የኮቪድ-19 ራዲዮ ስፖቶች

ጤና

Script

Spot 1

ሳውንድ ኢፌክት፡-
የዶሮ ጩኸት

ተራኪ፡-
ልብ በሉ አርሶ አደሮች!

ዶሮዎች እና ሌሎች እንስሳት ሰዎችን ኮቪድ-19 ሊያስይዙ ይችላሉ የሚል አሉባልታ አለ፡፡ ትክክል አይደለም! ማንኛውም እንስሳ ወደ ሰዎች ኮቪድ-19 ሊያስተላልፍ እንደሚችል የሚያሳይ መረጃ የለም፡፡

ሰዎች ቫይረሱ የሚይዛቸው ከሰው ጋር በሚኖር ንክኪ ወይም የተበከሉ እቃዎችን በመንካት ነው፡፡

በእርሻ ቦታችሁ ላይ ንጽህናችሁን በመጠበቅ እና አቃላዊ እርቀትን በመጠበቅ ራሳችሁን በበሽታው ከመያዝ መጠበቅ ትችላላችሁ፤ አካላዊ እርቀት ማለት የቤተሰባችሁ አባል ካልሆነ ወይም እርሻ ላይ አብሯችሁ ከማይውል ሰው ቢያንስ የአንድ ሜትር እርቀት መጠበቅ ማለት ነው፡፡


Spot 2

አልኮል መጠጣት ከኮቪድ-19 አይከላከልም!

አዎ፣ የአለም ጤና ድርጅት አልኮል ያለው የእጅ መጥረጊያ መጠቀም ይመክራል፡፡ ነገር ግን አልኮል መጠጣት ኮቪድ-19ን መከላከልም ማከምም አያስችልም፡፡

እንዲያውም አልኮል በየጊዜው ወይም አብዝቶ መጠጣት ከካንሰር እስከ ጉበት በሽታ ላሉ በሽታወች ሊያጋልጥ ይችላል፡፡


 

Spot 3

ባል፡-
ዛሬ መዳኒት ቤት ሂጄ ያየሁት መቼም ጉድ ነው!

ሚስት፡
– ምን አየህ?

ባል፡-
አንድም የጸረ ተህዋሲያን መድሃኒት የለም! መደርደርያው እንዳለ ባዶ ነበር! ባገሩ ሁሉ መዳኒት የለም አሉ፡፡ ሰዎች ከኮቪድ-19 የሚያድናቸው መስሏቸው ገዝተው ጨርሰውታል!

ሚስት፡
– (በጭንቀት ትተነፍሳለች) ይሄ አደገኛ ነው፡፡ ሰው ሁሉ አለምክንያት ገዝቶ ከጨረሰው፣ መዳኒቱ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ምን ሊውጣቸው ነው?

ተራኪ፡
– የጸረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች ኮቪድ-19ን ለመከላከለም ለማከምም አይችሉም፡፡ የጸረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች ለባክቴሪያ እንጂ በቫይረስ ለሚመጡ በሽታዎች አይሆኑም፡፡ ኮቪድ-19 በቫይረስ የሚመጣ በሽታ ነው፡፡

ኮቪድ-19ን ማከም እንደሚችሉ በሳይንስ ያልተረጋገጡ መዳኒቶችን አትግዙ፡፡ እናንተ ስትገዟቸው መድሃኒቶቹን ለከፋ የጤና ችግር የሚፈልጓቸው ታካሚዎች ከገበያ ላይ ሊያጧቸው ይችላሉ፡፡


Spot 4

አንደኛ ሰው፡-
አክስቴ ግራ እየገባት መጥቷል፡፡ የምታደርገውን ብታዩ!

ሁለተኛ ሰው፡-
ምን አረገች?

አንደኛ ሰው፡-
ኮሮናቫይረስ ለመከላከል የማታደርገው የለም፡፡ ሎሚ እና የዳቦ ማኮፈሻ ትጠጣለች፣ በአቼቶ ትጉመጠመጣለቸ፣ ብርቱካን እያፈላች እንፋሎቱን ትስባለች – ይሄ ሁሉ በጤና ይጠብቀኛል ትላለች፡፡

ሁለተኛ ሰው፡-
ይሄ አሳሳች መረጃ ይመስለኛል፡፡ ኮሮናቫይረስን መከላከል እንዲህ ቀላል ቢሆን ኖሮማ እንዲህ ያለ ከባድ ችግር አይሆንም ነበር፡፡

ተራኪ፡-
አንዳንድ ንጥረ ነገሮች ከኮቪድ-19 የመከላከል ወይም የማዳን ችሎታ እንዳላቸው የሚወሩ አሉባልታዎች አሉ፡፡ የአለም ጤና ድርጅት እንደሚለው ከሆነ ግን ለበሽታው መድሃኒትም ሆነ ክትባት እስካሁን የለም፡፡

ቫይረሱን እንዳይሰራጭ ለመከላከል ዋነኛው መንገድ እጅን ቶሎ ቶሎ መታጠብ፣ ከሚያስላቸው ወይም ከሚያስነጥሳቸው ሰዎች ቢያንስ አንድ ሜትር መራቅ፣ ፊትን አለመንካት እና ሲያስላችሁ ወይም ሲያስነጥሳችሁ አፍና አፍንጫችሁን በክርናችሁ ወይም በሶፍት መሸፈን ነው፡፡


Spot 5

አንደኛ ሰው፡-
ኧረረ ጸሃዩ እንዴት ያቃጥላል ዛሬ!

ሁለተኛ ሰው፡-
በጣም! የዘንድሮ በጋ አልተቻለም፡፡

ሶስተኛ ሰው፡-
ግንኮ የሙቀቱ ጥቅሙ ኮሮናቫይረስን መግደሉ ነው፡፡

አንደኛ ሰው፡-
(ይስቃል) ወዳጄ እንደሱማ ቢሆን ኖሮ አፍሪካ ውስጥ ኮሮናቫይረስ አይኖርም ነበር!

ተራኪ፡-
ጸሃይ በመሞቅ እና ከ25 ዲግሪ በላይ ላለው ሙቀት ራስን በማጋለጥ ኮቪድ-19ን መከላከል አይቻልም፡፡ ሞቃት የአየር ጠባይ ያላቸው አገሮች ውስጥ ብዙ ሰዎች ኮቪድ-19 ተገኝቶባቸዋል፡፡ በጸሃያማም ሆነ በሞቃት የአየር ሁኔታ ውስጥ በኮቪድ-19 ልትያዙ ትችላላችሁ፡፡

ራሳችሁን ለመከላከል እጃችሁን ቶሎ ቶሎ ታጠቡ፣ አይናችሁን፣ አፍና አፍንጫችሁን አትንኩ፡፡


Spot 6

በሙቅ ውሃ መታጠብ ወይም የእጅ ማድረቂያ ማሽን መጠቀም ከኮቪድ-19 አይከላከልም፡፡

የአለም ጤና ድርጅት እንደሚለው የኮቪድ-19 ምልክቶችን ማስታገስ የሚችሉ አንዳንድ መድሃኒቶች ሊኖሩ ይችላሉ፤ በሽታውን መከላከልም ሆነ ማዳን የሚችል መድሃኒት ስለመኖሩ ግን ምንም መረጃ የለም፡፡


Spot 7

ሕጻን ልጅ፡-
እምምምም … እማዬ ይሄ ሾርባ ይጣፍጣል፡፡ ምን አድርገሽበት ነው?

እናት፡-
ነጭ ሽንኩርት፡፡ ነጭ ሽንኩርት ከኮሮናቫረስ ይከላከላል አሉ፡፡ ስለዚህ ሁሉም ምግብ ውስጥ ሻይ ውስጥ ጭምር እያደረግሁት ነው፡፡

ሕጻን ልጅ፡-
(ሻይውን እፉት ይልና መልሶ ይተፋዋል) ሲያስጠላ!

ተራኪ፡-
ነጭ ሽንኩርት መመገብ ከኮቪድ-19 አይከላከልም፡፡ ነጭ ሽንኩርት ከብዙ በሽታዎች የሚከላከል ጤናማ ምግብ ነው፡፡ ነገር ግን ነጭ ሽንኩርት መመገብ ከኮቪድ-19 እንደሚከላከል የሚያሳይ ምንም መረጃ የለም፡፡


Spot 8

ሳውንድ ኢፌክት፡-
የቢምቢ ድምጽ፡፡ ጨብ የሚያደርግ የእጅ ድምጽ፡፡

ወንድ ሰው፡-
አሃ! ወባው አነሰና አሁን ደግሞ ቢምቢ ኮሮናቫይረስ እንዳያስይዘኝ ልጨነቅ፡፡:

ተራኪ፡-
ኮቪድ-19 በቢምቢ ንክሻ አይተላለፍም፡፡ ኮቪድ-19 የሚተላለፈው ሰው ሲያስለው ወይም ሲያስነጥሰው በሚፈናጠቁ ጠብታዎች ወይም በምራቅ እና በንፍጥ አማካኝነት ነው፡፡


Spot 9

አንደኛ ሰው፡-
ተመልከቱ ትንፋሼን ከ10 ሰከንድ በላይ መያዝ እችላለሁ፡፡ ዶክተሮች እንደሚሉት ኮቪድ-19 የለብኝም፡፡

ሁለተኛ ሰው፡-
የምር? እኔም ልሞክር እስኪ! (ትንፋሹን በደምብ ወደ ውስጥ ይስብና መሳል ይጀምራል፡፡)

ሦስተኛ ሰው፡-
ጓደኞቼ እራሳችሁን ልትገሉ ነው እንዴ? መቼም ኮቪድ-19 የሚረጋገጠው በላብራቶሪ ምርመራ ብቻ እንደሆነ ጠፍቷችሁ አይደለም!

ተራኪ፡-
አትሞኙ፡፡ ሳያስላችሁ ወይም ሳያስጨንቃችሁ ትንፋሻችሁን ለ10 ሰከንድ ወይም ከዚያ በላይ ስለያዛችሁ ከኮቪድ-19 ነጻ ናችሁ ማለት አይደለም፡፡

የአለም ጤና ድርጅት እንደሚለው ኮቪድ-19 ሊኖርባቸው እንደሚችል የጠረጠሩ ሰዎች ቤታቸው ውስጥ እንዲቆዩ እና ባካባቢቸው ያሉ የጤና ባለስልጣናትን ደውለው የሕክምና ክትትል እንዲያገኙ ማድረግ አለባቸው፡፡

የኮቪድ-19 ቫይረስ እንዳለባችሁ ማረጋገጫው ብቸኛ መንገድ የላብራቶሪ ምርመራ ነው፡፡ ትንፋሽን በመያዝ እራሳችሁን ላደጋ ልታጋልጡ ትችላላችሁ እንጂ ቫይረሱ ይኑርባችሁ ወይም አይኑርባችሁ ማረጋገጥ አትችሉም፡፡


Spot 10

ኮሮናቫይረስ የሞት ፍርድ አይደለም፡፡

ቫይረሱ ካለባቸው ሰዎች 80% የሚሆኑት ቀላል ሕመም የሚሰማቸው ሲሆን ሙሉ በሙሉ ያገግማሉ፡፡ በሌሎች ሰዎች የመገለል ችግር ግን ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡ ሰዎች ቫይረሱ የተገኘባቸውን ሰዎች ሊያገሏቸው፣ ጥሩ ያልሆነ ነገር ሊናገሯቸው ወይም ሌላ መጥፎ ነገር ሊያደርጉባቸው ይችላሉ፡፡

እንደዚህ አይነት ባሕሪ ሰዎች እንዳይመረመሩ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ያገገሙ ሰዎች ላይ የሚደረግ አድልኦ መቆም አለበት፡፡ እርስ በራሳችን በመጠባበቅ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ሰዎችን ከጉዳት እንከላከል፡፡ በዚህ ችግር ውስጥ ሁላችንም በአንድ ላይ እንገኛለን፡፡


Spot 11

ሳውንድ ኢፌክት፡-
መሳል እና ማስነጠስ

ኮቪድ-19 በጣም ተላላፊ በሽታ ነው! እንዴት እንደሚሰራጭ ታውቃላችሁ?

ሰዎች ኮቪድ-19 ካለባቸው ሌሎች ሰዎች ኮቪድ-19 ይተላለፍባቸዋል፡፡ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ሲያስላቸው፣ ሲያስነጥሳቸው እና ሲተነፍሱ በሚፈጠሩ ትናንሽ ፍንጣቂዎች አማካኝነት ይሰራጫል፡፡ በአቅራቢያ ያሉ ሰዎች እነዚህን ፍንጣቂዎች ሊተነፍሱ ይችላሉ፣ ወይም ፍንጠቂዎቹ በአካባቢ ባሉ እቃዎች ላይ ሊያርፉ ይችላሉ፡፡ ሰዎች ፍንጣቂዎቹን ሲተነፍሱ ወይም ፍንጣቂዎቹ ያረፉባቸውን እቃዎች ሲነኩ እና ከዚያ አይኖቻቸውን፣ አፍንጫቸውን ወይም አፋቸውን ሲነኩ ቫይረሱ ይተላለፍባቸዋል፡፡

ስለዚህ እራሳችሁን እና ሌሎችን ጠብቁ፡፡ ከቤት ውጭ ስትሆኑ ጭንብል ልበሱ፣ ከሌሎች ሰዎች ቢያንስ የአንድ ሜትር እርቀት ጠብቁ፣ በቻላችሁ ጊዜ ሁሉ እጃችሁን ታጠቡ፡፡


Spot 12

ሳውንድ ኢፌክት፡-
መሳል እና ማስነጠስ

ይሰማችኋል? የተለመደው የሳል ድምጽ አሁን አሁን አደገኛ የሆነ ችግር ምልክት ሊሆን ይችላል፡፡ ኮቪድ-19 ሳንባን የሚያጠቃ ተላላፊ በሽታ ነው፡፡ በሽታው ከበሽተኛ ሰው አይኖች፣ አፍንጫ ወይም አፍ የሚወጡ ፍንጣቂዎች ጤነኛ ሰውን ሲነኩ ይተላለፋል፡፡

የኮቪድ-19ን መተላለፍ ለመከላከል ሲያስነጥሳችሁ ወይም ሲያስላችሁ ሁል ጊዜ አፍና አፍንጫችሁን በክርናችሁ ወይም በሶፍት ሸፍኑ፡፡ የተጠቀማችሁበትን ሶፍት ወዲያው አስወግዱ፡፡

እነዚህን መመርያዎች በመከተል በዙርያችሁ ያሉ ሰዎችን ከኮቪድ-19 እና እንደ ጉንፋን እና ኢንፍሉዌንዛ ከመሳሰሉ በቫይረስ ከሚመጡ በሽታዎች መከላከል ትችላላችሁ፡፡


Spot 13

ገበያ የምትውሉ ነጋዴዎች ናችሁ?

ከሆናችሁ ብርና ሳንቲም ስትነኩ መዋላችሁ አይቀርም፡፡ ገንዘብ ግን ቆሻሻ ነው፤ እንደ ኮሮናቫይረስ ያሉ ቫይረሶችም በላዩ ላይ ይገኛሉ፡፡

ስለዚህ ምን ማድረግ ትችላላችሁ? ገንዘብ ስትይዙ ጓንት ተጠቀሙ፣ እቃና ገንዘብ ነክታችሁ ስትጨርሱ ደግሞ ቢያንስ ለ20 ደቂቃ ያህል እጃችሁን በዉሃ እና በሳሙና ታጠቡ፡፡ ከቻላችሁ ጥሬ ገንዘብ ላለመንካት የሞባይል ግብይት ተጠቃሚ ሁኑ፡፡


Spot 14

በኮሮናቫይረስ የመያዝ ከፍተኘ ስጋት ያለባቸው እነማን ናቸው?

በቫይረሱ የተያዘ የቤተሰብ አባል ያላቸው ሰዎች እና የሕክምና ባለመሉያዎች ናቸው፡፡

ለምን?

ምክንቱም እነሱ ቫይረሱ ካለባቸው ሰዎች ጋር ከፍተኛ ንክኪ አላቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች የበሽታውን ምልክት አያሳዩም፡፡

በመሆኑም ጭንብል በመልበስ፣ እጃችሁን በውሃና በሳሙና ደጋግማችሁ በመታጠብ እና ከሌሎች ሰዎች ቢያንስ የአንድ ሜትር እርቀት በመጠበቅ የቫይረሱን መተላለፍ በመከላከል እራሳችሁን እና ሌሎችን ጠብቁ፡፡


Spot 15

ሴት ልጅ፡-
እማማ ዛሬ ገበያ ሄጄ አናናስ መሸጥ አለብኝ፡፡

እናት፡-
(በመጨነቅ) አዬ ልጄ እንደዚህ ኮሮና በተስፋፋበት ጊዜ እዛ ሰው ሁሉ መሃል መሆንሽን አልወደውም፡፡

ሴት ልጅ፡-
እኔም ደስ አይለኝም፣ ግን ምን ማድረግ ይቻላል? እህል ውሃችን ግብርና ነው፤ ለምግብም ሆነ ለሌሎች የምንፈልጋቸው ነገሮች የሚስፈልገንን ገንዘብ የምናገኘው ከገበያ ነው፡፡

እናት፡-
እራስሽን ግን እንዴት ትጠብቂያለሽ? እንድትታመሚብኝ አልፈልግም!

ሴት ልጅ፡-
ቀኑን በሙሉ ጭንብል እለለብሳለሁ፡፡ መኪናው ጥቂት ተሳፋሪዎች ብቻ ስለሚጭን ተራርቀን እንቀመጣን፡፡ ብርና ሳንቲም ላለመንካት የሚገዙኝ ሰዎች በሞባይል እንዲከፍሉ እጠይቃቸዋለሁ፡፡

እናት፡-
እጂሽን መታጠብስ?

ሴት ልጅ፡-
ገበያ ባለው የቧንቧ ውሃ ቶሎ ቶሎ እታጠባለሁ፡፡ ሳሙና እና የጀርም ማጥፊያ የሚሸጥ አዲስ ነጋዴ ስላለ ላንቺ እና ላባባ ገዝቼ አመጣለሁ፡፡

እናት፡-
ልጁ ወደ ቤትሽ ተመልሰሽ እንድትመጭልኝ በጣም ተጠንቅቀሽ እራስሽን ጠብቂ፡፡


Spot 16

አንደኛ ሰው፡-
(ያማርራል) ከተማው እኮ እስካሁን እንቅስቃሴ እንደተከለከለ ነው፡፡

ሁለተኛ ሰው፡-
አዎ ሰው ያለጥርጥር እየተቅበጠበጠ ነው፡፡

አንደኛ ሰው፡-
እኔ ወዳገሬ ልሄድ እያሰብኩ ነው፡፡ ከቤተሰቦቼ ጋር ትንሽ ብቆይ ጥሩ ነው፡፡ አያቴ በጣም እያረጀች ነው፡፡

ሁለተኛ ሰው፡-
ቢቀርብህ ይሻላል፡፡ ኮሮናቫይረስ ሳታውቀው ወዳገርህ ይዘህ ልትሄድ ትችላለህ፡፡ ቫይረሱ እቃዎች ላይ መኖር ይችላል – አውቶብሱ እንዴት ቆሻሻ ሊሆን እንደሚችል አስበው እስኪ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ደግሞ የበሽታው ምልክት ሳይታይባቸው ቫይረሱ ሊኖርባቸው ይችላል፡፡ ሳታውቀው ቫይረሱን ለቤተሰብህ ብታስተላልፍ አስፈሪ ነው የሚሆነው፡፡ ለአያትህ አስብ!

የመጀመርያ ሰው፡-
ልክ ሳትሆን አትቀርም፡፡ ቤታችን አርፈን ብንቀመጥ ሁላችንም ደና አንሆናለን፡፡ ስልክ ብደውልላቸው ይበቃል፡፡

ሁለተኛ ሰው፡-
እንደሱ ብታደርግ ይገባቸዋል፣ ይረዱህማል፡፡


Spot 17

አባት፡-
ልጄ አንት ሕጻን የነበርክ ግዜ ኢቦላ የሚባል ገዳይ በሽታ ምዕራብ አፍሪካን አዳርሷት ነበር፡፡ አሁን ደሞ ሌላ ገዳይ በሽታ እየተሰራጨ ነው፣ ያሁን ግን ይብሳል፡፡

ልጅ፡-
በሽታው ምንድን ነው?

አባት፡-
ኮሮናቫይረስ ወይም ኮቪድ-19 ይባላል፡፡በዓለም ዙርያ በፍጥነት እየተሰራጨ ነው፡፡

ልጅ፡-
(በፍርሃት) ሁላችንም ያመናል?

አባት፡-
እንዳንታመም ቤታችን አርፈን መቀመጥ እና ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለንን አካላዊ መቀራረብ መወሰን ያስፈልገናል፡፡ ቫይረሱ ሰዎች ሲያስላቸው እና ሲያስነጥሳቸው ይተላለፋል፡፡ ስለዚህ ሁል ጊዜ ጭንብል መልበስ፣እጃችንን ቶሎ ቶሎ በውሃ እና በሳሙና መታጠብ እና አይናችንን፣ አፍ እና አፍንጫችንን በእጃችን አለመንካት አለብን፡፡

ልጅ፡-
እስከመቼ?

አባት፡-
አይታወቅም፡፡ ነገር ግን የጤና ባለ ስልጣናት እና የዓለም ጤና ድርጅት የሚለቋቸውን መረጃዎች በዜና መከታተል ያስፈልገናል፡፡ ሰወች አብዝተው የደህንነት ጥንቃቄዎችን ካደረጉ ሕይወታችን ቶሎ ወደ ዱሮው ይመለስልናል፡፡


Spot 18

አንደኛ ሰው፡-
በኛ ማህበረሰብ ውስጥ ያሉ ሽማግሌዎች አስተዋዮች ናቸው፡፡

ሁለተኛ ሰው፡-
ልክ ብለሃል፡፡ ልናከብራቸው ይገባል፡፡

አንደኛ ሰው፡-
እነሱን ልናከብርባቸው ከምንችላቸው መንገዶች አንዱ ከወጣቶች በላይ አረጋውያንን ከሚያጠቃው ኮሮናቫይረስ እነሱን ለመጠበቅ ይበልጥ መጠንቀቅ ነው፡፡

ተራኪ፡-
አረጋውያንን እና የስኳር በሽታ፣ የልብ ችግር እና ካንሰር የመሳሰሉ የጤና ችግር ያለባቸውን ሰዎች መጠበቅ አስፈላጊ ነው፡፡

ኮሮናቫይረስ ገዳይ ሊሆን ይችላል፣ ስለዚህ ግንዛቤ ጨምሩ፣ እንዳይሰራጭም የቻላችሁትን ሁሉ አድርጉ፡፡ እናንተ ወይም በቤታችሁ ውስጥ ያለ ማንም ሰው ሳል፣ የመተንፈስ ችግር ወይም ድንገተኛ ትኩሳት ካለበት ምልክቱ ቀላል ቢሆንም ቤት ውስጥ ቆዩ፡፡

ወደ ገበያ አትሂዱ፡፡ ወደ ከተማ አትሂዱ፡፡ ዘመድ አትጠይቁ፡፡ ምልክቶቹ ከጨመሩ የህክምና ክትትል ለማግኘት ወደ ሐኪም ቤት ሂዱ፡፡

ጭንብል በማድረግ፣ ከሌሎች ሰዎች በአንድ ሜትር በመራቅ እና እጃችሁን ቶሎ ቶሎ በመታጠብ እራሳችሁን እና ሌሎችን ጠብቁ፡፡


 

Acknowledgements

የጽሑፉ አዘጋጅ፡- ማክሲን ቤተሪጅ-ሞስ፣ ፍሪላንስ ጋዜጠኛ እና ከዚህ በፊት በፋርማ ራዲዮ ጋና የብሮድካስተር ሪሶርስስ አማካሪ

 

ይህ ጽሑፍ ከካናዳ መንግስት በግሎባል አፌይርስ ካናዳ በኩል በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ተዘጋጀ፡፡