሽፋን ነው፡፡

አባቡ፡-
ስለዚህ ለሽፋን የሚጠቅሙ ሰብሎች መዝራትና መትከል የሚሸፈን ማሳ ለመስፋት ይጠቅማል፡፡ እንዳያችሁት የእርሻ እቀባ ከተለመደው የእርሻ ዝኻ ይልቅ ሴቶች በቀላሉ በእርሻ ስራ እንዲሳተፉ ያደርጋል፡፡ እንግዲህ ለዛሬ ያገኘነው ልምድ ይበቃናል፡፡ እነ አቶ ንጉስና ወይዘሮ መሰሉን እናመሰግናለን፡፡ ሁሉም በአንድ ድምፅ ያመሰግናሉ፡፡

ንጉስ፡-
ወዳጆቼ በሉ ቤት ግቡና ቤት ያፈራውን ተቃሹመ ከሰው አገር እንግዲህ በባዶ ሆድ አትመለሱ ፡፡ /ይስቃሉ/

አባቡ፡-
እንግዲህ እምቢ አንልም ፡፡ በሉ እንግባ ግቡ፡፡

ደመቁ፡-
በሽኩሽኩታ/ እቴነሽ ያ ተመስገንን አየሺልኝ ፈለቁን የአቶ ንጉስ ልጅ ይዟት ውጪ ቀረ፡፡ አቤት ጉድ አየሻቸው?

እቴነሽ፡-
አረ ደመቁ ቀስ በይ እንዳይሰሙሽ ፍቅረኛው ናት እኮ ምን ነውር አለው፡፡ ደግሞስ ቆመው ነው እያወሩ ያሉት በይ ግቢ

ደመቀ፡-
በማሽሟጠጥ/ነውር የለውም አየጊዜ መቼ እነሱ ብቻ ሆኑና ብዙ እያየን ነው

እቴነሽ፡-
ማንን ማለትሽ ነው?

ንጉስ፡-
እናንተ ደግሞ ምን ሆናችሁ ነው ግቡ እንጂ

 

 

 

ትእይንት 4.

ቦታ፡-
በሰላሙ ቀበሌ፣ ፈለቁና ተመስገን
ተዋናዮች፡-
ተመስገን፣ ፈለቁ

ፈለቁ፡-
ተሜ እኛ ግን እዚህ ተለይተን ቀርተን ምን ይሉናለ?

ተመስገን፡-
እያወሩ ናቸው ይላሉ ምን ችግር አለው፡፡

ፈለቁ፡-
አየ ግን መቆጣቱ አይቀርም፡፡

ተመስገን፡-
ጓደኞች እንደሆንን ያውቃሉ፡፡

ፈለቁ፡-
አረ እጅህን ሰብስብ አንተየ ሰዎች ድንገት ሊያዩት ይችላሉ፡፡

ተመስገን፡-
አንቺ ደግሞ

ፈለቁ፡-
ይልቁንስ ዛሬ በመምጣትህ ደስ አላለህም?

ተመስገን፡-
ፈለቁየ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡

ፈለቁ፡-
አባትህ አልተቆጡም?

ተመስገን፡-
ያው ፈቅዶልኝ ነው የመጣሁት፡፡

ፈለቁ፡-
ጥሩ

ተመስገን፡-
ሌላው የምነገርሽ ነገር እእእ……..መጀመርያ ሳሚኝና

ፈለቁ፡-
ሰው እንዳይመጣ ብቻ/ የመሳሳም ድምፅ እሺ ንገረኝ

ተመስገን፡-
አባቴ ኮሌጅ እንድማር ፈቅዶልኛል

ፈለቁ፡-
በደስታ ትስቅና/ትስመዋለች

ተመስገን፡-
ቅድም እኔን መሳም አስፈርቶሽ ነበር

ፈለቁ፡-
ሂድ ምን ታሳፍረኛለህ ደስ ስላለኝ ነው

ተመስገን፡-
ስቀልድ ነው ደስ እንደሚልሽ አውቃለሁ

ፈለቁ፡-
አባትህ ትክክለኛ ውሳኔ ነው የወሰኑት

ተመስገን፡-
ሁሌም ሚዛናዊ ነው፡፡ በእንስሳት ማርባት ስራ ላይ እንዳግዘውና እኔም ገንዘብ እንዳገኝ ይፈልግ ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን ስወተውተው በቃ እንድማር ፈቀደልኝ፡፡

ፈለቁ፡-
አውቃለሁ አቶ ባዩ ሚዛናዊ ሰውናቸው፡፡

 

ተመስገን፡-
ዛሬ ደግሞ ስለ እቀባ እርሻ ያየሁትን እነግረዋለሁ፡፡ ስለከብቶቹ እንዳይሰጋ ላስረዳው እሞክራለሁ፡፡ ለከብቶቻች ከማሳ አቅራቢያ የሳር ቦታ እንተውላቸዋለን እለውና ከተረፈ ምርትም የተወሰነ እንደሚመገቡ ስነግረው ሊያምን ይችላል፡፡

ፈለቁ፡-
እኔ እንጃ አንተ ግን መጀመር አለብህ ድርሻህን ይስጡህ፡፡

ተመስገን፡-
ግድ የለም መስጠትማ ይሰጠኛል ልክ አንቺ ኮሌጅ ስትጨርሺ እኔ አንድ አመት ሲቀረኝ እንጋባና አንድ ላይ እንኖራለን፡፡

ፈለቁ፡-
ትደነግጣለች/ውይ ጉዴ አፈር በሆንኩ

ተመስገን፡-
ምን ሆነሽነው?

ፈለቁ፡-
ሰዎቹ አሁንም ከዚህ ቦታ ሳንንቀሳቀስ ከቤት ወጥተው መጡብን ወይኔ ወይኔ እያዩኝ ነው በቃ ልሂድ ቻው እኛ ጋ ከመድረሳቸው በፊት በዚህ በጎሮ አድርጌ ወደ ቤት ልሂድ፡- ሰዎች ሲሰነባበቱ ድምፃቸው ይሰማል/

 

የመሸጋገሪያ ሙዚቃ

ትእይንት 5.

ቦታ፡-
በእነ ንጉስ ቤት ደጃፉ

ተዋናዮች፡-
አባቡ፣ ደመቁ፣ እቴነሽ፣

አባቡ፡-
አቶ ንጉስና ወይዘሮ መሰሉ በጣም ነው የምናመሰግነው፡፡ ከገነቱ ቀበሌ ለመጡት እንግዶች ስላደረጋችሁት መስተንግዶ መስጋናች የላቀ ነው፡፡ በሉ ወደ ቀበሌያችን እንሂድ….. ተመስገንስ?

ደመቁ፡-
/ጎሮሮዋን ትጠርጋለች/ ውይ ጉድ ተመስገንማ ልጅትዋ ጋር ነበር…. ልጅትዋ ግን ወላጆችዋ አይቆጥዋትም?

እቴነሽ፡-
ለምን ይቆጥዋታል…. ተመስገን ጨዋ ልጅ ነው…… ደግሞስ ቆመው ላወሩትና ለተጫወቱት ምን ችግር አለው?

አባቡ፡-
አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም አብረው ነው የተማሩት ደስ ይላሉ፡፡

እቴነሽ፡-
እኛ ጋ አሁን አሁን ትዳር በፍቅር ተመስርቶ ነው እየተከናወነ ያለው፡፡

አባቡ፡-
አዎ ትዳር በፍቅር ሲመሰረት ጥሩ ነው፡፡

ደመቁ፡-
ትስቃለች/ወይ ፍቅር እቴ እኛ በፍቅር አላገባንም፡፡ ወላጆቻችን ያመጡልን ባል ጋር ነው እየኖርን ያለነው፡፡ ይሄው እኔና ዘለቀ 7 ልጆች ወልደን እየኖርን ነው፡፡

አባቡ፡-
ደመቁ አሁን ጊዜው ተቀይሯል፡፡

ደመቁ፡-
ጊዜውማ በጣም ተቀይሯል የተቀየረ ነገር ብዙ ነው /ትስቃለች/ አረ ልጁን ጥሩት

አባቡ፡-
ምን ሆነሽ ነው ሳቅ በሳቅ ሆንሽ? ደግሞስ ማንን ነው የምንጠራው?

ደመቁ፡-
እየሳቀስ/ተመስገንን ከፈለቁ ጋር እኮ ነው የዋለው እነንጉስ ቤትም አልገባም ወይ ፍቅር

አባቡ፡-
ተመስገን ከፊታችን ነው ቀድሞናል እኮ እንሂድ

እቴነሽ፡-
ደመቁ የጤና ነው ይህ ሁላ ሳቅ?

ደመቁ፡-
እየሳቀች/ሳቅ የደስታ ምንጭ ነው አለንኮ ሬድዮው አልሰማሽም

እቴነሽ፡-
ስለ እርሻ እቀባ የምትማሪበት ሬድዮ ነው ሌላ?

ደመቁ-
እርሻ እቀባማ ቁም ነገር ነው፡፡ የመዝናኛ ጣቢያው ነው እንጂ

አባቡና እቴነሽ፡-
ይስቃሉ

 

የመሸጋገሪያ ሙዚቃ

ትእይንት 6.

ቦታ፡-
በገነቱ ቀበሌ እነ ባዩ ቤት

ተዋናዮች፡-
ባዩ፣ ወይኒቱ፣ ተመስገን

– የከብቶች ድምፅ

ባዩ፡-
ተመስገን ከብቶችንማ እያቸው

ወይኒቱ፡-
ሁሌም የሚጠሩት ተመስገንን ልጆች አቤት አሉ የሚጠራው ተመስገን ነው

ባዩ፡-
እነሱ ትምህርት ቤት ውለው መጥተው ታዲያ ምን ልበላቸው

ወይኒቱ፡-
ተመስገንም እንግዲህ ትምህርት እየተጀመረ ነው አሁንስ ምን ሊሆን ነው?

ባዩ፡-
አንቺ አለሽልኝ ድሮስ ልጆች እራሳቸውን እየቻሉ ሲወጡ እኔና አንቺ ነን አንድ ላይ የምንኖረው ወይኒቱ

ወይኒቱ፡-
በድንጋጤ/አረ እሱንጊዜስ ያቆየው

ተመስገን፡-
አይዞሽ እማየ ራሳችን ብንችልም እየመጣን እንጠይቅሻለን

ባዩ፡-
ወሬ ተውና ጥጃዎቹን ልቀቃቸው እንዲሁም በጎችንም አስወጣቸው

ተመስገን፡-
እሺ

ወይኒቱ፡-
አግብቶ የወጣ ቀን ይሄ ልጅ ጉዳችን ነው፡፡

ባዩ፡-
እሱ የሚሆነው ትምህርትዋ ስትጨርስ ነው፡፡

ወይኒቱ፡-
እየሳቀች/ በቀደም ለእርሻ እቀባ ተሞክሮ ሰላሙ ቀበሌ የሄደ ቀን ከፈለቁ ጋር አፍለ አፍ ገጥሞ ነው የዋለው አሉ፡፡

ተመስገን፡-
ማን ነው እንደዛ ያለው? ያቺ ደመቁ ናት ወረኛ ምን ይሻላታል ግን?

ባዩ፡-
ተወው ልጄ ሰራህን ስራ

ተመስገን፡-
አባየ

ባዩ-
አቤት ልጄ ወይኒቱ ቁርስ አቅርቢልኝ እንጂ ረፈደ እኮ

ተመስገን፡-
አባ እንግዲህ በእርሻ አቀባ ላይ ሶስት አራት ጊዜ ስልጠና ተሰጠን፡፡

ባዩ-
እና ምን ይሁን?

ተመስገን፡-
የተወሰንን ሰዎች ዝግጁ ሆነናል፡፡

ባዩ-
እነማን ናቸው ?

ተመስገን ፡-
እነ እቴነሽ ደመቁና የላይ ሰፈር ሰዎችም አሉ፡፡

ወይኒቱ፡-
ምግብ እየቀረበ ነው

ባዩ፡-
እሺ ቁጭ በል እስኪ ልጄ

ተመስገን፡- እሺ አባየ አንተ ለምን ፈቃደኛ አትሆንም?

ባዩ፡-
ልጄ እኔ አሁን ከብቶቼን አስርቤ የተሻለ የሰብል ምርት ለማግኘት ላይ ታች አልልም፡፡

ተመስገን፡-
እሺ ለእኔ መሬት ስጠኝና እኔ ልዝራ?

ባዩ፡-
አስብበታለሁ

ተመስገን፡-
አባየ እቴነሽ እኮ 25 በ25 የሆነ የማሳ በሽፋን እየዘራ ነው፡፡ ያውምመ ራስዋ በዛቢያ ቆፍራ

ወይኒቱ፡-
ስንት ጥማድ ማለት ነው?

ተመስገን፡-
ግማሽ ጥማድ ለመጀመሪያ ጊዜዋ ስለሆነ ነው እንጂ ቀስ በቀስ አሰፋለሁ

እያለች ነው፡፡

ወይኒቱ፡-
እቴነሽ ታድላ ለእኔም ትንሽ መሬት ቢፈቀዱልኝ ጎመን ነበር የምዘራው

ተመስገን፡-
ጎመን ማሳ ሽፍነሽ ብትዘሪ እማ የአመት ሙሉ መሬቱ እርጥበቱ ስለማይደርቅ በየወሩ ሁለት ጊዜ ለገበያ ታቀርቢያለሽ

ወይኒቱ፡-
ለቤትም ቢሆን ይበቃል

ባዩ፡-
ወቸ ጉድ ወይኒቱም መሬት ፈለግሽ?

ወይኒቱ፡-
ለጎመን አዎ

ባዩ፡-
እንፋታ ማለት ነው

ወይኒቱ፡-
በድንጋጤ/ውይ ውይ ኪዳነምህረት ምነው አንቱየ የሰይጣን ጆቶ ይደፈን

ባዩ፡-
ይስቃሉ/ድርሻሽን እየጠየቀሽ ነው ብዬ ነው፡፡ ድሮ ቢሆን ከነውበቴ እንዲህ በቀላሉ የመፋታት ወሬ አያነሱም ነበር፡፡

ባዩ፡-
ይስቃሉ/አሁንም አይነሳም አይዞሽ ቀልዳችን ነው፡፡ ደግሞ እኮ ዛሬም ውበትሽ የተጠበቀ ነው፡፡

ወይኒቱ፡- በንዴት/ይተውኝ አሁን አሁን ሰው በስራ ተወጥሮ ቀልድ ያመረዋል፡፡

ተመስገን፡-
የእቴነሽ ማሳ ነገር አስከተለ እንዴ /ይሰቃል/

ባዩ፡-
እቴነሽ ባለቤትዎ ስለሞተ ሀብትዎንም መሬትዎንም እንዲሁም ልጆችዎንም ራስዎ ታስተዳድራለች፡፡ ችግር ሲገጥማትም ለብቻዋ ትወጣዋለች፡፡ እዚህ ቤት ግን እኔው አለሁ፡፡ አታስቢ ወይኒቱ፡፡

ወይኒቱ፡-
እኔ ሌላ ለማለት ሳይሆን እንደ ሴቶቹ ለመሳተፍ ነው፡፡ ትንሽ መሬት

ይፍቀዱልኝ ማለቴ

ተመስገን፡-
አባየ እሺ የእኔን ስጠኝ

ባዩ፡-
ላስብበት አልኮ እኮ

ተመስገን፡-
ደመቁም ግማሽ ጥማድ መሬት ሸፍናለች፡፡

ባዩ፡-
ዘለቀ ፈቅደ ነው?

ወይኒቱ፡-
አረ ምግቡ ቀርቦ እናንተን እየጠበቀ ነው፡፡

ባዩ፡-
መጣን አልንሽ እኮ ወይኒቱ ተመስገን የጠየኩህን መልስልኝ እንጂ

ተመስገን፡-
ጋሽ ዘለቀ የት አለና ደመቁ ራስዋ ናት ማሳ ሸፍና በራሷ የዘራችው

ወይኒቱ፡- በሉ ግን አሁን ቡናውም ፈላ፡፡

የስልክ ጥሪ ድምፅ

ወይኒቱ፡-
ይስቃሉ/ልጄ ስልክህ ከቡናው ጋር ደረሰ

ባዩ፡-
አሁንስ አሳቅሽኝ ወይኒቱ /ይስቃሉ/ የዛሬ ልጆች በቃ በስልክ ነው ሁሉም ነገር፡፡

-የስልክ ጥሪ ድንፅ

ተመስገን፡-
ቆይ እናንተ ግን ምን ሆናችሁ ነው? አሳፈራችሁኝ እኮ እኔ ገባሁ፡፡ አውራት ምን ይሽኮረመማል ወንድ ልጅ አይደለህም? ቆፍጠን በል

 

የመሸጋገሪያ ሙዚቃ

ትእይነት- 7

ቦታ፡-
በገነቱ ቀበሌ

ተዋናዮች፡-
ዘለቀ፣ ደመቁ፣ አባቡ፣ እቴነሽ፣ ተመስገን፣ ባዩ፣ ወይኒቱ

 

-ደመቁ ቤት ኡኡታ ይሰማል

– ውሻ ይጮሀል

 

ፈለቀች፡-
/ከ ውጪ ትጣራለች/ ተመስገን ተመስገን

ወይኒቱ፡-
ተመስገን ሰው እየተጠራ ነው

ተመስገን፡-
አረ ሰው እየጮኸ ነው

ባዩ፡-
እነማን ጋ?

ወይኒቱ፡-
ደመቁ ናት ደመቁ ጋሽ ዘለቀ መጣ ማለት ነው፡፡

ተመስገን፡-
እና መምጣቱ በዱላ ነው የሚነግረን

ባዩ፡-
እስኪ ዝም በሉ

እቴነሽ፡-
አረ ተመስገን ተመስገን

ወይኒቱ፡-
አቤት እቴነሽ /በር ሲከፍቱ ይሰማሉ/

እቴነሽ፡-
አረ ሴትየዋ ገደላት ቶሎ እንድረስላት

ባዩ፡-
እንሂድ ፍጠኑ ኑ ኑ

– ሰዎች እነ ዘለቀን ለማስታረቅ እየተነጋገሩ ነው?

– ውሻ ይጮሀል?

እቴነሽ፡-
ልጆች አረረ ውሻውን ያዙልን እንግባ….. አዎ እንደዛ ያዘው አቶ ዘለቀ ምን ሆነህ ነው..አረ እባክህን ተው

ደመቁ፡-
ለቅሳለች

ባዩ፡-
ዘለቀ ዘመን ሰልጥኖ የሴቶች እኩልነት አክብሩ እየተባልን ምነው ምነው?

ዘለቀ፡-
በንዴት/ሁላችሁም እስኪ ዝም በሉ፡፡ የመጣነው ምን ነክቶህ ነው

ወንድሜ?

ሴት መምታት እኮ በወረዳችን ድሮ ቀረ

ዘለቀ፡-
እኔ ጋ አልቀረም፡፡

ወይኒቱ፡-
አንተ ጋ እንዳቀረማ እያየን ነው ነገር ግን ነውር ነው የሰባት ልጆችህ እናት በዱላ ወግም አይደል፡፡

ዘለቀ፡-
ምን አጠፋች የሚል የለም፡፡

አባቡ፡-
አቶ ዘለቀ ደህና አመሸህ?

ዘለቀ፡-
ደህና ነኝ አባቡ

ባዩ፡-
ደህናማ አይደለህም

አባቡ፡-
ድምፃችሁ ማዶ ድረስ ይሰማል ከማዶ ነው የመጣሁት ምነው ምን

ሆናችሁ?

ባዩ፡-
ጥሩ ጥያቄ ነው አቶ ዘለቀ ምን ገጠመህ? በሰላም በውይይትስ አይፈታ

ሆኖብህ ነው?

ዘለቀ፡-
ጎረቤቶች እኔን የገጠመኝ አይግጠማችሁ

ባዩ፡-
ጥሬ ንገረና እንፍረድ

ዘለቀ፡-
ዘመድ ጥየቃ ብዬ ራቅ ሰነበትኩ

ባዩ፡-
አዎ እንዳልነበርክ ሰምተናል

ዘለቀ፡-
አባወራው በሌለሁበት ታዲያ ለከብት መኖ ያስቀነጥኩት መኖ እና ሳር እንዲሁም አገዳ ወይ ጉድ ማሳ ላይ አልብሳው፣ ነስንሳው፣ ጠበቀችኝ፡፡ ዘርም አውጥታ ዘራች፡፡ በተነችው እኮ ሳታማክረኘረ ወይኔ ዘለቀ ተዋረድኩኝ በቁሜ ሞትኩኝ

ባዩ፡-
ምነው ደመቁ እሱን ብታማክሪው በመንደራችን ሞባይል ስልክ ሞልቶ፡፡

ወይኒቱ፡-
የሄደበት አገርስ ሞባይል ስልክ ባይሰራ?

ተመስገን፡-
እየሳቀ/ እማየ እኛ ጋ ካለ ሌላ ቦታም ይኖራል፡፡

ወይኒቱ፡-
/በንዴት/ እንዲህ ናትና ወይኒቱ ምነው ጥሩ ስራ በሰራች ታዲያ ዱላ

ይገባታል?

ባዩ፡-
/ተናዶ/ወይኒቱ ነገር አብርጂ ለማስታረቅ እኮ ነው የመጣነው

አባቡ፡-
የእርሻ አቀባ መሬታቹ ላይ በመሞከሯ ደስ ሊልህ ይባል አቶ ዘለቀ እመነኝ ጥሩ ነበር አሁንም ቢሆን አልረፈደም ማሳውን ማስተካከል እንችላል መቼም ሽፋኑ ተነታተመ እምጂ ዘሩ አይነካም

አባቡ፡-
ዋናው እናንተ ሰላም አውርዲ ልጆቻችሁም ተሸመቀቁ የማሳውን ነገር ቀስ ብለን እንነጋገርበታለን፡፡

ደመቁ፡-
እያለቀሰች/ያ ሁሉ ጥረቴ ባክኖ እኔንም ገረፈኝ ተውኝ እኔ ቤተሰቦቼ ጋር እሄዳለሁ፡፡

ወይኒቱ፡- ቤተሰብ ይሁን ጉድ አይሰማም እኛ ጎረቤቶች እያለን ደግሞ ሰባት ልጆች ትተሽ ወዴት ነው የምትሔጅው ደመቁ? ነውርም አይደል

ዘለቀ፡-
ትሂድ ትጠረግ የምለምናት መስሎዋት ከሆነ ጥርግ ትበል ተመልሳ ግን ቤት አለኝ ብላ እንዳትመጣ

ወይኒቱ፡-
አረ እስዎ አትሔድም ይልቅ አንተ ተረጋጋገ

እቴነሽ፡-
ደመቁ ቁጭ በይ በሞቴ ተረጋጋ፡፡

ደመቁ፡-
እቴነሽ ደግሞ

አባቡ፡-
አቶ ዘለቀ ቀዝቃ በልና እንነጋገር በዚያውም ደመቁ ለምን ማሳውን እንደዛ እንደሸፈነችና ጥቅሙ ምን እንደሆነ ትንገረን፡፡ ከዛ ትረዳት ይሆናል፡፡ ትንሽ ስለ እርሻ እቀባ ስራዋ ታስረዳን፡፡ አዳምጣትና ትቀበለዋለህ፡፡

አቴነሽ፡-
እኔ ደግሞ ቡና ላፍላ ደመቁ የቡና እቃሽ የት ነው?

ደመቁ፡-
ልጆቹ ያመጡልሻል

ባዩ፡-
ጥሩ ቡና እየጠጣን እናውራ

አባቡለ-
በይ ደመቁ ንገሪን ለምን እርሻ እቀባ ላይ መሳተፍ እንደፈለግሽ ንገሪን፡፡ አቶ ዘለቀን አስረጂው

ደመቁ፡-
አሁንስ ተፈቅዶልኛል እንዳወራ ማለቴ ነው

አባቡ፡-
አዎን አስረጂው አቶ ዘለቀ እንዲገባው

ዘለቀ፡-
ሆሆይ……… በይ እንግዲህ በፊትም ለምን ሳታማክሪኝ ሳትነግሪኝ ነው ያልኩት

ደመቁ፡-
እሺ የደጎች ወረዳ ደጋ ነው ቆላ?

ዘለቀ፡-
ቆላ ባይባልም ፀሀያማ ነው ፡፡

አባቡ፡-
ንፋስም አለ

ዘለቀ፡-
አዎ አለ

ደመቁ፡-
ጎርፍም ይመጣል፡፡

ዘለቀ፡-
አዎ ዝናብ የዘነበ ጊዜ ተደፋቱ ጎርፍ ይልክብናል፡፡ 4

ደመቁ፡-
እንግዲህ እርሻ አቀባ መልክአ ምድርና የአየር ፀባይም ችግሮችን ጭምር ለማስተካከል ያግዛል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ጉልበት ይቆጥባል፡፡

ዘለቀ፡-
እኮ እንዴት?

ደመቁ፡-
በበሬ ሲታረስ በተለምዶ ማለት ነው ወንዶች ስንት ጊዜ ታርሳላችሁ?

ዘለቀ፡-
አራትም አምትም ጊዜ፡፡

ደመቁ፡
አንተም በሬዎችም በጣም ትደክማላችሁ፡፡

ዘለቀ፡-
እና ይህ ምን አገኛኘው?

ደመቁ፡-
እርሻ አቀባ ላይ ግን አሁን አዲስ ማረሻ እየመጣ ነው በርከን ማረሻ አወቅከው?

ዘለቀ፡-
ሲሉ ሰምቻለሁ

ደመቁ፡-
በቀደም እነ አቶ ንጉስ ጋር ሰላሙ ቀበሌ እንዳየሀሁት ሽምብራና ካሳባ ከሆነ የሚዘራት መስመር ብቻ በ80 ሳ.ሜ ተለክቶ ይቆፈራ፡፡ ከዘር ወደ ዘር ያለርቀት ደህሞ 40ሳሜ ይደረጋል፡፡ ዋናው ነሀር እኔ የገባኝ ግን መሬት ሳይታረስ ዘር የሚያርፍበትን ጥልቅ ቦታ በችካል ነገር ወይ በዛቢያ ጥልቅ ቦታ በማዘጋጀት ብቻ መዝራት እንደሚቻል ነው፡፡ ማሳው ስለማይታረስ ደግሞ የሰው ጉልበትም ይቀንሳል፡፡ አፈሩም በመታረስ ለነፋስና ጎር አይዳረግም፡፡

እቴነሽ፡-
በሬ ለሌለው ደግሞ

ደመቁ፡-
ወደዛ እየመጣሁ ነው እቴነሽ የአቀባ እርሻ በተለይ ለሴቶች ምቹ የሆነው ደግሞ በበሬ ማረስን ማስቀሩቱ ነው ለዘር የሚሆን ጥልቅ ቦይ ለማዘጋጀት በዛቢያ ወይም ባህላዊ መዶሻ በሲባጎ ተወጥሮ ዘር የሚያርፍበት ቦታ ብቻ እየተለየ ስለሚቆፈር ማሳውስ ለማይታረስ መሬት በፀሀይና በንፋስ አይወሰድም፡፡

ተመስገን፡-
የሽፋኑ ጥቅም ደግሞ

ደመቁ፡-
ቅድም እንደገለፅኩት አካባቢው ፀሀያማ በመሆኑ ወዲያው ሲደርቅ የነበረው አፈር እርጥበቱን ለብዙ ወራት ይዞ ስለሚቆይ ለአዝርአቱ ምቹ ነው፡፡ ቶሎ አይደርቅም፡፡ በተጨማሪም ንፋስም ጎርፍም የሚኖሩበት ጊዜ ማሳ ላይ የተሸፈነው ቅጠላቅጠልና የሰብል ተረፈ ምርት አፈሩ እንዳይወሰድ ይከላከላል፡፡ ቅጠላ ቅጠሎቹና ሳሩ ሲበሰብሱ እንዲጨምር ያደርጋሉ፡፡ ልክ አይደለሁ?

ተመስገን፡-
አረ ልክ ነሽ እንደ የእርግብ አተር፣ ላቭ ላቭ እና ካሳባ እንዲሁም እንሰትና ጎመን አመቱን ሙሉ ምርት የሚሰጡት ሽፋኑ የመሬቱን እርጥበት ይዞት ስለሚቆይ ነው፡፡

አባቡ፡-
ትክክል ነህ ተመስገን ወይዘሮ ደመቁ ይህንን ነበር ያደረገችው

ወይኒቱ፡-
ለጥቂት ደቂቃዎች ዝምታ ለሁሉም መደማመጥ ጥሩ ነው፡፡

አባቡ፡-
አሁንስ ምን አልክ አቶ ዘለቀ?

ዘለቀ፡-
ይህም ቢሆን እኔን ማማከር ነበረባት፡፡

ባዩ፡-
ለማንኛውም አሁን ቀዝቀዝ ብለሃል ቀለቀ እኛም እንሂድ፡፡

አባቡ፡-
አባቡ በሉ እኛ እንሂድ፡፡

-ውሻ ይጮሀል

ወይኒቱ፡-
አረ ውሻው

ባዩ፡-
አረ እባክሽ ዝም ብለሽ ውጪ

ወይኒቱ፡-
እየጮሀብኝ ወደ እኔ ሊመጣ ነው አረ ደመቁ

ደመቁ፡-
መጣሁ ውሻውን ትይዛለች? ና ቡቺ ቡቺ

የውሻ ጩኸት ድምፅ

 

የመሸጋገሪያ ሙዚቃ

ትእይነት – 8

ቦታ፡-
በሰላሙ ቀበሌ

ተዋናዮች ፡-
ንጉስ፣ መሰሉ፣ ፈለቁ

 

የበጎች ድምፅ

ንጉስ፡-
ይጣራል/ፈለቁ ፈለቁ

ፈለቀ፡-
አቤት አያ

ንጉስ፡-
በጎችን የማሳው ዳር ላይ እንዲበሉ አድርጊ

ፈለቀ፡-
ፈተና አለን እኮ ላጠና ብየ ነበር፡፡ እንዴት አድርጌ አይ እኔ እያጠናሁ ወደ ማሳብ ሄዱስ?

መሰለ፡-
ልጆችን ይዘሽ ሂጂና እነሱ ያግዙሽ አንቺ ማጥናተ አለብሽ፡፡ ዋ እኔ እናትሽ እንዳንቺ ተምሬ ኮሌጅ ብጨርስ ኖሮ እዚህ ገጠር ላይ አልገኝም ነበር፡፡

ንጉስ፡-
ወገኛ አሁንሰ ምን ጎደለሽ

መሰሉ፡
ይተው እነጂ ገጠርና ከተማ ደግሞ ከመቼ ነው መወዳደር የጀመረው፡፡

ንጉስ፡-
ምን ጎደለሽ አልኩ አኮ

መሰሉ፡-
የሚበላ የሚጠጣ አላጣሁም ፈጣሪ ይመስገን እኔ ባልማርም ልጆቼን እያስተማርኩ ነው ግን የከተማ ኑሮ አልኖርነውም፡፡

ንጉስ፡-
በእርግጥም የከተማ ኑሮ ከእኛውኑሮ ይለያል፡፡ ነገር ግን ከእነሱ ይልቅ እኛ ብዙ ወጪ የልንም አሁንም እድሜ ለሰለጠነው እርሻ ሰብል አዛን ቀን እየዘራን ቀለባች ሁሉ አጠገባች አለ፡፡ ጎመን በእጅሽ አተር በይ፡፡

መሰሉ፡-
እሱስ ተመስገን ነው፡፡

ንጉስ፡-
እንግዲህ ከአቶ ባዩ ጋር ተነጋግረን ነበር፡፡ ሽማግሌ ሊልክ እየተዘጋጀ ነው

መሰሉ፡-
ከመቼው?

ንጉስ፡-
ፈለቁ መመሪያቂዋም እየደረሰ አይደል? እንደተመረቀች አቶ ባዩ ከልጁ ጋር እንዲጋቡ ይፈልጋል

መሰሉ፡-
እርስዎስ ምን አሉ?

ንጉስ፡-
ለባለቤቴ ጋር ልምከር አልኩት /የፈለቁ ስልክ ይጠራል/

መሰሉ፡-
ትጣራለች/ፈለቁ ፈለቁ ስልክሽ እየጠራ ነው፡፡

ፈለቁ፡-
በርቀት/መጣሁ እቴቴ

ንጉስ፡-
ማን ነው ልጄ?

መሰሉ፡-
አላየሁት እኔን ምን ይሉኛል?

ፈለቁ፡-
የት አለ ስልኬ?

መሰሉ፡-
ያውና ማነው ደግሞ?

ፈለቁ፡-
ማንም

ንጉስ፡-
ማንም ስልክ ዝም ብሎ ይጠራል እንዴ? ለዛ ነው ስልኩን ይዛ የሮጠችው?

መሰሉ፡-
እርስዎ ደግሞ በጎችን ይዘሽ ውጪ አላልዋትም፡፡

ንጉስ፡-
ውጪ መውጣት ሌላ ጊዜ እንደዚህ አያፈጥንም ብየ ነው፡፡

መሰሉ፡-
እግዲህ ሄደች

ንጉስ፡-
እነ አቶ ባዩ ለሰርግ ሽማግሌ መላክ እንደሚፈልጉ እና እስዋ ሃሳብዋ ምን እንደሆነ ነገ ጠዋት እንናግራታለን፡፡

መሰሉ፡-
ተነጋግረው ቢጨርሱ ነው እባክዎት እሱ ግን እኮ ለመጨረስ አንድ አመት ይቀረዋል ገና መች ትምህርቱን ጨረሰ፡፡

ንጉስ፡-
ወንድ ምን ችገር አለበት፡፡ አያረግዝ አይወልድ ትዳሩን እየመራ ይጨርሰዋል

መሰሉ፡-
ዋናው ነገር እስዋ ልትጨርስ መሆንዋ ነው ፈጣሪ ይመስገን

ንጉስ፡-
መቼም ሁለቱም ወጣቶች በእርሻ እቀባ ውጤታማ ይሆናሉ፡፡

መሰሉ፡-
በተለይ የእኔ ልጅ አሁን ከእኛ ጋር ሆናም ጎመን እያመረተች ነው፡፡

ንጉስ፡-
እሱም አባቱ አሁን መሬት እንደሰጠው ነግሮኛል፡፡ ግማሽ ጥማድ ማሳ በሽፋን ሊዘራ ነው ብሎኛል አቶ ባዩ

መሰሉ፡-
በሉ እንገዲህ እኔም ለጠላ የሚሆን ነገር ማዘጋጀት ልጀማምር፡፡

ንጉስ፡-
አዎ ለዛ ብዬ ነው ቀድሜ እየነገርኩሽ ያለሁት፡፡

መሰሉ፡-
እኔ የምልዎት

ንጉስ፡-
አቤት

መሰሉ፡-
አቶ ባዩ ምን ሆነው ነው በእርሻ እቀባ ታቅፈው ማሳ ሸፍነው የማይዘሩት?

ንጉስ፡-
ከብቶቼ ይራባሉ ብሎ ሰግቶ ነው፡፡

መሰሉ፡-
እኛ ለምን አልሰጋንም?

ንጉስ፡-
የእሱ ከብቶች ብዙ ናቸው ሰውየው አዲስ ነገር መቀበል ላይ ችግር አልነበረበትም፡፡ አሁን ግን የእኛንም እያየ ነው፡፡ የተመስገንንም ያያል ያኔ እንግዲህ ምን እንደሚል ማየት ነው፡፡ ልጅትዋ እስካሁን ስልኩን አልጨረሰችም?

ንጉስ፡-
ጥናት አለኝ ብላም አልነበር? መሰሉ

መሰሉ፡-
አቤት

ንጉስ፡-
ይሄውልሽ ተመስገን ጥሩ ልጅ ነው፡፡ ነገር ግን ከጋብቻ በፊት እንዳትሳሳት ልጅሽን ምከሪ እንደማየው ከሆነ በጣም እየተቀራረቡ ነው፡፡

መሰሉ፡-
-ይስቃሉ/ ልጄ ልባም ናት፡፡ እርስዎስ እኔ ጋ ከመጋባታችን በፊት ሲመላለሱ አልነበር፡፡ ያኔ ከብቶች ይዤ ሜዳ ላይ ስወጣ ከየት መጡ ሳይባል ነበር ድምር የሚሉት፡፡

ንጉስ፡-
ቀልደኛ ነሽ አንድ ሶስት ጊዜ መጥቻለሁ መሰለኝ ለዛውም ሽማግሌ ከተላከ በኋላ ነው፡፡

ነሰሉ፡-
አረ ተረሳ ማለት ነው ለነገሩ ጊዜው አለፈ ከተጋባን 20 አመት አለፈ አሁን እኔ ብቻ ነኝ ስለእርስዎ የምጨነቀው፡፡

ንጉስ፡-
ምን አጎደልኩ ደግሞ የአራት ልጆች እናት አደረግኩሽ ነው የጎለ አለ ነይ እስኪ መሰሉየ የድሮ እኮ አስታወስሽኝ፡፡

መሰሉ፡-
አሁን ደግሞ ወዴት ወዴት ሆነ ነገሩ፡፡ ዋይ አረ ይልቀቁኝ የትአድረው ነው ሲነጋ የሚያቅፉኝ፡፡ በሉ ይልቀቁኝማ ይበሉ ልጆቹ ለቁርስ እየመጡ ነው፡፡

 

የመሸጋገሪያ ሙዚቃ

ትእይነት – 9

ቦታ፡-
በገነቱ ቀበሌ

ተዋናዮች ፡-
ወይኒቱ፣ እቴነሽ፣ ደመቁ

እቴነሽ፣
ቆንጆ ቡና ጠጣሁ ወይኒቱየ ዛሬ ደክሞኝ ነበር፡፡ በነብስ ደረስሽልኝ

ወይኒቱ፡-
ምንም አይደል እቴነሽ በስራ ደክመሽ ውለሽ እኮ ነው፡፡ እርሻ አቀባ ከጀመርሽ ስንት ሆነሽ?

እቴነሽ፡-
አሁንማ ስድስት ወራት አለፈኝ

ወይኒቱ፡-
በጣም ይደንቃል ጊዜው ከመቼው ነጎደ?

እቴነሽ፡-
አሁንማ እኔም በተራ የሞዴል አርሶ አደር ሆኜአለሁ፡፡ ደግሞ በቁጠባ ማህበር ታቅፌአለሁ፡፡ ከዛም ብድር አግኝቼ ጎመን ወደ ገበያ የማመላልስበት ባጃጅ እየገዛሁ ነው፡፡ ባጃጅ አትገዢም/ይስቃሉ፡፡

እቴነሽ፡-
ለነገሩ ከጎመን ሽያጭ ጥሩ አግኝቻለሁ፡፡ ስለማይበቃ ግን ተበድሬአለሁ፡፡

ወይኒቱ፡-
ጀግና ነሽ፡፡

እቴነሽ፡-
አሁን በወረዳችን አስር የቁጠባ ማህበራት አሉ፡፡ ከማህበራቱ አባላት ውስጥ እነዚህ ሰዎች የእኔን አሰራር አይተው ስልጠና ለማግኘት /ልምድ ለመውሰድ/ ወደ እኔ ይመጣሉ፡፡

ወይኒቱ፡-
የሚቆጥቡት ሰዎችስ ስንት ይሆናሉ?

እቴነሽ፡-
አንድ መቶ ሃምሳ፣ ከእነሱ ውስጥ ሀምሳ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው

ወይኒቱ፡-
እና ሁሉም በአንድቀን ይመጣሉ ማለት ነው?

እቴነሽ፡-
አይ አይደለም ዛሬ ሀምሳ የሚሆኑት ይመጣሉ ሌሎቹ ደግሞ በሌላ ቀን

ወይኒቱ፡-
ደስ ይላል፡፡ እኔም እንዳንቺ በሽፋን ብዘራ ደስ ይለኝ ነበር አቶ ባዩ የከብቶቼ መኖ ለሽፋን ከዋለ ከብቶቼ ይጎዳ ብለው አሻፈረኝ አሉ፡፡

እቴነሽ፡-
ተመስገን ዘራ አይደል? ደስ ይላል፡፡ ጎበዝ ነው፡፡ እንግዲህ አንድ ቀን አቶ ባዩም ይገለጥላቸዋል፡፡ ወይኒቱየ ያኔ በሽፋን የሚዘራው አንቺ ትሰሪዋለሽ አቶ አባቡ ደግሞ በበሬ የሚታረሰውን ይይዛል፡፡

ወይኒቱ፡-
መስገንንም አግዘዋለሁ ቡቃያው ለምርት አልደረሰም እንጂ

አቴነሽ፡-
ነገር ግን እየደረሰ ነው እኮ ምን ቀረው፡፡ በሽፋን መዝራት ለማሳችን ህምምና ነው፡፡ በተለይ ለእኛ ለሴቶች መሬቱን ማረስ ስለቀረልን ራሳችን ዘሩን የሚያርፍበት ቦታ ለይተን በመቆፈርያ ቆፍረን እንድንዘራና በእርሻ እንድንሳተፍ ያመቸናል፡፡ በዛ ላይ ያገኘነውን የቤት ጥራጊ ቅጠላ ቅጠል በየጊዜው ወደ ማሳችን ስለምንጨምር ማሳችን በማልማት እኛ እንሻላለን፡፡

ወይኒቱ፡-
አንቺ ግን ስንት ኩንታል አገኘሽ እቴነሽየ በሞቴ ሳትደብቂ ንገሪኝ?

እቴነሽ፡-
መጀመሪያ /ትስቃለች/ ግማሽ ጥማድ ላይ ነው የዘራሁት፡፡ በተጨማሪም የተለያዩ ሰብሎች እያፈራረቅኩ ነው የዘራሁት፡፡ በቆሎና የእርግብ አተር፡፡ በቆሎውን ሰበሰብኩ የእርግብ አተሩ ግን ይቆያል፡፡ አመቱን ሙሉ ይቆያል፡፡ በየጊዜው አተሩን መልቀም ነው፡፡ አከታትለን ደግሞ ጎመን በሌላ መሬት ዘርቼ በአንድ ወር ደረሰ፡፡ እሱንም እየሸጥኩኝ ነው፡፡ መጀመሪያ ላይ በቆሎ ከግማሽ ጥማድ ሶስት ኩንታል አሁን ግን 40 በ60 አድርጌ እየዘራሁኝ ነው፡፡

ወይኒቱ፡-
ጉድነው እኛ እኮ ግማሽ ጥማድ በልማድ ዘርተን አንድ ኩንታል ካገኘን ጥሩ ነው፡፡ ደግሞስ ድካሙ፡፡

እቴነሽ፡-
መጀመሪያ እኮ ዘመዶቼ ማሳውን አቆሸሽው ብለው ሊበሉኝ ደርሰው ነበር፡፡

ወይኒቱ፡-
ለነገሩ እውነታቸው ነው፡፡- ሲታይ ማሳው ሳር በሳር እንዲሁም ጭድናቅጠል ሲታይ ውጤቱ ላላወቀው አይፈረድበትም፡፡

እቴነሽ፡-
ትስቃለች

ወይኒቱ፡-
እርግብ አተሩን ሰንት አገኘሽ እቴኑ? የአርታዚው ማስታወሻ፡- እቴኑ የእቴነሽ ስም ሲቆላመጥ ነው:፡

እቴነሽ፡-
በቀደም ወደ 75 ኪሎ ገበያ ወሰድኩኝ፡፡ አሁንም እየሰበሰብኩ ነው፡፡ እሱ በማሳ ላይ እርጥበት እግኝቶ ስለሚቆይ አመት ሙሉ ፍሬው ይለቀማ፡፡ ጎመንም አመት ሙሉ መቀንጠስ ነው፡፡

ወይኒቱ፡-
በአጠቃላይ በማሳ ሽፋን ሰንት ጥማድ ዘራሽ ማለት ነው?

እቴነሽ፡-
በኋላ ከዘራሁት ጎመን ጋር ተደምሮ አንድ ጥማድ መሬት፡፡ ቀስ በቀስ ሌላውም በሽፋን መዝራትን አስፋፋለሁ፡፡ ደግሞ ሰብል ማፈራረቅ ጠቃሚ ነው፡፡ በቀጣይ በቆሎ የዘራሁት ማሳ ላይ ሽንብራ እዘራበታለሁ፡፡ ሰብል ማፈራረቅ ለምርታማነት ጥሩ ነው፡፡ ከሁለት አመት በኋላ ማፈራረቅ፡፡

ወይኒቱ፡-
ግሩም ጥበብ ነው፡፡

እቴነሽ፡-
ሰሞኑን ደግሞ ያቺ ደመቁ ተነስቶባታል፡፡ተጨማሪ ጎመን ዘርቼ ብታይ ቅናት ሊገድላት ነው፡፡

ወይኒቱ፡-
እስዋም በሽፋን ዘርት የለ? ምን አስቀናት?

እቴነሽ፡-
መጀመሪያ ባልየው አበላሸባት እኮ በኋላ ጎመን ተክላ አሁን ተሎ ደርሶላታል እኔ ምን አደረኳት እንጃ እኔን እያየች ጎረቤቶቼን አልቻልናቸውም ትላለች፡፡ እንግዳ ወደ ቤት ሲመጣ መከራ ነው ተንጠራርታ ታያለች፡፡

ወይኒቱ፡-
እንግዲህ እንደ ታናሽ እህትዋ እያየችሽ ይሆናል፡፡ መቀራረብም ሊሆን ይችላል፡፡ ቻያት እቴኑ አንቺ እንደሆንሽ ጨዋ ጀግና ጎበዝ ከልጆችዋ ጋር የምትማር እናት ነሽ፡፡ አሁንማ ትምህርቱንም አፈጠንሽው አይደል?

ደመቁ፡-
– በርቀት ትጣራለች? እቴነሽ እቴነሽ

ወይኒቱ፡-
ደመቁ እየጠራችሽ ነው፡፡ /ይስቃሉ/

እቴነሽ፡-
ምን ሆናነው ደግሞ ምን ሆነሽ ነው?

ደመቁ፡-
የታች ሰፈር ሰዎች ለስልጠና ወዳንቺ እየመጡ ነው

እቴነሽ፡-
ውይ ልብሴ ሳይቀር፡፡ ሄድኩኝ ወይኒቱ

– የሰዎች ድምፅ ጫጫታ እየቀረበ ይመጣል

 

የመሸጋገሪያ ሙዚቃ

ትእይነት – 10

ቦታ፡-
በገነቱ ቀበሌ እነ ባዩ ቤት

ተዋናዮች ፡-
ባዩ፡- ወይኒቱ፣ ተመስገን፣ ፈለቁ

 

– የሰዎች ጫጫታ ይሰማል

– የከብቶች ድምፅ ይሰማል

– የስልክ ጥሪ ድምፅ

 

ወይኒቱ፡-
ተመስገን ስልክህ እየጠራ ነው

ተመስገን
ፈለቁ ናት አባየ በሰጠኸኝ መሬት በማሳ የዘራሁትን ሰብል ለማየት እመጣለሁ ብላ ነበር፡፡

ወይኒቱ፡-
በል ሂድና ተቀበላት ልጄ ቤቱን ላሰናዳ

ባዩ፡-
ከውጪ እየገቡ/ ወዴት ነህ ልጄ?

ወይኒቱ፡-
እንግዳ ይቀበላል እርስዎ ይግቡ

ባዩ፡-
እህህ መጣች እንደተ ግቢ በላት ሽማግሌዎችም ጥሩ መልስ ይዘው መጥተዋል፡፡

ወይኒቱ፡-
ድሮስ ተዋደው የለ እንዴ

ባዩ፡-
ቢሆንም አባት አሁንም አይሆንም ማለት ይችል ነበር፡፡

ወይኒቱ፡-
ሲጀምር ልጃችን ጥሩ ልጅ ነው ሲቀጥል እነሱም ከእኛ ጋር ዝምድና ይፈልጋሉ፡፡

ባዩ፡-
ልጃቸውም ጥሩ ልጅ ናት ይልቅ ዝግጅትሽን ጀምሪ፡ ለሰርግ

ወይኒቱ
ወይ አሁን ሊነግሩኝ? መዘጋጀመት ከጀመርኩ ቆየሁ፡፡ ውይ ልጆቼ መጣችሁ ግቡ ግቡ ደህና ነሽ ፈለቁየ ልጄ ግቢ

ፈለቁ፡-
ደህና ነኝ ደህና ናችሁ

ባዩ፡-
በሉ እኔ ውጪ ጉዳይ አለኝ ተጫወቱ ወይኒቱ

ወይኒቱ፡-
አቤት

ባዩ፡-
ልጆቹን አስተናግጂያቸው

ወይኒቱ፡-
በደንብ ነዋ!

ተመስገን፡-
አየሽ ፈለቁ የእኔ እናት እንዲህ ናት ፍትዋ እንደብርሀን የበራ

ወይኒቱ፡-
/እየሳቁ/ አጭበርባሪ የስዋ እናትም ብርሀን ናቸው

ተመስገን፡-
እሱማ ነው አሁን ግን ስላንቺ ነው ያወራሁት

ወይኒቱ፡-
መርዋትሽ እየደረሰ ነው አሉ ፈለቁ?

ፈለቁ፡-
አዎ እየደረሰ ነው

ተመስገን፡-
ከዛ በኋላማ ሰርግና ምላሽ ነው የሚባለው እናቴ ወገብዋን ሸጥ አድርጋ እየተዘጋጀች ነው፡፡

ወይኒቱ፡-
ያኔማ ያን ቀንማ የደስታ ቀን ነው፡፡ ማነው ልጄ በር ላያ ያለው ፖሊስ ነው እንዴ… ልጄን ምን ፈልጎት ነው ማነህ ምን ፈልገህ ነው፡፡

ተመስግን፡-
ቆይ እስኪ እኔ ልየው ውይ ፓሊስ ትያለሽ? /ይስቃሉ/ ካኪ ለብሶ አይተሸ ነው ይሄ እኮ ነጋዴ ነው አየ እማየ ፖሊስ አይታ አታውቅም እንዴ የሰፈር ጥበቃ መስሎሽ ነው አይደል?

ፈለቁ፡-
ማን ነው?

ተመስገን፡-
ነጋዴ ነው ማሳ ላይ በሽፋን የዘራሁትን በቆሎ ገና ሳይታጨድ ስለዋጋ ለመስማማት ነው የመጣው ለመግዛት ልውጣና ላናግረው መጣሁ

 

የመሸጋገሪያ ሙዚቃ

ትእይነት – 11

ቦታ፡-
በገነቱ ቀበሌ እነ ዘለቀ ቤት

ተዋናዮች ፡-
ዘለቀ፣ ደመቁ፣ አባቡ፣

 

-ውሻ ይጮሀል

ዘለቀ፡-
ደመቁ የሆነ ሰው ሳይመጣ አይቀርም ውሻው እየጮሀ ነው

ደመቁ፡-
ማነው

አባቡ፡-
አባቡ ነኝ ደመቁ

ደመቁ፡-
ውይ አባቡ ግባ ደህና ነህ?

አባቡ፡-
ደህና ነኝ አቶ ዘለቀ አለ?

ዘለቀ፡-
አለሁኝ አባቡ ግባ

አባቡ፡-
እርሳ እቀባ እንዴት ይዟችኋል የቸገረ ነገር አለ ወይ?

ዘለቀ፡-
አሁንማ ተግባብተናል ያኔ ደመቁ ስትሰለጥን በቆሎ ነበር የሰለጠነችው፡፡ በኋላ እኔና እስዋ ተመካክረን እኮ ለጊዜው ጎመን ሰራ

አባቡ፡-
ጎመን ደግሞ በሽፋን ቶሎ የደርሳል ሽፈኑ የአፈሩ እርጥበት ስለሚጠብቅ አመቱን ሙሉ ይቆያል፡፡

ዘለቀ፡-
የሚገርም እውቀት ነው ሞክረው ውጤቱን እያየን ነው

ደመቁ፡-
አቤት አቤት የኔ ሀጢያት

አባቡ፡-
ምነው ደመቁ?

ደመቁ፡-
አባቡ በፊት አንተ እቴነሽ ቤት ስትመላለስ እውነት ለመናገር ሌለ ነገር መስሎኝ ነበር

ቀለቀ፡-
በቁጣ/ ምን እያልሽው ነው?

ደመቁ፡-
ዛሬ ንስሀ ገባሁ እኛንም ተመላልሶ ሲያስረዳ መመላለሱ ለእገዛ መሆኑ አሁን በኔ ላይ ሳየውገባኝ ለማለት ነው፡፡

ዘለቀ፡-
ነገር ሳያጣሩ አይደመደምም

አባቡ፡-
ምንም አይደለም፡፡ /ይስቃል/ ያኔ ስላልገባሽ ነው፡፡ ዋናው አሁን እውነታውን ማወቅሽ ነው፡፡

ደመቁ፡-
ዛሬ እንኩዋን እንደ ጎረቤቶቼ ወግ ደረሰኝ ወደ 70 ኮሎ የሚሆን ጎመን ሰብስቤአለሁ፡፡ ውደ ገበያም እወስደዋለሁ፡፡ ብቻ እቴነሽ ቀድማ ስለጀመረች ብዙ ተጠቅማለች፡፡

አባቡ፡-
አሁንም ትደርሽበታለሽ፡፡ ዋናው መጀመርሽ ነው ደመቁ፡፡

ዘለቀ፡-
ትላንት ታች ሰፈር ስልጠና እየሰጠህ ነበር አሉ፡፡

ዘለቀ፡-
ለምን መሰለህ አባቡ በፊት ተሰባስብን ስለ እርሻ እቀባ እናወራ ነበር፡፡ አንደኛው ንደ ችግር የሚነሱት እንዴት አንድ ጊዜ ብቻ ታርሶ ወይም ተቆፍሮ ጥሩ ምርት ይገኛል የሚል ጥያቄ ነው፡፡ 2ኛው ደግሞ የሰብል ተረፈ ምርት ሰብል ላይ መተው የሰነፍ ገበሬ ምልክት ነው ብለን እናምን ነበር፡፡ ሌላው ደግሞ በሽፋን መዝራትና የሰብል ቅሪት ማሳ ላይ ተጋድሞ ስናይ ቆሻሻ ማሳ ነው ብለን እናስብ ነበር ሌላው ሳይታረስ ሳይለሰልስ ጥሩ ምርት ይገኛል ብለን አስበን አናውቅም፡፡

አባቡ፡-
አሁንስ አቶ ዘለቀ?

ዘለቀ፡-
አሁን አኮ እርሻ አቀባ የተጠቀምን ሰዎች አመቱን ሙሉ የመርት ስራ አለ፡፡ በፊት በጋ ላይ ዛፍ ጥላ ስር ቁጭ ብለን የምናሳልፈው ጊዜ ቀረ፡፡ አሁን አይደለም እኛ ሴቶቻችንም ስራ ላይ ናቸው፡፡

አባቡ፡-
አዎ በእርሻ አቀባ አሰራር ስራዎቹ የወንዶች ብቻ ሳይሆኑ የሴቶችም ጭምር ናቸው፡፡

ደመቁ፡-
ሬድዮ ማዳመጥንም ለምደናል፡፡ ስናዳምጥ ስለ እርሻ እቀባ ብዙ ጥያቄ ይመለስልናል፡፡

አባቡ፡-
በቡድንን ሆናችሁ ማዳመጣችሁ በእርሻ እቀባ ዙሪያ እውቀት ታገኛላችሁ ጥሩ ነው፡፡

ደመቁ፡-
እኔ አሁን ሙሉ በሙሉ ማሳ ላይ እየሰራሁ ነው በፊት ግን ቤት ውስጥ ሆኜ ምግብ ከማዘጋጀታችን ልጆች ከመንከባከብ ውጪ በቀጥታ በእርሻ ስራ ተሳታፊ አልነበርኩም፡፡

አባቡ፡-
አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ አቶ ዘለቀ

ዘለቀ፡-
እሺ

አባቡ፡-
እርሻ እቀባ ታቅፈህ በማሳሽፋን መዝራት ምን አስቸጋሪ ነገር አለው ትላልህ

ዘለቀ፡-
ሁሉም መሬታችን በማሳ ሽፋን እና በእርሻ እቀባ ቢዘራ ልዩ ውጤት ያስገኘ ነበር፡፡ አሁን ግን በውስን ማሳ ነው እየዘራን ያለነው፡፡ እናም ሁሉም ሰብላችን በሽፋን እንድንዘራ አግዙን

አባቡ፡-
ለሁሉም ማሳ በቂ ሽፋን ማግኘት ከባድ ነው እያልክ ነው?

ዘለቀ፡-
አዎ

አባቡ፡-
ማሳን ለመሻፈን የሚጠቅሙ የተክል አይቶችን ማብቀል ጥሩ ሀሳብ ነው፡፡ ለምሳሌ እንደ ከሳባ፣ ላቭ ላቭ፣ የእርግብ አተር፣ አኩሪ አተር፣ እንሰት፣ ሙዝ የመሳሰሉት የመዝራት ልምድ ማዳበር ከዚያ ውጪም እንደ ብሳና ያሉ ዛፎች በመትከል ብዙ መሸፈኛ ማግኘት ይቻላል፡፡ ይህም ከዛቢያ ለማስፋት ይጠቅማል

ደመቁ፡-
በሉ እናንተ አውሩ እኔ ጎመን ይዤ ገበያ ልሂድ

አባቡ፡-
እናንተን አሳምኜ እኔማ ገና ያላመኑትን ለማሳመን መስራቴን እቀጥላለሁ፡፡ እኔም ልሂድ

ዘለቀ፡-
በል ደህና ዋል አባቡ አንቺ ደግሞ ቆይ ጎመኑን ላሸክምሽ

ደመቁ፡-
ደህና አሁን ነው እንጂ እንደ እቴነሽ እኔም ባጃጅ እገዛለሁ፡፡

 

የመሸጋገሪያ ሙዚቃ

ትእይነት – 12

ቦታ፡-
በገነቱ ቀበሌ

ተዋናዮች ፡-
ጠባዩ፣ ወይኒቱ፣ ተመስገን፣ እቴነሽ፣ ደመቁ፣ አባቡ
 

– የወንዶችና የሴቶች ወሬ ድምፅ በሰርግ ዋዜማ ስራ ላይ

– የከብቶች ድምፅ

 

ወይኒቱ፡-
ና ተመስገን ጎሽ፣ ዛሬ ደግሞ ምን ሆነሀል ለራሴ የሰርግ ዋዜማ ስራ በዝቶብኛል

ተመስገን፡-
እማየ ከብቶቹን እኔ አያቸዋለሁ ወደ ስራሽ ሂጂ

እቴነሽ፡-
የሰርጉን ስራማ ጎረቤት አለን አትጨነቂ ወይኒቱ ደግሞ እኮ ብዙው ስ ተሰራ

ባዩ፡-
ወይኒቱ

ወይኒቱ፡-
አቤት

ባዩ፡-
ቅድም ምን ብየሽ ነበር

ወይኒቱ፡-
እባክዎትን ልስራበት

ባዩ፡-
በይ ተይው

ወይኒቱ፡-
እሺ ይንገሩኝ

ባዩ፡-
ልስራበት አላልሽምባዩ፡-

ወይኒቱ፡-
እንግዲህ ይንገሩኝ፣ የምስራች እነግርሻለሁ ብለውኝ ነበር እሺ ምስር ይብሉና /ይንገሩኝ /ይስቃሉ/

ባዩ፡-
እርሻ እቀባን እና በሽፋን መዝራትን መጠቀም ልጀምር ነው፡፡ እውነት ነው በአንድ ጥማድ መሬት ከአባቡ ጋር ተነጋግሬ ወሰንኩ፡፡ ላቭ ላቭ ካሳባ እተክላለሁ አንቺ ደግሞ በግማሽ ጥማድ ጎመንና በርበሬ ለከብቶቼ ቀለብም የሆነ መሬት ላይ መኖ እዘራለሁ፡፡

ወይኒቱ፡-
/በደስታ/ እልልልልልል

እቴነሽ፡-
ወይኒቱ ምን ተገኘ

ወይኒቱ፡-
አቴነሽ ነይ ስሚ ባዩ በማሳ ሽፋን ሊዘሩ ነው፡፡ እኔም ጎመን ልዘራ ነው፡፡

እቴነሽ፡-
ደስ የሚል ነገር ነው በስተመጨረሻ ወሰኑ ድሮም እንደሚሆን ተስፋ ነበረኝ፡፡

ባዩ፡-
አውጥቼ አውርጄ ሳየው እኔና አባቶቼ ስንጠቀምበት የነበረው በልማድ የሚከናወን እርሻ አድካሚ እንደሆነ ብቻ ሳይሆን መርቱም የድካሙ ያክል አለመሆኑን ተገንዝቤአለሁ፡፡ እናም በቀሪው ህይወቴ በእርሻ እቀባ በማሳ ሽፋን በመዝራት የተሻለ ኑሮ ለመምራት ወስኛለሁ፡፡ በሉ የሰርጉን ስራ አቀላጥፉት፡፡

ወይኒቱ፡-
ባዩ በልጄ ሰርግ ዋዜማ ደርብ ደስታ አደረግክልኝ ባዩ አልልልልል ትላለች

ተመስገን፡-
በደስታ? አባየ ደስታ በደስታ አደረግከን እኮ አሁን ደግሞ የእኔ ሚዜዎች እየመጡ ነው ወደ ሙሽሪት ቤት ጥሎሽ ሊወስዱ

እቴነሽ፡-
ወይኒቱ ከበሮውን አምጪው

-የከበሮ ድምፅ

ደመቁ፡-
ከርቀት እቴነሽ ከገበያ መመሌ ነው፡፡ እኔም መጣሁ

አባቡ፡-
ቀስ በይ ደመቁ እንዳትወድቂ?

ደመቁ፡-
አረ እባክህ የተመስገንንና የፈለቁ ሰርግ ዋዜማ እ ነው

-ከበሮው እና ዘፈኑ ደምቆ ይሰማል

 

 

Acknowledgements

ምስጋና

ለአልማዝ በየነ- ጋዜጠኛና ደራሲ

አርትኦት፡ ቪጀይ ኩዴ ፎርድ

Reviewed by: Sahlemariam Menamo, Conservation agriculture training specialist, Canadian Foodgrains Bank

This work was created with the support of Canadian Foodgrains Bank as part of the project, “Conservation Agriculture for building resilience, a climate smart agriculture approach.” This work is funded by the Government of Canada, through Global Affairs Canada, www.international.gc.ca