Notes to broadcasters
የአዘጋጆች ማስታወሻ
በሳብ ሳሃራን አፍሪካ የሚገኙ ቦቆሎ አምራች አርሶ አደሮች ሰብሎቻቸውን በፈጣን ሁሉን አውዳሚ እና በሌሎች ተምቾች እንዳይጎዱባቸው ተለያዩ ዘዴዎችን ለመተግበር ይሞክራሉ፡፡ ፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምች ቦቆሎን ፍለጋ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀስ ተምች ነው፡፡ በአፍሪካ መከሰቱን ይፋ ከተደረገበት ከ2016 ጀምሮ ከ40 በላይ በሚሆኑ የአፍሪካ አገራት የቦቆሎ ምርት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል፡፡ አሁንም ቢሆን አፍሪካ ውስጥ እንደሚገኝ ባለ ሙያዎች ይጠቁማሉ፡፡
በኢትዮጵያ 55 ሚልዮን ህዝብ የቦቆሎን በምግብነት እና በገቢ ምንጭነት ያመርታሉ፡፡ በገጠራማ አካባቢዎች ሰዎች አንድ አምስተኛው ካሎሪያቸውን ከቦቆሎ ያገኛሉ፡፡
አርሶ አደሮች ኬሚካሎችን በመተው የሳት ራቶችን ከቦቆሎ ማሳቸው በእጃቸው በመልቀም በማስወገድ ሰብሎቻቸው ፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምችን በተሻለ ሁኔታ እንዲቋቋሙ እና ጤናማ እንዲሆኑ የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ፡፡
የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች በዚሁ ዝናባማ ወቅት (ከሰኔ እስከ መስከረም) ቦቆሎን ዘርተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ከአዲስ አበባ 400 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው በጎጃም አካባቢ የሚገኙ አርሶ አደሮችን አነጋግረናል፡፡
አስቸጋሪ ከነበረው ከባለፈው ዓመት የምርት ዘመን በኋላ በአሁኑ ሰዓት አርሶ አደሮች ሰብላቸው መብቀል ከሚጀምርበት ደረጃ ጀምረው ከፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምች ለመከላከል ቁጥጥር እያደረጉ ነው፡፡ በዚህ ፅሁፍ ያካተትናት ሴት አርሶ አደር እንደነገረችን ከሆነ አሁን ላይ እያደረገች ባለው ተከታታይ ቁጥጥር በዚህ ዓመት ጥሩ ምርት ለማግኘት ተስፋ እድርጋለች፡፡ ማንኩሳ በተሰኘች ጣቢያ የሚገኙ አርሶ አደሮች ፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምችን ለይተው እንደሚያውቁ እና ሰብሎቻቸው በተምቹ እንዳይወድም ቁጥጥር እያካሄዱ እንደሚገኙ የግብርና ባለሙያ ገልፆልናል፡፡
ይህ ፅሁፍ በተግባራዊ ቃለ መጠይቅ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ በኣካባቢዎ በተመሳሳይ ርእሰ ጉዳይ ዙርያ ምርምር ለማካሄድ እና ፅሁፍ ለማዘጋጀት ይህን ፅሁፍ መጠቀም ይችላሉ፡፡ አልያም ፅሁፉን ድምፅ አክተሮችን ተጠቅመው በፕሮግራም መልኩ ማዘጋጀት ይችላሉ፡፡ ይህን ለማድረግ ከወሰኑ በፕሮግራሙ መጀመሪያ ላይ በፕሮግራሙ እየተደመጡ ያሉት ሰዎች በቃለ መጠይቅ የተሳተፉት ሰዎች ራሳቸው ሳይሆኑ በድምፅ ተዋንያን መሆኑን ለአድማጮችዎ በግልፅ ማሳወቅ ይኖርብዎታል፡፡
ይህን ፅሁፍ እንደ ምርምር ግብአት ወይም ተምቾችን ከመቆጣጠር አኳያ የማሳ ቁጥጥር የሚያስገኘውን ጠቀሜታ አስመልክተው የራስዎን የፕሮግራም ፅሁፍ ለማዘጋጀት እንደ መነሻነት መጠቀም ይችላሉ፡፡ አርሶ አደሮችን፣ የግብርና መኮንኖችን ፣ እና ሌሎች ባለሙያዎችን ያነጋግሩ፡፡ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ማቅረብ ይችላሉ :
- በዚህ አካባቢ ዋና ዋናዎቹ የፀረ ሰብል ተባዮች ምን ምን ናቸው?
- እነዚህን ተምቾች እና የሚያደርሱትን ጉዳት ለመቆጣጠር ተመራጭ ዘዴዎች ምን ምን ናቸው?
- አርሶ አደሮች ማሳዎቻቸው በሚያጋጥማቸው ሁኔታ መሰረት ሊወስዱኣቸው የሚገቡዋቸው ተግባራት ምን ምን ናቸው?
- አርሶ አደሮች ይህን ዓይነት የቁጥጥር ዘዴ በሚያከናውኑበት ጊዜ የሚያጋጥሟቸው ፈተናዎች ምን ምን ናቸው እንዴትስ እነዚህን ፈተናዎች በተሻለ ሁኔታ ማለፍ ይችላሉ?
አርሶ አደሮችን እና ባለ ሙያዎችን ከማናገር ባሻገር እነዚህን ጥያቄዎች በፕሮግራምዎ የስልክ ወይም የፅሁፍ መልዕክት ፕሮግራም ላይ መጠቀም ይችላሉ፡፡
ለዚህ ፕሮግራም ሊያዝ የሚችለው ክፍለ ጊዜ የመለያ ድምፅን ፣መግቢያን እና መውጫን ጨምሮ ከ 15-20 ደቂቃዎች ይደርሳል፡፡
Script
የተሻለው የቁጥጥር ዘዴ ከማሳው የተለያዩ ክፍሎች በዘፈቀደ በመምረጥ ቁጥጥር ማካሄድ ነው፡፡ እኔ በዘፈቀደ ከመሃል ሶስት ወይም አራት ሰብሎችን ፤ ከግራ፣ ከቀኝ ፣ እንደዚሁም ከፊት እና ከኋላ በመምረጥ ነው የምከታተለው፡፡
ሌላው ምልክት ነጣ ያለ ዱቄት መሳይ ትንሽ ነገር ይታያል፡፡ እነዚያ ማለት እንቁላሎቹ ናቸው፡፡ እንቁላሎቹን ሳያድጉ ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡
ግንዱ ላይ ወይም የቅጠሉ ጥምዝ ላይ ብሩህ ቡናማ ቀለም ያለው ቀዳዳ ካለ ተምቹ ሰብሉ ውስጥ መግባቱን ያመለክታል፡፡ በዚህ ሁኔታ በአጠገቡ ያሉ ሰብሎችን እንዲሁም በተምቹ የተጣሉ እንቁላሎች እንዳይኖሩ በአንክሮ እመለከታለሁ፡፡
እጩ ጉዳት የሚያደርስበት የሳት ራት ደረጃ ላይ የሚደርስበትን አካላዊ ሁኔታ ላይ ብዙ ተምረናል፡፡ ከላይ ወደ ታች ግንባሩ ላይ የባላ ቅርፅ ይታይበታል፤ ከጀርባው ጫፍ ደግሞ በአራት መአዘን የተቀመጡ ጥቁር ነጥቦች አሉት፡፡
ቅጠሉ ላይ ዱቄት መስለው የሚታዩትን እንቁላሎቹን እንዳያድጉ እና እንደ አምናው ለሳት ራትነት ደርሰው ሰብሉን እንዳያወድሙ አሽቼ እንቁላሎች መኖር አለመኖራቸውን ለማረጋገጥ በየቀኑ ወይም በየሁለት ቀኑ ማሳዬን እፈትሻለሁ፡፡ በሰብሎቼ ሁኔታ በጣም ደስ እሰኛለሁ፡፡ በጣም ጥሩ ነው፡፡ አመርቂ ምርት እንደማገኝም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
በመጀመሪያ አብዛኛዎቹ አርሶ አደሮች ፈጣን ሁሉም አውዳሚ ተምችን የተለመደው ተምች አድርገው ያስባሉ፡፡ ለየት ያለ የሳት ራት አድርገውም ያስቡት ነበር ፡፡ ሆኖም ባለሙያዎቹ ፎቶዎቹን እኛም ሳት ራቶቹን ና እንቁላሎቻቸውን በአካል ለማየት ችለናል፡፡ ባለፈው ዓመት ይህ ትልቅ ርዕሰ ጉዳያችን ነበረ፡፡ በዚህ ዓመት ተምቹን በራሳችን አይተን መለየት ችለናል፡፡
ባለፈው ዓመት ችግሩን አይተነዋል፡፡ ፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምች ሰብሎቻችንን አውድሞብናል፡፡ በዚያ ጊዜ እኛም በጣም ጠንቃቃ አልነበርንም እንደ አሁኑ ክትትል ናደርግም ፡፡ ተምቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ ነበር ሰብሎቻችንን የወረረው፡፡ የተወሰኑ አርሶ አደሮች ተምቹን ለመከላከል ኬሚካሎችን ተጠቅመው ነበር፡፡ ብቻ ያለፈው ዓመት ትልቅ መማሪያ ነበረ፡፡ ክትትላችንን እንድንጨምር አስተምሮናል፡፡ ለዚህ ክትትሌን በየቀኑ የማደርገው፡፡
ማሳዎቹ አባባቢ ላሳይሽ እችላለሁ፡፡ አርሶ አደሮች ማሳዎቻቸው በፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምች ሊወረሩ ይቸላሉ ብለው ሲያስቡ ወዲያው ይነግሩናል፡፡ እኛም ሄደን እናረጋግጣለን፡፡ ነገር ግን እስከ አሁን የደረሰ አደጋ የለም፡፡
እኔ እስካየሁት ድረስ አርሶ አደሮቹ ማሳዎቻቸው በፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምች እንዳይወረር መቆጣጠር ላይ በጣም ንቁ እንደሆኑ ነው የማምነው፡፡ በሳምንት ሁለት ጊዜ ሚሰራጨውን ፕሮግራም በቡድን ሆነው ይከታተላሉ፡፡ ስለዚህ በተምቹ ወይም በእንቁላሉ የተጠቃ ሰብልን የመለየት ብቃት አዳብረዋል፡፡ ተምቹን እንዲገድሉት ነው የምንመክራቸው፡፡ ሆኖም ግን ከመጠን ያለፈ የተምች ወረራ ሲያጋጥም እና በእጅ መልቀምን፤ የከብቶች ሽንት ሰብሉ ላይ መጨመር፤ ተምቾችን የሚይዙ አረሞችን ማብቀል ፤ ደጋግሞ ማረስን እና የመሳሰሉ ባህላዊ ዘዴዎችን መጠቀም በቂ ሆኖ ካልተገኘ በማለት ኬሚካል ዝግጁ አድርገናል፡፡
አርሶ አደሮች ፈጣን ሀሉን አውዳሚ ተምችን በእጅ በመልቀም እና በመግደል ማስወገድ አለባቸው፡፡ ተምቹ ግንዱ ላይ ወይም ቀዳዳዎች ላይ መግባቱን ካረጋገጡ የከብት ሽንት በማስረፅ መግደል ይችላሉ፡፡ ቅጠሎቹ ላይ የሚገኙ ነጫጭ እንቆላሎችን በእጅ በመልቀም እና በጣቶቻቸው በመጨፍለቅ ማስወገድ ይችላሉ፡፡
ከአስሩ ሰብሎች አንዱ ላይ የመጠቃት ምልክት ከተስተዋለ ለግብርና ባለሙያዎች ማሳወቅ ይኖርባቸዋል፡፡
በተጨማሪ አርሶ አደሮች ማሳዎቻቸውን በቀን ሁለት እና ሶስት ጊዜ ቢያዩ እና ሃያ በመቶ የሚሆነውን የሰብል መጠን በፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምች መጎዳቱን ካስተዋሉ ኬሚካል እንዲጠቀሙ እንመክራለን፡፡
ማዳበሪያን ከጨመሩ በኋላ የማሳ ቁጥጥርን መጀመር ያስፈልጋል፡፡የተምቹን መከሰት የሚያሳዩ ማናቸውም ምልክቶች ከታዩ ማሳው በከፍተኛ ወይም በመጠኑ የተጠቃ ብለን እንደ ሁኔታው እንለየዋለን፡፡ ማሳው በጣም የተጎዳ ከሆነ ኬሚካል እንጠቀም ወይስ ባህላዊ ዘዴዎችን የሚለውን ለመወሰን የሚረዳንን አንድ ሜትር በአንድ ሜትር የክብ ሩብ ዘዴን ንጠቀማለን ፡፡
አርሶ አደሮች በሰብሎቹ የመጀመሪያ የዕድገት ደረጃ ወቅት የመከላከል ተግባር በሚከውኑበት ጊዜ ተምቹን መቆጣጠር ይችላሉ፡፡ የቁጥጥር ዘዴዎቹ ሰብሎች ላይ የከብት ሽንት መጨመርን ፤ ተምቹ ከተክል ተክል የሚያደርገውን ጉዞ ለማሰናከል አጫጭር እና ከአምስት በታች ቅጠሎች ሏቸው ተክሎች መንቀልን ፤ እና ተምቹን የሚገፉ እፅዋቶች መትከልን ፤ እንቁላሎች መጨፍለቅን ፤ እና ተምቾችን በእጅ መልቀምን ያካትታሉ፡፡ ሆኖም አስቀድሞ መቆጣጠር ካልተቻለ ተምቹ ወደ ሌሎችም ማሳዎች በመዛመት ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል፡፡
ፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምች በምን ያህል ፍጥነት ማሳዎቻቸውን ሊያወድም እንደሚችልም ይገነዘባሉ፡፡ በሳምንት ሁለት ጊዜ የሬድዮ ፕሮግራም ይሰራጫል፡፡ በዚህም አድማጭ ቡድኖች ወቅታዊ መረጃዎችን ያገኛሉ፡፡ በማህበራዊ ግንኙነታቸው አጋጣሚ አርሶ አደሮቹ መረጃ የመለዋወጥ ልምድም አላቸው፡፡ የሬድዮ ፕሮግራሙ በፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምች ዙርያ ያላቸውን ዕውቀት ለማጠናከር እና የተምቹን ርዕሰጉዳይነት ለመጠበቅ በእጅጉ ይረዳል፡፡
ስለዚህ ተምቹን እና እንቁላሎቹን የሚለዩ አርሶ አደር ማየት ተስፋ የሚሰጥ ነው፡፡ በግሌ ዘንድሮ የሰብሎቻቸው ደህንነት አስተማማኝ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ይህም መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ቦቆሎ አምራች አካባቢዎች በፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምች ዙሪያ የሰሩትን ስራ የሚመሰገን መሆኑን ያሳያል፡፡
አቶ ተመስገንንም ለሰጡን ግልፅ ማብራሪያ እናመሰግናለን፡፡ ከአንደበታቸው እንዳዳመጣችሁት ኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች የቦቆሎ ማሳዎቻቸውን በጊዜ የመቆጣጠር ልምድ በማዳበራቸው የቦቆሎ ምርቶቻቸውን በፈጣን ሁሉን አውዳሚ ተምቹ ከመውደም እንዲተርፍ እያስቻላቸው ነው፡፡ “ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ” እንዲሉ አርሶ አደሮች ቀድመው በሚያደርጉት ክትትል በተምቹ የመጎዳት ዕድልን እየቀነሱ ይገኛሉ፡፡
Acknowledgements
ምስጋና
አስተዋፅኦ ያደረጉ: አክቲንግ ፕሮግራም ማናጀር የማን ሃይለ ስላሴ ሳህሌ፤ 105.3 አፍሮ ኤፍ ኤም አዲስ አበባ፤ ኢትየጵያ፡፡
ገምጋሚ: የእፅዋት ጥበቃ ተማራማሪ ዶር. በላይ ሃብተ ገብርኤል ፤ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሰብል ምርምር ዳይሬክቶሬት፤ የእፅዋት ጥበቃ ምርምር ዳይሬክተር ዲፓርትመንት ፤ አምቦ የእፅዋት ጥበቃ ምርምር ማዕከል አምቦ- ኢትዮጵያ ፡፡
This work was created with the support of the USAID Feed the Future Ethiopia Value Chain Activity as part of the project, “ICT-enabled Radio Programming on Fall Armyworm (FAWET).”
Information sources
የመረጃ ምንጮች
ቃለ መጠይቆች:
ወይዘሮ አይናዲስ ጥላሁን
አቶ ደረጀ ብሩክ
አቶ መልካም አበበ
አቶ መልክያለው ፋንታ
አቶ ተመስገን ምህረተ
ሁሉም ቃለመጠይቆች መስከረም 3, 2018 የተካሄዱ ናቸው