በደቡብ ወሎ አርሶ አደሮች ማሽላን በመንከባከብ ኑሮአቸውን እያሻሻሉ ነው

Notes to broadcasters

Save and edit this resource as a Word document.

ለብሮድካስተሮች ማስታወሻ

ማሽላ በደቡብ ወሎ ዞን ዋና ምርት የሆነና በባህበረሰቡ ኑሮ ላይ የጎላ ተፅዕኖ መፍጠር የቻለ እህል ነው፡፡ ማሽላ ከሳር ቤተሰብ የሚመደብና በአገራችን ለእንጀራ፣ ለባህላዊ መጠጦች (ጠላ፣አረቄና ቦርዴ)፣ ለእንስሳት መኖነት፣ ለቤት መስሪያና ለአጥር ማጠሪያም ግልጋሎት ይውላል፡፡

የማዕከላዊ እስታትስቲክ ኤጀንሲ የ2006 ዓ.ም. መረጃ በኢትዮጵያ ከሚሸፍነው መሬት ስፋትና በአጠቃላይ ዓመታዊ የምርት መጠን ከጤፍና ከበቆሎ ቀጥሎ በ3ኛ ደረጃ የሚገኝ ሲሆን በምርታማነት ደግሞ ከበቆሎ፣ ስንዴና ሩዝ ቀጥሎ በ4ኛ ደረጃ ይገኛል፡፡ በአገራችን በየዓመቱ ከሚታረሰው መሬት 1.7 ሚሊዮን ሄክታር የሚሆነው በማሽላ ሰብል የሚሸፈን ሲሆን ምርቱም 3.8 ሚሊዮን ቶን ይደርሳል፡፡

የአርሶ አደሮች የማሽላ ምርታማነታቸው እንዲያድግ የሰብል ልማት ባለሙያዎች የተለያዩ ሙያዊ ምክሮች እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ በማሽላ አመራረት ሂደት ውስጥ አርሶ አደሮች ምርታማ የሆኑ የማሽላ ዝርያዎችን እንዲጠቀሙ፣ የተቀናጀ የአረም ቁጥጥር እንዲከተሉ፣ የተሻሻሉ የአመራረት ዘዴዎች አንዲተገብሩ፣ ትክክለኛውን የሰብል ፈረቃ ጠብቆ አንዲዘሩ፣ ተገቢውን ማሳ ዝግጅት እንዲያከናውኑ፣ የእርጥበት ዕቀባ ስራዎችን አንዲሰሩ አንዲሁም የአገዳ ቆርቁርን እንዲከላከሉ ምክር ይሰጣቸዋል፡፡በዚህም የተነሳ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቃሉ ወረዳ ባሉ አካባቢዎች አርሶ አደሮች የምርታቸው መጠን እየጨመረ መሆኑን ይገራሉ፡፡

የአከባቢው አርሶ አደሮች በሙያተኞች የሚመከሩ ዘዴዎችን ከአገር በቀል እውቀቶች ጋር እያጣጣሙ ተግባራዊ ያደርጋሉ፡፡

ይህ ስክሪፕት በእውነተኛ ቃለ መጠይቅ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ በዚህ መነሻነት በማሽላ ወይም ሌላ ምርት ላይ መሰል ፅሁፎችን ለመፃፍ ወይም ጥናት ለማድረግ መጠቀም ትችላላችሁ፡፡ ይህን ስክሪፕት በመደበኛ የግብርና ፕሮግራማችሁ ላይም ወካይ ድምፆችን በመጠቀም ግብዓት ማድረግ ትችላላችሁ፡፡ ይህን ስክሪፕት ወደ ሬዲዮ ፕሮግራም መቀየር ከፈለጋችሁ ግን ለአድማጮች የሚሰሙት ድምፅ በቃለ መጠይቁ ላይ የተሳተፉ ሳይሆኑ ወካይ ድምፆች መሆናቸውን ማስገንዘብ ይኖርባችኋል፡፡

ፕሮግራሙ ማሽላ በሚመረትበት አካባቢ የሚተላለፍ ከሆነ ለአካባቢው ማህበረሰብ በሚስማማ መልኩ ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ አድማጮች ሀሳባቸውን ወይም ጥያቄአቸውን በስልክና በአጭር የፅሁፍ መልዕክት በመላክ እንዲሳተፉ መጋበዝ ትችላላችሁ፡፡ የሚከተሉት ጥያቄዎች ለውይይት መነሻ ሊሆኑ ይችላሉ፡-

  • በድርቅ ወቅት ወይም በእርጥበት ወቅት በአካባቢያችሁ አርሶ አደሮች ለምርታቸው ውሃን እንዴት አመጣጥነው ይጠቀማሉ?
  • አስተራረስ በአከባቢያችሁ ተባዮችንና አረማን ለመከላከል ያስችላሉ? ከሆነ በትኛው ጊዜና የአስተራረስ ዘዴ ቢተገበር ጥሩ ውጤት ያስገኛል?
  • በአካባቢያችሁ በማሽላ ምርት ሂደት ውስጥ ዋና ተግዳሮት ምንድን ነው?
  • አርሶ አደሮቹ ወይም ባለሙያዎች እነዚህን ችግሮች ለመቋቋም ምን ዓይነት መፍትሄዎችን ተግባራዊ ያደርጋሉ? ዘዴዎቹ በተግባር ውጤት አስገኝተዋል?

ይህ ስክሪፕት በግምት ከመግቢያና መውጫ ሙዚቃ ጋር ለ25 ደቂቃ ፕሮግራም ይሆናል

Script

ነፃነት ኃይሉ፡
ጤና ይስጥልን፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ የደቡብ ወሎ ዞን አርሶ አደሮች የማሽላ ምርታቸውን ተንከባክበው እንዴት ኑሮአቸውን እንዳሻሻሉ እንመለከታለን፡፡
የድምፅ ግብዓት፡-
የመኪና ድምፅ እና የዝናብ ድምፅ፣ ከስር በትንሹ ይሰማል
ነፃነት ኃይሉ፡
ወሩ ነሓሴ ነው፡፡ ይህ ወቅት በአብዛኛው ኢትዮጵያ አካባቢዎች ዝናባማ የክረምት ወቅት ነው፡፡ መሬቱ ረጥቦ አካባቢው አረንጓዴ ለብሷል፡፡ መላከዓ ምድሩ ማራኪ ነው፡፡ በመንገዳችን ላይ ዝንጀሮዎች ከዛፍ ዛፍ ይዘላሉ፡፡ የተራራዎችን ሰንሰለት ተከትሎ ሳይቋርጥ የሚታየው አርንጓዴ ገፅታ መንፈስን ያድሳል፡፡ ሰማዩ በደመና የተሸፈነ በመሆኑ በየትኛውም ሰዓት ዝናብ ሊዘንብ እንደሚችል ያመላክታል፡፡ የጉዞዬ ዓላማ የማሽላ አምራች አርሶ አደሮችን ለማነጋገር ወደ አንድ መንደር ላማምራት ነው፡፡

ከአዲስ አበባ በስተ ሰሜን አቅጣጫ ተነስቼ ከሰባት ሰዓታት የመኪና ጉዞ በኋላ ኮምቦልቻ ከተማ ደርሻለሁ፡፡ ኮምቦልቻ በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ ውስጥ ትገኛለች፡፡ ከኮምቦልቻ ወጣ ብላ የምትገኘው ተረፎ መንደር በአካባቢው እንደሚገኙ ሌሎች አርሶ አደሮች ሁሉ ማሽላ ለበርካታ ዓመታት ዋና ምርታቸው ሆኖ ቆይቷል፡፡

የድምፅ ግብዓት፡-
የመኪና ድምፅ እና የዝናብ ድምፅ በትንሹ ከተሰማ በኋላ ይቆማል
ነፃነት ኃይሉ፡
ኮምቦልቻ ገብቼ ቦርሳየን በያዝኩት ክፍል ውስጥ ካስቀመጥኩኝ በኋላ ከቃሉ ወረዳ የሰብል ምርት ባለሙያ አቶ ጌታቸው ወልደአረጋይን ጋር ተገናኘን፡፡ የጉዞ እቅዴን ከነገርኩት በኋላ በማግስቱ ወደ ተረፎ መንደር ለማምራት ቀጠሮ ይዘን ተለያየን፡፡ በማግስቱ በጠዋት አርሶ አደሮችን ለማነጋገር ወደ ተረፎ መንደር ሄድን፡፡ እንደደረስን ያገኘነው የመጀመሪያው አርሶ አደር መሐመድ አሊ ይባላል፡፡ ማሳውን እያረመ ነበር ያገኘነው፡፡
ነፃነት ኃይሉ፡
ጤና ይስጥልን አቶ መሓመድ
መሐመድ አሊ፡
አብሮ ይስጥልን፡፡ መረሃባ፡፡ እንኳን በሰላም መጣችሁ
ነፃነት ኃይሉ፡
እንኳን በሰላም ቆያችሁን፤ ቤተሰብ፣ ስራ አንዴት ነው
መሐመድ አሊ፡
ሁሉም ሰላም ነው ይመስገነው
ነፃነት ኃይሉ፡
አስቲ አካባቢያችሁን በአጥሩ ግለፅልኝ
መሐመድ አሊ፡
አካባቢያቸን በሄማ ይባላል፡፡ በቃሉ ወረዳ ተረፎ መንደር ውስጥ የሚገኝ ነው፡
ነፃነት ኃይሉ፡
ማሽላ እዚህ አካባቢ በስፋት እንደሚመረት ለመመልከት ችያለሁ፡፡ ማሽላን ማምረት ከጀመራችሁ ምን ያህል ጊዜ ይሆናል?
መሐመድ አሊ፡
ከልጅነቴ ጀምሮ ማሽላ ዋነኛ ምርታችን ነው፡፡ በርግጥ ቅድመ አባቶቻችን ጊዜም ማሽላ አብይ ምርት እንደነበር እንሰማለን፡፡ ስለዚህ ማሽላ በትውልድ ቅብብሎሽ እዚህ የደረሰ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ነፃነነት ኃይሉ፡
አሁን ምን እየሰራህ እንደሆነ እስቲ ንገረኝ?
መሐመድ አሊ፡
ማሽላ እያረምኩ ነው፡፡ ማሽላ በቂ ውሃ፣ አየርና ንጥረ ነገሮች አግኝቶ በስርዓት እንዲያድግ አረም ማስወገድ በጣም ወሳኝ ነው፡፡
ነፃነት ኃይሉ፡
ማሽላን ለማምረት መጀመሪያ የምታከናውነው ተግባር ምንድን ነው
መሐመድ አሊ፡
መጀመሪያ መሬት አዘጋጃለሁ፡፡ ማሽላ አገዳ ቅሪቶችን ከማሳ ላይ አፀዳለሁ፡፡ ከዚያም መጀመሪያውን እርሻ አከናውናለሁ፡፡ ይህ ዝናብ ቢዘንብም ባይዘንብም ይከናወናል፡፡ የመሬት ዝግጅት ማሽላ ምርት ወሳኝ ምዕራፍ ነው፡፡ በጊዜ ካልታረሰ የመዝሪያ ወቅት ሊያመልጥ ይችላል፡፡ ስለዚህ ከመጀመሪያው በጊዜና በትኩረት እሰራለሁ፡፡
ነፃነት ኃይሉ፡
በመሬት ዝግጂት ወቅት የማሽላ አገዳን ከማሳው ላይ እንዴት ነው የምታስወግደው?
መሓመድ አሊ፡
በአንድ ቦታ ላይ እሰበስባቸዋለሁ፡፡ ከዚያም አንድም አገዳ ሳይቀር ከማሳ ላይ አፀዳቸዋለሁ፡፡ የቀሩ ካሉ በመጀመሪያው እርሻ ከነስራቸው በመንቀል ከማሳ ውስጥ አስወግዳለሁ፡፡ ባለሙያዎች እንደመከሩን የማሽላ አገዳን ከማሳ ውስጥ ማፅዳት የማሽላ አገዳ ቆርቁር ትል ቁጥርን በእጅጉ ስለሚቀንስ ለቀጣይ ምርት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡
ነፃነት ኃይሉ፡
የትኛውን ዓይነት የማሽላ ዝርያ ይዘራሉ?
መሐመድ አሊ፡
ጠንገላይ የሚባል የማሽላ ዝርያ ነው የምንዘራው፡፡ ቶሎ ደራሽ ስለሆነ በጣም ውጤታ ነው፡፡ ዘንድሮ ግንቦት ላይ ነው የዘራሁኝ፡፡ ሌሎች የማሽላ ዘሮች ቀድመው ተዘርተው ይሀኛው ግን አሁን ቀድሞአቸው አድጓል፡፡
ነፃነት ኃይሉ፡
ቶሎ የሚደርስ ዘር ስትዘሩ የእርጥበት መጠን ማነስን እንዴት ትቆጣጠራላችሁ?
መሐመድ አሊ፡
ቶሎ የሚደርሱ ዝርያዎች ድርቅ ሳያይል መድረሳቸውና የመቋቋም ብቃት ያላቸው መሆኑ በራሱ አንዱ ጠቀሜታ ነው፡፡ ነገር ግን የእርጥበት እጥረት እንዳይጎዳው በእርጥበት እቀባ ዘዴ እንቋቋማለን፡፡ በማሳው ዙሪያ ቦይ በማበጀት ውሃውን በማሳው ዙሪያ በማከማቸትና በየመስመሮቹ መሃል ባሉት ቦዮች በማሰራጨት ሰብሉ እርጥበት እንዲያገኝ እናደርጋለን፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ ቦዮቹን ቀደም ብለን ነው የምናዘጋጀው፡፡ የውሃ ክምችቱ እንዳይዛባ ሽልሻሎ እንኳን በማስቀረት በሬ ሳላስገባ በአካፋ ነው ሰብሉን የመንከባከብ ስራ የምንሰራው፡፡
ነፃነት ኃይሉ፡
ሰብሉ በሚደርስበት ጊዜ ዝናብ ሲዘንብ አንዳይጎዳ ምን ታደርጋላችሁ?
መሐመድ አሊ፡
ሰብሉ ደርሶ ዝናብ የመዝነብ አዝማሚያ ከተገነዘብን ሰብሉን ተረባርበን ቶሎ እንሰበስባለን፡፡ የሜትዎሮሎጂ ዘገባም በንቃት ተከታትለን ምርቱ እንዳይጎዳ በአካባቢያችን የመረዳዳት ባህል መሰረት በመረዳዳት ከጉዳት እናድናለን፡፡ ባለሙያዎችም ቀደም ብለው ስለሚያስገነዝቡን ቀድመን አንዘጋጃለን፡፡
ነፃነት ኃይሉ፡
የማሽላ አገዳ ቆርቁርን በምን መልኩ ነው የምትከላከሉት?
መሐመድ አሊ፡
የማሽላ አገዳ ቆርቁር በአካባቢያችን በጣም አሳሳቢ ችግር ነው፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ስለ አገዳ ቆርቁር ጥሩ ግንዛቤ አግኝቻለሁ፡፡ በባህላዊ መንገድ የተጎዳውን አገዳ ነቅለን እናስወግዳለን፡፡ በባለሙያዎች ምክር የአገዳ ቆርቁር ምልክቶችን ለመረዳት ችያለሁ፡፡ ፀረ-አገዳ ቆርቁር ኬሚካልም እጠቀማለሁ፡፡ እነዚህ ኬሚካሎች በማህበራት ቀደም ብለው ይቀርቡልናል፡፡ ውጤቱም አስተማማኝ ነው፡፡
ነፃነት ኃይሉ፡
ማሽላን በወቅቱ የመዝራት ልምዳችሁ እንዴት ነው?
መሐመድ አሊ፡
በወቅቱ መዝራት የማሽላን ምርታማነት ለማሳደግ ወሳኝ ነው፡፡ በጊዜ ለመዝራት መሬቱን ቀድሞ ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ወቅቱን ጠብቀን ካልዘራን ምርቱ ይቀንሳል፡፡ የሚመከረው የመዝሪያ ወቅት የመጀመሪያው ዝናብ ዘንቦ ከአንድ ሳምንት በኋላ ነው፡፡ ይህ በአፈር ውስጥ በቂ እርጥበት መኖሩን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡
ነፃነት ኃይሉ፡
ማሽላን ከመንከባከብ አንፃር እስካሁን ችግሮችን በመመከት ያካበታችሁት ልምድ ምን ይመስላል?
መሐመድ አሊ፡
ለበርካታ ዓመታት በተለምዶ በምንዘራበት ወቅት በእውቀት ማነስ የተነሳ በጣም ትንሽ ምርት ነበር የምናገኘው፡፡ ከአንድ ጥማድ መሬት አምስት ወይም ስድስት ኩንታል ነበር የምናመርተው፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በባለሙያዎች ምክር በመስመር የመዝራትና ግብዓቶችን የመጠቀም ግንዛቤያችን በመዳበሩ አሁን ከአንድ ጥማድ እስከ አስራ አምስት ኩንታል እናገኛለን፡፡ ለምሳሌ ዱሮ ግንደ ቆርቁርን በዱኣ ካልሆነ በስተቀር እንደዚህ በተደራጀ መንገድ መከላከል አናቅም ነበር፡፡
ነፃነት ኃይሉ፡
ከምርት መጨመር ጋር በተያያዘ በኑሮህ ላይ ምን ለውጥ መጣ?
መሐመድ አሊ፡
አሁን ምርቴ መጨመሩ ኑሮዬን አሻስሎልኛል፡፡ ከብቶቼን በአግባቡ መንከባከብ ችያለሁ፡፡ ስድስት ልጆች አሉኝ፡፡ አራት ወንዶችና ሁለት ሴቶች፡፡ አንድ ድሬያለሁ ሌሎቹን እያሳደኩና እያስተማርኩ ነው፡፡ የተሻለ ቤትም ለመስራት ችያለሁ፡፡ ባለቤቴ በጣም ታታሪ መሆኗ ደግሞ ጉልበት ሆኖኛል፡፡ በብዙ መልኩ ታግዘኛለች፡፡ ተመካክረንና ተግባብተን ነው የምንሰራው፡፡
ነፃነት ኃይሉ፡
ለነበረን ጊዜና ለቃለመጠይቁ አመሰግናሉ?
መሐመድ አሊ፡
እኔም አመሰግናለሁ፡፡ በሰላም ግቡ

አድማጮቻችን የመሐመድ አሊን ማሳ ተዘዋውረ ጎብኝቻለሁ፡፡ የምርቱ አያያዝ እጅግ በጣም የሚያረካ ነው፡፡ ቄአያቸውን በንፅህና ነው የሚጠብቁት፡፡ ለስራ ያላቸው ተነሳሽነትና የመለወጭ ጉጉታቸው ያረካል፡፡ አሁን ደግሞ ወደ ሌላ አርሶ አደር ቤት ላምራችሁ፡፡

ወ/ሮ ሰንደል አህመድ ይባላሉ፡፡ የተረፎ ሰፈር ነዋሪ ናቸው፡፡ እርሳቻውም ለበርካታ ዓመታት ማሽላን የማምረት ልምድ አላቸው፡፡

ነፃነት ኃይሉ፡
የአፈር ውስጥ እርጥበትን እንዴት ያቆያሉ?
ሰንደል አህመድ፡
– በአፈር ውስጥ ያለውን እርጥበት የማቆየው ከትንሽ ካፊያ ጀምሮ ደለል ይዞ የሚሄደውን ውሃ ወደ ማሳው በመቀልበስ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በቂ እርጥበት ከማግኘት ባሻገር የአፈር ለምነትንም ይጠብቅልኛል፡፡
ነፃነት ኃይሉ፡
የማሽላ አገዳ ቆርቁርን እንዴት ይከላከላሉ?
ሰንደል አህመድ>፡
በአብዛኛው አገዳውን በፀሐይ አስጥቶ ማስወገድ ነው፡፡ ከማሳ ላይ ሙልጭ አድርጌ አፀዳለሁ፡፡ ቁርቁራ የሚባል ጉቶ በተለይ የአገዳ ቆርቁር መጠለያ ስለሚሆን እሱንም ከማሳ ውስጥ አፀዳለሁ፡፡ ኬሚካልም በመርጨት እከላከላለሁ፡፡ ነገር ግን ብዙም ወጪ ሳያስወጣኝ በልማዳዊ መንገድ የከብቶችን ሽንት ለሁለት ሳምንታት ከድኖ በማስቀመጥ ማሽላው ላይ በመርጨት እከላከላለሁ፡፡ በዋናነት ግን ጉዳት ከማድረሱ በፊት እከላከላለሁ፡፡ የተጎዳ አገዳ ደግሞ ነቅዬ አስወግዳለሁ፡፡ ስለዚህ በምርቱ ላይ ብዙም ጥቃት አያደርስብኝም፡፡
ነፃነት ኃይሉ፡
ሌላ በምን መንገድ ነው ግንዛቤ የምታገኙት?
ሰንደል አህመድ፡
ባለሙያዎች ከሚሰጡን ትምህርት በተጨማሪ በመደበኛነት የግብርና ፕሮግራሞችን በሬዲዮ አዳምጫለሁ፡፡ በተለይ በፋርም ሬዲዮ የሚዘጋጀውን ሳምታዊ ፕሮግራም በአማራ ሬዲዮ ላይ ሀሙስና ሰኞ አዳምጣለሁ፡፡ ከዚያም ያዳመጭኩትን ከሬዲዮ ላይ ቀድቼ ለአድማጭ ቡድናችን አስደምጣለሁ፡፡ ከዚያም በየአስራ አምስት ቀን በቡድን እንወያይበታለን፡፡ የገባው ላልገባው ያስረዳል፡፡ በዚህም በጋራ ግንዛቤያችንን እናዳብራለን፡፡ በዚህ መንገድ ብዙ የሰፈራችን ሴቶች ተነቃቅተዋል፡፡ በራስ መተማመናቸው እጅጉን ተሸሽሏል፡፡
ነፃነት ኃይሉ፡
ወቅቱ ሳያልፍ ማሽላን በጊዜ መዝራት ጥቅሙ ምንድን ነው?
ሰንደል አህመድ፡
ዘሩን በጊዜ ለመዝራት መጀመሪያ መሬቱ በጊዜ መዘጋጀት ይኖርበታል፡፡ በዚህም መሰረት እኔም ማሳዬን በማፅዳት በጊዜ አርሼ አዘጋጅና ልክ የመዝሪያ ወቅት ሲደርስ ሳልዘናጋ ቶሎ እዘራለሁ፡፡ እህልን ዘርቶ ምርታማ መሆን ልክ ልጆቼን እንደማሳድገው ነው የማየው፡፡ ልጆች በቂ እንክብካቤ ካላገኙ በበሽታ ስለሚጠቁ በተገቢው መልኩ ማደግ እንደማይችሉ ሁሉ የሰብል ምርትም ከመጀመሪያው ተገቢውን ትኩረትና እንክብካቤ ካላደረግን ጥሩ ምርት አይወጣውም፡፡ ስለዚህ የምርታማነት መጠን የሚወሰነው ለሰብሎቹ በምናደርገው እንክብካቤ ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡ ይህ ነገር ተያያዥነት አለው፡፡
ነፃነት ኃይሉ፡
ማዳበሪያ ይጠቀማሉ?
ሰንደል አህመድ፡
አዎ በመዝሪያ ወቅት ዳፕን ከ20 – 30 ቀናት መካከል ደግሞ ኤንፒእስ ማዳበሪያዎችን እንጠቀማለን፡፡
ነፃነት ኃይሉ፡
ምርቱን በመንከባከበችሁ ያገኛችሁት ጥቅም ምንድን ነው?
ሰንደል አህመድ፡
አዝመራ ችግር የለብንም፡፡ በደንብ ስለምንንከባከብ ጥሩ ምርት እናገኛለን፡፡ አሁን እህል ተወዷል፡፡ አንድ ጭነት ስድስተ መቶ ብር እየተሸጠ ነው፡፡ የተረጋጋ ገቢ ስለነበረኝ በግብር ወቅትና በርካሽ ጊዜ ባለመሸጤ ተጠቅሜያለሁ፡፡ ይኸን ማድረግ የቻልኩት ደግሞ በቂ ምርት ማምረት በመቻለ ነው፡፡ አራት ልጆች አሉኝ፡፡ አንዷ መምህር ናት፡ አንዱ ሹፌር ነው፡፡ አንዷ ትዳር መስርታለች፡፡ አንዱ ነው አሁን እቤት ያለው፡፡ እሱንም ስራ ለማስጀመር እያሰብኩ ነው፡፡ ከምንም በላይ ከጄልቱ አለመሆን ነው፡፡ የሰውን እጅ እንደማየት ከባድ ነገር የለም፡፡ የሰው ዓይን ማየት ከባድ ነው፡፡ ራስን መቻል ማለት ይሀንን ማስወገድ ነው፡፡
ነፃነት ኃይሉ፡
አመሰግናለሁ ወ/ሮ ሰንደል አህመድ
ሰንደል አህመድ፡
– እኔም አመሰግናለሁ

አቶ ጌታቸው ወ/አረጋይ የቃሉ ወረዳው ሰብል ልማት በለሙያ ናቸው፡፡ ስለ ማሽላ የእርጥበት አያያዝና የአገዳ ቆርቁር መከላከያ ዘዴዎችን አጫውተውናል፡፡

ነፃነት ኃይሉ፡
በወረዳችሁ የማሽላ ምርት በምን ደረጃ ሊገለፅ ይችላል?
ጌታቸው ወ/አረጋይ፡
ማሽላ በሚመረትበት ወቅት የተለያዩ ችግሮች ያጋጥሙታል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የሚገለጸው የዝናብ እጥረት ችግር ነው፡፡ ሁለተኛው የአገዳ ቆርቁር ችግር ነው፡፡ ሶስተኛው የዘር አብዝቶ መዝራት ናቸው፡፡ በተከታታይ ዓመታት ይህንን ችግሮች ለማስወገድ የተወሰደው እርምጃ አንዱ በመስመር መዝራት ነው፡፡ በአንድ ማሳ ወይም ሄክታር ውስጥ ሊኖር የሚገባውን የዘር መጠን በመወሰን ሰርተናል፡፡ ፓኬጁ በሚያዘው መሰረት በመስመር መካከል 75 ሳ.ሜ በተክል መካከል ደግሞ 20 ሳ.ሜ ርቀት አንዲኖር ተደርጎ እንዲዘራ እንመክራለን፡፡ አርሶ አደሮችን እየተገበሩት ይገኛሉ፡፡ ይህ አዘራር ደግሞ ለእርጥበት እቀባ ስራ አጋዥ ሊሆን ችሏል፡፡
ነፃነት ኃይሉ፡
እርጥበት በአፈር ውስጥ የማቆያ ዘዴዎች ምንድን ናቸው?
ጌታቸው ወ/አረጋይ፡
የመጀመሪያው ስራ የማሳ አናት ትሬንች መስራት ነው፡፡ ይህ ዘዴ ዝናብ መዝነብ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በጎርፍ ምክንያት የሚመጣውን ውሃ ማሳ ውስጥ ከመግባቱ በፊት በማሳ አናት ላይ በማቆር እርጥበት እንዲከማች ያደርጋል፡፡ ይህ የአካባቢውን የውሃ መጠን ለመጨመር ያስችላል፡፡

ሌላው ከመሬት ዝግጅት ወቅት ጀምሮ በማሳ ውስጥ በየሁለት ወይም ሶስት ሜትሮች ርቀት እንደ አፈሩ ዓይነት በባለሙያዎች እገዛ ቦይ እየታሰረ ማሳ ውስጥ የገባውን ውሃ እንዲከማች ማድረግ ነው፡፡ በእርሻ ወቅት ይህን ያልሰሩ አርሶ አደሮች ካሉ በአካፋ እየቀደዱ መስመሩን ማበጀት ይችላሉ፡፡ ዝናብ በሚዘንብበት ጊዜ አርሶ አደሮቹ በማሳ ውስጥ በመገኘት እንደየውሃው መጠን መስመሩን እንዲዘጉና እዲከፍቱ አንመክራለን፡፡ ይህ ስራ ካልተሰራ የሚፈለገውን ምርት ማግኘት አዳጋች ነው፡፡ ምክንያቱም በፍሬ መሙላት ወቅት በመስከረም ውስጥ የዝናብ እጥረት ሊያጋጥም ስለሚችል ምርታማነቱን እንዳይቀንስ በቂ እርጥበት ማቆየት መቻል አለብን፡፡ ይህን ስራ በሁሉም ቀበሌዎች ላይ በዘመቻ ነው የምንሰራው፡፡

ነፃነት ኃይሉ፡
በእርጥበት እቀባ ስራ ውስጥ ያጋጠሙ ችግሮችና የተፈታበት አግባብ ምን ይመስላል?
ጌታቸው ወ/አረጋይ፡
ይህንን ስራ በመስራት የሚገኘውን ውጤት በጊዜው ሊያዩት ስለማይችሉ ብዙ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለው ያለመውሰድ ነው፡፡ ነገር ግን ካለፉት ዓመታት ልምድ በመነሳት የተገኘውን ውጤት በማየታቸው የአርሶ አደሮቹ የመተግበር ዝንባሌ አሁን ላይ በጣም ሰፊ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ሊታጣ የነበረውን ምርት ማግኘት ተችሏል፡፡
ነፃነት ኃይሉ፡
የአገዳ ቆርቁርን አርሶ አደሮች እንዴት እንዲከላከሉ ይመክራሉ?
ጌታቸው ወ/አረጋይ፡
በወረዳችን የአገዳ ቆርቁር ስርጭት በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይህን ለመከላከል ከመጀመሪያው ከእርሻ ዝግጅት ጀምሮ እያንዳንዱ ገበሬ ማድረግ ያለበትን ነገር እንመክራለን፡፡ እኛም ክትትል እናደርጋለን፡፡ የመጀመሪያው ስራ የዚህ ዓመት ምርት ሲነሳ ማሳው ላይ አገዳውን ቆርጦ አንጥፎ ማቆየት ነው፡፡ ከዚያም የደረቁ አገዳዎችን ከማሳው ላይ ሰብስቦ ማስወገድና በጊዜ በማረስ ቆረኖችን ማስወገድ ነው፡፡ ከዚህ ስራ በኋላም ቢሆን የአገዳ ቆርቁሩ ሙሉ በሙሉ ይወገዳል ብለን አንጠብቅም፡፡ በመሆኑም ዘር ከተዘራ በኋላ በማህበራት በኩል ከአቅራቢ ድርጅቶች በቀጥታ ግዢ መድሃኒት እንዲገባ በማድረግ አርሶ አደሮች እንዲጠቀሙ ያደርጋል፡፡ ርጭቱ እስከ ሶስት ጊዜ ይመከራል፡፡ የመጀመሪያው ከቁርጭምጭምት በላይ ጉልበት አካባቢ ሲደርስ ይረጫል፡፡ ከዚያ ሁለተኛው ርጭት ከ15 እስከ አንድ ወር መካከል ቢደገም ጥሩ ነው፡፡ የመጨረሻው ርጭት ስርጭቱ ከተስፋፋና በባለሙያ ምክር የሚከናወን ነው፡፡

ሌላው ከመከላከያ መንገዶች አንዱ በሳቢና አባባራሪ ዘዴ በሳሮች መከላከል በሚከናወን ነው፡፡ ብራኬሪያ ሳር የአገዳ ቆርቁሩን የምትጥለው ቢራቢሮን ይስባታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ዲስሞዲየም ሳር ቢራቢሮዋና ያባራታል፡፡ ብራኬሪያ ሳር በማሳ ዙሪያ ይተከላል፡፡ ሳሩ ከማሽላው ቀድሞ ማደግ አለበት፡፡ ዲስሞዲየም ሳር ደግሞ በየ50 ሳ.ሜ በየሶስት መስመር በየሰብሉ መካከል ይተከላል፡፡ ብራብሮዋ ልክ ማሽላ ላይ ለማረፍ ስትመጣ በማሳው ውስጥ የበቀሉ ዲስሞዲየም ሳሮች በሽታ ያባሯታል፡፡ ከዚያም ከማሳ ውስጥ ትወጣና በስበት ብራኬሪያ ላይ ታርፋለች፡፡ አሱ ላይ እንቁላሏን ጥላ ትሄዳለች፡፡ ብራኬሪያ ሳር ደግሞ እንቁላሉን የመግደል ባህሪ አለው፡፡ በዚህ ዘዴ የአገዳ ቆርቁር ማሽላ ላይ ሳይሰራጭ መከላከል ይቻላል፡፡ ይህን ዘዴ አሁን በተወሰኑ አርሶ አደሮች ዘንድ ብቻ ነው የተገበርነው፡፡ ወደ ፊት በስፋት ለማዳረስ እየሰራን ነው፡፡

ነፃነት ኃይሉ፡
አመሰግናለሁ

ጌታቸው ወ/አረጋይ፡
እኔም አመሰግናለሁ

አድማጮቻችን በአፈር ውስጥ እንዴት እርጥበትን ማቆየት፣ በየ2 – 3 ሜትሮች ቦይ በማበጀት ውሃ በማሳው ውስጥ እንዲንሸራሸር ማድረግ፣ የመሬት ዝግጅትና የማሽላ አገዳ ቆርቁርን በተመለከተ አርሶ አደሮችን አነጋግረን ልምዳቸውን ቀስመናል፡፡

አርሶ አደሮቹ እንደነገሩን ማሽላን መንከባከብ ኑሮአቸውን ለማሻሻል ከፍተኛ አስተወፅዖ አድርጎላቸዋል፡፡ የሰብል ሙያተኛውም ማሽላን የመንከባከቢያ ዘዴዎችን በተመለከተ ሙያዊ ምክሩን ለግሶናል፡፡ ከዚህ በተረፎ መንደር በተደረገው ቃለ ምልልስ ትምህርት እንደወሰዳችሁ ታስፋ አደርጋለሁ፡፡

Acknowledgements

ምስጋና
ቃለ መጠይቅ አድራጊ – ነፃነት ኃይሉ – ጋዜጠኛ፣ አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
አርትኦት – ዶ/ር ታዬ ታደሰ – በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ብሄራዊ የማሽላ ፕሮጄክት አስተባባሪ፣ መልካሳ፣ ኢትዮጵያ
የመረጃ ምንጭ

Information sources

ቃለ ምልልስ፡
መሓመድ አሊ – ነሓሴ 18 ቀን 2009
ሰንደል አህመድ – ነሓሴ 18 ቀን 2009
ጌታቸው ወልደአረጋይ – ነሓሴ 19 ቀን 2009