የሐሰት ዜና፡- እንዴት መለየት እና እርምጃ መውሰድ ይቻላል

Script

Save and edit this resource as a Word document.

የሀሰት ዜና ምንድን ነው?

ብዙ ሰዎች በማሕበራዊ ሜዲያ አማካኝነት ታሪኮችን፣ ፎቶ፣ ቪዲዮ እና ዜና ለጓደኞቻቸው ያካፍላሉ፡፡ ያስቃል ወይም ይጠቅማል ብላችሁ ስለምታስቡ ሰዎች እንዲያውቁት ታካፍላላችሁ፡፡

አንዳንድ ጊዜ ሰዎች እውነት እንደለሆነ የሚያውቁትን መረጃ ያካፍላሉ፡፡ እንደዚ ያለ አሳሳች መረጃ በኢንተርኔት እና ከዚያ ውጭ ባሉ መንገዶች፣ ኢንተርኔት በሚጠቀሙ አዳዲስ ሜዲዎች ወይም በነባሩ ሜዲያ ሊሠራጭ ይችላል፡፡

እንደ ራዲዮ ጋዜጠኝነታችሁ አንድን ታሪክ፣ ፎቶ ወይም ቪዲዮ ከማካፈላችሁ በፊት ቆም ብላችሁ ትመረምራላችሁ? ልታካፍሉት ያላችሁት ነገር ሙሉ በሙሉ ትክክል መሆኑን ታረጋግጣላችሁ? የምናየውና የምናነበው ነገር ሁሉ እውነት አይደለም፡፡

ሃሰተኛ ታሪኮች በፍጥነት ሊሰራጩ ይችላሉ፤ ከባድ ችግርም ናቸው፡፡ ይህ የየእለቱ ሕይወታችን አስከፊ እውነታ ሆኗል፣ ምክንያቱም የፖለቲካ ወይም የግል ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማንኛውም ምክንያት ሲሉ ሰዎች፣ ድርጅቶች እና የሜዲያ አካላት እውነት ያልሆኑ ታሪኮችን ይፈጥራሉ፡፡ ይህ ክስተት “ሐሰተኛ ዜና” ይባላል፡፡ የራዲዮ ጋዜጠኞች ሐሰተኛ ዜናን እንዴት መለየት እንደሚችሉ ማወቅ ያስፈልጋቸዋል፤ ሐሰተኛ ዜናን የሚደግፍ አስተዋጽኦም ማድረግ የለባቸውም፡፡

ሁኔታውን ያወሳሰበው ደግሞ “ሐሰተኛ ዜና” የሚለውን ስያሜ ተቃራኒ የፖለቲካ አቋም ያላቸው ወገኖች ትክክለኛ መረጃ በጥርጣሬ እንዲታይ ለማድረግ ይጠቀሙበታል፡፡

“ሐሰተኛ ዜና” ሆን ተብሎ ለማሳሳት እና ብዙውን ጊዜ ኢንተርኔት ላይ የወጣ ይዘታቸው ክሊክ/ጠቅ እንዲደረግላቸው ለማድረግ ሰዎች ፈጥረው የሚያዘጋጁት ታሪክ ነው ብሎ ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ይተረጉመዋል፡፡ ሐሰተኛ ዜና ከተሳሳተ እና የመረጃ ግድፈት ካለው ዜና ይለያል፡፡ ማንም ጋዜጠኛ ፍጹም አይደለም፣ መረጃ ስንሰበስብና ስንዘግብ ልንሳሳት እንችላለን፡፡ በተቃራኒው ግን ሐሰተኛ ዜና ሆን ተብሎ የሚሰራጭ አሳሳች መረጃ ነው፡፡

ሐሰተኛ ዜናን መረዳት ለአድማጮቼ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እንዴት ይረዳኛል?

  • ዜና በፖለቲካ፣ ማህበራዊ እና ሳይንሳዊ ጉዳዮች ላይ ትክክለኛ መረጃ ለመስጠት በጣም የሚጠቅም መሣርያ ነው፡፡ እርግጠኛ እና ሚዛናዊ የሆነ ዜና ሲቀርብ አድማጮች ስለ አንድ ሁኔታ መረጃ ተቀብለው የራሳውቸን ሃሳብ እና አመክንዮ እንዲያዘጋጁ ዕድል ይፈጥርላቸዋል፡፡
  • ትክክለኛ እና በደንብ የተጠና ዘገባ በማቅረብ የሕዝቡን እምነት እና የአድማጮችን ታማኝነት ማትረፍ ትችላላችሁ፡፡

ሐሰተኛ ዜናን በጥንቃቄ መከታተል የተሻለ ፕሮግራም ለማዘጋጀት እንዴት ይጠቅማል?

ሳታውቁ በራሳችሁ ፕሮግራም ላይ እንዳታሰራጩት ሓሰተኛ ዜናን ለይቶ ማወቅ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ በመረጃ ተደግፎ በትክክል የቀረበን መረጃ ሐሰት እንደሆነ ከምታውቁት ወይም አጠራጣሪና ዕውነተኛነቱን ማረጋገጥ ከማትችሉት መረጃ በመለየት እና ትክክለኛ መረጃን በመሰብሰብ ፕሮግራሞቻችሁ ትክክለኛ፣ አስተማማኝ እና ተዓማኒነት ያላቸው መሆናቸውን ማረጋገጥ ትችላላችሁ፡፡

ከየት ልጀምር? (ስለነዚህ እና ሌሎች ጉዳዮችም ከታች ባለው ክፍል ያለውን ዝርዝር በማንበብ ማወቅ ትችላላችሁ፡፡)

  1. ሐሰተኛ ዜናን መለየት
  2. የችግሩ አካል አትሁኑ
  3. የዕውነት አስፈላጊነት

ዝርዝር

 
1) ሐሰተኛ ዜናን መለየት
በዓለም ዙርያ ማለቂያ የሌለው ውሸት የሆነ መረጃና የሐሰት ዜና ይሰራጫል፤ “ሐሰቱን” ከ“ዜናው” በመለየት እና ትክክለኛውን መረጃ ለአድማጮቻችሁ ማራኪ በሆነ መልክ ማቅረብ ክብር ያለው ጋዜጠኛ ሥራ ነው፡፡
ስለሚቀርቡላችሁ ታሪኮች ከዚህ በታች ባለው መልክ ጥያቄ አቅርቡ፡-

ጠያቂ አይምሮ ይኑራችሁ
ብዙ የሐሰት መረጃዎች የሚሠራጩት ታሪኮቹ ተዓማኒነት ያላቸው ስለሚመስሉ ነው፡፡ ብዙዎቹ የተወሰነ ዕውነትነት ያላቸው ሆነው በፍጹም ተቀባይነት የሌለው መደምደሚያ ላይ ይደርሳሉ፡፡ ብዙ የሐሰት ዜናዎች ድንጋጤ እንዲፈጥሩ ሆነው ይዘጋጃሉ*፡፡ ስለዚህ እነዚህን ዜናዎች ስታነቡ፣ ስትመለከቱ ወይም ስታዳምጡ ስሜታዊነታችሁን ወደ ጎን መተው አለባችሁ፡፡ ነገር ግን ጉዳዩን በጥያቄ አስተናግዱት፤ ሁል ጊዜ ራሳችሁን የሚከተሉትን ጥያቄዎች ጠይቁ፡-

  • ይህ ታሪክ ለምን ተጻፈ?
  • የሆነ አመለካከት እንድይዝ ተጽእኖ ሊያሳድርብኝ እየሞከረ ነው? (አስተያየት እና ርዕሰ አንቀጽ ጽሑፎች* በጋዜጣ፣ ራዲዮ እና በተለይም ኢንተርኔት ላይ የተለመዱ መሆናቸውን ልብ በሉ፡፡ (ለምሳሌ አንድ ጡሮታ የወጣ ፖለቲከኛ፣ ሳይንቲስት ወይም ፀሓፊ በአንድ ጉዳይ ላይ የግሉን አስተያየት ሊሰጥ ይችላል፡፡) አንዳንድ ጊዜ ዜናዎች የአንድ ሰው ብቻ አስተያየት መሆናቸው ሳይገለጽ አድማጮች ወይም አንባቢዎች ላይ የአንድ የፖለቲካ አመለካከት ተጽእኖ ለማሳደር ሊጻፉ ይችላሉ፡፡
  • የሆነ አይነት ምላሽ እንድሰጥ ሊገፋፋኝ እየሞከረ ነው? ለምሳሌ ስሜታችሁ ላይ ጫና በመፍጠር በምርጫ ወቅት ድምጻችሁን ወዳንድ ወገን ለመውሰድ በሚደረግ ጥረት በራዲዮ፣ ጋዜጣ ወይም ኢንተርኔት ላይ የሚወጣ ጽሑፍ የአንድ ፖለቲከኛን ውድቀቶች ሳይገልጽ ስኬቶቹንና ጥንካሬዎቹን ሊዘረዝር ይችላል፡፡
  • ሊሸጥልኝ የሚፈልገው ምርት አለ?
  • አንድ ዌብ ሳይት ከፍቼ እንድገባ ወይም ታሪኩን እራሴ እንዳካፍል ሊገፋፋኝ እየሞከረ ነው?

ከነዚህ ጥያቄዎች ውስጥ ለማንኛውም መልሳችሁ “አዎ” ከሆነ ታሪኩን ለሌላ ሰው ከማካፈላችሁ በፊት በጥልቀት መርምሩት፡፡

ምንጩን አጣሩ

ከማታውቁት ምንጭ አንድ ታሪክ ካገኛችሁ ጥቂት ጥናት አድርጉ፡፡ በታዋቂ የዜና ምንጭ ወይም የታወቀ ጋዜጠኛ የተጻፈ ነው? ወይስ ከማይታወቅ የጦማር ገጽ የተገኘ ነው?

አብዛኛዎቹ የታወቁ የዜና ማሰራጫዎች ታማኝነታቸውን ለማጎልበት እና ታሪካቸው ውስጥ የተለያዩ አመለካከቶችን ለማካተት ሲሉ ጥቅሶችን እና የመረጃ ምንጮቻቸውን ያካትታሉ፡፡ ታሪኩ ምንም ምንጭ ከሌለው እያነበባችሁት ያለው የግል አስተያየት ወይም የሐሰት ዜና ሊሆን ይችላል፡፡

ታሪኩ የታተመው በማታውቁት የዜና ማሰራጫ ከሆነ ተጠንቀቁ፡፡ ድረ ገጹ “about us” (ሰለ እኛ) የሚለው ገጹ ላይ የጻፈውን በማንበብ ድርጅቱ ጽንፈኛ አመለካከት ያለው መሆን አለመሆኑን ወይም ጽንፈኛ አመለካከት ባለው ድርጅት ወይም ግለሰብ የተቀጠረ ወይም ግንኙነት ያለው መሆን አለመሆኑን አጣሩ፡፡ በተጨማሪም “contact us” የሚለውን ገጽ ተመልከቱ፡፡ ባለቤቱ ማን እንደሆነ፣ ማን እንደሚደጉመው እና ድረ ገጹን የሚቆጣጠረው ባለሙያ ማን እንደሆነ ግልጽ መሆን አለበት፡፡ ለምሳሌ የድረ ገጹ አድራሻ የጂሜይል አካውንት ቢሆን የድረ ገጹን እውነተኛነት መጠርጠር አለባችሁ!

የድረግጹ ስም ያልተለመደ ዓይነት ከሆነ ሊያቃጭልባችሁ ይገባል፡፡ ብዙ ጊዜ የድረ ገጽ ስሞች የዶሜይን ስማቸው .com, .org, .ac, .gov, .net, ወይም የአገር ኮድ (ለምሳሌ .gh ለጋና እና .ml ለማሊ) ከሆነ ችግር የለውም፤ ከዚያ ውጭ ግን የማይታወቁ አይነት ወይም በጣም ረጅም የዶሜይን ስሞች ካሏቸው ግን ችግር ያለባቸው ድረ ገጾች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አንዳንድ የሐሰት ዜና ድረ ገጾች ደግሞ የትክክለኛ ዜና ማሰራጫዎችን አድራሻ አስመስለው ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡ የድረ ገጽ ስማቸው፣ አርማቸው ወይም የድረ ገጾቹ ገጽታ/ዲዛይን ያልተለመደ አይነት ከሆነ በጥንቃቄ መርምሯቸው፡፡

ድረ ገጹ ያወጣቸውን ሌሎች ጽሑፎችም ተመልከቱ፡፡ አብዛኞቹ ጽሑፎች የተጋነነ ርዕስ፣ ለማመን የሚያስቸግር ይዘት፣ አስደንጋጭ ምስሎች እና የእርቃን ሰዎች ስዕሎች ካላቸው ያንን ጽሑፍ አምናችሁ ለሌሎች እንዳታካፍሉ መጠንቀቅ አለባችሁ፡፡

ያንን ታሪክ ሌላ የዘገበው አካል ካለ አረጋግጡ

ዓለም አቀፍ ዜና ከሆነ እንደ ቢቢሲ፣ አል ጀዚራ፣ ሲቢሲ፣ ሮይተርስ፣ ሲኤንኤን፣ አርኤፍአይ እና ኦልአፍሪካ ዶት ኮም የመሳሰሉ ታዋቂ የዜና ድርጅቶች ዘግበውት እንደሆነ አጣሩ፡፡ ከልሆነ ታሪኩ በከፊል ወይም በሙሉ እውነትነት የሌለው ሊሆን ይችላል፡፡ ታወቂ የዜና ድርጅቶች እያንዳንዱን ታሪክ ከማሰራጨታቸው ወይም ከማተማቸው በፊት ትክክለኛነቱን ያረጋግጣሉ፡፡ ያንን ታሪክ እነሱ ካላወጡት ሐሰት የመሆን ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡

የአገር ውስጥ ታሪክ ከሆነ ታዋቂ እና የተከበሩ ያአገር ውስጥ ዜና ማሰራጫዎች አውጥተውት እንደሆነ አጣሩ፡፡

ማስረጃውን አረጋግጡ

ተኣማኒነት ያለው ዜና የባለሙያ አስተያየት፣ ጥናቶች እና የታወቁ የስታቲስቲካል የቁጥር መረጃዎች ይኖሩታል፡፡ እነዚህ መረጃዎች ከሌሉና የመረጃው ምንጭ በስም ያልተጠቀሰ “ባለሙያ” ወይም “በአካባቢው የነበረ ሰው” ከሆነ የታሪኩን ትክክለኛነት መጠራጠር አለባችሁ፡፡

ተኣማኒነት ያለው ጋዜጠኝነት መረጃ በመሰብሰብ ይካሄዳል፡፡ ስለዚህ ጥናት የማድረግ ክፍተት ካለ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ዘገባ ክፍተት ይኖራል ማለት ነው፡፡ ታሪኩ ውስጥ ተሳትፎ ያላቸው ሰዎች ጥቅስ ከሌለበት መረጃው “የግል አስተያየት” ጦማር ወይም አምድ እንደሆነ አመላካች ነው፤ ይህ ደግሞ የሐሰት ዜና መሆኑን ሊያሳይ ይችላል፡፡ ተኣማኒነት ያላቸው የዜና ማሰራጫ ድርጅቶች ደግሞ ግልጽነት አላቸው፤ ለታሪኩ የሚያስፈልገው መረጃ በሙሉ ከሌላቸው ለምሳሌ አንድ የመረጃ ምንጭ ጋር ለመገናኘት ሞክረው እንዳልተሳካለቸው ይገልጻሉ፡፡

መረጃዎችን የሚያረጋግጡ ድረ ገጾችን ለመጠቀም ሞክሩ፡፡ https://africacheck.org/ እና Snopes.com የመረጃ እውነተናነትን ለማረጋገጥ የተቋቋሙ ድረ ገጾች ናቸው፡፡

ማን እንደጻፈው አረጋግጡ

ጸሓፊው ሌሎች የጻፋቸው ጽሑፎች ካሉ ፈልጉ፡፡ ከዚህ በፊት የጻፋቸውን ጽሑፎች ማግኘት ካልቻላችሁ፣ ወይም የጸሓፊው ስም ቦታ ላይ የታዋቂ ሰው ስም ከተጻፈ ወይም ጸሓፊው የማይታወቅ ከሆን ጠርጥሩ!

አንዳንድ ጊዜ ጽሑፎች አጭበርባሪ ታዋቂ ሰው ሼር ካደረጋቸው (ለሌሎች ካካፈለ) በኋላ ይሰራጫሉ – ይህ የሚሆነው በታዋቂ ሰው ስም በተከፈቱ የውሸት የማህበራዊ ሜዲያ አካውንት አማካኝነት ነው፡፡

ቀኑን አረጋግጡ

አንዳንድ የዜና ጽሑፎች መጀመርያ ሲያዩዋች 100% ትክክል ይምስላሉ፡፡ ምንጩ አስተማማኝ ነው፣ ጸሓፊው ይታወቃል፤ ጽሑፍ በሚገባ ተሰናድቶ ተጽፏል፡፡ ነገር ግን አሁንም መጠንቀቅ አለባችሁ … ጽሑፉ ከተጻፈ አስር ኣመት አልፎት ሊሆን ይችላል! የሐሰት ዜና የሚፈጥሩ ሰዎች ጽንፈኛ አለመካከታቸውን የማጠናከርያ አጋጣሚ ሲያገኙ አሮጌ ጽሑፎችን ጎርጉረው አውጥተው እንደገና ሊያትሙ ይችላሉ፡፡

ለምሳሌ 2009 ላይ የተከሰከሰ አይሮፕላን ታሪክ የሽብር ጥቃትን የሚጠቁም ንዑስ ርዕስ ተጨምሮበት በ2019 አዲስ ዜና መስሎ እንደ ገና ሊታተም ይችላል፡፡ በአሜሪካ ውስጥ አዲስ የሽብር ጥቃት እንደተደረገ አድርገው ሰዎች በስህተት እንዲያስቡ እና የጸረ-ሽብር እንቅስቃሴ ላይ ተጨማሪ በጀት እንዲመደብ ወይም የሰብኣዊ መብቶች እንዲገደቡ ለመቀስቀስ እንዲያገለግል ፎቶው ሊሰራጭ ይችላል፡፡ ፎቶዎች አሳሳች መረጃዎችን ለማሰራጨትም ሊያገለግሉ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ የቆየ ሁነት ላይ የተነሳ የሕዝብ ፎቶ ቅርብ ጊዜ ላይ ከተደረገ ሁነት ጋር ቀላቅሎ በማውጣት በቅርብ የተደረገውን ሰልፍ ለማጉላት ወይም ለማኮሰስ ሊያገለግል ይችላል፡፡

ምስሎቸን አረጋግጡ

እንደ ፎቶ ሾፕ ያሉ የፎቶ ማስተካከያ የኮምፒዩተር ፕሮግራሞች ትክክለኛ የሚመስሉ የውሸት ፎቶዎችን ለመፍጠር ያገለግላሉ፡፡ እነዚህ ፎቶዎች ማስጠንቀቂያ ምልክቶች ስለሚኖሯቸው በጥንቃቄ ተመልከቷቸው – ለምሳሌ ጥላቸው በተሳሳተ አቅጣጫ ሊሆን ይችላል፤ ፎቶው ውስጥ ካሉ ምስሎች ውስጥ አንዳንዱ ጠርዙ የተቆራረጠ ሊሆን ይችላል፤ የከለር ልዩነት ሊኖር ይችላል፤ ወይም ከጀርባ እና ከፊት ለፊት ያሉ ምስሎች ላይጣጣሙ ይችላሉ፡፡

አንዳንድ የሐሰት ዜና ማሰራጫ ድረ ገጾች ሆን ብለው የጻፉት ጽሑፍ እንዲነበብላቸው የሚረብሹ እና የሚዘገንኑ ምስሎችን ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡ ወይም ከላይ እንደተጠቀሰው አሮጌ እና እውነት ከሆነ ታሪክ ላይ ፎቶ አውጥተው በሐሰተኛ ታሪካቸው ውስጥ ይጠቀሙታል፡፡
ከተጠራጠራችሁ ምስሉን ጉግል አድርጉትና ከሌሎች ታሪኮች ጋር ግንኙነት አለው እንደሆነ አረጋግጡ፡፡

ቪዲዮዎችም ለማሳሳት ሊያገለግሉ ይችላሉ፡፡ ለዚህ ማስረጃ እንዲሆን ይህንን ሊንክ ይጫኑ (https://www.theverge.com/tldr/2018/4/17/17247334/ai-fake-news-video-barack-obama-jordan-peele-buzzfeed)፡፡ ይህ ዲፕፌክ (deepfake*) አንድ ምሳሌ ነው፡፡

ጥራቱን አረጋግጡ

ከልክ ያለፈ የቃለ አጋኖ፣ የጥያቄ ምልክት እና ሌሎች ምልክቶች ወይም ኢሞጂዎች ካያችሁ – ?!!!!!????!!??!!??! በጥንቃቄ ቀጥሉ፡፡ ስመ ጥር የዜና ማሰራጫዎች ከማተማቸው እና ከማሰራጨታቸው በፊት ሁሉም ጽሁፍ በጥንቃቄ መታረሙን ያረጋግጣሉ፡፡ ለቪዲዮዎችም ተመሳሳይ ነው – ምስሉ መነካካቱን የሚያሳዩ ምልክቶችን ፈልጉ፡፡

ርዕሱ እና ታሪኩ አንድ መሆናቸውን አረጋግጡ

የሐሰት ዜናዎች ርዕስ ትኩረት ለመሳብ እና ስሜት ለመኮርኮር በጣም ትልቅ ሆኖ ይጻፋል፡፡ ጠለቅ ብላችሁ ስታነቡ ወይም ሊንኩን ስትጫኑ፣ ወይም ቪዲዮውን በጥንቃቄ ስመለከቱ ግን ታሪኩ ከርዕሱ ጋር እንደማይገናኝ ታውቃላችሁ፡፡

ሁል ጊዜ የታሪኩን ዋና ክፍል በጥንቃቄ አንብቡ – ርዕሱና መግቢያ አንቀጹ መስማማታቸውን ብቻ አትዩ፡፡ አለበለዚያ ከርዕሱ ውጭ የሆነ ታሪክ ልትወስዱ ትችላላችሁ፡፡

የሐሰት ዜናዎች ብዙ ጊዜ የተለያዬ የኋላ ታሪክ ወይም የሃሳብ ልዩነት ያላቸውን ሁለት ቡድኖችን የበለጠ ለማለያየት ይፈጠራሉ፡፡ አንድ ርእስ መስመር ለቆ ጠብ አጫሪ ከሆነ እና ቁጣ ወይም ፍርሃት ለመቀስቀስ ከተጻፈ ታሪኩ ውሸት ለመሆኑ ከፍተኛ አመላካች ነው፡፡

የተፈጥሮ ዕውቀታችሁን ተጠቀሙ

አንድ ታሪክ ስታዩት በጣም የተጋነነ ወይም የማይታመን ከመሰላችሁ — ስሜታችሁ ልክ ሊሆን ይችላል!

የሐሰት ዜና የሚዘጋጀው አስተሳሰባችሁን ለመለወጥ፣ ስለ አንድ ነገር ወይም ሰው ጠንካራ ስሜት እንዲኖራችሁ ለማድረግ፣ ፍርሃት አና አድልኦን ለመቆስቀስ እና አስተሳሰባችሁን ከሆነ አመለካከት ጋር ለማመሳሰል ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ አንድ ታሪክ እናንተ ያላችሁን አመለካከት ስለሚያጠናክር እና በጣም ቀና መስሎ ስለሚታያችሁ አውነት ሳይሆን እውነት እንዲሆን ልትፈልጉ ትችላላችሁ፡፡ አስታውሱ፡- አንድ ታሪክ ኢንተርኔት ላይ ስለተገኘ፣ በራዲዮ ወይም በቴሌቪዝን ስለተላለፈ ወይም በጋዜጣ ስለታተመ ወይም የምታምኗቸው ጓደኞቻችሁ ስላካፈሏችሁ እውነት ነው ማለት አይደለም፡፡

ይህንንም አስታውሱ፡- አንድ ታሪክ እናንተ ካላችሁ አስተሳሰብ ጋር ስለተጣጣመ እውነት ነው ማለት አይደለም፡፡ እንደነዚህ አይነት ታሪኮች ላይ የበለጠ መጠንቀቅ አለባችሁ!

2) የችግሩ አካል አትሁኑ

የአንድን ታሪክ እውነተኛነት እና የመረጃ ትክክለኛነት ጊዜ ሰጥቶ ማረገገጥ ጥሩ ነው፡፡ የምታሰራጩት የሐሰት ዜና ሰዎችን ወይም የተፈጥሮ አካባቢን ሊጎዳ እንደሚችል ልብ በሉ፡፡ የእናንተን እና የምትሠሩበትን የራዲዮ ጣቢያ ተአማኒነትም ሎጎዳ ይችላል፡፡ አሉባልታን ማሰራጭት እና ሰዎች እውነት ያልሆነን ነገር እንዲያምኑ አስተዋጽኦ ማድረግ አትፈልጉም፡፡

ዜና ስትዘግቡ ሁል ጊዜ በመረጃ ተደግፋችሁ እና በስነ ምግባር መሆን አለበት፡፡ (የፋርም ራዲዮን ስታንዳርድ እዚህ ማየት ትችላላችሁ፡፡) የሚከተሉትን መመርያዎች ለመጠበቅ ሞክሩ፡-

  • እውነቱን አጣርታችሁ በሚዛናዊነት ዘግቡ
  • ተጠያቂነትና ግልጽነት ይኑራችሁ፡፡ ለምሳሌ ስትሳሳቱ ስህተታችሁን አምናችሁ እና ይቅርታ ጠይቃችሁ ማስተካከያ ዜና ስሩ፤ የሜዲያው ባለቤት ማን እንደሆነ፣ የሜዲያውና የባለቤቱ የፖለቲካ ግንኙነት ምን እንደሆነ በግልጽ አስቀምጡ፡፡ የኒዉ ዮርክ ጋዜጣን የይቅርታ ቅጽ እዚህ (https://www.nytimes.com/2004/05/26/world/from-the-editors-the-times-and-iraq.html)፣ የዩጋንዳውን ዴይሊ ኔሽን ጋዜጣ የይቅርታ ቅጽ ደግሞ እዚህ (https://www.newvision.co.ug/news/1505149/apology-readers) ተመልከቱ፡፡
  • ጉዳትን ቀንሱ፤ ሁሉንም ሰዎች በእኩል አክብሮት ተመልከቱ፡፡
  • መረጃዎቹን ወይም የታሪኩን አውድ አታጣሙ ወይም አታጋኑ፡፡
  • ሁል ጊዜ የተለያዩ ምንጮችን አነጻጽሩ፣ ስማቸው የማይጠቀሱ ምንጮችን አትመኑ፡፡

ድምጻችሁን አሰሙ!

የሜዲያ ፕሮግራሙ አዘጋጆች እና ተከታታዮቻቸው የሀሰት ዜናን የመዋጋት ሃላፊነት አለባቸው፡፡ የሐሰት ዜና ወይም አጠራጣሪ ይዘት ብታዩ ባቅማችሁ ያለውን እርምጃ ሁሉ ውሰዱ – ፕሮግራሙን በራዲዮም ሆነ በሌላ በማንኛውም መንገድ እንዳይሰራጭ አድርጉ፡፡ መረጃውን ካካፈላችሁ ሰው ጋር ተገናኝታችሁ መረጃው ለምን የሚታመን እንዳልመሰላችሁ ተነጋገሩ፡፡ ይህ አይነት እርምጃ ሌሎች ሰዎች የሐሰት ዜና ወጥመድ ውስጥ እንዳይወድቁ ሊረዳቸው ይችላል፡፡

3) የእውነት አስፈላጊነት

በልጅነታችን እውነትን መናገር መልካም አንደሆነ እንማራለን፡፡ እውነት ለጋዜጠኞች በጣም አስፈላጊ የሆነ ጽንሰ ሃሳብ ነው፡፡ የጋዜጠኞች የሙያ ማሕበራት እውነትን ጠብቀው ለመሥራት የሚረዷቸው የስነ ምግባር መመርያዎች አሏቸው፡፡ እነዚህ መመርያዎች ተኣማኒነትን እና አክብሮትን ለማግኘት ያስችሏችኋል፡፡

ሁሉም ሰው የራሱ ሃሳብ ሊኖረው እና የሕዝብ ውይይቶች ላይ አስተዋጽኦ የማበርከት መብት ቢኖረውም እንኳን ጋዜጠኞች ግን የሐሰት ዜናን እና ተቀባይነት ያለውን ዜና የመለየት ክሂሎት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በተጨማሪም ጋዜጠኞች ለተለያዩ ሃሳቦች እና ቡድኖች ምን ያህል የአየር ሰዓት መስጠት እንዳለባቸውም መወሰን መቻል አለባቸው፡፡ ለምሳሌ ሁሉም ሰው የራሱ ሃሳብ እንዲኖረው መብት ቢኖረውም እንደ አየር ንብረት ለውጥ ባሉ ሳይንሳዊ ጉዳዮች ግን የአየር ንብረት ሳይንቲስቶቸ አስተያየት ሳይንቲስት ካልሆኑት ሰዎች አስተያየት ይበልጣል፤ ጣቢያችሁም ያንን ማንጸባረቅ አለበት፡፡ ይህን ካላደረጋችሁ ጣቢያችሁ የሰውን ጤና እና የተፈጥሮ አካባቢን ሊጎዳ የሚችል የተሳሳተ ሃሳብ ሊያስተላለፍ ይችላል፡፡

ሕዝቡ በመንደሩ፣ በከተማው፣ በክልሉ ምን እየተካሄድ እንደሆነ ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት እንደናንተ አይነት ጋዜጠኞችን ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ ከመዘገባችሁ በፊት ጊዜ ሰጥታችሁ ትክክለኛ መረጃ የማሰባሰብ ሃላፊነት አለባችሁ፡፡ ይህን ካላደረጋችሁ አድማጮቻችሁ ስለ አካባቢያቸው በቂ መረጃ ወደማይሰጡ እና አስተማማኝነታቸው ዝቅ ወዳለ ሌሎች ምንጮች ይሄዱና ለአሳሳች መረጃዎች ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡

በሜዲያ እምነት ማጣት ለሕዝብ የሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችሉ ሕዝባዊ ውይይቶችን ሊያዳክም ይችላል፡፡ የሐሰት ዜናን እንዴት መለየት እንደሚቻል ማወቅ እና ምን ማድረግ እንደምትችሉ ማወቅ በትጋት ነቅቶ መመልከትን ይፈልጋል፣ የልፋቱን ያህል ግን ጠቃሚ ነው፡፡ ለራዲዮ ጋዜጠኞች ታማኝነት እና ትክለኛነት የሙያ መሣርያዎቻችሁ ናቸው፡፡

ስለ ሐሰተና ዜናዎች ተጨማሪ መረጃ የት ማግኘት እችላለሁ?

 

  1. Arc du Canada (Alliance des radios communitaires), 2018. Fausses nouvelles : 5 questions à vous poser pour éviter d’en partager. https://radiorfa.com/index.php/fausses-nouvelles-5-questions-pour-eviter-partager/
  2. BBC Newsround, undated. Fake News: What is it? And how to spot it. https://www.bbc.co.uk/newsround/38906931
  3. Bellemare, Andrea, 2019. The real ‘fake news’: how to spot misinformation and disinformation online. Canadian Broadcasting Corporation. https://www.cbc.ca/news/technology/fake-news-misinformation-online-1.5196865
  4. Bellemare, Andrea, 2019. So, you think you’ve spotted some ‘fake news’ — now what? Canadian Broadcasting Corporation. https://www.cbc.ca/news/technology/fake-news-disinformation-propaganda-internet-1.5196964
  5. Berdik, Chris, 2016. How to Teach High-School Students to Spot Fake News. https://slate.com/technology/2016/12/media-literacy-courses-help-high-school-students-spot-fake-news.html
  6. British Council, undated. How to Spot Fake News. https://learnenglish.britishcouncil.org/intermediate-b1-reading/how-to-spot-fake-news
  7. Charlton, Emma, World Economic Forum, 2019. Fake News: What it is, and how to spot it. https://www.weforum.org/agenda/2019/03/fake-news-what-it-is-and-how-to-spot-it/
  8. EAVI, undated. Infographic: Beyond Fake News – 10 Types of Misleading News – Sixteen Languages. https://eavi.eu/beyond-fake-news-10-types-misleading-info/
  9. Mackintosh, E., 2019. Finland is winning the war on fake news. What it’s learned may be crucial to Western democracy. CNN (Cable News Network). https://edition.cnn.com/interactive/2019/05/europe/finland-fake-news-intl/
  10. McGonagle, Tarlach, NQHR, 2017. Fake News: False Fears or Real Concerns? https://journals.sagepub.com/doi/pdf/10.1177/0924051917738685
  11. McManus, Melanie Radzicki, How Stuff Works, undated. 10 Ways to Spot a Fake News Story. https://history.howstuffworks.com/history-vs-myth/10-ways-to-spot-fake-news-story.htm
  12. Mind Tools, undated. How to Spot Real and Fake News. https://www.mindtools.com/pages/article/fake-news.htm
  13. Nagler, Christina, Harvard University, undated. 4 Tips for Spotting a Fake News Story. https://www.summer.harvard.edu/inside-summer/4-tips-spotting-fake-news-story
  14. National Observer, undated. How to spot fake news. https://www.nationalobserver.com/spot-fake-news
  15. Posetti, J. and Matthews, A., 2020. #CoveringCOVID: Six Recommendations for Disinformation Combat. ICFJ (International Center for Journalists). https://www.icfj.org/news/coveringcovid-six-recommendations-disinformation-combat
  16. Selini, Alberto, 2019. Pour répondre à la désinformation, il faut d’abord se poser les bonnes questions. EJO (European Journalism Observatory). https://fr.ejo.ch/deontologie-qualite/pour-repondre-desinformation-se-poser-les-bonnes-questions-fake-news-ethique-disinformation
  17. Society of Professional Journalists, 2014. SPJ Code of Ethics. https://www.spj.org/ethicscode.asp
  18. Waugh, Rob, The Telegraph, 2019. 10 Tips on How to Spot Fake News. https://www.telegraph.co.uk/technology/information-age/how-to-spot-fake-news/
  19. White, Aidan, undated. Fake News: Facebook and Matters of Fact in the Post-Truth Era. https://ethicaljournalismnetwork.org/resources/publications/ethics-in-the-news/fake-news

Audio

Africa Check. Audio and podcasts (from African radio stations and mostly on COVID-19). https://africacheck.org/spot-check/audio-and-podcasts/

የቃላት ፍቺ

 
Blogger/ ጦማሪ:- ኢንተርኔት ላይ ብሎግ/ጦማር የሚጽፍ ሰው (የአንድ ሰው ሃሳቦች፣ አስተያየቶች ወይም ተሞክሮዎች ሌሎች ሰዎች እንዲያነቧቸው ኢንተርኔት ላይ በመደበኛነት ሲወጡ)

Bot/ቦት:- በይነመረብ ላይ ያለ እራሱን ችሎ የሚንቀሳቀስ እና ከኮምፒዩተር ስርዓቶች ወይም ተጠቃሚዎች ጋር ግንኙነት የሚችል የኮምፒዩተር ፕሮግራም

Clickbait/ክሊክቤይት:- (ኢንተርኔት ላይ) ዋና አላማው ትኩረት መሳብ እና ጎብኝዎች ሊንኮችን በመጫን ወደ ዌብ ሳይት እንዲገቡ ማድረግ የሆነ ይዘት

Deepfake/ዲፕፌክ:- ዲፕፌክ (“deep learning/በጥልቀት መማር” እና “fake/የተጭበረበረ” ከሚሉት ቃላት ውህደት የተፈጠረ) መለት በአንድ ምስል ወይም ቪዲዮ ውስጥ ያለ ሰው በሌላ ሰው መልክ የተቀየረባቸው የሜዲያ ውጤቶች

Disinformation/የመረጃ ማወናበድ:- የሕዝብ አስተያየት ላይ ተጽእኖ ለመፍጠር ወይም እውነትን ለማድበስበስ ሆን ብሎና ሕቡዕ በሆነ መንገድ (ለምሳሌ አሉባታ በማስጀመር) የሚሰራጭ የሐሰት መረጃ

GIF/ጂአይኤፍ:- በዌብ ብራውዘር ወይም ሌላ ሶፍትዌር አማካኝነት ተንቀሳቃሽ ስዕል የሚፈጥር ግራፊክስ ኢንተርቼንጅ ፎርማት በመጠቀም አንድ ላይ የተወሃዱ የአንድ ምስል በርካታ ፍሬሞች

Going viral/እንደ ሰደድ መሰራጨት:- አንድ ጽሁፍ፣ ቪዶዮ ወይም ምስል በማሕበራዊ ሜዲያ ወይም ኢሜይል አማካኘት በኢንተርኔት ላይ በፍጥነት እና በስፋት ሲሰራጭ

Infographics/ኢንፎግራፊክስ:- ቻርት ወይም ዲያግራም በመጠቀም መረጃ ወይም ዳታ የሚቀርበት ምስል

Meme/ሚም:- በዘር ከመውረስ ውች ባሉ መንገዶች በዋናነት አስመስሎ በመሥራት ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው ሊተላለፍ ይችላል ተብሎ የሚቆጠር የባህል ወይም የባሕሪ ክፍል

Opinion piece/የአስተያየት ጽሑፍ:- አንድ ሰው በአንድ ጉዳይ ወይም በዜና በሰማው እና በተለይም አነጋጋሪ በሆነ ርዕሰ ጊዳይ ላይ የራሱን አስተያየት የሚያሰፍርበት ጽሑፍ

Photoshop/ፎቶሾፕ:- በአዶቤ ኮርፖሬሽን የተመረት ምስሎችን በኮምፒዩተር ለመቀየር የሚያስችል የአርትኦት ሶፍትዌር፡፡

Shock value/አስደንጋጭ እሴት:- አንድ ምስል፣ ቪዶዮ ወይም ጽሑፍ ከፍተኛ መጸየፍ፣ ድንጋጤ፣ ንዴት፣ ፍርሃት ወይም ተመሳሳይ ስሜቶችን ሲፈጥር

URL: Uniform Resource Locator – በይነ ኮምፒዩተር ላይ ያለበትን ቦታ የሚያመለክት የድረ ገጽ አድራሻ በሚለው ስሙ ይበልጥ ይታወቃል

Yellow journalism/የሎው (ቢጫ) ጋዜጠኝነት:- በስሜት ቀስቃሽነት እና ደስ በማይል ማጋነን ላይ የተመሠረተ ጋዜጠኝነት

Acknowledgements

ምስጋና
የጽሑፉ አዘጋጅ፡- አንዲ ኤቨረት የኸርት ኤፍአም ምክትል ማናጂንግ ኤዲተት፣ ዩኬ፤ ሲልቪ ሃሪሰን በፋርም ራዲዮ ኢንተርናሽናል የራዲዮ ክራፍት ሥራ አስኪያጅ፤ እና ቪጃይ ከደፎርድ፣ ፋርም ራዲዮ ኢንተርናሽናል ማኔጂንግ ኤዲተር

ይህ ጽሑፍ ከካናዳ መንግስት በግሎባል አፌይርስ ካናዳ በኩል በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ተዘጋጀ፡፡