Script
Save and edit this resource as a Word document.
አስቸኳይ ስንል ለአርሶ አደሮች ምንድነው ?
አስቸኳይ ስንል ድርቅ፣ ጎርፍ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ ከባድ መብረቅ፣ የጭቃ መንሸራተት፣ ወረርሽኝ፣ ግጭት እና ዓመፅ ፣ እና የተባይ መወረርን ጨምሮ ሌሎች የተለያዩ ጫፍ የደረሰ ተፈጥሮአዊ ወይም ሰው ሰራሽ አደገኛ ችግር ህይወትን የሚያወዛግብበት እና አስቸኳይ የእርዳታ ጥሪን የሚጠይቅ ሁኔታ ማለት ነው፡፡
የአርሶ አደሮች የአስቸኳይ ምላሽ ፕሮግራም ምንድነው ?
የአርሶ አደሮች የአስቸኳይ ጊዜ አደጋ ምላሽ ኮሚዩኒኬሽን እና የአደጋ ማረጋጋት ፕሮግራም አርሶ አደሮች ቀጥለው የተዘረዘሩትን እንዲተገብሩ የሚያግዝ ተግባር ነው፤
– ለተፈጠረው ችግር ዝግጁ መሆን፤
– በተቻለ መጠን በችግሩ ወቅት ችግሩን መቋቋም እና በቀጣይም የግብርና ልምዳቸውን በመለወጥ አደጋው በግብርናቸው እና በህይወታቸው ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት አነስተኛ እንዲሆን መዘጋጀት
የአስቸኳይ ጊዜ አደጋ ምላሽ ዝግጅቴ በምን መልኩ አድማጮቼን የበለጠ ሊያገለግልኝ ይችላል ?
- ሊከሰት እንደሚችል ስለተገመተው አደጋ ዝርዝር መረጃ አድማጮችን ያዘጋጃል፤
- አደጋው በሚከሰትበት ወቅት ሊቋቋሙባቸው ስለሚችሉባቸው አገልግሎቶች አስፈላጊ መረጃዎችን ለአድማጮች ይሰጣል፡፡
- አደጋው ከመከሰቱ በፊት፣ በተከሰተበት ሰዓት ፣እና በኋላ ማህበረሰቦች አደጋውን ስለሚቋቋሙበት ዘዴ እርስ በርስ መረጃ እንዲለዋወጡ ይረዳቸዋል፡፡
- ማህበረሰቦች በተመሳሳይ ችግር ሊደርስ የሚችለውን አደጋ እንዲቀንሱ የግብርና ተግባራትን ጨምሮ አስቀድመው፣ በችግሩ ወቅት ፣እና በኋላ ሊተገብሩዋቸው የሚገቡ ተግባራትን እንዲለዩ ይረዳቸዋል፡፡
- የአስቸኳይ አደጋ ድጋፍ እና ማረጋጋት ለተቋማት ጠቃሚ ግብረ መልስ ይሰጣል፡፡
የአስቸኳይ አደጋ የህዝብ ግኑኝነት ስራ /ኮሚዩኒኬሽን/ እና የማረጋጋት ፕሮግራም በምን መልኩ የተሻሉ ፕሮግራሞችን ለማዘጋጀት ይረዳኛል?
- በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ማህበረሰቦቼ እንዴት ምላሽ እንደሚሰጡ ለመረዳት ያግዘኛል፤
- ለአድማጮቼ ጠቃሚ መረጃ የሚሰጡኝን ሃላፊዎች እና ድርጅቶች የት እንደማገኝ ለማወቅ ይረዳኛል፡፡
- በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ሰላምንና ጠቃሚ አመራር ሊሰጡልኝ የሚችሉ ዜጎችን እንድለይ ይረዳኛል፡፡
- በርካታ አርሶ አደሮች በሁኔታቸው ላይ እንዲወያዩ እና ከችግር እንዲያገግሙ መከተል ስላለባቸው ቅደም ተከተል ላይ እንዲወስኑ ለማገዝ ዕድል ይሰጠኛል፡፡
በምን መልኩ እጀምራለሁ? (ለእነዚህ ነጥቦች እና ተዛመጅ ይዘቶች የሚከተለውን ክፍል ተመልከት)
- የአስቸኳይ ጊዜ አደጋ የተለያዩ ደረጃዎችን እና ለእያንዳንዳቸው የሚያስፈልገውን ፕሮግራም አነዳደፍ ተረዳ፡፡
- ለማሰራጨት የሚያስፈልግህን ትክክለኛ መረጃ ሊሰጡህ የሚችሉ የትክክለኛ ድርጅት ሰዎችን አግኝ፡፡ በተጨማሪም በአደጋ ጊዜ መሪነትን ከሚወስዱ ሀገራዊ ወይም ክልላዊ ጥምረቶች ወይም ተቋማትና ኤጀንቶች ቡድኖች ጋር ግንኙነት እንዳለህ አረጋግጥ፡፡
- አድማጮችህን የፕሮግራምህ ማዕከል አድርግ፡፡
- ስሜታዊነትን አስወግድ
- አስቀድመህ አቅድ ነገር ግን የበለጠ አስቸኳይ ጉዳይ በሚያጋጥምበት ጊዜ ዕቅድህን ለማስተካከል ዝግጁ ሁን፡፡
- በአስቸኳይ የአደጋ ጊዜ ለጣቢያህ መጠባበቂያ የሚሆን ዕቅድ ያዝ፡፡
- ለአድማጮችህ ለማስተላለፍ ለፈለግከው መረጃ ተስማሚ የሆነ የአስቸኳይ ጊዜ መረጃ እና ትክክለኛ የአደጋው ደረጃ የሚመጥኑ ፎርማቶችን ተጠቀም፡፡
1) የአስቸኳይ አደጋ የተለያዩ ደረጃዎችን እና የእያንዳንዱ ደረጃዎች የፕሮግራም አሰራርን ተረዳ ፡፡
አስቸኳይ አደጋ ሶስት የተለያዩ ደረጃዎች አሉት፡፡ አርሶ አደር አድማጮችህ ለእነዚህ የተለያዩ ደረጃዎች የተለያዩ ዓይነት መረጃዎች እና በተለያዩት ደረጃዎች የተለያዩ የሬድዮ የመስተጋብር ዘዴዎችን ይፈልጋሉ፡፡ ትክክለኛ ፕሮግራም ለማዘጋጀት አደጋው በየትኛው ደረጃ ላይ መሆኑን ማወቅ ይጠበቅብሃል፡፡ ደረጃወቹ አንድ ላይ የሚደራረቡበት ሁኔታ እንደሚያጋጥም መገንዘብ እና ስታሰራጭ አንደኛውን እና ቀጣዩን ደረጃ ለያይተህ መሰራጨት አስፈላጊ ነው፡፡
– የቅድመ አደጋ ደረጃ:
ይህ አደጋው ቀድሞ የሚተነበይ ወይም የሚታወቅበት ደረጃ ነው፡፡ አካባቢያዊ ሁኔታን የሚቆጣጠሩ እና ሊከሰት የሚችል የአደጋን ሂደት የሚተነብዩ ድርጅቶች ጋር ተገናኝ፡፡ በአካባቢህ ምን ሊከሰት እንደሚችል ፤ የተተነበዩት ተፅዕኖዎች ምን እንደሆኑ ፤ የክብደታቸው መጠን ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል እንዲሁም አርሶ አደሮች ችግሩን ለመቀነስ ምን ማድረግ እንዳለባቸው በቻልከው መጠን እተማማኝ መረጃ አሰባስብ፡፡ በመቀጠል በመደበኛ ፕሮግራምህ መረጃውን ለአድማጮችህ በማስተላለፍ እና አርሶ አደሮች ምን ሊፈጠር እንደሆነ እና ከባድ አደጋን ለመቀነስ እንዲዘጋጁ አየር ላይ እንዲወያዩበት አድርግ፡፡
ለምሳሌ፡ በኢትዮጲያ ድርቅ እንደሚከሰት በተተነበየበት ወቅት የሬድዮ ጣቢያዎች ስለ መተንበዩ እና እንደ መፍትሄም ቶሎ የሚደርሱ ሰብሎችን እንዲዘሩ እና ሌሎች ማድረግ ያለባቸውን ነገሮች አርሶ አደር አድማጮቻቸውን አሳውቀዋል፤፤
እንደየ አደጋው ዓይነት የቅድመ አደጋው ደረጃ ጥቂት ወራቶች (ለድርቅ) ወይም ጥቂት ሰዓታት (ለመሬት መንቀጥቀጥ) ሊወስድ ይችላል፡፡
ትንበያዎችን በትክክለኛው ሰዓት ማሰራጨት አስፈላጊ ነው፡፡ በምትሰጣቸው መረጃ መሰረት አድማጮችህ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ትንበያዎችን ቀደም ተደርገው ካልተላለፉ በጣም ጠቃሚ አይሆኑም፡፡ በአንፃሩ ትንበያዎችን በጣም ቀድመው መተላለፋቸውም መረጃዎቹ ለመጠቀም አስተማማኝ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ በዚህ ላይ ጥብቅ ክትትል ካላደረግክ እና አደጋው የመከሰት እና የአደጋውን መዘዝ በትክክል ካላስተላለፍክ በአድማጮችህ ዘንድ ተኣማኒነትን ታጣለህ፡፡
– የአደጋ ደረጃ:
ይህ አደጋው የደረሰበት ሰዓት እና አድማጮችህም የአደጋውን ጉዳት የሚጋፈጡበት ወቅት ነው፡፡ ጣቢያህ አድማጮች አደጋው እያደረሰባቸው ስላለው ተፅዕኖ፤ በጉዳዩ እያደረጉ ያሉትን ነገር፤ የሚወያዩበትን ዕድል መፍጠር እንዲሁም ለሁሉም አድማጮች ልዩ የየቀኑ ፕሮግራም ማዘጋጀት ይኖርበታል፡፡
በተጨማሪ ጣቢያህ በሚከተሉት ነጥቦች ላይ በየቀኑ አጭር እና መደበኛ በሆነ መግለጫ አዳዲስ መረጃዎችን ማቅረብ ይኖርበታል፤
- የአደጋው ሂደት (ለምሳሌ፤ አደጋው በመጀመሪያ ደረጃ ላይ ነው? እየተባባሰ ሊሄድ ይችላል? በቀጣይ ቀናት እና ሳምንታት ምን ይጠበቃል? የአደጋው ሁኔታዎች እየቀነሰ ነው?)
- ከአደጋው ጋር የሚያያዙ የአየር ሁኔታዎች፤
- አመፅ ወይም ግጭት በሚፈጠርበት ጊዜ ሁኔታው ያለበት ደረጃ ላይ በመደበኛነት ከፖሊስ እና ከሌሎች ባለስልጣናት ወቅታዊ መረጃን አድርስ፡፡
- በአደጋው ተፅዕኖ ለደረሰባቸው ሰዎች የተዘጋጀ ልዩ አገልግሎቶች፤
እነዚህ መግለጫዎች በሁሉም ዘንድ መሰማታቸውን ለማረጋገጥ በተደጋጋሚ በመደበኛነት መተላለፍ አለባቸው፡፡
እነዚህ ልዩ ዕለታዊ ፕሮግራሞችህ እና መደበኛ መግለጫዎች በሁሉም አድማጮች ላይ ትኩረታቸውን በሚያደርጉበት ጊዜ መደበኛው የአርሶ አደር ፕሮግራምህም በዚሁ የአደጋ ደረጃ አሳሳቢ ጉዳዮች ላይ ሊያተኩር ይገባል፡
- ምን ዓይነት እርዳታ እንዳለ—ምግብ፣ ውሃ ፣ የመድሃኒት ድጋፍ ወይም ሌሎች ምንጮች፤
- እርዳታውን እየሰጠ ያለው ማን እንደሆነ፤
- አርሶ አደሮች እርዳታውን ለማግኘት በትክክል የት መሄድ እንዳለባቸው፤ እንዲሁም
- እየሰጡ ያሉትን እንዴት ማወቅ እንዳለብህ እና ተጨማሪ መረጃ እንዴት ማግኘት እንደምትችል
እንደ ድርቅ ባለ አደጋው የተተነበየ እና ቀላል ለማይባል ጊዜ ሊቆይ እንደሚችል የተገመተ ጉዳይ ሲሆን ለስልክ ደወል እና ለውይይቶች የተወሰነ ጊዜ ልትሰጥ ትችላለህ፡፡ በእነዚህ ሰዓታት አርሶ አደሮች ጭንቀቶቻቸውን እና ሌሎች ከችግሩ ጋር የተያያዘዙ ስሜቶቻቸውን ሊያካፍሉ ይችላሉ፤ ችግሩን እየተቋቋሙበት ስላለው ዘዴም መረጃቸውን ሊያካፍሉ ይችላሉ፡፡ ጣቢያዎች አርሶ አደሮች የፅሁፍ መልእክትን ጨምሮ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ገጠመኞቻቸውን እና ግብረ መልሶቻቸውን እንዲልኩ ሊጋብዙ ይችላሉ፡፡ በኢትዮጵያ ጣቢያዎች አንዳንዴ አደጋ በሚፈጠርበት ወቅት በስልክ በመገናኘት ፈንታ አርሶ አደሮችን ማሳዎቻቸው ድረስ ሄደው ጉብኝት ማድረግን ይመርጣሉ፡፡ ይህም ሁለት ጥቅሞችን ያስገኛል፡፡ አዘጋጆቹ ችግሩን በቅርበት እንዲመለከቱ እንዲሁም አርሶ አደሮች ስልክ በመደወል ብር ከማባከን እንዲድኑ ያግዛቸዋል፡፡
የአደጋ ደረጃ ፕሮግራም ዝግጅት አደጋው በአድማጮችህ ላይ አጣዳፊ ተፅዕኖ መፍጠሩን እስካላቆመ ድረስ መቀጠል አለበት፡፡
– የድህረ አደጋ ደረጃ:
ይህ የከፋው አደጋ ሁኔታዎቹ ካለፉ በኋላ ፤ አርሶ አደሮቹ ስለ ወደፊቱ ለማሰብ እፎይታ የሚያገኙበት ፤ በቀጣይ ሊከሰቱ በሚችሉ አደጋዎች ሊደርስባቸው የሚችልን ተፅዕኖ ለመቀነስ የሚያስችሏቸው አዳዲስ የግብርና ልምዶችን ፤ ሊተገብሩ የሚችሉበት ደረጃ ነው፡፡
መደበኛ መግለጫዎች በዚህኛው ደረጃ አያስፈልግም፡፡ ሆኖም በአደጋው ማግስት በሚኖረው አለመረጋጋት ላይ ባሉት ችግሮች ዕለታዊ የአርሶ አደር ፕሮግራም ለማስተላለፍ አልያም ትኩረት የተሰጣቸው አርሶ አደሮች በሚያስፈልጉዋቸው ጉዳዮች ዕለታዊ የድህረ አደጋ ፕሮግራሞች ላይ ለማተኮር ከእነሱ ጋር መነጋገር ያስፈልጋል፡፡
እንዲህ ዓይነቱ የፕሮግራም አዘገጃጀት አርሶ አደሮች የሚከተሉትን ዕድሎች እንዲያገኙ እስከተፈለገ ድረስ መቀጠል አለባቸው፡
- አብነታዊ ብቃትን አሞግሶ፤ መልካም የመቋቋም ልምዶችን ፡
- የአደጋ ጊዜ የአገልግሎቶች ውጤታማነትን እና በቀጣይ በተሸለ ሁኔታ ምን መሰራት እንዳለበት ገምግም፤
- የተሻሻሉ የግብርና ልምዶችን ላይ፣ ተወያይ እንዲሁም ሞክር፡፡
እንደ አደጋው ባህርይ እና ክብደት ይህ የአደጋ ደረጃ ከጥቂት ቀናት እስከ ብዙ ወራት ሊቆይ ይችላል፡፡
ይህ የማገገም እና ፈጠራ ያላቸው ተግባራዊ የመፍትሄ ታሪኮችን ለማካፈል የምትፈልግበት ደረጃ ነው፡፡ አደጋው በፈጠረው ተፅዕኖ ዙሪያ እና እገዛ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የማህበረሰብ ውይይቶችን ለማካሄድ ጠቃሚ ወቅት ነው፡፡ እነዚህ ውይይቶች በአገልግሎቶች ዙሪያ ያለውን ክፍተት ለመለየት፤ አርሶ አደሮች ሁኔታውን እንዲቋቋሙ እና በቀጣይም ሊደርስ በሚችል አደጋ ሊፈጠር የሚችልን ችግር ለመቀነስ ይረዳል፡፡.
2) ማሰራጨት የምትፈልገውን መረጃ ሊሰጡህ የሚችሉ ትክክለኛ ሰዎች ካሉባቸው ድርጅቶች ጋር መደበኛ ግንኙነት ይኑርህ፡፡
በአደጋ ጊዜ ውጤታማ የአርሶ አደር ለፕሮግራም ለማዘጋጀት አስተማማኝ መረጃ ያስፈልገሃል፡፡ መረጃ ሊሰጠህ ከሚችሉ ከመንግስት ሚንሰቴር መስሪያ ቤቶች እና ድርጅቶች ቁልፍ ሰዎችጋር ግንኙነት አጠናክር፡፡ ለምሳሌ፡- የግብርና ሚንስቴር፤ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ፤ በአደጋ መቆጣጠር እና መከላከል ላይ ከሚሰሩ ድርጅቶች ጋር ፤ የመንግስት ኮሚዩኒክሽን መስሪያቤቶች ጋር ከግብርና ምርምር ማዕከላት ፤ በአደጋ ነክ ፕሮግራሞች ከሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር እንዲሁም ከራዴዮ ጣቢያዎች ጋር ግንኙነትን በመገንባት ጀምር፡፡
በተቻለ መጠን አደጋ ከመፈጠሩ በፊት ወሳኝ ሰዎችን እና ድርጅቶችን በመደበኛ ሁኔታ እያገኘህ አነጋግራቸው፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች በሬድዮ ፕሮግራሞችህ ለአድማጮችህ አስፈላጊ በሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ባለሙያ እንግዳ አድርገህ በመጋበዝ እነዚህን ግንኙነቶችህን ማጠናከር ትችላለህ፡፡ በአደጋ ጊዜው መሃል ሚንስቴሮች እና የእርዳታ ወኪሎች ሊረዱዋቸው የሚችሉ የህዝብ ግኑኝነት አጋሮቻቸውን ለማፈላለግ እና ለመገምገም ጊዜ ላኖራቸው ይችላል፡፡ ዓመቱን ሙሉ ከእነሱ ጋር ጥብቅ ግኑኝነት በመፍጠር አደጋው የማይቀለበስ በሚሆንበት ጊዜ እና መንግስት ወይም የእርዳታ ወኪሎች ህዝቡን ለማሳወቅ ሲፈልጉ አንተ ተባባሪያቸው ትሆናለህ፡፡ .
3) አድማጮችህ የፕሮግራሞችህ ማዕከል እንዲሆኑ አድርግ፡፡
በእያንዳንዱ ፕሮግራም መረጃ ትክክለኛ መሆኑን፤ ግልፅ እና በቀላሉ ለመረዳት በሚቻል ቋንቋ መገለፁን ፤ ወቅታዊነቱን ፣እና በእያንንዱ የአደጋ ደረጃዎቹ የአድማጮች ፍላጎት ላይ ማተኮሩን አረጋግጥ፡፡ አድማጮችህ ከአንተ ጋር እንዴት እንደሚግባቡ እና ከአንተ ሊያገኙ የሚችሉትን የመረጃ ዓይነት በግልፅ አብራራ፡፡ በተቻለ አጋጣሚ አርሶ አደሮችን ቃለ መጠይቅ በማድረግ ፤ በስልክ በማሳተፍ እና በፓነል ውይይት፤ ምን ዓይነት መረጃ እና እገዛ እንደሚፈልጉ ለማወቅ እና አርሶ አደሮች አስቸጋሪ ሁኔታን እንዴት እንደሚቋቋሙ ምርጥ ተሞክሮ ለማሰራጨት ሞክር፡፡
4) ስሜታዊነትን አስወግድ፡
ስሜታዊነት ማለት ከአድማጮች ከፍተኛ ፍላጎትን ወይም ግብረመልስን ለመቀስቀስ አድማጮችን ሊጎዳ በሚችል ሁኔታ አስደንጋጭ ወይም የተጋነነ ቋንቋ ከእውነት የራቁ ታሪኮችን መጠቀም ማለት ነው፡፡ በአደጋ ጊዜ ስሜታዊ አስተያየቶችን መጠቀም አላስፈላጊ ጭንቀት እና ውጥረት ሊያስከትል ይችላል፡፡
5) አስቀድመህ አቅድ ሆኖም ግን ይበልጥ አንገብጋቢ ጉዳዮች ቢፈጠርሩ ዕቅድህን ለማስተካከል ዝግጀ ሁን፡፡.
አደጋ በአንድ የተለየ ክስተት ላይ ብቻ የሚወሰንበት አጋጣሚ በጣም አነስተኛ ነው፡፡ የተለያዩ ምክንያቶች በአጠቃላይ ለአደጋው አስተዋፅኦ ያደርጋሉ፡፡ አደጋዎች አንደ አንድ ነገር ሊጀምሩ ይችላሉ–ለምሳሌ፤ የመሬት መንቀጥቀጥ እና ፍንዳታ ወደ እሳት ወይም ወደ ጎርፍ ሊቀየሩ ይችላሉ፡፡ ውጤታማ የአደጋ ምላሽ ፕሮግራም ለማዘጋጀት ትልቁ ቁልፍ አደጋዎቹ የሚለወጡበትን ሁኔታ መለየት እና በዚያ መሰረት ፕሮግራምን መቃኘት መቻል ነው፡፡ ለምሳሌ አድማጮችህ ለወራት በቆየ የድርቅ ልምዳቸው እና ድርቁን ተከትሎ አከባቢያቸውን ጎርፍ ቢመታው አዲሱን ምክንያት (ጎርፉን) በፕሮግራመህ ማካተት ይኖርብሃል፡፡
6) ለጣቢያህ ለአደጋ ጊዜ የሚሆን ዝግጅት አቅድ
በአደጋ ወቅት ለአድማጮችህ ያለህ ጠቃሚነት እንዲቀጥል አየር ላይ መቆየት አለብህ! ጣቢያህ ስርጭቱን እንዲቀጥል ጥሩ የተግባር መርሃ ግብር አዘጋጅ፡፡ ዕቅድህ የሀይል አቅርቦትን፤ ምግብ፣ ውሀ ፣ ወዘተ ከግምት ማስገባት ይኖርበታል፡፡ይህም አድማጮችህን ማገልገልህን እንድትቀጥል ይረዳሀል፡፡
7) ለማስተላለፍ ለምትፈልገው መልእክት ትክክለኛ እና አደጋው ላለበት ደረጃ የሚስማሙ ፎርማቶችን ተጠቀም፡፡
በአደጋ የህዝብ ግኑኝነት/ኮሚዩኒኬሽን /እና ማረጋጋት ወቅት የተለያዩ ፕሮግራም ፎርማቶችን መጠቀም ትችላለህ፡፡ ጠቃሚ እና አደጋው ላለበት ደረጃ ተስማሚ የሆነውን መምረጥ ደግሞ ስኬታማ እና ጠቃሚ ፕሮግራም ለማዘጋጀት ቁልፉ ጉዳይ ነው፡፡ ቀጥሎ የፎርማቶች ዝርዝሮችን እና በአደጋ ምላሽ ፕሮግራሞች ወቅት ልትጠቀምባቸው የምትችላቸው ሁኔታዎችን እናያለን፡፡
- ቃለመጠይቆች: በተግባር እየሰሩ ካሉ የድርጅት ሰዎች ጋር እና በአደጋው ቀጥተኛ ተጠቂ ከሆኑ ሰዎች ጋር ቃለ መጠይቅ ማካሄድ ትክክለኛ እና ወቀታዊ መረጃ ለማግኘት ትልቁ መንገድ ነው፡፡ ከድርጅቶች ጋር የሚደረጉት ቃለመጠይቆች ሁኔታውን ለማሻሻል የሚረዱ ተግባራዊ እና ቀላል ቅደም ተከተሎች ፤ ባሉ አገልግሎቶች ላይ መመሪያ እና የት እንደሚገኙ የሚጠቁሙ አንገብጋቢ እና ጠቃሚ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ የተጎዱ ሰዎችን ማነጋገር የሚያሳስቡዋቸውን ጉዳዮች እንዲያካፍሉ እድል ይሰጣቸዋል፡፡ ሌሎች ተጎጂ አድማጮችም በዚሁ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉት እነሱ ብቻ እንዳልሆኑ እንዲገነዘቡ ይረዳቸዋል፡፡ ቃለመጠይቆች በተጨማሪ አድማጮችን ሰዎች አደጋውን እንዴት እየተቋቋሙ እንደሚገኙ የሚጠቁም ተግባራዊ ዘዴ በማስደመጥ የሚያበረታቱ መሆን አለባቸው ፡፡
- የስልክ ተሳትፎ: የስልክ ግንኙነት ሰዎች በአስቸኳይ ስለሚፈልጓቸው ጉዳዮች ጥያቄዎችን ለማቅረብ እና ከሚመለከተው አካል ትክክለኛ እና አፋጣኝ መልሶችን ለማግኘት ይረዳቸዋል፡፡ ይህንን ውጤታማ ለማድረግ ታዲያ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ከአንተ ጋር ሰቱድዮ ሆኖ በአስተማማኝ የስልክ መስመር የሚናገር የተዘጋጀ እንግዳ ሊኖርህ ያስፈልጋል፡፡ የስልክ ውይይት አድማጮችን በአሳሳቢ ጉዳዮች ዙሪያ ሌሎች ስለሚሰጡት መረጃ ለመስማት ያስችላቸዋል ፤ በተለይ አደጋውን ለመቋቋም የሚወስዷቸውን አማራጭ መፍትሄ ለመገንዘብ ይረዳቸዋል፡፡ ጣቢያዎች አድማጮች አደጋውን በተመለከተ ጥያቄዎቻቸውን የሚያቀርቡበት እና ስሜቶቻቸውን የሚገልፁበት ነፃ የ 24 ሰዓታት የስልክ መስመር መስጠት ይችላሉ፡፡ ጣቢያው አድማጮቹ ነፃ የስልክ መስመሩን እንዲጠቀሙ ለማስቻል በተደጋጋሚ የሚያስተዋውቅ ማስታወቂያ ማስተላለፍ ይችላል፡፡
- መግለጫዎች: መግለጫዎች አጭር፣ ቀጥተኛ እንዲሁም የአደጋውን ሂደት እና እየተሰጡ ስለሚገኙ ልዩ አገልግሎቶች ግልፅ መረጃ የሚሰጡ ናቸው፡፡ አንገብጋቢ መረጃዎችን በድጋሚ ለማግኘት ዕድል ይሰጣሉ፡፡ ለምሳሌ፡- የኬንያ ሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት በ 2015 ሊከሰት በሚችለው የኢሊኖ ዝናብ ላይ የሬድዮ የማንቂያ መልዕክት አስተላለፏል፡፡ ማንቂያዎቹ የሚመለከታቸው ሃላፊዎች በመፋሰሻ አከባቢዎች የሚገኙ ቆሻሻዎችን ለመፀዳት ፤ ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ ረባዳ ስፍራዎች አከባቢየሚኖሩ ሰዎችን ለማስነሳት ተጠቅመውበታል፡፡
- ስፖት ወይም የህዝብ አገልግሎት ማስታወቂያዎች: እነዚህ አንድ ጉዳይ የያዙና ቀለል ያሉ መልዕክቶችን በመደበኛነት እየደጋገሙ ለማስተላለፍ እጅግ ተመራጭ ዘዴዎች ናቸው፡፡ ስፖቶች አንድን በአግባቡ የተቀረፀ ቀላል መልዕክት ወይም ሚኒ ድራማዎችን ለማስተላለፍ ይጠቅማሉ፡፡ ስፖቶች ከአንድ ደቂቃ የማይበልጡ፤ ግልፅ እና በቀላሉ የሚገቡ ቋንቋዎችን የሚጠቀሙ ፎርማቶች ናቸው፡፡ ለምሳሌ፡-“በአየር ሁኔታ መዛባት የተነሳ የዝናብ ወቅቱ አርሶ አደሮች ከሚጠብቁት ቀድሞ ሊጀምር ይችላል፡፡” ይህ በሚተነበይበት ጊዜ ጣቢያዎች አርሶ አደሮች ሁኔታውን ለመቋቋም እንዲችሉ ሰብሎቻቸውን አስቀድመው ለመዝራት እንዲዘጋጁ የሚያሳስቡ አጫጭር ማስታወቂያዎችን ማስተላለፍ ይችላሉ፡፡
- ድራማዎች: ድራማዎችን ለማዘጋጀት ውስብስብ ቢሆኑም ለቅድመ አደጋ እና ድህረ አደጋ ደረጃዎች ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ስሜትን የሚነኩ ርዕሰ ጉዳዮችን እና ኋላ ቀር አባባሎችን ለመታገል ትልቅ ዘዴ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ስለ እነዚህ ጉዳዮች የሚናገሩ ልቦለዳዊ ገፀ-ባህርያትን መያዝ መልዕክቶቹን በሚገባ ለማስተላለፍ የተሻለ ዕድል ይሰጣሉ፡፡ ድራማዎች በሰዎች ህይወት ዳግም የመገንባት ሂደቱ ላይ በተወሰነ መልኩ አስፈላጊ የመዝናኛ ጣዕም ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ ስኬታማ ድራማ መፃፍ እና ማዘጋጀት ቀላል ስራ አይደለም ! በማህበረሰብህ ባለው የተለየ ችግር ላይ አተኩረው ስሜት በሚሰጥ እና ውጤታማ በሆነ መልኩ ድራማዎችን ለማዘጋጀት ከአከባቢህ ከሚገኙ የቲአትር ቡድኖች ጋር ስራ፡፡ ለምሳሌ ፡- በማላዊ በርካታ የሬድዮ ጣቢያዎች ድርቅ እና ረሃብ ተጋርጦበት በነበረ አንድ ቤተሰብ ላይ አተኩረው የአምስት ደቂቃ ድራማዎችን ያዘጋጃሉ፡፡ የቀረበው ድራማ እንደ የበጋ መስኖን እና የምግብ ስብጥርን፤አበጃጀትን፤ የጓሮ አትክልቶችን የመሳሰሉ አማራጮችን እንዲጠቀሙ፤ እንዲሁም ቦቆሎ መሸጥን የመሳሰሉ ጎጂ ልምዶችን እንዳይበረታቱ ይመክራል ፡፡ ጣቢያዎች በተጨማሪም አዝናኝ እና አስተማሪ የሆኑ የ አምስት ደቂቃ ክፍሎችን በታዋቂ ኮሜዲያን ያዘጋጃሉ፡፡
- ፓነል ውይይት : ፓነሎች በድህረ አደጋ ደረጃዎች ወቅትም አየር ላይ መዋል አለባቸው፡፡ የማህበረሰቡ አባላት እና ባለሙያዎች ከአደጋው ጋር በተያያዘ በማህበራዊ ፣ በፖለቲካዊ ፣ እና በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ እንዲወያዩ መልካም ዕድል ይፈጥርላቸዋል፡፡ በተጨማሪ የማህበረሰብ አባላት የትኞቹን ስትራተጂዎች እንዴት መተግበር እንዳለባቸው እንዲወያዩ ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡ (ለምሳሌ፡- የቅርብ ጊዜ ክስተትን ተከትሎ ኢቦላን የመቆጣጠር ስትራተጂዎች ላይ ያተኮረ ውይይትን ማዳመጥ ትችላለህ፡፡ (www.bbc.co.uk/programmes/p03b196q) ፓነል ውይይቶች የማህበረሰብ አባላትን ድርጅቶች በተልዕኮ ለሚሰጡዋቸው አገልግሎቶች ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግ ያስችላቸዋል፡፡ አዘጋጆችም በተወያዮች የተለዩ ቁልፍ ጉዳዮችን መከታተል ይችላሉ፡፡
ስኬታማ ስለ አደጋ ጊዜ እና ስለመረጋጋት የሬድዮ ፕሮግራም አዘገጃጀትን ተጨማሪ ከየት መማር እችላለሁ?
ቢቢሲ ሚድያ አክሽን ቀኑ ያልተጠቀሰ፤ላይፍ ላይን የፕሮዳክሽን መመሪያ “Lifeline Production Manual” https://www.bbcmediaactionilearn.com/mod/page/view.php?id=796
ቢቢሲ ሚድያ አክሽን ቀኑ ያልተጠቀሰ፤ አድማጮችህ በአደጋ ወቅት ለማወቅ የሚፈልጉት ነገር”What your audience needs to know in an emergency”: ህይወት አድን መረጃ “Life-saving information” ርዕስ በርዕስ መመሪያዎች “Topic-by-topic guides.” https://www.bbcmediaactionilearn.com/mod/page/view.php?id=797
ፍቺዎች
ማመቻቸት” Adaptation”: ማመቻቸት “Adapting” ማለት በተከሰተ ወይም በተተነበየ አደጋ ላይ በሚሰጥ ምላሽ መሰረት ማስተካከያዎችን ማድረግ ማለት ነው ፡፡ ለምሳሌ፡- (የአየር ሁኔታ መዛባት በሚያጋጥምበት ወቅት ቶሎ የሚደርሱ ወይም እንደ ስኳር ድንች ያሉ ሰብሎች እንዲያበቅሉ መጠቆም) እነዚህ ማስተካከያዎች አደጋዎችን ይቀንሳሉ፤ ጠቃሚ ዕድሎችንም ያስገኛሉ፡፡”
ማገገም ፡- የስርዓቶች ፣ የማህበረሰቦች፣ የቤተሰቦች፣ ወይም የግለሰቦች የመከላከል፣ የመታገል፣ ችግሮችን የመቋቋም እና ከችግሮቹ የማገገም አቅምን ይመለከታል፡፡
Acknowledgements
ምስጋና
አስተዋፅኦ ያደረጉ: ሲልቪ ሃሪሰን፣ የፋርም ሬድዮ ኢንተርናሽናል የሬድዮ ቡድን መሪ፣ ዱዋግ ዋርድ የፋርም ሬድዮ ኢንተርናሽናል ቦርድ ሊቀ መንበር እና ቪጄ ኩድፎርድ የፋርም ሬድዮ ኢንተርናሽናል ማኔጂንግ ኤዲተር ፤ ፍሬ ህይወት ናደው በኢትዮጵያ የፋርም ሬድዮ ኢንተርናሽናል ካንትሪ ዳይሬክተር ፤ ሙሉ በርሄ በኢትዮጵያ የፋርም ሬድዮ ኢንተርናሽናል ሚድያ እና ስልጠና አስተባባሪ፤ ኤልያስ ወልዴ በኢትዮጵያ የፋርም ሬድዮ ኢንተርናሽናል የፕሮጀክት ኦፊሰር ፤ ጂግሳ ተስፋዬ በኢትዮጵያ የፋርም ሬድዮ ኢንተርናሽናል የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ኦፊሰር ፤ ፓኡሊን ምቡኳ በማላዊ ፋርም ሬድዮ ትረስት የፕሮጀከት ኦፊሰር፡፡
ይህ ፕሮጀክት ካናዳ መንግስት ፋይናንሳዊ ድጋፍ በካናዳ ዓለም ዓቀፍ ጉዳዮች በኩል በሚሰጠው ድጋፍ የሚሳለጥ ነው፡፡
ይህ ሰነድ ወደ አማርኛ የተተረጎመው በቢልና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ለስቴፕልስ ፕሮጀክት በሰጠው ድጋፍ ነው፡፡