Script
Save and edit this resource as a Word document.
ሴቶችንም ወንዶችንም አርሶአደሮች አሁንስ ቢሆን በሚገባ እያገለገልኩ አይደለሁም እንዴ?
ለአሥርት ዓመታት ለአርሶ አደሮች የሚዘጋጁ የራዲዮ ፕሮግራሞች የወንድ አርሶ አደሮችን ፍላጎቶች ብቻ ሲያሟሉ ነበር፡፡ ወንድ የራዲየ ፕሮግራም አስተናጋጆች ወንዶች ስለዘሯቸው ሰብሎች እና ስለሚያሳድጓቸው እንስሳት ወንድ ባለሙያዎችን እና ወንድ አርሶ አደሮችን ቃለ መጠይቅ ሲያደርጉ ኖረዋል፡፡
ዛሬ አነስተኛ ይዞታ ባላቸው እርሻዎች ላይ ሴቶች ከወንዶች እኩል የግብርና ሥራ እንደሚሠሩ እናውቃለን፡፡ ከዚያ ጎን ለጎን ቤተሰባቸውን ይመግባሉ፣ ልጆችን እና ሽማግሌዎችን ይንከባከባሉ!
በመሆኑም ሴቶች ለቤተሰብ ግብርና መኖር እና መጎልበት ወሳኝ ናቸው፡፡ ስለዚህ አነስተኛ የመሬት ይዞታ ያላቸውን አርሶ አደሮች ለማገልገል የሚዘጋጁ የራዲዮ ፕሮግራሞች የሴት እና ወንድ አርሶ አደሮችን ችግሮች እና ፍላጎቶች እንዲዳስሱ ግድ ይላል፡፡
አስቡት እሰኪ፡፡ እውነት ሴት አርሶ አደሮቻችሁን በሚገባ እያገለገላችሁ ነው? ከታች ያሉትን ነጥቦች ተመልከቱና ምን ያህሉን አሁን እያደረጋችሁ እንደሆነ እዩ፡፡ ከዚያ የቻላችሁትን ያህል አካትታችሁ ለመሥራት ሞክሩ!
ይህ መመርያ አድማጮቼን በሚገባ ለማገልገል እንዴት ይረዳኛል?
– ሴቶች አርሶ አደሮች የተሻለ ግብርና ሥራ ለመሥራት የሚያስፈልጋቸውን መረጃ ያገኛሉ፡፡
– ሴቶች አርሶ አደሮች ለነሱ አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሃሳባቸውን ማሰማት ይችላሉ፡፡
– ሴቶች አርሶ አደሮች የናንተን ፕሮግራም የበለጠ ይወዱታል፡፡
– ወንድ አድማጮች ለሴት አርሶ አደሮች ጠቃሚ ስለሆኑ ነገሮች የተሻለ ዕውቀት አግኝተው ታሳቢ ያደርጓቸዋል፡፡
ይህ መመርያ የተሻለ ፕሮግራም አዘጋጅቶ ለማቅረብ እንዴት ይረዳኛል?
– ሴት አርሶ አደር አድማጮችን ለመሳብ እና ለማገልገል እና የአድማጮቼን ቁጥር ለማሳደግ የሚረዱ ልሠራቸው የምችላቸው ሃሳቦችን ይሰጠኛል፡፡
– በራዲዮ ጣቢያዬ የጾታ እኩልነትን ለማበረታታት የምጠቀምባቸው ሃሳቦች ይሰጠኛል፡፡
እንዴት ልጀምር?
1) ለሴቶች አርሶ አደሮች የሚገባቸውን ክብር ስጥ፡፡
2) ለሴቶች አርሶ አደሮች አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮችን በማወቅ ሽፋን ስጥ፡፡
3) ሴቶች አርሶ አደሮች ማዳመጥ በሚችሉበት ሰዓት አሰራጭ፡፡
4) ሴቶች አርሶ አደሮች በአየር ላይ እንዲናገሩ አበረታታ፡፡
5) ጣቢያህ ለጾታዊ ጉዳዮች ክፍት እንዲሆን አድርግ፡፡
ዝርዝር
1) ለሴቶች አርሶ አደሮች የሚገባቸውን ክብር ስጥ፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው በአነስተኛ እርሻዎች ላይ ሴቶች አብዛኛውን ሥራ ይሠራሉ፡፡ ይህንንም የሚያደርጉት ሕጻናትን እና ሽማግሌዎችን ከመንከባከብ ሥራቸው ጎን ለጎን ነው፡፡ የቤተሰብ ግብርና እንዲሳካ የሴቶች ሥራ ወሳኝ ነው፡፡ በምታደርጉት ሁሉ – የራዲዮ ፕሮግራሙን ስታዘጋጁ፣ ቃለ መጠይቅ ስታደርጉም ሆነ ስታቀርቡ – ጠንክረው ለሚሠሩ፣ ለቤተሰባቸው ደህንነት እና ጤንነት አስፈላጊ ውሳኔዎችን ለሚወስኑ እና አሉታዊ እና የተሳሳቱ በሆኑ አመለካቶች ተገድበው ላሉ ሴቶች የሚገባቸውን ክብር ማስተላለፋችሁን እርግጠኛ ሁኑ፡፡ በመጨረሻም ሴቶች እና ወንዶች በማሕበረሰቦቻቸው እና በቤታቸው ውስጥ ለሚያደርጓቸው ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሚናዎች እውቅና ስጡ፡፡
ለምሳሌ:-
– ሴቶችን እንደ አርሶ አደር እንጅ የአርሶ አደር ሚስት ብላችሁ አትግለጹ
– በስማቸው ጠርታችሁ አነጋግሯቸው – ሰዎች ናቸው
– አስፈላጊ በሆኑ የግብርና ጉዳዮች ላይ አስተያየታቸውን ጠይቁ፡፡ የሚያፈልቋቸው ሃሳቦች ያስገርሟችኋል፡፡
– የጾታዊ ሚናዎችን መቀላቀል የሚያሳዩ የስኬት ታሪኮን አቅርቡ – ለምሳሌ ለገበያ የሚቀርቡ ሰብሎች ላይ የሚሳተፉ ሴቶች እና በቤተሰብ ጤንነት ውሳኔ ላይ የሚሳተፉ ወንዶች፡፡
2) ለሴቶች አርሶ አደሮች አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮችን በማወቅ ሽፋን ስጥ፡፡ በተለምዶ ግብርና ወንዶች ብቻ የሚችሉት ከባድ ሥራ አድርገን ነው የምናስበው፡፡ ሴቶች ደግሞ የጓሮ አትክልት ብቻ እንደሚንከባከቡ አድርገን እናስባለን፡፡ ነገር ግን ሴቶች የአዝመራቸውን ጥራት እና መጠን ጨምሮ የቤተሰባቸውን ጤንነት የሚነኩ የግብርና ጉዳዮች በሙሉ ይመለከቷቸዋል፣ ተሳትፎም ያደርጋሉ፡፡ ለምሳሌ:-
– አፈርን ማሻሻል እንዴት እንደሚቻል
– ላሚቷ መቼ መሸጥ እንዳለባት
– የሰብል ምግብን እንዴት ማሻሻል እንደሚቻ
– የሚዘሩትን እርሻ ለማሳደግ እንዴት በጥንቃቄ ገንዘብ መበደር እንደሚገባቸው
– ለሚያስፈለጉ የቤተሰብ ጉዳዮች መጠቀም እስከሚፈልጉ ድረስ የቆጠቡትን ገንዘብ እንዴት መጠበቅ እንደሚቻል
ወደ አንድ መንደር ሂዱና ከሴቶች ጋር ስብሰባ አድርጉ፡፡ በግብርና ሥራቸው ውስጥ ስለሚያጋጥሟቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ጠይቋቸው፡፡ በጥንቃቄ አዳምጡ እና ከሰማችሁት ውስጥ የእነሱ አንገብጋቢ ጉዳዮች ሆነው ያገኛችኋቸው ነገሮች ምን እንደሆኑ ንገሯቸው፡፡ ወደ ጣቢያችሁ ስትመለሱ እነዚህን ጉዳዮች እንዴት በአየር ላይ መሸፈን እንደሚቻል አስቡ፡፡
3) ሴቶች አርሶ አደሮች ማዳመጥ በሚችሉበት ሰዓት አሰራጭ፡፡ ለሴት አርሶ አደሮች ትልቅ ጥቅም ያላቸው ጥሩ ጥሩ ፕሮግራሞችን ልታዘጋጁ ትችላላችሁ፡፡ ሴቶች ራዲዮዋቸው አጠገብ በማይሆኑበት ሰዓት የምታሰራጩት ከሆነ ግን ድካማችሁ ከንቱ ነው! መንደሮችን ስትጎበኙ እና ሴቶችን ስታነጋግሩ የግብርና ራዲዮ ፕሮግራም ለማዳመጥ የሚመቻቸውን ሰዓት ጠይቃችሁ ተረዱ፡፡ ወንዶችንም ይህን ጥያቄ ጠይቁ፡፡ ወንዶችም ሴቶችም በአንድ አይነት ሰኣት የሚገኙ ከሆነ ለሁለቱም ጾታዎች የሚሆን ፕሮግራም ታሰራጫላችሁ፡፡ ነገር ግን ለወንዶች በሚመቻቸው ሰዓት ሴቶች የማይመቻቸው ከሆነ ፕሮግራማችሁን ሁሉም አርሶ አደሮች እንዲያዳምጡት በሳምንት ሁለት ጊዜ ማሰራጨት ያስፈልጋኋል፡፡ ፕሮግራማችሁ በቀጥታ የሚሰራጭ የስልክ ፕሮግራም ካለው ይሄ ትንሽ ሊያስቸግራሁ ይችላል፡፡ እንደዚህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥማችሁ የድጋሚ ስርጭቱ ጊዜ የቀጥታ የስልክ ስርጭት ሰዓት ትመድባላችሁ፡፡ እንደ አማራጭ አንድ ለወንድ አርሶ አደሮች እና አንድ ለሴት አርሶ አደሮች የሚሆኑ ሁለት የተለያዩ ፕሮግራሞችን በየሳምንቱ ልታዘጋጁ ትችላላችሁ፡፡
4) ሴቶች አርሶ አደሮች በአየር ላይ እንዲናገሩ አበረታታ፡፡ በብዙ ባህሎች ሴቶች ዝም ብለው ወንዶች ስለራሳቸው፣ ስለሚስቶቻቸው እና ስለቤተሳበቻው እንዲናገሩ ያደርጋሉ፡፡ ጊዜው ግን እየተቀየረ ነው፡፡ ሴቶች ለራሳቸው የመናገር መብት አላቸው፡፡ በአስፈላጊ ጉዳዮች ላይ በሚደረጉ ውይይቶች የሴቶች ድምጾች ከወንዶች ድምጾች እኩል ቢሰሙ የናንተም ማህበረሰቦች ጤነኛ፣ ደህንነታቸው የተጠበቀና የበለጠ ምርታማ ይሆናሉ፡፡ ሴቶች ለማውራት የሚመቻቸው ቦታ ቤት ውስጥ ይሁን ወይም ሜዳ ላይ ወይም ከጓደኞቻቸው ጋር ተሰብስበው እንደሆነ እወቁና በሚመቻው ቦታ አግኟቸው፡፡ በዚህ መመርያ ውስጥ ሴቶች በአየር ላይ እንዲያወሩ ለማበረታታት የሚጠቅሟችህ ሃሳቦች ታገኛላችሁ፡፡ ከነዚህ ውስጥ የሚከተሉት ይገኛሉ:-
– በአየር ላይ መናር የማይፈሩ ሴቶችን ፈልጎ ማግኘት
– ሴቶችን በቡድን ቃለ መጠይቅ ማድረግ
– ለየት ባሉ ሁኔታዎች ጊዜ አንድ ሴት ማንነቷ ሳይታወቅ እንድትናገር ማድረግ
5) ጣቢያህ ለጾታዊ ጉዳዮች ክፍት እንዲሆን አድርግ፡፡ እድማጮች አንድ የራዲዮ ጣቢያ ለጾታዊ ጉዳዮች ክፍት መሆን አለመሆኑን በተለያየ መንገድ ያውቃሉ፡፡ የሚከተለውን ዝርዝር ተመልከቱ፡-
– ሴቶች ለጉዞ አመቺ የሆነላቸውን ጊዜ መርጣችሁ ወደ ራዲዮ ጣቢያችሁ እንዲመጡ ትጋብዛላችሁ?
– ለሴቶች የሚመቹ መጸዳጃ ቤቶች አሏችሁ?
– በጣቢያው ያሉ ሰዎች በሙሉ ለሴቶች እና ለወንዶች እኩል ክብር አላቸው?
– እድማጨቻችሁ ሴቶች አሰራጮች በአየር ላይ ወንዶች የሚሠሯቸውን ሥራዎች ሲሠሩ ይሰሟቸዋል? (ሴቶች ፕሮግራም አስተናጋጆችን በተመለከት ራዲዮ ጣቢያዎች ጥሩ ዝና የላቸውም፡፡)
– ጣቢያችሁ በሥራ ላይ የዋለ እና በሁሉም ደረጃ ድጋፍ የሚደረግለት የጾታ ፖሊሲ አለው?
ሴቶችን በሚገባ ለማገልገል የሚረዱ ሌሎች ሃሳቦች
– ለሴት ደዋዮች የተለየ መስመር አዘጋጁ፡፡ ሴቶች በሞባይል ስልክ የመደወል አድላቸው ከወንዶች ያነሰ ነው፡፡ 90% የሚሆኑ ሞባይሎችን ወንዶች የሚይዟቸው ከሆነ በስልክ ጥሪ ፕሮግራሞች ወቅት 90% ጥሪ የሚመጣው ከወንዶች ሊሆን ይችላል፡፡ ለሴቶች የተለየ መስመር ካዘጋጃችሁ ግን የስልክ መስመሩን በማቀያየር ግማሹን የአየር ሰዓት ከሴቶች የሚመጡ ጥሪዎች እንዲያገኙት ማድረግ ትችላላችሁ፡፡ የተወሰነ ወጭ የሚያስወጣ ቢሆንም እና በሴቶች መስመር የሚደውሉት ሴቶች ብቻ መሆናቸውን ለማጣራት ቢያስፈልግም ሴቶች አስተያየቶቻቸውና ሃሳቦቻቸው ጠቃሚ መሆናቸው እንዲሰማቸው ለማድረግ በጣም ከሚጠቅሙት መንገዶች አንዱ ይሄ ነው፡፡
– ወጣ በሉና ሴት አርሶ አደሮችን አግኙ፡፡ ወደ ግብርና ማሕበረሰቦች ለመሄድ ትራንሰፖርት አመቻቹ፡፡ ጉዟችሁን በፕሮግራማችሁ በማስተዋወቅ ብዙ አርሶ አደሮችን ለማግኘት እንድትችሉ አድርጉ፡፡ ወንድ አሰራጭ ከሆኑ ሴት አሰራጭ አብረው ይዘው ይሂዱ፡፡ ያንን በማድረግ ሴቶች እንዳይጨናነቁና ለመናገር እንዲችሉ ማድረግ ትችላላችሁ፡፡
– በአየር ላይ ለመናር የማይፈሩ ሴቶችን ፈልጋችሁ አግኙ፡፡ በአየር ላይ ለመናር የማትፈራና ጥሩ አስተያየቶችና ሃሳቦች ያላት ሴት ስታገኙ የሞባይል ቁጥሯን ተቀብላችሁ በሌሎች ጉዳዮች ላይ እንድትናገር መልሳችሁ ደውሉላት፡፡ ይህን በማድረግ በቀጣይ ፕሮግሞቻችሁ ላይ ሌሎች ሴቶች እንዲናገሩ ለማበረታታት ትችላላችሁ፡፡
– ሴቶችን በቡድን ቃለመጠይቅ ማድረግ፡፡ አንድን ሴት ብቻዋን ቃለ መጠይቅ ካደረጋችሁ እናንተ እንደ ባለሙያ ስለምትታዩ ያቺ ሴት ልትፈራ ትችላለች፡፡ ሴቶችን በቡድን ካነጋገራችሁ ግን ነገሮች ይለወጣሉ! ሴቶች ቁጥራቸው ሲበዛ ጥንካሬ ያገኛሉ፡፡ አንድ ሴት ሃሳቧን ስትሰጥ ሌላ ሴት ያንን ሃሳብ በማስፋት ጠንከር ያለ ሃሳብ መስጠት እንደምትችል ይሰማታል፡፡ ሦስተኛ ሴት ደግሞ ያንን ሃሳብ ይዛ በመነሳት ሃሳቡ እየሰፋ ሄዳል፡፡
– በሩቅ አካባቢ ላሉ ሴቶች የሞባይል ስልክ ስጡ፡፡ ባንዳንድ መንደሮች ሴቶች የሞባይል ስልክ አቅርቦት የላቸውም፡፡ አቅማችሁ ከፈቀደ በዚያ መንደር ለአንዲት ሴት በአደራ አንድ ሞባይል ሰጥታችሁ የፈለጉ ሴቶች ወደ ራዲዮ ጣቢያችሁ እንዲደውሉ አድርጉ፡፡
– የሴት አርሶ አደርሴቶችን ሕይወት እና ተሞክሮ በፕሮግራማችሁ አቅርቡ፡፡ ሁላችንም እንደኛ ስላሉ ሰዎች ሕይወት መስማት እንፈልጋን፡፡ ሌሎች ሰዎች በሕይወት የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች እንዴት ነው የሚያሸንፏቸው? የሚያስደስታቸው እና የሚያሳዝናቸውስ ምንድን ነው? ሴቶች አርሶ አደሮችን ቃለመጠይቅ በማድረግ ታሪካቸውን በአየር ላይ እንዲናገሩ አድርጉ፡፡ ይሄ ተመሳሳይ ተግዳሮቶች ለሚያጋጥሟቸው ሰዎች አበረታች ይሆናል፡፡
– ከሴቶች ቡድኖች ጋር ግንኙነት ፍጠሩ፡፡ የተመሰረቱ የሴቶች ቡድኖችን አግኙና ፕሮግራማችሁን አዳምጠው ምን ህል የአርሶ አደሮች ጉዳዮችን እንዳሟላችሁ ግብረመልስ እንዲሰጧችሁ አድርጉ፡፡ የአድማጭ ቡድኖችን በተመለከት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ይህን ይጫኑ፡፡
– ሴቶች የሚጠቀሟቸውን የግብርና ቃላት ተጠቀሙ፡፡ ባንዳንድ ቦታዎች አንዳንድ ሰብሎችን እና የግብርና ሥራዎችን ለመግለጽ ሴቶች የተለዩ ቃሎች አሏቸው፡፡ እነዚህ ቃሎች ብዙ ጊዜ በወንድ አሰራጮች፣ ወንድ ባለሙያዎች እና አንዳንዴ ጊዜም በወንድ አርሶ አደሮች ላይታወቁ ይችላሉ! ሴቶች የሚጠቀሟቸውን እና የሚረዷቸውን ቃሎች ተጠቀሙ፡፡
– ልዩ የሆኑ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟችሁ የሴቶች ማንነታቸው ስይገለጽ እንዲናገሩ አድርጉ፡፡ አንዲት ሴት በቤቷ ወይም በሥራዋ በደል እየደረሰባት ከሆነ እና ማንነቷን ሳትገልጽ ታሪኳን ብትናገር የበቀል እርምጃ ሊወሰድባት እንደሚችል ስጋት ካለባት ታሪኳ ለአድማጮች እንዲደርስላት እርዷት፡፡ የሴትዮዋን ስም እና እውነተኛነቷን እርግጠኛ እስከሆናችሁ ድረስ ስሟን ወይም ማንነቷን የሚገልጽ ማንኛንም መረጃ ማሰራጨት የለባችሁም፡፡ ድምጽዋን በኮምፒዩተር ቀስ በማድረግ ወይም በማፍጠን ልትደብቁላት ትችላላችሁ፡፡ ስሟን ሳትጠቅሱ ታሪኳን መንገር ትችላላችሁ፡፡ የሷን ታሪክ ስታቀርቡ ሌሎች ብዙ ሴቶች ከራሳቸው ሕይወት ተመሳሳይ ታሪኮችን እንዲናገሩ ልትረዱ ትችላላችሁ፡፡ ይሄን በማድረግ እነሱ እና እናንተ መሰረታዊ ጉዳዮችን መዳሰስ እንድትችሉ ትረዳላችሁ፡፡ ድምጽዋን እና ስሟን ብቻ ሳይሆን ሌሎችም የእሷን ማንነት ለመለየት የሚረዱ ነገሮችንም ከማሰራጨት መቆጠብ እንደሚኖርባሁ ልብ በሉ፡፡
– ሴቶች አርሶ አደሮችም ባለሙያዎች ናቸው! አንዳንድ ሴቶች አርሶ አደሮች ሰብል ልማትን በተመለከት ራዲዮ ጣቢያው ከሚያቀርባቸው ባለሙያዎች እኩል ያውቃሉ፡፡ እነዚህን ሴቶች በአየር ላይ ቃለ መጠይቅ አድርጉላቸው፡፡ የነሱ መረጃ ለሁሉም አርሶ አደሮች ከመጥቀሙም በተጨማሪ የነሱ ምሳሌ ሴቶች ለግብርና ያላቸውን ዋጋ ሁሉም ሴቶች እንዲገነዘቡት ሊረዳ ይችላል፡፡
– ወንድ ባለሙያዎችን እና ወንድ አርሶ አደሮችን የምትጠይቁበትን መንገድ ቀይሩ፡፡ አንድ ባለሙያ ላምን ማስከተብ (ወንድ) ገበሬን እንዴት እንደሚጠቅም ካስረዳ ክትባቱ ሴቷን አርሶ አደር እና ቤተሰቡን በሙሉ እንዴት እንደሚጠቅም ባለሙያውን ጠይቁ፡፡ ክትባቱም አቅርቦቱ ለሴቶቹም ከወንዶቹ እኩል መሆኑን ጠይቃችሁ አረጋግጡ፡፡
– ሴቶችን ስለ ጓሮ አትክልት ብቻ አትጠይቁ፡፡ አብዛኛውን የጓሮ ሥራ ሴቶች እንደሚሠሩት እውነት ነው፡፡ ነገር ግን ቤተሰባቸው በሚሳተፍበት የግብርና ሥራ በሙሉ ተሳትፎ አላቸው፡፡ አንድ ላም ወይም ሰብል መቼ ቢሸጥ ጥሩ እንደሆነ፣ አፈርን ለማዳበር የትኛው መንገድ እንደሚሻል ወይም ገንዘብ ተበድሮ ግብዓት መግዛት ጥሩ ይሁን አይሁን ሃሳብ አላቸው፡፡
– ሴቶችን ሞባይል ስልክ አጠቃቀም አስተምሯቸው፡፡ አንዳንድ ሴቶች በትምሕርት ቤት ቁጥር የመማር ዕድል ኖሯቸው አያውቅም፡፡ ሞባይል ስልክ ቢያገኙ እንኳን ትክክለኛውን ቁጥር እንዴት መጫን እንዳለባቸው አያውቁም፡፡ ሴቶችን በራሳቸው ቋንቋ ቁጥሮችን ለማስታወስ የሚረዷቸው ዘዴዎች አዘጋጁ፡፡ ዘዴው የሚጠቅም እንደሆነ ሴቶች ላይ በተናጠል ሞክራችሁ እዩት፡፡ ከሠራ በራዲዮ ፕሮግራማችሁ አስተላልፉት፡፡
ወደ ራሳችሁ ቋንቋ ተርጉማችሁ በዜማ ልታስተላልፉት የምትችሉት የቁጥር ማስታዋሻ መንገድ ከዚህ በታች አለ፡፡ የተሻለም ልታገኙ ትችላላችሁ፡፡ ሳምንቱን በሙሉ በጣቢያችሁ ፕሮግራሞች ማሃል አጫውቱት፡፡ ጠቅሟቸው እንደሆነ ሴቶችን ጠይቁ
በሞባይል ስልካችሁ
ከዓለም ጋር ማውራት ትችላላችሁ
የትኞቹን ቁጥሮች መጫን እንዳለባችሁ
ማወቅ ብቻ ነው የሚያስፈልጋችሁ
ከግራ ወደ ቀኝ እነዚሁላችሁ፡-
– ከላይ መስመር፡- አንድ ሁለት ሦስት
ቀጣይ መስመር፡- አራት አምስት ስድስት
– ሦስተኛ መስመር፡- ሰባት ስምንት ዘጠኝ
– የስረኛው መስመር፡- ኮከብና ዜሮ ቁጥር ምልክት ነን፡፡
– በአየር ላይ ዘና በሉ! አድማጮቻችሁ አዝናኝ እና መረጃ ሰጭ ከሆኑ ፕሮግራሞች እንደሚጠቀሙ አስታውሱ፡፡ ሴቶች እና ወንዶች ወደፕሮግራማችሁ እንዲሳቡ ባህላዊ እና ዘመናዊ ታሪኮችን (ተረቶችን) እና ዘፈኖችን የምታካትቱበትን መንገድ ፈልጉ፡፡
– ስኬትን አክብሩ፡፡ ሴቶች አርሶ አደሮች በየቀኑ እንቅፋቶችን እያሸነፉ ትላልቅ ውጤቶችን እያገኙ ነው፡፡ እነዚያን የስኬት ታሪኮች እያገኛችሁ በአየር ላይ አክብሯቸው፡፡
ሴት አርሶ አደሮችን በራዲዮ ለማገልገል የሚረዱ ተጨማሪ መረጃ የት ማግኘት እችላለሁ?
- AMARC-WIN International, 2008. Gender Policy for Community Radio. http://www.amarc.org/documents/Gender_Policy/GP4CR_English.pdf
- Adamou Mahamane, Fatouma Déla Sidi, and Alice Van der Elstraeten. 2014. Guidelines for the production of gender responsive radio broadcasts. Food and Agriculture Organization of the United Nations. http://www.fao.org/3/a-aq230e.pdf
የቃላት ፍችዎች
ጾታዊ ፍትህ፡- ጾታዊ ፍትህ ማለት ሴቶችና ወንዶች ልዩነታቸው እንደተከበረ በአግባብ ይታያሉ ማለት ነው፡፡ በአሁኑ ያሉ ሴቶች ወይም ወንዶችን የሚጎዱ ኢሚዛናዊነቶችን የሚያስተካክሉ እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ለሴቶች የተለየ የስልክ መስመር በመዘርጋት የሴቶችን እና የወንዶችን ድምጽ እኩል ማሳተላለፍ ይቻላል፤ ወይም የስብሰባ ወይም የስልጠና እድሎች የሚዘጋጁበትን ሰዓት ለሴቶች በማመቻቸት እኩል እንዲሳተፉ ማድረግ ይቻላል፡፡
ጾታዊ እኩልነት፡- ጾታዊ እኩልነት ማለት ሴቶች እና ወንዶች መብቶችን፣ አጋጣሚዎችን እና የሕይወት እድሎችን በጾታቸው ስይገደቡ እና ልዩነት ሳይደረግባቸው መጠቀም ይችላሉ ማለት ነው፡፡ በጾታዊ እኩልነት ውስጥ ሰዎች በሚኖሩባቸው እና በሚሠሩባቸው ሁኔታዎች በሚኖሯቸው ሚናዎች፣ ሃላፊነቶች እና ውሳኔ የመስጠት ሂደቶች ውስጥ የሴቶች እና ወንዶች አመለካከቶች፣ ፍላጎቶች፣ የሚያስፈልጉ ነገሮች እና ቅድሚያ የሚሰጧቸው ጉዳዮች እኩል ሚዛን ተሰጥቷቸው ታሳቢ ይደረጋሉ፡፡ ለምሳሌ ሴቶች እና ወንዶች ሥራ የማግኘት፣ የስልጠና፣ የእድገት፣ የሥራ ሁኔታ እና የደሞዝ አንድ አይነት መብቶች እና ጥቅሞች አሏቸው፡፡ ጾታዊ እኩልነት ላይ ተጽእኖ የሚያደርጉ እና ግንኙነት ያላቸው ሌሎች ማሕበራዊ መዋቅሮች የሚከተሉትን ይጨምራሉ፡- መደብ፣ ዕድሜ፣ ብሔር፣ ጾታዊ ዝንባሌ እና በነዚህ ዘርፎች ውስጥ እኩነትን ለመፍጠር የሚደረጉ ጥረቶች፡፡
ለጾታዊ ጉዳዮች ክፍት መሆን፡- ለጾታዊ ጉዳዮች ክፍት መሆን ማለት ጾታዊ እኩልነትን እና ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ እንዲቻል የጾታ አደሎኣዊነትን ለማስተካከል እርምጃ መውሰድ ማለት ነው፡፡ ጾታዊ እሳቤዎች የፕሮግራም ዲዛይኖችን ይመራሉ፤ የወንዶች እና የሴቶች ልዩ ፍላጎቶች ይዳሰሳሉ፣ የተዛቡ ጾታዊ አለመካከቶች በዝምታ አይታለፉም፣ ጾታዊ እኩልነተም ይስፋፋል ማለት ነው፡፡