ከየወር አበባ ላይ ያለ የመረጃ ድህነት እስከ ተደራሽነት፦ የሴቶችን ደህንነት መጠበቅ እና ደስተኛ ማድረግ

Notes to broadcasters

ለብሮድካስተር ማስታወሻ፦

የወር አበባ ኡደት የሴቶች ሰውነት በየወሩ ሊከሰት ለሚችል እርግዝና በሚያደርገው ተፈጥሯዊ ቅድመ ዝግጅት የተነሳ የሚፈጠር በሴቶች ብልት በኩል የሚፈስ ደም ነው። ይህ የደም መፍሰስ በአማካይ በወር አበባ ዑደት ውስጥ ከሁለት እስከ ሰባት ቀናት ውስጥ ይከሰታል። የወር አበባ ዑደት በየ21-35 ቀናት በመዋለጃ እድሜ ውስጥ ሊከሰት ይችላል። በበርካታ የዓለማችን ክፍሎች የወር አበባ መከሰትን በሚመለከት በግልጽ ውይይቶች ባለመደረጉ ሳቢያ እንዲሁም ከሃይማኖታዊ እና ልማዳዊ እምነቶች የተነሳ፣ አሳፋሪ፣ እና “ቆሻሻ” ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

ይህ ዓይነቱ ርዕሱን በግልጽ ያለማውራት እና መገለል ልጃገረዶች ወር አበባ የማያ ጊዜያቸው ሲደርስ ዝግጁ እንዳይሆኑ ወይም እንዴት ማስተናገድ እንዳለባቸው እንዳይረዱ ደርጋል። በአለም አቀፍ ደረጃ ቢያንስ 500 ሚሊዮን ሴቶች እና ልጃገረዶች የወር አበባ ንፅህናን መጠበቂያ በቂ ቁሶች እንደሌላቸው ፣ ሳሙና እና ውሃ እንዲሁም የንጽህና መጠበቂያ ለመቀየር ወይም የሚያስወግዱበት ስፍራ እጥረት እንዳለ  የአለም ባንክ ገልጿል። ልጃገረዶች የወር አበባ ዑደታቸውን የመጀመሪያ የወር አበባ ከማየታቸው በፊት በቂ መረጃ ማግኘታቸው በጣም አስፈላጊ ነው። ይህ ማለት ልጃገረዶች በእድሜያቸው ገደብ የተዘጋጁ ወቅታዊ መረጃዎችን እንዲያገኝኙ ይጠይቃል። በሚያሳዝን ሁኔታ ግን ስለእነዚህ ጉዳዮች ማውራት አስቸጋሪ በሆነበት ሁኔታ ውስጥ ስላሉ የንጽህና መጠበቂያ ቁሶች እጥረት እንዲሁም ስለጉዳዩ በግልጽ ከመነጋገር የተቆጠበ ማህበረሰብ ውስጥ ስለሚሆኑ አስፈላጊው መረጃ አይደርሳውም።

ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ ወይም በወር አበባ ወቅት የሚደረግ ንጽህና አጠባበቅ ላይ መረጃ አለማግኘት በወር አበባቸው ወቅት ትክክለኛ ንጽህና አለመደረጉ ለህመም እና ከትምህርት ቤት መስተጓጎልን ያስከስታል። የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት እ.ኤ.አ. በ2014 ባወጣው ሪፖርት በአፍሪካ ከሰሃራ በታች ካሉት 10 ልጃገረዶች አንዷ በወር አበባዋ ወቅት ትምህርት ታቋርጣለች። የዩኔስኮ ጥናት አጥኚዎች እንዳረጋገጡት የተሻለ የንፅህና አጠባበቅ እና የልጃገረዶች የስነ ተዋልዶ ጤና ትምህርት ማስተማሩ ሴቶች ከትምህርት የመቅረት እድላቸውን ይቀንሳል ብለዋል።

በዚህ ፕሮግራም በኬንያ እና በዩጋንዳ በወር አበባ ጤና እና ንፅህና ላይ ምን ምን ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ እንሰማለን። ከፓድ ሄቨን ፍሎረንስ ካማይታን ከአፍሪ ፓድስ ደግሞ ጄፍሪ ቡሲንጌን አጥቦ መልሶ መጠቀም ስለሚቻለው የንጽህና መጠበቂያ እንዲሁም ለሴቶች የወር አበባን በሚመለከት መረጃ እንዴት እያስተላለፉ እንደሆነ እንሰማለን። ኩዊንተር እና ሉሲ  ኬንያዊ ልጃገረዶች ሲሆኑ የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ቁስ ማግኘት ባለመቻላቸው በትምህርት ቤት እንቅስቃሴዎች ላይ ያደረባቸውን ገደብም እናዳምጣለን።

በዚህ ግብዓት እንደተካተተው “የወር አበባ ላይ ያለ የመረጃ ድህነት “ ስለ የወር አበባ ጤና ስጋቶች ተመሳሳይ ፕሮግራም ለማዘጋጀት ከፈለጉ ይህን ስክሪፕት እንደ መመሪያ ሊጠቀሙበት ይችላሉ። ስክሪፕቱን በመደበኛ ፕሮግራምዎ ላይ ለማቅረብ ከወሰኑ፣ ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸውን ሰዎች ለመወከል የድምጽ ተዋናዮችን ወይም የሬዲዮ ፕሮግራም መሪዎችን መጠቀም ይችላሉ። ስክሪፕቱን በዚህ መንገድ ለመጠቀም ከወሰኑ እባክዎ በፕሮግራሙ መጀመሪያ ላይ ለአድማጮችዎ በፕሮግራሙ ላይ የሚያደምጧቸው የድምጽ ተዋናዮች እንጂ ትክክለኛ ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው ሰወች እንዳልሆኑ ግልጽ ያድርጉላቸው።

ስለ የወር አበባ ጉዳዮች ፕሮግራሞችን ማዘጋጀት ከፈለጉ የስነ ተዋልዶ ጤና ሃኪምን ወይም የማህበራዊ ጉዳይ ሰራተኛን ያነጋግሩ። ለምሳሌ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ሊጠይቋቸው ይችላሉ፦

  • ስለ ወር አበባ በግልጽ መነጋገር ለምን ያስፈልጋል?
  • ሊጣሉ ከሚችሉ የንፅህና መጠበቂያ ቁሶች በተጨማሪ ሌሎች ምን አስተማማኝ የንፅህና መጠበቂያ አማራጮች አሉ?
  • በወር አበባ ወቅት በገጠርም ሆነ በከተማ ጥሩ ተብለው የሚፈረጁ የንፅህና አጠባበቅ ልማዶች ምንድን ናቸው?
  • ማህበረሰቡ የወር አበባ ጤናን በሚመለከት (በትምህርት ቤትም፣ በቤትም ውስጥ) ንቃት እንዲኖረው እንዴት ማበረታታት ይቻላል?

መግቢያ እና መውጫን ጨምሮ የሙሉው ፕሮግራሙ ቆይታ፦ ከ20-25 ደቂቃ ነው።

Script

መግቢያ ሙዚቃ

የፕሮግራም መሪ፦
በአፍሪካ ያሉ በርካታ ልጃገረዶች በወር አበባቸው ወቅት የንፅህና መጠበቂያ ቁስ መግዛት ስለማይችሉ ከትምህርት ቤት ለመቅረት ይገደዳሉ። የአለም ባንክ በቅርቡ ባደረገው ጥናት እንዳመላከተው በአማካይ ልጃገረዶች በየአራት ሳምንቱ ለአራት ቀናት ከትምህርት ገበታቸው ይቀራሉ።

በዛሬው ኘሮግራም በዚህ ጉዳይ አስቸጋሪ ሁኔታን እያሳለፉ ያሉ ልጃገረዶች የሚያካፍሉንን እንሰማለን። በተጨማሪም የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ምርቶች አቅርቦት እጥረት ችግርን ለመታደግ እንደ መፍትሄ የሚወሰዱትን በተመጣጣኝ ዋጋ እና በድጋሚ ጥቅም ላይ ስለሚውሉ የንፅህና መጠበቂያ ፓዶች እንማራለን። ይህ ትኩረት ለሴቶች እና ለልጃገረዶች የተሰኘው ፕሮግራማችን ነው። እኔ ስሜ _____ነው።

አጃቢ ድምጽ፦
ደውል ሲደወል። ህጻናት ጨዋታ ድምጽ።

መሻገሪያ እና አጃቢሙዚቃ።

የፕሮግራም መሪ፦
በናይሮቢ በሚገኘው የኪቤራ ሰፈር መሀል በሶዳ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ከቀኑ 9 ሰአት ነው። የአስራ አራት ዓመቷ ኩዊንተር እና ጓደኛዋ ሉሲ በክፍላቸው ውስጥ ተቀምጠው የክፍል ጓደኞቻቸው በአቅራቢያው ወዳለው የመጫወቻ ቦታ ሲሄዱ ይመለከታሉ። ዛሬ ሉሲ አብራቸው መጫወት አትችልም፥ ኩዊንተር ደግሞ ጓደኛዋ ብቻዋን እንዳትሆን አብራት ተቀምጣለች።

ሉሲ፦
እንደሌሎቹ መጫወት ስለማልችል ያሳዝነኛል። መምህሩ መጥቶ ለምን ውጭ ከሌሎቹ ጋር እንደማልጫወት ከጠየቀኝ ሰበብ እሰጣለሁ… እውነቱን መናገር ያሳፍረኛል።

ኩዊንተር፦
አንዳንድ ጊዜ የወር አበባ ላይ ሲኮን ቤት መሆኑ ይሻላል። ብቸኛው ችግር ለወላጆች ማስረዳቱ ነው። በጣም አሳፋሪ ነው፤ አንዳንዴ ደግሞ አባቴ ለመረዳት እንኳን አይፈልግም።

የፕሮግራም መሪ፦
በአፍሪካ ከሚገኙት አብዛኛዎቹ ልጃገረዶች መካከል፤ ቢያንስ ከሁለት እስከ ሰባት ቀናት በወር አበባቸው ወቅት እፍረት ከሚሰማቸው ውስጥ ሉሲ እና ኩዊንተር ሁለቱ ብቻ ናቸው። ከልጃገረዶቹ ጋር በወር አበባቸው ወቅት ስለሚጠቀሙት ንጽህና መጠበቂያ እና ምን እንደሚሰማቸው በበለጠ ለመረዳት አብሪያቸው ተቀመጥኩ። ሉሲ በወር አበባዋ ወቅት ምን እንደምትጠቀም ጠየቅኳት።

ሉሲ፦
እናቴ ከሱፐርማርኬት ፓድ የመግዛት አቅም ስለሌላት አንዳንዴ ሶፍት ወይም ብርድ ልብስ ቁራጭ እጠቀማለሁ።.

የፕሮግራምመሪ፦
ይወድቃክ ብለሽ አትሰጊም?

ሉሲ፦
(ሳቅ)አንዳንድ ይወድቃል ወንዶቹ ልጆች ይህን ሲያዩ ይስቁብናል።

ኩዊንተር፦
(ሳቅ) ለዚህም ነው ከሌሎቹ ጋር ከመጫወት ይልቅ እዚህ የምንቀመጠው።

የፕሮግራምመሪ፦
ከተጠቀማችሁ በኋላ ታጥቡታላችሁ?

ሉሲ፦
አዎ አንዳንዴ ግን ውሃ የሌለበት ጊዜ ስላለ ውሃ እስክናገኝ ድረስ መጠበቁ ግዴታ ነው። ነገር ግን አንዳንድ የቆሸሹ ጨርቆች አሉ እና እርስዎን ሊነኩ ይችላሉ። አንዳንድ የቆሸሹ የጨርቅ ቁርጥራጮች ደግሞ ተጽዕኖ ያሳድራሉ።

የፕሮግራም መሪ፦
አንቺስ ኩዊንተር፤ ምን ትጠቀሚያለሽ?

ኩዊንተር፦
እኔም እንደ ሉሲ የጨርቅ ቁራጭ እጠቀማለሁ ወይም ደግሞ ከፍራሽ ላይ ስፖንጅ ቆርጬ እጠቀማለሁ።

የፕሮግራም መሪ፦
በምን መልኩ ነው የምታስቀምጫቸው?

ኩዊንተር፦
ታናሽ እህቴ እና ወንድሜ እንዲያዩት ስለማልፈልግ ከአልጋው ስር አስቀምጣቸዋለሁ። ይህ ማለት እንደገና ልጠቀምበት ስፈልግ ቆሻሻ ሊሆን ይችላል ይህ ደግሞ በእኔ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል ብዬ ሁሌም እሰጋለው።

የፕሮግራም መሪ፦
በአለም ላይ ያሉ የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ቁሶች የመግዛት አቅም የሌላቸው ወይም ማግኘት የማይችሉ ሴቶች እና ልጃገረዶች በወር አበባቸው ወቅት አሮጌ ልብሶችን፣ ወረቀትን እና ቅጠሎችን በመጠቀም የወር አበባ ንጽህና ለመጠበቅ ይገደዳሉ። ይህ ሁኔታ እንደ ሉሲ እና ኩዊንተር ላሉ ተማሪዎች የከፋ ነው። ምክንያቱም በወር አበባቸው ወቅት ከትምህርት ቤት መቅረታቸው ብቻ ሳይሆን እነዚህን ባካቢያቸው ያሉ ንጽህና የጎደላቸው ቁሳቁሶች መጠቀማቸው በመራቢያ እካል እንደ ኢንፌክሽን ያሉ ችግሮችን ሊያስከትሉ ይችላሉ። ሆኖም ገበያ ላይ የሚገኙ የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያዎች ዋጋ ለወላጆች ውድ ናቸው። የንፅህና መጠበቂያ ቁሶች ዋጋቸው ምን ያህል ተመጣጣኝ እንደሆኑ ለማወቅ በአቅራቢያው ወደሚገኝ የሸቀጥ መደብር ሄጄ ነበር።

አጃቢ ድምጽ፦
የሸቀጥ መደብር ድምጾች (ገንዘብ መቀበያ ማሽን፣ ሳንቲሞች እና ሰዎች ሲገበያዩ የሚገልጽ ድምጽ)

የፕሮግራም መሪ፦
በሸቀጥ መደብሩ መተላለፊያ ላይ ቆሜያለሁ። ቢያንስ 2፣ 3፣ 4. . .7 የተለያዩ የንፅህና መጠበቂያ ብራንዶች ቆጠርኩ። ከአንድ እስከ ስድስት የአሜሪካ ዶላር የሚሸጥ በእሽግ ውስጥ ስምንት ፍሬ ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ ፓዶች ይይዛል። ይህ ዋጋ በኬንያ ቤተሰብ ለሩብ ኪሎ ግራም ስጋ የሚከፍሉት ዋጋ ሲሆን ስጋን ገዝተው ለምግብነት ለማዋል አቅሙ ያላቸው ቤተሰቦች ደግሞ እጅግ በጣም ጥቂት ናቸው። ይህ ማለት አብዛኛዎቹ ቤተሰቦች ለንፅህና መጠበቂያ ቁሶች በጀት ለመመደብ ቅድሚያ አይሰጡም ማለት ነው።

ታዲያ ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ ውለው ሊጣሉ ከሚችሉ የንጽሕና መጠበቂያ ቁሶች ይልቅ ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸው አማራጮች አሉ? ታጥበው ድጋሚ ጥቅም ላይ የሚውሉ ማልኪያ ተብለው የተሰየሙት የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ ቁሶች የሚያቀርበው በኬኒያ የሚገኘው የፓድ ሄቨን ድርጅት መስራች የሆነችውን ፍሎረንስ ካማይታን ስለ ወር አበባ ንጽህና የማስተዋወቅ ስራዋ አነጋግሬያታለሁ። ጥያቄዬን የጀመርኩት ወር አበባ ንጽህና ስራ ላይ ለመሰማራት ምን እንዳነሳሳት በመጠየቅ ነው።

ፍሎረንስ ካማይታ ፦
ይህ ተነሳሽነቴን የጀመርኩት እ.ኤ.አ. በ2012 በገጠር የሚገኝ ትምህርት ቤትን ከጎበኘሁ በኋላ እና በመጫወቻ ሜዳው ላይ ያሉት ወንድ ልጆች ብቻ መሆናቸውን ካየሁ በኋላ ነው። ይህ ለምን እንደሆነ ስጠይቅ፣ አብዛኞቹ ልጃገረዶች የወር አበባቸው ላይ ስለሆኑ እና የንፅህና መጠበቂያ ቁስ ገዝቶ ለመጠቀም አቅሙ ስለሌላቸው ቤታቸው ለመቅረት እንደተገደዱ ተነግሮኛል። ከዚያ በኋላ ነው በተቻለኝ መጠን ልጃገረዶች የወር አበባቸውን በክብር እንዲያልፉት የተቻለኝን ለማድረግ የወሰንኩት።

የፕሮግራም መሪ፦
ጥሩ የወር አበባ ንፅህና ለልጃገረዶች እና ለሴቶች ጠቃሚ የሆነው ለምንድነው?

ፍሎረንስ ካማይታ፦
በኬንያ ያሉ ሴቶች እና ልጃገረዶች የወር አበባ ንፅህና አጠባበቅ ሊረዳቸው የሚችል በቂ አገልግሎት የላቸውም። ይህም በወር አበባቸው ወቅት ንፁህ ውሃ ማግኘት፣ የሚቆለፉ መጸዳጃ ቤቶችን ወይም መቀየር የሚችሉባቸውን ጉድጓዶች መጸዳጃ ቤቶችን ማፅዳት፣ ያገለገሉ ፓዶቻቸውን የማስወገድ ትክክለኛ መንገድ እና ፍሰታቸውን ለመቆጣጠር ተመጣጣኝ እና ጥራት ያለው የንጽህና መጠበቂያ ቁስ አለማግኘትን ያካትታል። ጥሩ የወር አበባ ንፅህና አጠባበቅ በባክቴሪያ የሚመጡ በሽታዎችን እና የቆዳ መቆጣትን እንዲሁም የቶክሲክ ሾክ ሲንድረምን ይከላከላል። ልጃገረዶች እና ሴቶች ስለ የወር አበባ ንፅህና እና ጤና መረጃ የላቸውም።

የፕሮግራም መሪ፦
ስለ የወር አበባ ጤንነት መረጃ ማግኘታቸው በምን መልኩ ይጠቅማቸዋል?

ፍሎረንስ ካማይታ፦
የወር አበባ ጤናን በሚመለከት መረጃ ሴቶች እና ልጃገረዶች በወር አበባ ፍሰታቸው ወቅት ፓድ እና ታምፖን ለስንት ሰአት ተጠቅመው ማስወገድ እንዳለባቸው፣ ትክክለኛ የምርት አይነቶችን ለመምረጥ እንዲሁም ትክክለኛ አወጋገድ ላይ መመሪያ ይሆናቸዋል። ስለ የወር አበባ ትክክለኛ መረጃ ሲኖራቸው ልጃገረዶች እና ሴቶች ለሰውነታቸው ጤናማ እና ትክክለኛ ምርጫዎችን ያደርጋሉ። ልጃገረዶች በትምህርት ቤት ውስጥ የወር አበባ ንፅህናን መቆጣጠር አለመቻላቸው ከትምህርት ገበታቸው እንዲቀሩ ያስገድዳቸዋል፣ ይህ ደግሞ በህይወታቸው እና በአገሪቷ ላይ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጫናን ያስከትላል።

የፕሮግራም መሪ፦
ታድያ ይህን ሁኔታ ለመቀየር ፓድ ሄቨን ምን እየሰራ ይገኛል?

ፍሎረንስ ካማይታ፦
በትምህርት ቤት የማሳያ ፕሮግራሞች ወቅት፣ ሴቶች የወር አበባ ፍሰታቸውን ለመያዝ የሚጠቀሙባቸውን ቁሶች አይቻለሁ። አብዛኛዎቹ የሚጠቀሙት የነበረው የተጣጠፈ ብጣሽ ጨርቅ ነበር። አንዳንድ ልጃገረዶች ቀደም ሲልም ጨርቅ እየተጠቀሙ እና ከተጠቀሙ በኋላ አጥበው በድጋሚ ጥቅም ላይ ያውሉት ስለነበር፣ እኔም እንደገና ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል፣ ሊያፈስ የማይችል አስተማማኝ እና ተመጣጣኝ ዋጋ ያለው ፓድ ለማዘጋጀት ወሰንኩ። ፓዶቹ 650 የኬንያ ሽልንግ የሚሸጡ ሲሆን ይህም ወደ ስድስት የአሜሪካ ዶላር የሚጠጋ እና እስከ አንድ አመት ድረስ እየታጠበ ድጋሚ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል።

ሌላው የተገነዘብኩት ደግሞ ብዙ ልጃገረዶች ለአቅመ ሄዋን የሚደርሱት ስለ ወር አበባ በጣም ውስን ወይም ምንም መረጃ ሳይኖራቸው እንደሆነ ነው። ስለዚህ “ነውር” ተብሎ በመፈረጁ ብዙዎች በግልጽ የማያወሩት ርዕስ ላይ በይፋ ለመናገር አላማዬ አድርጌ ተነሳሁ። ለሴት ልጆች መረጃ እንዲሰጥ የወር አበባ ንጽህና ላይ አንድ መጽሐፍ ያሳተምኩ ሲሆን በመጽሃፉ የስለ አቅመ ሄዋን መድረስ፣ የወር አበባ፣ የንፅህና መጠበቂያ ቁሶች አጠቃቀም እና አወጋገድ፣ አመጋገብ፣ የህመም ማስታገሻ እና የወር አበባን በሚመለከት ያሉ አፈ ታሪኮች ተሸፍነዋል።

የፕሮግራም መሪ፦
እስካሁን ምን ያህል ፓዶችን አሰራጭተሻል?

ፍሎረንስ ካማይታ፦
ስምንት ሴት የቀድሞ እስረኞች ቀጥሬ በጋራ ከ50,000 በላይ ታጣቢ የንፅህና መጠበቂያ ፓዶችን አምርተናል።

የፕሮግራም መሪ፦
በዛሬው ፕሮግራማችን ስለ የወር አበባ ጤንነት እና ንፅህና እየተነጋገርን እንገኛለን። በፕሮግራሙ ቀደም ብሎ በናይሮቢ ከሚገኙ ሁለት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሴት ተማሪዎች እንደበት በወር አበባቸው ወቅት ስለሚጠቀሙባቸው ቁሳቁሶች ሰምተናል። የፓድ ሄቨኗ ፍሎረንስ እየሠራችው ስላለው እንደገና ጥቅም ላይ ሊውል የሚችሉ ፓዶች እና ስለ ወር አበባ ጤንነት እና ንፅህና ለሴቶች እና ልጃገረዶች መረጃ እንዴት እያደረሰች እንደሆነም አድምጠናል። በመቀጠል ወደ ዩጋንዳ ተሻግረን ስለ የወር አበባ ጤና እና ንፅህና እየተሰራ ያለውን እንሰማለን። መጀመሪያ ግን ሙዚቃ።

ሙዚቃ፦

የፕሮግራም መሪ፦
ይህ ትኩረት ሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ የተሰኘው ፕሮግራማችን ነው። በዛሬው ፕሮግራማችን ስለ የወር አበባ ጤንነት እና ንፅህና እየተነጋገርን እንገኛለን። በዩጋንዳ እ.ኤ.አ. ከ2016 ዓ.ም. አንስቶ ባለው መረጃ መሰረት 21 በመቶ የሚሆኑት ልጃገረዶች በጁኒየር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፤ 7 በመቶው በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እየተማሩ የሚገኙ ሲሆኑ፣ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 91 በመቶው ናቸው። ጥናት አድራጊዎች የንጽህና መጠበቂያ ምርቶች ዋጋ እና የወር አበባ አያያዝ ላይ ያሉ ችግሮች ልጃገረዶች ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዳይገቡ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ ያምናሉ።

አፍሪፓድስ በዩጋንዳ የሚገኝ አንድ ድርጅት ሲሆን ለሴቶች እና ልጃገረዶች የሚታጠቡ እና እንደገና ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ የጨርቅ ፓዶችን በማቅረብ እንዲሁም በአካባቢው የሰለጠኑ የማህበረሰብ ነርሶች ጋር በመተባበር ስለ የወር አበባ ጤንነት እና ንፅህና ከልጃገረዶች ጋር ይነጋገራሉ። ድርጅቱ እየሰራ ስላለው ስራ የአፍሪፓድስ ሥራ አስኪያጅ ጄፍሪ ቡሲንጌን አነጋግሬዋለሁ።

የፕሮግራም መሪ፦
የወር አበባ ጤንነት እና ንፅህና ስራዎች ውስጥ የተሳተፈ ወንድ ማነጋገር ጥሩ ነው። በእነዚህ ጉዳዮች ላይ እንድትሳተፍ የሚያነሳሳህ ምንድን ነው?

ጄፍሪ ቡሲንጌ፦
በስራዬ ውስጥ ወንዶች በየወሩ በሴት ላይ የሚደርሰውን ሂደት ባለመረዳታቸው ሴቶች በወር አበባቸው ወቅት ሲሰቃዩ ተመልክቻለሁ። ሁሌም ወንዶች ሴቶች እና ልጃገረዶች ለምን ድጋፋቸውን እንደሚያስፈልጋቸው እንዲረዱ እና ስለልጃገረዶች የወር አበባ ሂደት እንዲገነዘቡ የማስረዳቱን ሃላፊነት ራሴ ወስጃለሁ።

የፕሮግራም መሪ፦
በስራህ ላይ ሴቶች እና ልጃገረዶች በወር አበባቸው ወቅት ከሚያጋጥሟቸው ነገሮች ምን እንዳስተዋልክ ምሳሌ ስጥ።

ጄፍሪ ቡሲንጌ፦
በትምህርት ቤቶች ውስጥ ካስተዋልኩት፤ ልጃገረዶቹ ምን እየደረሰባቸው እንዳለ በደንብ ስላልገባቸው ወንዶች ልጆች አንዳንድ ጊዜ ሴት ልጆችን ሲያዋርዱ አስተውያለሁ። በቤቶች ውስጥም አስተያ፡አሁ፤ አንዳንድ ወንድ የቤተሰብ አባላቶች የወር አበባ ደም ቆሻሻ ነው ብለው ስለሚያምኑ በወር አበባዋ ወቅት ከሴት ልጅ ይርቃሉ። ሴት ልጅ በወር አበባ ምክንያት ህመም ላይ ስለሆነች የሚጠበቁባትን የቤት ስራዎች መወጣት የተሳናት እንደሆነ አካላዊ እና የቃል ጥቃት፤ ሁለቱም ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ውስጥ የሚመደቡ፤ ሊደርስባት ይችላል።

የፕሮግራም መሪ፦
በወር አበባ ጤና መስክ ላይ እንደተሰማራ አንድ ወንድ ይህንን እንዴት ለማስተካከል ትጥራለህ?

ጄፍሪ ቡሲንጌ፦
በመጀመሪያ ከልጃገረዶቹ ጋር እንነጋገራለን፤ ምን እየደረሰባቸው እንዳለ እና በወር አበባቸው ወቅት እራሳቸውን እንዴት እንደሚይዙ እንዲረዱ እንረዳቸዋለን። ከዚያም የወር አበባ የተለመደ እና ተፈጥሯዊ እና ቆሻሻ እንዳልሆነ እንዲገነዘቡ ለወንዶች እናስረዳለን፤ ሴቶች እና ልጃገረዶች የወር አበባቸው ላይ ሲሆኑ በተለየ ሁኒታ ሊገለሉ እንደማይገባም እንገልጽላቸዋለን።

የፕሮግራም መሪ፦
ለውጦችን አስተውላሃል?

ጄፍሪ ቡሲንጌ፦
ደህና ፣ ብዙ ጊዜ ወስዷል፣ ግን አሁን በተለይ በትምህርት ቤቶች ትንሽ ለውጥ እያየን ነው። ይህ ተፈጥሯዊ ሂደት መሆኑን ለወንዶች በመንገሩ ረገድ መምህራን ንቁ እንዲሆኑ እያበረታታናቸው ነው። ትምህርት ቤቶችም ልጃገረዶች በወር አበባቸው ወቅት ከመደበኛ ትምህርት እና ከትምህርት ቤት ጋር ከተያያዙ እንቅስቃሴዎች እንዳይስተጓጎሉ ድጋፍ እንዲያደርጉ አበረታተናቸዋል። የወር አበባን በሚመለከት ገለጻ ላይ የተሳተፉ ወንዶች ልጆች አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ልጃገረዶችን ለመርዳት ፍቃደኛ እንደሆኑም ያሳወቁበት ሁኔታ አለ። ይህ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ታይቶ የማይታወቅ ነበር። ቤቶች ውስጥ አሁን አንዳንድ አባቶች ሴት ልጆቻቸውን የንፅህና መጠበቂያ ፓድ ለመግዛት ገንዘብ ሲሰጡ እያየን ነው፤ ነገር ግን ይህ ብዙም የተለመደ አይደለም።

የፕሮግራም መሪ፦
እንደገና ጥቅም ላይ የሚውሉ እና የሚታጠቡ አፍሪፓዶች ለሴቶች ረድቷቸዋል?

ጄፍሪ ቡሲንጌ፦
አዎ። በወር አበባቸው ወቅት ልጃገረዶች መደበኛ ህይወታቸውን እንዲመሩ ከመርዳት አንፃር ጠቀሜታ አለው። ይህ እውነት የሆነው በተለይ ከባድ ድህነት ባለባቸው ቦታዎች እና ቤተሰቡ የንፅህና ፓዶችን ማቅረብ በማይችልበት ሁኔታ ነው።

የፕሮግራም መሪ፦
ልጃገረዶቹ ከአንድ ጊዜ በላይ ጥቅም ላይ የሚውሉ የንፅህና መጠበቂያዎች ቢኖራቸውም እንኳን፣ አሁንም የውሃ፣ የንፅህና መጠበቂያ ስፍራ፣ በአንዳንድ ሁኔታዎች የወር አበባ ቆሻሻን የማስወገጃ ስፍራም ያስፈልጋቸዋል። ይህ እንዴት ነው እየተስተናገደ ያለው?

ጄፍሪ ቡሲንጌ፦
የወር አበባ ጤና እና ንፅህና ጉዳዮች በተሳካ ሁኔታ ሊፈቱ የሚችሉት በባለብዙ ዘርፍ መፍትሄ ብቻ ነው። እንደገና ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ ፓዶችን እኛ እናቀርባለን ነገርግን የንጹህ ውሃ አቅርቦት፣ የአካባቢ ጽዳትና የግል ንፅህና ዘርፍ ሳኒቴሽን ለማቅረብ የመንግስት እና አጋሮች ድጋፍ ያስፈልጉናል። ለአሁን፣ እንደገና ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉትን የንጽህና መጠበቂያዎች ማሰራጨት የምንችለው ልጃገረዶች እና ሴቶች ውሃ በሚያገኙባቸው አካባቢዎች ብቻ ነው። ሁላችንም የበኩላችንን ካደረግን የወር አበባ ላይ ያለው የመረጃ ድህነት እና እፍረት ዙሪያ ያሉትን ሁሉንም ጉዳዮች መፍታት እንችላለን።

የፕሮግራም መሪ፦
በወር አበባቸው ወቅት ልጃገረዶችን እና ሴቶችን ለመርዳት ብዙ መሰራት የጠበቅበታል ነገር ግን በተለያዩ የአህጉሪቱ ክፍሎች መጠነኛ መሻሻል አለ። ከሰሃራ በታች ያሉ ብዙ ሀገራት ለሴቶች የንፅህና መጠበቂያ ፓድ ለማቅረብ መነሳሳት ጀምረዋል። ኬንያ ለገጠር ልጃገረዶች የንፅህና መጠበቂያ ምርቶችን ወጪ በመቀነስ እና ከምርቶቹ ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ በማንሳት የመጀመሪያዋ ነች። ከፓድ ሄቨን ፍሎረንስ በኬንያ የተደረጉ አንዳንድ እርምጃዎችን ትዘረዝርልናለች።

ፍሎረንስ ካማይታ፦
ኬንያ እ.ኤ.አ. በ2019 የወር አበባ ንፅህና ፖሊሲን ጀምራለች። ልጃገረዶች እና ሴቶች በወር አበባ ወቅት ንጽህና ለመጠበቅ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማሟላት ምን መደረግ እንዳለበት ይዘረዝራል። መንግስት በርካታ ሴት ተማሪዎች ለጥቂት አመታት የሚገለገሉበት ፓዶችን በትምህርት ቤቶች ውስጥም በነጻ አድለዋል። ነገር ግን፣ እ.ኤ.አ በ2021-2022 በጀት፣ ለወር አበባ ምንም በጀት አልተመደበም። ልጃገረዶች እና ሴቶች የወር አበባቸውን በንጽህና፣ በነጻነት፣ በክብር እና ያለ መገለል እንዲይዙ ለማድረግ በትምህርት ቤት እና በስራ ቦታ ተጨማሪ ስራዎችን መስራት እንደሚቻል አምናለሁ።

የፕሮግራም መሪ፦
የ14 አመቶቹ የኪቤራ ሴት ልጆች ሉሲ እና ኩዊንተር፣ የሚፈልጉት ከትምሀርት ቤት አለመቅረት እና እንደሌሎች የክፍል ጓደኞቻቸው በነጻነት መጫወት መቻል ነው። ነገር ግን ይህንን ማድረግ የሚችሉት የንፅህና መጠበቂያ ፓዶች፣ ውሃ እና የወር አበባ ጤና ሲሟላላቸው ነው።

ልክ እንደሌሎች ልጃገረዶች ፓድን መጠቀም ትፈልጊያለሽ ኩዊንተር?

ኩዊንተር፦
አዎ፣ ከዛ ከትምህርት ቤት ሳንቀር፣ ፓድ ይወድቃል ብለን ሳንጨነቅ በነጻ ከጓደኞቻችን ጋር መጫወት እንችላለን።

የፕሮግራም መሪ፦
እኛም በአፍሪካ ውስጥ ያለች እያንዳንዷ ልጃገረዶች በወር አበባዋ ወቅት ይህን ማድረግ እንድትችል ተስፋችን ነው። የኪቤራ ሰፈር ነዋሪ የሆነችው ኩዊንተር አንድ ቀን ፓድ ለመጠቀም ተስፋ እንደምታደርግ በተናገረችው በእነዚህ ቃላት ፕሮግራማችንን እንቋጫለን።

ዛሬ ስለ የወር አበባ ጤንነት እና ንፅህና ስንነጋገር ቆይተናል። ከፓድ ሄቨን ፍሎረንስ ካማይታ እና ከአፍሪፓድስ ጄፍሪ ቡሲንጌ እያቀረቧቸው ባሉት በሚታጠቡ እና እንደገና ጥቅም ላይ በሚውሉ ፓዶች ላይ እንዲሁም የወር አበባን በተመለከተ መረጃ እንዴት እንደሚያጋሩ ሰምተናል። የወር አበባ ጤና፣ የንፅህና መጠበቂያ ምርቶችና መገልገያዎችን የማያገኙ ሁለት ልጃገረዶች ኩዊንተር እና ሉሲንም አዳምጠናል። በቀጣዩ ሳምንት በተመሳሳይ ሰዓት ትኩረት ሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ ፕሮግራማችን ላይ ታሪኮችን እና መረጃዎችን ያዳምጡ። እኔ … ነኝ።

Acknowledgements

ምስጋና

አዘጋጅ፦ ዊኒ ኦኒምቦ፤ ትራንስ ወርልድ ሬዲዮ፤ ናይሮቢ፤ ኬኒያ

ገምጋሚ፦ ፍሎረንስ ካማይታ፤ መስራች፤ ፓድ ሄቨን ኢኒሼቲቭ፤ ዳያና ኔልሰን እና ኤሌና ስቴፋነስ፣ የልጃገረዶች ቀናት

This resource was translated thanks to the donors of Farm Radio International.

ሉሲ እና ኩዊንተር እ.ኤ.አ ህዳር 18 ቀን 2021 ዓ.ም. የተደረገ ቃለ መተይቅ

ይህ ግብዓት የተዘጋጀው ከኤም.ኤል.ጄየር በተገኘ ድጋፍ ነው።

Information sources

ቃለመጠይቆች፡– 

አቶ ጄፍሪ ቡሲንጌ፤ የክልል ንግድ ልማት እና አጋርነት ሥራ አስኪያጅ፤ አፍሪ ፓድስ፤ እ.ኤ.አ ታህሳስ 15 ቀን 2021 ዓ.ም.

የተደረገ ቃለ መጠይቅ

 

ፍሎረንስ ካማይታ፤ መስራች፤ ፓድ ሄቨን ኢኒሼቲቭ፤ እ.ኤ.አ ታህሳስ 8 ቀን 2021 ዓ.ም. የተደረገ ቃለ መጠይቅ

 

የመረጃ ምንጮች

AFRIpads website: https://www.afripads.com/

Pad Heaven Initiative website: https://padheaven.org/

Tofaris, E., 2020. Keeping African girls in school with better sanitary care. The Impact Initiative. https://opendocs.ids.ac.uk/opendocs/bitstream/handle/20.500.12413/13575/KeepingAfricanGirlsInSchool.pdf?sequence=1&isAllowed=y

UNESCO, 2014. Puberty education & menstrual hygiene management. Good policy and practice in health education, Booklet 9. https://unesdoc.unesco.org/ark:/48223/pf0000226792

Verma, R., 2019. Menstrual hygiene in Africa: No pad or no way to dispose it. Down to earth.  https://www.downtoearth.org.in/news/waste/menstrual-hygiene-in-africa-no-pad-or-no-way-to-dispose-it-63788

World Bank, 2018. Menstrual Hygiene Management Enables Women and Girls to Reach Their Full Potential. https://www.worldbank.org/en/news/feature/2018/05/25/menstrual-hygiene-management