ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ለመለማመድ የሚያስፈልጉ የአርሶ አደር ስትራቴጂዎች

Notes to broadcasters

Save and edit this resource as a Word document

Download the Tigragna version of this script .

Download the Oromifa version of this script.

ማስታዎሻ ለአሰራጩ
ኢትዮጵያን ጨምሮ ለአፍሪካ ሃገሮች ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር መለማመድ ትልቅ ተግዳሮት ነው፡፡ እንደሌሎች ሃገሮች ሁሉ ኢትዮጵያም  ከአየር ንብረትለውጥ ጋር ለመለማመድ የሚጠቅሙ ዕቅዶችን እያወጣችና እየተገበረች ትገኛለች፡፡ ነገር ግን ውጤታማ የመለማመድ ፖሊሲዎችን ለማውጣት ኢትየጵያ የአየር ንብረቷ እንዴት እንደሚለወጥና ምን ምን ስጋቶችን እንደሚያስከትል የሚያስረዳ የተሻለ መረጃ ያስፈልጋታል፡፡ በአሁኑ ሰዓት አርሶ አደሮች ከሚያጋጥማቸው የአየር ንብረት ለውጥ ጋር ለመለማመድ እንዲችሉ ምን ማድረግ እንዳለባቸው የሚያስረዳ መመርያ ብዙም የለም፡፡

እነዚህን የእውቀት ክፍተቶች ለመሙላት እንዲቻል የፖትስዳም የአየር ንብረት ተጽእኖ ምርምር ተቋም የተባለ የጀርመን ድርጅት በቀጣይ በርካታ አስርት ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያ የአየር ንብረት እንዴት ሊለወጥ እንደሚችል ጥልቅ ሳይንሳዊ ጥናት አካሂዷል፡፡ ጥናቱ የአየር ንብረት እንዴት ሊለወጥ እንደሚችል እና አርሶ አደሮች ላይ ምን ዓይነት ተጽእኖ ሊኖረው እንደሚችል መረጃ ሰጥቷል፡፡

የአትዮጵያ የአየር ንብረት እንዴት ሊቀየር እንደሚችል ከማጥናት በተጨማሪ ወደ ፊት ከሚፈጠሩ የአየር ንብረት ለውጦች ጋር ለመለማመድ የሚያስችሉ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ሊያደርጓቸው የሚችሉ የግብርና ሥራዎችንም አጥንቷል፡፡

ይህ ስክሪፐት በሁለት የራዲዮ ፕሮግራም አቅራቢዎች መካከል የሚደረግ ልቦለዳዊ ጭውውትን ያቀርባል፡፡ ሁለተኛው አቅራቢ የፖትስዳሙን ሳይንሳዊ ጥናት ያቀርባል፡፡ የመጀመርያው አቅራቢ ጥናቱ ምን እንዳገኘ ይጠይቃል፣ ሁለተኛው ይመልሳል፡፡ ሁለቱ አቅራቢዎች ጥናቱ ስለ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ምን እንደሚተነብይ ይወያያሉ፡፡ የኢትዮጵያን አርሶ አደሮች ከአየር ንብረት ለውጡ ጋር ለመለማመድ ስለሚረዷቸው የግብርና ዘዴዎችም ገለጻ ያደርጋሉ፡፡

ስለአየር ሁኔታለውጥና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ለመለማመድ ስለሚረዱ የግብርና ዘዴዎች የራሳችሁ ፕሮግራም ለማዘጋጀትም ይህንን ስክሪፕት እንደ መነሻ ልትጠቀሙበት ትችላላችሁ፡፡ አድማጮቻችሁ የሚሰሙት መረጃ እንዲገባቸው እና እንዲጠቀሙበት አመቻችታችሁ ለማቅረብ የሚከተሉትን መንገዶች መጠቀም ትችላላችሁ፡-

  • የአየር ንብረት ወይም የግብርና ተመራማሪ በመጋበዝ ጥናቱ ስለአየር ንብረት ለውጥ ያቀረባቸውን ትንበያዎች እና በኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ላይ ስለሚኖረው ተጽእኖ መወያየት ትችላላችሁ
  • የግብርና ባለሙያ ጋብዛችሁ ሳይንሳዊው ጥናት ስለመከራቸው የግብርና ዘዴዎች እና እነዚህ ዘዴዎች ስላላቸው ጠቀሜታ እንዲያብራሩ መጋበዝ እና አርሶ አደሮች እነዚህን ዘዴዎች እንዴት መተግበር እንደሚችሉ ጥያቄዎችን እንዲመልሱ ማድረግ ትችላላችሁ

ይህ ስክሪፕት መግቢያና መውጫ ሙዚቃዎችን ጨምሮ 20 ደቂቃ ይወስዳል፡፡

Script

አቅራቢ 1:
እንደምን አደራችሁ አድማጮቻችን

አቅራቢ 2:
አዎ ሁላችሁም እንደምን አደራችሁ፡፤ ስለአየር ንብረት ለውጥ መችም ሳትሰሙ አትቀሩም፡፡

አቅራቢ 1:
(ይስቃል) እንዴት አይሰሙም፡፡ ለኢትዮጵያ አርሶ አደሮች የአየር ንብረት ለውጥ እለታዊ ሃቅ ነው፡፡ ያለተጠበቁ ዝናባማና ደረቅ ወቅቶች እንዲሁም ጎርፍ እና ድርቅ ደጋግመው ያጋጥሟቸዋል፡፡

አቅራቢ 2:
አዎ ትክክል ነው፡፡ ያንን ታሳቢ አድርገን የኢትዮጵያ አርሶ አደሮችን ከተለዋዋጭ የአየር ሁኔታ ጋር ለመለማመድ ስሚረዷቸው ዘዴዎች እንነጋገራለን፡፡ የፖትስዳም የአየር ንብረት ተጽእኖ ምርምር ተቋም የተባለ የጀርመን ድርጅት ሁለት ጥያቄዎችን በማንሳት ሳይንሳዊ ጥናት አካሂዷል፡፡ የመጀመርያው ጥያቄ የኢትዮጵያ የአየር ንብረት በሚቀጥሉት 30 ዓመታት እንዴት ሊለወጥ ይችላል የሚለው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ አርሶ አደሮች ቤተሰቦቻቸውን ለመደገፍ የሚስፈልጋቸውን በቂ ምግብ እና ገቢ እያገኙ ከአዳዲስ የአየር ጸባዮች ጋር ለመለማመድ የግብርና ሥራቸውን እንዴት መቀየር ይችላሉ የሚለው ነው፡፡

አቅራቢ 1:
ይሄ በጣም መጠናት ያለበት ጉዳይ ይመስላል፡፡ ወደ ጉዳዩ እንግባ፡፡ ባለሙያዎቹ የኣየር ሁኔታው እንዴት ሊለወጥ እንደሚችል ተመልክተውታል ብለሃል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ በሚቀትሉት 30 ኣመታት የኢትዮጵያን የአየር ሁኔታ እንዴት ሊለውጠው ይችላል?

አቅራቢ 2:
የተለያዩ ለውጦች ይኖራሉ፤ የሙቀት፣ የውሃ መጥን እና የዝናብ ስርጭት ለውጦች ይኖራሉ፤ እንደ ጎርፍ የመሳሰሉ የአየር ሁኔታ ክስተቶች ይኖራሉ፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ ምርታማነትም ላይ ለውት ያመጣል፡፡ የተለያዩ አካባቢዎች ለተለያዩ ሰብሎች ያላቸውን ተስማሚነትም ይቀይራል፡፡

አቅራቢ 1:
በጣም ብዙ ለውጥ ነው፡፡ እስኪ ከሙቀት እንጀምር፡፡ በሚቀጥሉት 30 ዓመታት የኢትዮጵያ የአየር ሙቀት ምን ያህል ይለወጣል?

አቅራቢ 2:
የአየር ንብረት ተመራማሪዎች በ2040 ዓ.ም. የኢትዮጵያ የአየር ሙቀት በአንድ ዲግሪ እንደሚጨምር ይተነብያሉ፡፡ የሞቃት ቀኖች እና ሌሊቶችም ቁጥር ይጨምራል ይላሉ፡፡

አቅራቢ 1:
አንድ ዲግሪ ብዙም አይመስልም፡፡ ሙቀት በአንድ ዲግሪ ቢጨምር ብዙ ሰው የሚሰማው አይመስለኝም፡፡ በአርሶ አደሮች ላይ ብዙ ለውጥ ያመጣል?

አቅራቢ 2:
የአንድ ዲግሪ ለውጥ በሚገርም ሁኔታ በጣም ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል፡፡ ለምሳሌ ሙቀት በአንድ ዲግሪ ቢጨምር የብዙ ሰብሎች ምርት ይቀንሳል፡፡ ነገር ግን የተለያዩ ሰብሎች የተለያዩ ለውጦችን ያሳያሉ፡፡

አቅራቢ1:
ውነትም ይገርማል፡፡

ስለዚህ በ2040 ዓ.ም. የአየር ሁኔታው ይበልጥ ሞቃት ይሆናል፤ ሞቃት የሆኑ ቀኖች እና ሌሊቶች ቁጥር ይጨምራል እያልከኝ ነው፡፡ ስለ ውሃ መጠንም ጠቀስ አድርገሃል፡፡ ይሄ ለአርሶ አደሮች አሳሳቢ ሁኔታ ይመስለኛል፡፡ የውሃ መጠን በምን መልኩ ይለወጣል?

እየጣደፍን እንደሆነ ይሰማኛል ግን ብዙ መሸፈን ያለብን መረጃ አለ፡፡

አቅራቢ2:
የአባይ እና ሌሎች ዋና ዋና ወንዞች ፍሰት ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል፤ ይህም ረጃጅም የዝናብ ወቅቶች እንደሚኖሩ ያሳያል፡፡

የአየር ንብረት የሰብል ምርት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እንዳለው እናውቃለን፡፡ ስለዚህ ሙቀቱ ሲጨምር እና የዝናብ ወቅቱ ረዝም ሲሆን የተለያዩ አካባቢዎች ለተለያዩ ሰብሎች ያሏቸው ተስማሚነቶች ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳድራል፡፡

ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት በቀጣይ 30 ዓመታት ብዙ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ለበቆሎ፣ ስንዴ እና ጤፍ ያላቸው ተስማሚነት ይቀንሳል፡፡ አንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ማሽላ ለማብቀል ተስማሚ ይሆናሉ፡፡ በተጨማሪ በሚቀጥሉት 30 ዓመታት አጠቃላይ አገራዊው የበቆሎ ምርት ሲጨምር በአንዳንድ አካባቢዎች ግን ይቀንሳል፡፡

አቅራቢ1:
የበቆሎ ምርት የሚቀንስባቸው አካባቢዎች የትኞቹ ናቸው?

አቅራቢ2:
የበቆሎ ምርት በድሬ ዳዋ፣ ጋምቤላ፣ ሶማሌ፣ ኦሮምያ አና ደቡብ ክልሎች ውስጥ በተለይም በአርብቶ አደር አካባቢዎች ይቀንሳል፡፡

አቅራቢ1:
ስለዚህ የአየር ሁኔታው ሞቃት በሆነና ዝናባማው ወቅት በረዘመ መጠን በቆሎን ጨምሮ የሰብል ምርቶች መጠን ይለወጣ

ማለት ነው፡፡ አንዳንድ ቦታወች ላይ የበቆሎ ምርት ይጨምራል አንዳንድ በታዎች ላይ ይቀንሳል ማለት ነው?

አቅራቢ2:
በትክክል፡፡

አቅራቢ1:
መልካም፡፡ ከእንደዚህ ዓይነት የአየር ንብረት ለውጦች ጋር ለመለማመድ አርሶ አደሮች ማድረግ ስለሚገባቸው ሥራዎች ያጠናውን ጥናት ጠቅሰህ ነበር፡፡ ተመራማሪዎቹ አርሶ አደሮች ለመለማመድ እና የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ የሚረዱ በግልጽ የለዩዋቸው ሥራዎች አሉ?

አቅራቢ2:
ገበሬዎች ከአዲስ ዓይነት የአየር ንብረት ጋር ለመለማመድ እንዲረዷቸው የግብርና አሠራራቸውን መቀየር የሚችሉባቸው ብዙ መንገዶች አሉ፡፡ ነገር ግን ተመራማሪዎቹ ለኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ይጠቅማሉ ያሏቸውን አራት አሠራሮች ለይተዋል፡፡ ሁለቱ የግብርና ደን ልማት እና የመኖ ማሻሻያዎች ናቸው፡፡ በተጨማሪም የመስኖ እና የተሻሻሉ የሰብል ቁጥጥር ሥራዎች ከአየር ንብረት ለውጡ ጋር ለመለማመድ ይረዳሉ፡፡ አንድ ሌላ ነጥብ ልጨምር – አርሶ አደሮች እነዚህን አሠራሮች ቀላቅለው ሲጠቀሙ የተሻለ ውጤት የማግኘት ዕድላቸው ይጨምራል፡፡

አቅራቢ1:
ለምሳሌ የግብርና ደን ልማትንና መስኖን ባንድ ላይ እንደመጠቀም ማለት ነው? ወይም የመኖ ማሻሻል እና የመስኖ ሥራዎችን አንድ ላይ ማካሄድ?

አቅራቢ2:
በትክክል፡፡

አቅራቢ1:
እሺ በግብርና ደን ልማት እንጀምር እስኪ፡፡ መጀመርያ የግብርና ደን ልማት ማለት ምን ማለት ነው?

አቅራቢ2:
የግብርና ደን ልማት በአርሶ አደሩ መሬት ላይ በእርሻ ሰብሎች እና በዛፎች መካከል ያለውን መስተጋብር ያሳያል፡፡ የኢትየጵያ አርሶ አደሮች የተለያዩ ዓይነት የግብርና ደን ልማት እንቅስቃሴዎችን ያደርጋሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተተገበሩ ያሉ ሦስት ዓይነት የግብርና ደን ልማት ሥራዎችን ልጥቀስ፡፡ የመጀመርያው አንዳንድ አርሶ አደሮች በቤታቸው ባሉ ጓሮዎች የሚተክሏቸው ዛፎች ናቸው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ አንዳንድ ገበሬዎች የተለያየ ቁመት ያላቸውን ሰብሎች ባንድ ቦታ ላይ የመትከል ልምድ አላቸው፡፡ በእንደዚ ዓይነት የግብርና አሠራር ረጃጅሞቹ ዛፎቹ ፍራፍሬ፣ ጣውላ እና የከብት መኖ ይሰጣሉ፤ የአፈርን ለምነት ያሻሽላሉ፣ ከሥራቸው ያሉትን መካከለኛ ቁመት ያላቸውን እንደ ቡና እና እንሰት ላሉ ተክሎች ጥላ ይሰጣሉ፡፡ አትክልቶች እና የተለያዩ መዳኒትነት ያላቸው ቅጠላቅጠሎች ደግሞ ከሥር ይበቅላሉ፡፡ ሦስተኛ ደግሞ አንዳንድ አርሶ አደሮች በርካታ ጥቅም ያላቸውን ዛፎች ይተክላሉ፡፡

አቅራቢ1:
በርካታ ጥቅም ያላቸው ዛፎች ምንድን ናቸው?

አቅራቢ2:
በርካታ ጥቅም ያላቸው ዛፎች ማለት የተለያዩ አገልግሎቶች ያሏቸው ዛፎች ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ አኬሻ ኒሎቲካ የተባለው የግራር ዓይነት ለማገዶ፣ ለመጠጥ ዝግጅት እና ንፋስን ለመከላከል ይጠቅማል፡፡ ሊውኪኒያ ለማገዶ፣ ለማገር እና ለከብት ምግብነት ይውላል፡፡

ሬቪሊያ ደግሞ ለጣውላ፣ ማገዶ እና የግንባታ ግብዓት ሆኖ ያገለግላል፡፡አዛዲራችታ ኢንዲካ ወይም ኒም ደግሞ ለጣውላ፣ ለማገዶ፣ ቀልዝ ለመሥራት፣ መዳኒትነት ያላቸው ዘይቶች እና ተባይ ማጥፊያ ለመሥራት ያገለግላል፡፡ እነዚህ እንግዲህ አሁን በኢትዮጵያው ውስጥ እየተሠራባቸው ያሉ የግብርና ደን ልማት ሥራዎች ናቸው – ማለትም ዛፍ የተተከለባቸው የጓሮ አትክልት ቦታዎች፣የተለያየ ቁመት ያላቸውን ሰብሎች ባንድ ቦታ ላይ መትከል እና የተለያዩ ጥቅሞች ያሏቸውን ዛፎች በአርሶ አደሩ መሬት ላይ መትከል ናቸው፡፡

አቅራቢ1:
እንደነዚህ ያሉ የግብርና አሠራሮችን እኔም ሰምቼ አውቃለሁ፡፡ ጥቅማቸው ግን ምንድን ነው? የግብርና ደን ልማት ሥራ አርሶ አደሮችን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ለመለማመድ እና የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ በምን መልኩ ይጠቅማቸዋል?

አቅራቢ2:
በብዙ መልኩ፡፡ ዛፎች ለሰብሎች ጥላ ይሰጣሉ፣ ይሄ ጥላ ደግሞ የአፈሩን ሙቀት በመቀነስ እርጥበት ይዞ እንዲቆይ ይረዳዋል፡፡ በተጨማሪ የዛፎቹ ቅጥል ሲወድቅ ብስባሽ በመፍጠር እና የናይትሮጅን ምንጭም በመሆን የአፈርን ለምነት ይጠብቃል፡፡ በናይትሮጅን የበለጸጉ ዛፎች ለምሳሌ ካሊያንድራ እና ሴስባን ለዚህ ይጠቅማሉ፡፡ ዛፎች በተጨማሪ ተባይን እና የበሽታ ችግሮችን ለመቀነስ ይረዳሉ፡፡ ዛፎች አፈር ባለበት እንዲቆይ በማድረግ የአፈር መሸርሸርን ይቀንሳሉ፤ ተዳፋት መሬት ላይ ለሚያርሱ አርሶ አደሮች ይህ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ እንደዚህ በመሳሰሉ መንገዶች በሌሎችም ዛፎች አርሶ አደሮችን በሙቀት መጨመር እና ባልተጠበቀ ዝናብ ከሚመጡ ስጋቶች ይከላከሏቸዋል፡፡

አቅራቢ1:
ግን ዛፎች ጥላ ሲጥሉበት የበቆሎ ምርት አይቀንስም?

አቅራቢ2:
ይሄ እንግዲህ እንደ አካባቢው ይለያያል፡፡ በድሬ ዳዋ፣ ጋምቤላ፣ ሶማሊ፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎች ከአየር ንብረት ለውጡ ጋር ተያይዞ በ2040 አካባቢ የበቆሎ ምርት ይቀንሳል፡፡ በነዚህ አካባቢዎች የዛፎቹ ጥላ ምርት እንዳይቀንስ ይረዳቸዋል፡፡ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የበቆሎ ምርት የማይቀንስባቸው አካባቢዎች ግን ልክ ነህ የዛፎቹ ጥላ መኖር ብዙም ላይጠቅም ይችላል፡፡

አቅራቢ1:
አንድ አርሶ አደር የግብርና ደን ልማትን ከአየርንብረት ለውጥ ጋር ለመለማመድ እንዴት መጠቀም እንደሚችል ተግባራዊ ምሳሌ ስጠኝ እስኪ?

አቅራቢ2:
አንድ አርሶ አደር ሁለት ቀርጥ በቆሎ ዝርቷል እንበል፡፡ ይሄ አርሶ አደር እርሻው ውስጥ የማንጎ ዛፎች ቢተክል ዛፎቹ የተለያየ ጥቅም ስላላቸው የበቆሎ ምርቱ እንዲጨምር ይረዳዋል፡፡ በተጨማሪም አርሶ አደሩ ማንጎውን መመገብ እና መሸጥ ይችላል፤ ይህን ማድረጉ የቤተሰቡ አመጋገብ እንዲሻሻል እና የገቢ ምንጩንና የገቢውን መጠን እንዲያሳድግ ይረዳዋል፡፡

አቅራቢ1:
ግን እኮ የማንጎ ችግኞቹን ለመግዛት ወጭ ያወጣል፡፡ ማንጎውን የሚተክልበት ቦታ ላይም በቆሎ አይዘራም፡፡ ይሄ ችግር የለውም?

አቅራቢ2:
የመጀመርያዎቹ ጥቂት አመታት ላይ በርግጥ በነዚህ ወጭዎች ምክንያት የአርሶ አደሩ ገቢ ሊቀንስ ይችላል፡፡ ነገር ግን ሦስትና አራት አመት ካለፈ በኋላ የበቆሎው እርሻ ላይ ማንጎ የዘራው አርሶ አደር ገቢ ካልዘሩት ይልቅ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ይሄዳል፡፡

አቅራቢ1:
እሺ ስለ ግብርና ደን ልማት ተነጋግረናል፡፡ የተሻሻለ የእንስሳት መኖ እና ምግብም በቀጣይ 30 ዓመታት አርሶ አደሮች ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር እንዲለማመዱ ይረዳቸዋል ብለህ ነበር፡፡ የእንስሳት መኖ እና ምግብ ላይ ምን መሻሻል አለበት ነው የምትለው?

አቅራቢ2:
ለምሳሌየእንስሳት መኖ እና ምግብ የንጥረ ነገር ይዘትን ማሻሻል፣ በቀላሉ ሆድ ውስጥ የሚፈጭ ማድረግ እና የአቅርቦቱንም መጠን ማሳደግ ሊሆን ይችላል፡፡

አቅራቢ1:
እስኪ ተግባራዊ ምሳሌዎችን ስጠኝ፡፡

አቅራቢ2:
ኢትዮጵያ ውስጥ ተሞክረው የተሳኩ አሠራሮች አሉ፡፡ አንዳንድ አርሶ አደሮች ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የተሻሻሉ የመኖ እጽዋት ዝርያዎችን ተክለዋል፡፡ እነዚህም የናፒየር ሳር (ሙጃ)፣ ደሾ፣ አጃ እና የሮድስ ሳርን ይጨምራሉ፡፡ ሌሎች አርሶ አደሮች ደግሞ ከጥራጥሬ ሰብሎቻቸው ጋር ዴስሞዲየመ፣ አልፋልፋ፣ አደንጇሬ ወይም ጓያ የመሳሰሉ እጽዋትን ዘርተዋል፡፡ በመስኖም መኖ እያለሙ ያሉ አሉ፣ አረሙን ነቅለው እያስወገዱ የተፈጥሮ ግጦሽ ቦታዎች እንዲለመልሙ ያደረጉ አሉ፡፡ በእንደዚህ ዓይነት መንገዶች የእንስሳት መኖ እና ምግብን በማሻሻል አርሶ አደሮች የቁም ከብት ምርታቸውን እና ከዚያ የሚያገኙትን ገቢ በማሻሻል ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር መለማድ ይችላሉ፡፡

አቅራቢ1:
በዚህ መስክ ተስፋ ሰጭ የሆኑ አሠራሮች ይኖራሉ?

አቅራቢ2:
አንድ ተስፋ ሰጭ እና አዋጭ የሆነ ሥራ ሙጃ (የናፒየር ሳር) መትከል ነው፡፡ ይሄ ሳር ብዙ ውሃ ስለሚፈልግ በመስኖ መልማት አለበት፡፡ አማራ ክልል ውስጥ በተደረገ ሙከራ ሙጃ በመስኖ ማልማት የወተት ምርትን በእጥፍ እንዲያድግና የአርሶ አደሩ ገቢ እንዲጨምር አድርጓል፡፡

አቅራቢ1:
የወተት ምርትን በእጥፍ ጨመረ? እንዴት አድርጎ ባክህ?

አቅራቢ2:
ለእንስሳት የሚቀርበውን ምግብ መጠንና ጥራት ስለሚጨምር ወተቱም አብሮ ይጨምራል፡፡ ገበሬዎች መጀመርያ ላይ ሙጃ ለማልማት ወጭ ይኖርባቸዋል፡፡ ከሁለት እና ከሦስት አመታት በኋላ ግን ወጫቸውን መልሰው ያገኛሉ፡፡

አቅራቢ1:
በዚህ ሂደት የሚያጋጥሙ አስቸጋሪ ነገሮች ይኖራሉ?

አቅራቢ2:
ይህ አሠራር በተለይ አርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር በሆኑ ቆላማ አካባቢዎች ማስለመድ ይቀላል፡፡

በተጨማሪም የተሻሻሉ የግብርና አሠራሮችን የሚጀምሩ አርሶአደሮች አንዳንድ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል፡፡ ለምሳሌ ገንዘብ ላያገኙ ይችላሉ፣ ገበያም በቅርባቸው ላያገኙ ይችላሉ፡፡ ስልጠናና መረጃም የማግኘት ችግር ሊኖርባቸው ይችላል፡፡

አቅራቢ1:
እሺ በተወሰነ ደረጃ እንግዲህ ስለ ግብርና ደን ልማት እና ስለ እንስሳት መኖ እና ምግብ ተነጋረናል፡፡ ተመራማሪዎቹ በቀጣይ 30 ዓመታት የኢትዮጵያ አርሶ አደሮችን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ለመለማመድ ይረዳሉ ያሏቸው ሁለት ዓይነት የግብርና አሠራሮች እነዚህ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ከነዚህ ጋር ተቀላቅለው ሲተገበሩ ተስፋ ሰጭ የሆኑ ሌሎችም ዓይነት የግብርና አሰራሮች አሉ ብለህ ነበር፡፡ እስኪ ስለነዚህ ጥቂት ንገረኝ፡፡

አቅራቢ2:
እነዚህ ሥራዎች መስኖ እና የተሻሻለ የሰብል ቅጥጥር ናቸው፡፡ በመስኖ እንጀምር፡፡ መስኖ መጠቀም ከከፍተኛ ሙቀት እና ወቅቱን ካልጠበቀ እና ዝቅተኛ ከሆነ የዝናብ መጠን ጋር ለመለማመድ ይረዳል፡፡ በደረቅ ወቅት እንዲያለሙ ያስችላቸዋል፣ በዝናብ ወቅትም ላይ ሳይዘንብ በሚቀርባቸው ጊዜያት ተጨማሪ ውሃ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል፡፡ በደረቅ ወቅት በመስኖ የሚለሙ ሰብሎች ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት ይረዳሉ፡፡ መስኖ በተጨማሪ አርሶ አደሮች ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው የፍራፍሬ እና የመስኖ ሰብሎችን እንዲያለሙ ያስችላቸዋል፡፡

አቅራቢ1:
ኢትዮጵያ ውስጥ መስኖ ሁሉም ቦታ ላይ መጠቀም ይቻላል?

አቅራቢ2:
የመስኖ ስርዓትን ለመዘርጋት የሚያስፈልገው ወጭ ከባድ ካ

ሆነ እና በቂ የውሃ አቅርቦት ካለ ተመራማሪዎቹ መስኖ ጠቃሚ ሥራ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በሚሊዮን ሄክታር የሚቀጠር መሬት ለማልማት የሚያስችል በቂ ውሃ አለ፤ ይሄንን ውሃ የውሃ መሳብያ ሞተር፣ የመሬት ስበት፣ ግፊት በመጠቀም እና የከርሰ ምድር ውሃን በማውጣት እና ውሃ በማቆር መጠቀም ይቻላል፡፡

አቅራቢ1:
እሺ የተሻሻለ የሰብል ቁጥጥርስ ምንድን ነው?

አቅራቢ2:
የተሻሻለ የሰብል ቁጥጥር ብዙ ጉዳዮችን ይሸፍናል፡፡ ከነዚህ ውስጥ የተሻለ ተስፋ ሰጭ የሆኑት የሰብል ቁጥጥር መንገዶች ምርጥ ዘር መዝራት፣ ማዳበርያ መጠቀም እና የመትከያ ቀኖችን መቀየር ናቸው፡፡ ምርጥ ዘር መዝራት ከፍ ያለ የምርት መጠን እንዲገኝና ተባይ እና የበሽታ ችግሮች እንዲቀንሱ ይረዳል፡፡ የተለያዩ ማዳበርያዎችን በመጠቀም አፈር ውስጥ ያለው ኦርጋኒክ ካርቦን መጠን እንዲጨምር ማድረግ ይቻላል፡፡ የተራቆተ አፈር ባለባቸው አካባቢዎች በአፈር ውስጥ ያለውን ኦርጋኒክ ማዳበርያ እንዲጨምር በማድረግ በቆሎ፣ ስንዴ፣ ጤፍ እና ማሽላ የመሳሰሉ ሰብሎችን ማልማት ይቻላል፡፡ አርሶ አደሮች የዘር ወቅትን በመቀየር ከተባይ እና ዘግይቶ ከሚመጣ ዝናብ የተነሳ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመቀነስ ይረዳል፤ ነገር ግን የዘር ወቅትን ለመቀየር አርሶ አደሮች የባለሙያ ምክር መከተል አለባቸው፡፡ለምሳሌ ስንዴ፣ ጤፍ፣ በቆሎ እና ማሽላን አራት ሳምንት ቀድመው ቢዘሩ ጥሩ ምርት የማግኘት እድላቸው ዝቅተኛ ይሆናል፡፡

ሌላኛው የሰብል ቁጥጥር ዘዴ እያፈራረቁ መዝራት ነው፡፡ ለምሳሌ መጀመርያ በቆሎ ከዘሩ ቀጥሎ ማሽላ መዝራት፡፡ ይሔ አሠራር ግን ውጤታማ ለመሆን ጥቂት ዓመታት ሊወስድ ይችላል፡፡

አቅራቢ1:
ብዙ ሃሳብ ነው የሰጠኸን፡፡ ለማጠቃለል ግን መጀመርያ በቀጣይ 30 ዓመታት እስከ 2040 ድረስ በኢትዮጵያ ስለሚኖረው የአየር ንብረት ለውጥ፤ ሙቀት እንደሚጨምርና የዝናባማው ወቅት እንደሚረዝም እና ከዚህ የሙቀት እና ዝናብ ለውጥ ጋር ለመለማመድ አርሶ አደሮች ምን ማድረግ እንደሚችሉም ነገረኸናል፡፡ የግብርና ደን ልማት እና የተሻሻለ የእንስሳት መኖ እና ምግብ ዝግጅት ተስፋ ሰጭ አሠራሮች እንደሆኑም አጫውተኸናል፡፡ ከነዚህ አሠራሮችም ጋር በማዳበል መስኖ እና የተሻሻለ የሰብል ቁጥጥር ሥራዎች መሥራት እንደሚቻልም ነግረኸናል፡፡ ልክ ነኝ?

አቅራቢ2:
አዎ፣ የፖትስዳም የአየር ንብረት ተጽእኖ ምርምር ተቋም ተመራማሪዎች ድምዳሜ ይህንን ይመስላል፡፡ የሚጠበቁት ለውጦች እና ለውጦችን ተከትለው አርሶ አደሮች መልመድ የሚገቧቸው አሠራሮች እነዚህ ናቸው፡፡

በእርግጥ አርሶ አደሮች ሁል ጊዜ ዛፎች ለመትከል፣ የእንስሳት መኖ ለማሻሻል፣ በመስኖ ለማልማት ወይም የሚዘሩትን ሰብል ለመቀየር ቢፈልጉ በአካባያቸው እና በክልል ያሉ የግብርና በላሙያዎችን ቢያማክሩ የተሻለ ነው፡፡ ትክክለኛው ምክር አርሶ አደሮች እንደሚኖሩበት ቦታ እና እንዳሉበት ሁኔታ ይለያያል፡፡

ቢሆንም ግን አርሶ አደሮች የትም ቢኖሩ እነዚህን ምክሮች እንዲያስቡባቸው ይመከራሉ፡፡

አቅራቢ1:
ለዛሬ ቆይታችን በጣም እናመሰግናለን፡፡ በቀጣይ ሳምንት በ [የፕሮግራሙ ስም] ሌሎች ዝግጅቶችን ይዘን እንመለሳለን፡፡

አቅራቢ2:
እስከሚቀጥለው ሳምንት ድረስ ደና ሁኑ፡፡

 

Acknowledgements

Contributed by: Vijay Cuddeford, Managing editor, Farm Radio International

Reviewed by: Dr. Christoph Gornott, Head of working group “Adaptation in Agricultural Systems” at the Potsdam Institute for Climate Impact Research (PIK), and Lisa Murken,

Research Analyst in the working group “Adaptation in Agricultural Systems” at PIK.

Information sources

Murken, L., Cartsburg, M., Chemura, A., Didovets, I., Gleixner, S., Koch, H., Lehmann, J., Liersch, S., Lüttringhaus, S., Rivas-Lopez, M., Roehrig, F., Schauberger, B., Shukla, R., Tomalka, J., Yalew, A. & Gornott, C., (2020). Climate risk analysis for identifying and weighing adaptation strategies in Ethiopia’s agricultural sector. A report prepared by the Potsdam Institute for Climate Impact Research for the Deutsche Gesellschaft für Internationale Zusammenarbeit GmbH on behalf of the German Federal Ministry for Economic Cooperation and Development, 150 pp. https://www.pik-potsdam.de/en/en/institute/departments/climate-resilience/projects/project-pages/agrica/climate-risk-analysis_ethiopia_en