ጭንቀትና ተስፋን ማመዛዘን፡- የኢትዮጵያ አርሶ አደሮችየአየር ጸባይ ለውጥ ስላሳደረባቸው ተጽእኖ ይናገራሉ

Notes to broadcasters

Save and edit this resource as a Word document.

ማስታወሻ ለአሰራጮች

የአየር ጸባይ ለውጥ ያመጣው የተዘበራረቀ የአየር ንብረት የአፍሪካ አርሶ አደሮችላይ እየተጋረጠባቸው ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የዝናቡ ወቅት ዘግይቶ ይመጣል፣ ሌላ ጊዜ ቶሎ ያቆማል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ዝናቡ ዘግይቶና ኃይለኛ ሆኖ በመምጣት ጎርፍ ይፈጥራል፡፡ ሌላ ጊዜ ጭራሽ ሳይዘንብ በመቅረት ድርቅ ያመጣል፡፡ በእንደዚህ አይነት የአየር
ንብረት መለዋወጥ የተነሳ አርሶ አደሮችየትኛውን ሰብል እንደሚያመርቱ፣ ማሳቸውን መቼ እንደሚያዘጋጁ፣ መቼ መዝራት እንዳለባቸው እና ሌሎችንም የግብርና ሥራዎች ለማቀድ ይቸገራሉ፡፡

በአየር ንብረት መለዋወጥ የመጣባቸውን ችግር ለመቋቋም አርሶ አደሮችብዙ ነገሮችን እየሞከሩ ነው፡፡ አዳዲስ ዓይነት ሰብሎችን እያበቀሉ ነው፣ ድርቅን የመቋቋም ችሎታ ያላቸው ዘሮችን እየሞከሩ ነው፣ ሌሎች የግብርና አሠራሮችንም እየቀየሩ ነው፡፡

በኢትዮጵያ 45% የሚሆነው ኢኮኖሚ በግብርና ላይ የተመሰረት ነው፡፡ የብዙ ሰዎች ምጣኔ ሃብት እና ትዳር በአየር ንብረት በተለይም በዝናብ ላይ ጥገኛ ነው፡፡ የአየሩ ንብረቱ በሃገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች፣ በተለይ በቆላና በደጋ፣ የተለያየ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ደጋማ ቦታዎች ላይ አየሩ ቀዝቀስ ያለ ሆኖ ለግብርና የሚመች በቂ ዝናብ አለው፡፡
በኢትዮጵያ ደጋማ አካባቢዎች ሁለት ወቅቶች አሉ፡፡ የደረቁ ወቅት ከጥቅምት እስከ ግንቦት ሲሄድ የዝናቡ ወቅት
ደግሞ ከሰኔ እስከ መስከረም ይቆያል፡፡ በቆላማ ቦታዎች ያለው የአየር ሁኔታ ከደጋው በጣም የሚሞቅ እና ደረቅ ነው፡፡ በሃገሪቱ ዙርያ ያለው የግብርና አሠራር እንደ አየሩ ሁኔታ ይለያያል፡፡

ይህ ሰክሪፕት የኢትዮጵ የደጋ አርሶ አደሮችየአየር ጸባይ ለውጥ ምን እደረጋቸው እንደሆነ የተናገሩትን ያካትታል፡፡ ገበሬዎቹ ከአየር ጸባይ ለውጥ ጋር የተያያዙ ችግሮችን እና ከሁኔታው ጋር ለመጣጣም ምን ዓይነት ሥራዎችን
እየሠሩ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

የኢትዮጵያን የደጋ አርሶ አደሮችየሚያሳስቧቸው ትልቆቹ ጉዳዮች የዝናብ ወቅት እና መጠን መቀያየር እና እየሞቀ የመጣው የአየር ሁኔታ ነው፡፡ ምን እንደያሚበቅሉ ለመወሰን ከመቸገራው በተጨማሪ ምርትም እየቀነሰባቸው ነው፡፡ የአየር ጸባይ ለውጥ እንደ ደን መመንጠር እና የአካባቢ መራቆት የመሳሰሉ መሬት ላይ ጫና ከሚያሳድሩ
ችግሮች ጋር ሆኖ የገበሬዎችን የመቋቋም አቅም እየቀነሰው ነው፡፡ አርሶ አደሮችግብዓቶችን እንዲጠቀሙ፣ ዛፍ
እንዲተክሉ፣ ድርቅ

የሚቋቋሙ ሰብሎችን እንዲጠቀሙ፣ ቶሎ የሚደርሱ ሰብሎን እንዲዘሩ እና የከብት እና የዶሮ እርባታ የመሳሰሉ ሥራዎችን እንዲያጎለብቱ በመምከር የአየር ጸባይ ለውጥን ለመቋቋም እንዲችሉ የኤክስቴንሽን ወኪሎች እና የመንግስት ፕሮግራሞች እየሠሩ ነው፡፡ ገበሬዎችም እነዚህን አሠራሮች በመቀበል ውጤት እያገኙ ነው፡፡

ይህ ስክሪፕት ሦስት አሠራሮችን ያስተዋውቃል፣ ወደ ዝርዝር ማብራርያ ግን አይገባም፡፡ አርሶ አደሮችከነዚህ አሠራሮች አንዱን ወይም ሁለቱን እንዲጠቀሙበት ይህንን ፕሮግራም ለራሳችሁ ዝርዝር ጨምሩበት – ለምሳሌ ዶሮ ማርባት፣ ለተለመዱ የምግብ ሰብሎች ድርቅ የሚቋቋም የዘር ዓይነት መጠቀም ወይም ዛፍ መትከል፡፡ በጣም ብዙ መረጃ በመጠቅጠቅ አድማጮቻችሁ ለማስታወስ የሚያስቸግራቸው ፕሮግራም እንዳይሆንባቸው ተጠንቀቁ፡፡ ይህንን ፕሮግም አስከትላችሁም እነዚህን አሠራሮች እንዴት ባካባቢው መገተግበር እንደሚቻል መናገር ከሚችል ኤክስፐርት ጋር በስልክ ዝርዝር ውይይት ማድረግ ትችላላችሁ፡፡
በናንተ አካባቢ ያሉ አርሶ አደሮችየአየር ጸባይ ለውጥ እያጋጠማቸው ነው? አነጋግሯቸው እና በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ ፕሮግራም ሥሩ፡፡

በዚህ ጉደይ ላይ አድማጮቻችሁ ስልክ በመደውል ወይም የጽሑፍ መልዕክት በመላክ የአየር ጸባይ ለውጥን እና እሱን ለመቋቋም ምን እያደረጉ እንደሆነ የራሳቸውን ተሞክሮ እንዲካፍሏችሁ ጋብዙ፡፡ ከምትጠይቋቸው ጥያቄዎች ውስጥ የሚከተሉትን መጨመር ትችላላችሁ፡-

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ወይም ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ የአየር ንብረቱ ምን ያህል ተለውጧል?

በግብርና ሥራችሁ ላይ ያሳደረው ተጽእኖ ምንድን ነው?

የአየር ንብረቱን መለወጥ ተከትሎ የመጣው ከባዱ ችግር ምንድን ነው?

ከአየር ንብረት ለውጡ ጋር ለመለማመድ ምን እርምጃዎችን እየወሰዳችሁ ነው?

ከአየር ንብረቱ ጋር ለመለማመድ በምታድረጉት ጥረት ምን ስኬቶችን አግኝታችኋል?

ይህ ስክሪፕት በትክክለኛ ቃለ መጠይቆች ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀ ነው፡፡ በአካባቢያችሁ ያሉ አርሶ አደሮችላይ የአየር ጸባይ ለውጥ ምን ተጽእኖ እንዳሳደረባቸው ፕሮግራም ለማዘጋጀት ይህን ስክሪፕት ሃሳብ ለማግኘት ልትጠቀሙበት ትችላላችሁ፡፡ ወይም ተናጋሪዎችን በድምጽ ተዋንያንን ወክላችሁ ይህንን ስክሪፕት በመደበኛ የአርሶ አደር ፕሮግርማችሁ ላይ ልታዘጋጁት ትችላላችሁ፡፡ እንዲህ ካደረጋችሁ የፕሮግራማችሁ መጀመርያ ላይ ድምጾቹ የተዋንያን
እንጂ ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው አርሶ አደሮች እንዳልሆኑ ለአድማጮቻችሁ መንገር እንዳትዘነጉ፡፡

የመግቢያ እና መውጫ ሙዚቃን ሳይጨምር ይክ ስክሪፕት 13-14 ደቂቃዎች ይወስዳ፡፡

ይህ ፕሮግራም በዓመቱ በማንኛውም ጊዜ ሊተላለፍ ቢችልም አርሶ አደሮችለሚቀጥለው የሰብል ወቅት የትኘውን ሰብል ለመዝራት፣ መሬታቸውን እንዴት ማዘጋጃት እንዳለባቸው እና ሌሎችም መከተል ስላባቸው
ሥራዎች ማጤን በሚጀምሩበት ጊዜ ቢተላለፍ የተሻለ ውጤታማ ይሆናል፡፡

Script

የፕሮግራም ሙዚቃ

አስተናጋጅ፡
የአየር ጸባይ ለውጥ በዓለም ዙርያ የአየር ንብረትን እየለወጠው ነው፡፡ የሞቃት ቀኖች ቁጥር እየጨመረ ነው፤ ከባድ የዝናብ ኩነቶችም ካለፉት አሥርት ዓመታት በተለየ እየተደጋገሙ ነው፡፡ በኢትዮጵያና በሌሎችም የአፍሪካ ሃገሮች አርሶ አደሮችእየተቸገሩ ነው፡፡ ዛሬ የአየር ጸባይ ለውጥ ጋር ከፊት ሆነው እየታገሉ ያሉ አርሶ አደርዎችን ትሰማላችሁ፡፡ እነዚህ ሰዎች እያጋጠሟቸው ስላሉ ችግሮች እና ከሁኔታው ጋር ለመለማመድ ምን እያደረጉ እንደሆን
ይነግሯችኋል፡፡ ከኛ ጋር ቆዩ፡፡

ኢትዮጵያ ሁለት የአየር ጸባይ ክልልሎች ያሏት ሲሆን አንደኛው የኢትዮጵያ ደጋማ ቦታዎች እየተባለ የሚጠራው ማአከላዊ ፕላቶ ሲሆን ሁለተኛው እሱን ከቦ የሚገኘው ቆላማ ሥፍራ ነው፡፡ ደጋማ ቦታዎች ቀዝቀዝ ሉ ሲሆን ቆላማ ቦታዎች በጣም ሞቃት እና ደረቅ ናቸው፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ ደጋማ ቦታዎች ላይም ያለው የአየር ሁኔታ እየተለወጠ ነው፡፡ አርሶ አደሮችበተራራማ መሬቶች ላይ እያጋጠሟቸው ካሉ ችግሮች በተጨማሪ ከዚህ የአየር ለውጥ ጋር ለመለማመድ እየተቸገሩ ነው፡፡ ዛሬ ከአየር ጸባይ ለውጡ ጋር ለመለማመድ ምን እደረጉ እንደሆን ከአንዳንድ የደጋ አርሶ አደሮች ጋር እንነጋራለን፡፡

የፕሮግራሙ ሙዚቃ

አስተናጋጅ:
ከጥቂት ወራ በፊት ከአዲስ አበባ ተነስቼ 60ኪሜ ወደ ምዕራብ ወደ ሞግሌ ተራራ ተጉዤ ነበር፡፡ ከአየር ጸባይ ለውጥ ጋር ፊት ለፊት እየታገሉ ካሉ አርሶ አደሮች ጋር ተነጋግሬ ያዘጋጅሁትን የጉዞ ማስታወሻ ይሄው ይዤላችሁ ቀርቢያለሁ፡፡

SFX:
የነፋስ፣ የቤት እንስሳት (በሬ፣ አህያ፣ ከብቶች)፣ እና የወፎች ድምጽ ከቃለ መጠይቁ ጀርባ

አስተናጋጅ:-
በሞግሌ ተራራ ዙርያ ያለው አካባቢ ተራቁቷል፡፡ ተራራው እና ዙርያውን ያለው አካባቢ በደን የተሸፈነ እና የብዙ እንስሳት መኖርያ የነበረ ነው፡፡ አሁን ግን ተራራው ተራቁቷል፣ ደኑም ተመንጥሯል፡፡ ከዚህም በላይ የአየሩ ሁኔታ ከደጋማነት ወደ ቆላማነት እየተቀየረ ነው፡፡

ጸሃይዋ አናት ሳትደርስ የእግር ጎዞ ጀምሪያለሁ፡፡ በመንገዴ የማገኛቸው አርሶ አደሮች በቡድን ሆነው የማረስ ሥራ ላይ ተጠምደዋል፡፡ አንዳንዶቹ አርሶ አደሮቹ እንዳይደክሞ ለማበረታታት የአካባቢውን ዘፈኖች ይዘፍኑላቸዋል፡፡ በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ መዝራት ይጀምራሉ፡፡ ረጅም የግር ጉዞ ካደረኩኝ በኋላ አያኖ መገርሳ የተባሉ ያካባቢው አርሶ አደር አገኘሁ፡፡

አስተናጋጅ:-
አያኖ መገርሳ ስንዴ ለመዝራት እያረሱ ነው፡፡ ሰብሎች እያፈራረቁ ስለሚዘሩ አሁን የስንዴ ተራ ነው፡፡ ማሳውን ማረስ አረም ለመቆጣጠርም ይጠቅማቸዋል፡፡ የደከማቸው ቢመስሉም በሰላምታ ተቀብለውን በሬዎቹን ለልጃቸው ለቱሉ አሳልፈው ሰጡ፡፡ የዛፍ ጥላ ስር ቁጭ ብለን ዘር ከመዝራት በፊት ስላለባቸው ሥራዎች እንዲህ ነገሩን፡፡

አያኖ:-
ዝናቡ ከመጀመሩ በፊት ብዙ ጊዜ የለንም፡፡ ዝናብ ሳይጀምር ጠንክረን መሥራት አለብን፡፡

አስተናጋጅ:-
እዚህ ወረዳ ውስጥ ለምን ያህል ጊዜ ኖረዋል?

አያኖ:-
እዚህ ከ45 ዓመት በፊት ተወልጄ እዚሁ አድጊያለሁ፡፡ የቤተሰቤ መተዳደርያ ግብርና ነው፡፡

አስተናጋጅ:-
እዚህ አካባቢ መዝነብ የሚጀምረው መቼ ነው?

አያኖ:-
ዋናው ዝናብ በሰኔ ይጀምራል፣ ግን ቀኑ ሊለያይ ይችላል፡፡ በቅርብ ዓመት ዝናቡ ቆይቶ ይጀምርና ቶሎ ሊያቆም ይችላል፡፡ ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የአየር ጸባይ ለውጥ ዝናቡን እንደሚያዘበራርቀው ነግረውናል፡፡

አስተናጋጅ:-
እንዲህ መሆኑ የግብርና ሥራችሁ ላይ ተጽእኖ አሳድሮባችኋል?

አያኖ:-
እንዴ ምን ጥያቄ አለው! ጫካውም የተፈጥሮ ሃብቱም እየተመነጠረ፣ እየተራቆተ ስለሆነ አስቸጋሪውን የአየር ንብረት ለመቋቋም እያስቸገረ ነው፡፡ የአፈራችን ለምነት ቀንሷል፡፡ ከፍያለ ምርት ለማግኘት ግብዓት መጨመር እና ምርት ዘር መጠቀም አለብን፡፡ የውሃ ችግርም አለ፡፡ እሱም በአየር ጸባይ መለወጥ የተነሳ ይመስለኛል፡፡

አስተናጋጅ:-
አርሶ አደሩ የአየር ንብረት መለዋወጥ ስላመጣባቸው ተጽእኖ ሲያወሩን የተጨነቁ ይመስላሉ፡፡ አሁን ጥሩ ምርት ታገኛላችሁ?

አያኖ:-
አዎ፡፡ የኤክስቴንሽን ሠራተኞች መሬታችንን በእርከን እንድንጠብቅ መክረውናል፡፡ ድርቅ የሚቋቋሙ ዘሮችንም እየሰጡን ነው፡፡ አሁን ደና ነን፡፡ የነገን ወይም የዛሬ ዓመት የሚኖረውን የአየር ንብረት ግን ሁልጊዜም ባለው የአየር ጸባይ ለውጥ የተነሳ መተንበይ ከባድ ነው፡፡

የበሬዎች ድምጽ

አስተናጋጅ:-
የአየር ጸባይ ለውጥ አርሶ አደሮች ላይ ያደረገው ትልቁ ተጽእኖ ምንድን ነው?

አያኖ:-
የዝናቡን ወቅት መናገር አይቻልም፡፡ አንዳንዴ ዝናቡ ይቆማል ወይም በበልግ ሳይዘንብ ይቀራል፡፡ (የአርታኢው ማስታወሻ፡- ይህ አጭር የዝናብ ወቅት ከመጋቢት እስከ ግንቦት ይቆያል፡፡) አሁን አሁን የአየሩ ሁኔታ ነው ዋናው ችግራችን፡፡ በደረቁ ጊዜ ከብቶቻችን የሚግጡት ሳር ስለማያገኙ ከብቶቻችንን ለመሸጥ እንገደዳለን፡፡

የቦታ ለውጥ

አስተናጋጅ:-
ሁለተኛ የቆምኩት ጌጤ ቶሎሳ ቤት ላይ ነበር፡፡ የቤታቸው ውስጡ እንደማንኛውም አርሶ አደር ቤት ነው፡፡ ብዙ ባህላዊ እቃዎች ግድግዳው ላይ ተሰቅለዋል፡፡ የጭቃ መደብ ላይ ተቀምጠን ምሳ በላን፣ ቡናም ተፈልቶልን ጠጣን፡፡ ግድግዳው ላይ ብዙ የሚያማምሩ ነገሮች አሉ – ልብሶች፣ የእርሻ መሣርያዎች፣ ጌጦችና መሰል ነገሮች፡፡ በእሳቸው የግብርና ሥራ ላይ የአየር ጸባይ ለውጥ ያመጣው ተጽእኖ ምን እንደነበር ጌጤን ጠየኳቸው፡፡

ጌጤ:-
እነዚህን የተሻሻሉ የግብርና አሠራሮች መንግስት ባያመጣልን ኖሮ ምን ይውጠን እንደነበር አላውቅም፡፡

አስተናጋጅ:-
ምን አሠራሮች?

ጌጤ:-
ድርቅና በሽታ የሚቋቋም ምርጥ ዘር፡፡ ደሞ አሁን አሁን በተራቆተ መሬት ላይ ዛፎች እየተከልን ነው፡፡

አስተናጋጅ:-
ከባድ እየሆነ የመጣው የአየር ጸባይ ለውጥ ያስጨነቃቸው ይመስላሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ለመናር ሲቸገሩ በግልጽ ያስታውቃሉ፡፡ አሁን ያላቸው ምርት ጥሩ እንደሆነ ጠየኳቸው፡፡

ጌጤ:-
አዎ፣ የራሳችንን ዘር ዘርተን ከምናገኘው የተሻለ ምርት አለን፡፡ አሁን የቸገረን ዝናቡ ከጊዜ ጊዜ መለያየቱ ነው፡፡ ከባድ ዝናብና ጎርፍ ሊኖር ይችላል፡፡ ዝናቡ አስቀድሞም በጊዜ ሊቆም ይችላል፡፡

አስተናጋጅ:-
አሁን ያለው የዝናብ ወቅት ከከዚህ ቀደሙ ጋር ሲነጻጸር ምን ይመስላል?

ጌጤ:-
የዝናቡ ወቅት አጭር እየሆነ ነው፡፡ ከአሥር አሥራ አምስት ዓመት በፊት በጣም ዝናብ ነበር፤ አሁን ግን ከቀን ቀን እየተቀየረ ነው፡፡ ስንዴያችን ቢያንስ የሦስት ወር ዝናብ ይፈልጋል፡፡ ለከብቶቻችንም በጣም አስፈላጊ ነው፡፡

አስተናጋጅ:-
ይህን ችግር ለመቋቋም ምን እያደረጋችሁ ነው?

ጌጤ:-
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የኤክስቴንሽን ሠራተኞች የተፈጥሮ መከላከያ ዘዴዎችን
እንድንጠቀም ሲመክሩን ቆይተዋል፡፡ አሁን የእርሻ መሬታችንን ከኣፈር መሸርሸር ለመጠበቅ እርከን እየሠራን ነው፡፡ አትክልትም እየተከልን ነው – ቶሎ ይደርሳሉ፣ ብዙ እርጥበትም አይፈልጉም፡፡

መተላለፊያ ሙዚቃ፣ ድምጹ እየቀነስ ይሄዳል

አስተናጋጅ:-
የአየር ጸባይ ለውጥ ለኢትዮጵያ አርሶ አደሮች አስቸጋሪ ጉዳይ ነው፡፡ ወደሚቀጥለው አርሶ አደር ልውሰዳችሁ፡፡ ባዮ ዳባ 72 ዓመታቸው ሲሆን ሙሉ ዕድሜያቸውን እዚህ ስለኖሩ አሁን ያለውን የአየር ሁኔታ ካለፉት አሥርት ዓመታት ጋር ከነበረው የአየር ሁኔታ ጋር ለማነጻጸር ብቁ ናቸው፡፡ ስንዴ ይዘራሉ፣ ከብትም ያረባሉ፡፡

ባዩ ዳባ በእርሻቸው ማሃል ላይ ቆመዋል፡፡ ባለቤታቸው ብርቄ እንደ ጥቅል ጎመን እና ድንች ያሉ የጓሮ አትክልቶች ያበቅላሉ፡፡ ለአትክልታቸው እና ለቤት ፍጆታ የሚሆን ውሃ የሚያገኙበት አነስተኛ የውሃ ጉድጓድ ቆፍረዋል፡፡ ራሴን አስተዋውቄ መነጋር ጀመርን፡፡ አሮጌ ባርኔጣ አድርገዋል፡፡ የደከማቸው ይመስላሉ፡፡

የዎፎች ድምጽ

ባዩ:-
በዚህ ወቅት እኛ በጣም ሥራ ይበዛብናል፡፡ እንደምታየው የቅድመ-ዘር እና የዘር ሥራዎችን እየሠራን ነው፡፡ አሁን ዝናቡ ደና ይመስላል፣ የዛሬ ወር ግን ምን እንደሚመስል መገመት አይቻልም፡፡ አየሩ በጣም ተለዋዋጭ ነው፡፡ መሬታችንን እያዘጋጀን ነው፣ ግብዓትም እንጠቀማን፡፡

አስተናጋጅ:-
የዛፍ ጥላ ሥር ቁጭ ብለናል፡፡ አርሶ አደሩ ያለፈገግታ ቁጭ ብለዋል፡፡ የተጨነቁ ይመስላሉ፡፡ ስለ አየር ጸባይ ለውጥ ሲያወሩን ድምጻቸው ቀስ ብሎ ነበር፡፡

ባዩ:-
ግብርና በያመቱ በጣም አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ ከአሥራምናምን ዓመት በፊት ግብዓትም ምርት ዘርም አንጠቀምም ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ አየሩ የታወቀ የደጋ አየር ነበር፡፡ ስለዚህ የራሳችንን ዘር ተጠቅመን ብዛትና ጥራት ያለው ምርት እናገኝ ነበር፡፡

አየሩ እየተለዋወጠ ሲሄድ ግን የግብርና ሥራችንን ለመጠበቅ የተሻሻሉ የግብርና አሠራሮችን መጠቀም ግድ ሆኗል፡፡ ባካባቢያችን ያለን ዘር እንደ ምርጡ ዘር ድርቅ አይቋቋምም፡፡ አኗኗራችንም እንደ አየሩ እየተለወጠ ነው፡፡ የተሻሻለ ቴክኖሎጂ ብንጠቀም ምርታችንን እጥፍ ያደርግልናል፡፡

አስተናጋጅ:-
አርሶ አደሩ መልስ ለማግኘት ወደኔ እየተመለከቱ እንደሆነ ገባኝ፡፡ በነዚህ ጉዳዮች ላይ ባለሙያ መስያቸዋለሁ፡፡ የአየር ጸባይ ለውጥ በሕይወታቸው ላይ በቀጥታ ያመጣው ለውጥ ምን እንደሆነ ጠየኳቸው፡፡

ባዩ:-
ለውጦቹ የሚገርሙ ናቸው፡፡ የመሬታችን ለምነት ሁልጊዜ እየቀነሰ ነው፡፡ አየሩ እየሞቀ ነው፡፡ በአየር ጸባይ ለውጥ የተነሳ ይመስለኛል፡፡ ትክክል አይደለሁም? ነገ፣ ዛሬ ከሰዓት በኋላም ቢሆን አየሩ ምን እንደሚሆን መገመት አልችልም፡፡ አየሩ በየወቅቱ ምን እንደሚመስል በጊዜ ገምተን እናቅድ ነበር፡፡ አሁን ግን የኤክስቴንሽን ሠራተኛውን ምክር ብቻ እንቀበላለን፡፡

የኛ ግብርና በዝናብ እና በሌሎች የግብርና ሁኔታዎች ላይ ጥገኛ ነው፡፡ በተፈጥሮ ላይ እንጂ በመስኖ ላይ የተመሰረተ ሥራ አይደለም፡፡ የአየር ጸባይ ለውጥ የአካባቢያችንን ተፈጥሮ ሕይወታችንንም እየቀየረው ነው፡፡

አስተናጋጅ:-
እንዴት ነው ሕይወታችሁን የቀየረው?

ባዩ:-
የእርሻ መሬታችን የተለየ ነበር፡፡ ከሃያ ከሰላሳ ዓመት በፊት የእርሻ መሬታችን ሰፊ ነበር፣ ባካባቢው ያለው ሰውም ትንሽ ነበር፡፡ መንደራችን አጠገብ የዱር እንስሳት ማየት ቀላል ነበር፡፡ የደጋ አየር ነበር፡፡ አየሩ በሙሉ ተቀይሯል፡፡ ደጋው አገራችን አሁን እንደ ቆላ እየሆነ ነው፡፡ ስለዚህ የግብርና ስራችንም አብሮ ተቀይሯል፡፡ ይህ ቦታ ለብዙ ሰብሎች ተስማሚ ነበር፡፡

አስተናጋጅ:-
ታሪኩን እና ተግዳሮቶቹን ገለጹልን፡፡ እነዚህን ተግዳሮቶች ለማሸነፍ ምን መደረግ አለበት?

ባዩ:-
አሁን አሁን መንግስት ድርቅና በሽታ የሚቋቋሙ ዘሮችን እያቀረበልን ነው፡፡ ምርጥ ዘር እና የተባይ ቁጥጥር እንድንጠቀም እያበረታቱን ነው፡፡ እርከን እየሠራን ዛፍም እየተከልን ነው፡፡ የደን መልሶ ማልማት ሥራችን የመንደራችንን ተፈጥሮ እንድንጠብቅ እበረታታን ነው፡፡ ደን መልሶ በማልማት እንዲያገግሙ የተደረጉ ቦታዎች ላይ የምንጭ ውሃ እያገኘን ነው፡፡

የወፎች ድምጽ ይወጣና ይወርዳል

አስተናጋጅ:-
አሁን 47 ዓመት እድሜ ያላቸውን የባዩን ባለቤት ብርቄን እንሰማለን፡፡ ለዚህ ላልተጠበቀ የአየር ሁኔታ ምክንያቱ ምን ይመስለወታል?

ብርቄ:-
የዝናቡ ወቅት መቸ እንደሚጀምር አይታወቅም ወይም ዘግቶ ይመጣል፡፡ በዚህ የተነሳ የስንዴ ምርታችን በቀጥታ ተጎድቷል፡፡ ለከብቶቻችንም በቂ ሳር ወይም መኖ አላገኘንም፣ ስለዚህ ባለሙያዎቹ የከብቶቻችንን ቁጥር እንድንቀንስ መክረውናል፡፡ ከብቶቻችን እንዲግጡ እየፈቀድንላቸው አይደለም፡፡ አሁን የፋብሪካ ተረፈ ምርት እየገዛን እና ካለችን ትንሽ መሬት ላይ የሚበቅለውን ሳር እያበላን በሬዎችን እያደለብን ነው፡፡

አስተናጋጅ:-
ይህንን ተግዳሮት ለመቋቋም ሌላ ምን እያደረጋችሁ ነው?

ብርቄ:-
አሁን መንግስት ድርቅና በሽታ የሚቋቋሙ እና ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ ምርጥ ዘሮችን እንድንጠቀም እያበረታታን ነው፡፡ የራሳችንን ዘር ስንጠቀም ከነበረው ካለፉት ጥቂት ዓመታት ምርታችን አሁን በእጥፍ አድጓል፡፡

የቦታ የውጥ

አስተናጋጅ:-
አሁን የየሺ ቤኛ ማድቤት ውስጥ ገብቻለሁ፡፡ ለልጆቻቸው ዳቦ እየጋገሩ ነው፡፡ ማድቤቱ በጢስ ሞልቷል፡፡ ሦስት ልጆቻቸው ዳቦ ለመቀበል እናታቸውን ከበዋል፡፡ በደቂቃዎች ውስጥ ጋግረው እንደሚጨርሱ ነገሩኝ፡፡

ከ15 ደቂቃ በኋላ ትኩስ ዳቦ ቀመስኩኝ፡፡ ልጆቹ ዳቦ ስጭን እያሉ እሳቸው ለማቀዝቀዝ እየሞከሩ ነው፡፡ መጀመርያ ዳቦዉን ለልጆቻቸው ቆራረሱ፡፡ እም! የሚጣፍጥ ዳቦ ነው! ለቤት ፍጆታ ብለው ስንዴ ያበቅሉ እንደሆን ጠየኳቸው፡፡

የሺ:-
ዱሮ የራሳችንን ዘር ተጠቅመን ለቤት ፍጆታ ብቻ እናመርት ነበር፡፡ አሁን ነገሮች ተለውጠዋል፡፡ ለልጆቻችን የሚሆኑ ነገሮችን ለመግዛት የሚሆን ገንዘብ ለማግኘት ምርጥ ዘር ያስፈልገናል፡፡ እነዚህ ምርጥ ዘሮች ከፍተኛ ምርት ለማግኘት በጣም አስፈላጊ ናቸው፡፡ ትርፍ ምርት ካለን ገበያ ወስደን እንሸጣለን፡፡

አስተናጋጅ:-
ይሄ ዳቦ ከምርጥ ዘር የተገኘ ነው?

የሺ:-
አይደለም፣ ይሄ የራሳችን ዘር ነው፡፡ ዩሪያና ዳፕ የመሳሰሉ ግብዓቶችን አይጠቀምም፡፡ (የአርታኢው ማስታወሻ፡- ዩሪያና ዳፕ ማዳበርያዎች ናቸው፡፡)

አስተናጋጅ:-
የራሳችሁን ዘር ለዳቦ የምትጠቀሙት ለምንድን ነው?

የሺ:-
ምርጥ ዘሩን ብዙ ጊዜ ለገበያ እና ለሚቀጥለው ወቅት ለዘር እንጠቀምበታለን፡፡ በነገራችን ላይ አዲሱ ዘር ነባሩን በቅርብ ይተካዋል፡፡

አስተናጋጅ:-
የሺ እየተነጋገሩ ዳቦ መጋገራቸውን አላቋረጡም ነበር፡፡ እንጨቱ ይጤሳል፣ ጢሱ አንዳንድ ጊዜ ቃለመጠይቁን ይረብሻል፡፡

አስተናጋጅ:-
በሳምንት ስንት ጊዜ ዳቦ ይጋግራሉ?

የሺ:-
እንደሁኔታው ነው፡፡ ብዙ ጊዜ በሳምንት ሁለት ጊዜ እጋግራለሁ፡፡ ባለቤቴ ከቤት የምንፈልገውን ልብስም ሆነ ሌላ መግዣ ገንዘብ ለማግኘት ስንዴውን ወደ ገበያ ይወስደዋል፡፡

አስተናጋጅ:-
ስለ አየር ጸባይ መለዋወጥ ምን ያስባሉ? ሕይወትዎት ላይ ተጽእኖ አለው?

የሺ:-
ከአየር ጸባይ ለውጥ ጋር ተያይዞ ብዙ ችግሮች እያጋጠሙን ነው፡፡ ለከብቶቻችንም ለኛም ውሃ ችግር አለ፡፡ እንደሚገባኝ የአየር ለውጥ ተጽእኖ ነው፡፡ ሁለቱም የዝናብ ወቅቶች ለመገመት አስቸግረዋል፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት የበልግ ጊዜ ምንም ዝናብ አልነበረም፡፡

አስተናጋጅ:-
በየሺ ልጆች መሀል ቆሚያለሁ፡፡ ስማቸው ደያሳ እና መቲ ይባላሉ፡፡ ደያሳ ዘጠኝ ዓመቱ ነው፡፡ እናቱ ዳቦ እስኪሰጡት ሲጠብቅ እናቱ ዳቦውን ከየት እንደሚያመጡት ጠየኩት፡፡

ደያሳ:-
ብዙ ስንዴና ዱቄት ጎተራችን ውስጥ አለ፡፡ አባታችን ከእርሻ ይዞት መጣ፡፡

የወፎች ድምጽ ለጥቂት ሰከንዶች ይወጣና ይወርዳል

አስተናጋጅ:-
በወረዳው ውስጥ ያለ የኤክስቴንሽን ሠራተኛም አገኘሁ፡፡ መገርሳ ኢሬና ላለፉት አራት ዓመታት የግብርና ባለሙያ ሆኖ አገልግሏል፡፡

አስተናጋጅ:-
በዚህ አካባቢ አየር ጸባይ ለውጥ ተጽእኖ ምን ይመስላል?

መገርሳ:-
የአየር ጸባይ ለውጥ በግብርና ሥራ ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ አለው፡፡ አየሩ ሞቃት እና ከባድ እየሆነ ነው፡፡ የብዙ አርሶ አደሮችን ሕይወት እየቀየረ ነው፡፡ በሰብል ምርት እና ከብት እርባታ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አለው፡፡

አስተናጋጅ:-
የአርሶ አደሮችን ሕይወት እየቀየረው ነው ስትል ምን ማለትህ ነው?

መገርሳ:
በዚህ አካባቢ ግብርና በዝናብ ላይ ጥገኛ ነበር፡፡ አርሶ አደሮችም ኑሯቸው በሰብል ምርት ላይ የተመሰረተ ነበር፡፡ አሁን ግን በአየር ጸባይ ለውጥ የተነሳ ሕይወታቸው እየተቀየረ ነው፡፡ ሰብል ብቻ ማምረት አይችሉም፡፡ የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጥ ካለባቸው እንደ ከብት ማድለብ እና ዶሮ ማርባት የመሳሰሉ ሌሎች እድሎችን እንዲፈልጉ ተፈጥሮ አስገድዳቸዋለች፡፡

አስተናጋጅ:-
የነዚህ አዳዲስ ሥራዎች ውጤት ምንድን ነው?

መገርሳ:-
አንዴ ወደነዚህ ዓይነት ሥራዎች መዞር ተስፋ ሰጭ እና ጠቃሚ ነው፡፡ ዱሮ በዝናብ ላይ ብቻ ጥገኛ ነበሩ፡፡ ዝናብ ካልመጣ ችግር ላይ ነበሩ፡፡ ሌላ እንጀራ አልነበራቸውም፡፡

አስተናጋጅ:-
እየተቀየረ ያለውን የአየር ጸባይ ለመቋቋም ምን እርምጃዎችን እየወሰዳችሁ ነው?

መገርሳ:-
መንግስት “የአየር ጸባይ ለውጥን የሚቋቋም አረንጓዴ ልማት መገንባት” የሚል መፈክር ያለው ትልቅ ስትራቴጂ አለው፡፡ እርከን መሥራት እና ደንን መልሶ ማልማት የዚህ ስትራቴጂ አካሎች ናቸው፡፡ ስለዚህ በየወረዳው ያሉ የኤክስቴንሽን ሠራተኞች አርሶ አደሮች እርከን እንዲሠሩ እና ደን መልሰው እንዲያለሙ እየመከሩ ነው፡፡ በጥቂት ወረዳዎች አበረታች ውጤቶችን አይተናል፡፡ ዋናው ውጤት አንዳንድ የተራቆቱ ቦታዎች እያገገሙ መሆናቸው ነው፡፡ ይህ አሠራር አካባቢውን መልሶ በደን ይሸፍናል ብየ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

የፕሮግራሙ ሙዚቃ ከፍ ብሎ ይወርዳል

አስተናጋጅ:-
እየተለወጠ ያለው የአየር ንብረት አርሶ አደሮችላይ ብዙ ዓይነት ተጽእኖ አለው፡፡ እንደምታዩት አርሶ አደሮች ተጨንቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ የደጋ አርሶ አደሮች ዋና ችግር የዝናቡ ሁኔታ መለዋወጥ እና አየሩ በጣም ሞቃት እየሆነ መምጣት ነው፡፡ ምን እንደያሚበቅሉ ለመወሰን ከመቸገራው በተጨማሪ ምርትም እየቀነሰባቸው ነው፡፡ የአየር ጸባይ ለውጥ እንደ ደን መመንጠር እና የአካባቢ መራቆት የመሳሰሉ መሬት ላይ ጫና ከሚያሳድሩ ችግሮች ጋር ሆኖ የአርሶ አደሮችን የመቋቋም አቅም እየቀነሰው ነው፡፡ አርሶ አደሮች ግብዓቶችን እንዲጠቀሙ፣ ዛፍ እንዲተክሉ፣ ድርቅ
የሚቋቋሙ ሰብሎችን እንዲጠቀሙ፣ ቶሎ የሚደርሱ ሰብሎን እንዲዘሩ እና የከብት እና የዶሮ
እርባታ የመሳሰሉ ሥራዎን እንዲያጎለብቱ በመምከር የአየር ጸባይ ለውጥን ለመቋቋም እንዲችሉ የኤክስቴንሽን ወኪሎች እና የመንግስት ፕሮግራሞች እየሠሩ ነው፡፡ አርሶ አደሮችም እነዚህን አሠራሮች በመቀበል ውጤት እያገኙ ነው፡፡

አርሶ አደሮች በመንግስት እርዳታ በመታገዝ የቻሏቸውን እርምጃዎች እየወሰዱ ነው፡፡ እነዚህን አሉታዊ ተጽእኖዎች ለመጋፈጥ ሁሉም አብሮ መሥራት እንዳለበት እናውቃለን፡፡ በዚህም በቀጣይ እስከምንገናኝ በደህና ቆዩን ብለን እንሰናበታለን፡፡

የፕሮግራሙ ድምጽ

Information sources

ምስጋና
የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ፡- ኃይለአምላክ ካሳዬ፣ ጋዜጠኛ፣ አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ፡፡
የዚህ ጽሑፍ ገምጋሚ፡- ጂመና ኢይዛጉይር፣ ሲኒየር ክላይሜት ቼንጅ ስፔሻሊስት፣ ኢኤስኤስኤ ቴክኖሎጂስ ኢንኮርፖሬትድ፣ ካናዳ፡፡
የመረጃ ምንጮች
ከሚከተሉት ሰዎች ጋር የተደረጉ ቃለ መጠይቆች፡- አያኖ መገርሳ፣ አርሶ አደር፣ ሚያዚያ 18፣ 2006 ጌጤ ቶሎሳ፣ አርሶ አደር፣ ሚያዚያ 18፣ 2006 ባዩ ዳባ፣ አርሶ አደር፣ ሚያዚያ 19፣ 2006
ብርቄ ዎቆ፣ አርሶ አደር፣ ሚያዚያ 19፣ 2006 ከበደ ጅሩ፣ ያገር ሽማግሌ፣ ሚያዚያ 21፣ 2006
መገርሳ ኢሬና፣ ግብርና ባለሙያ (አግሮኖሚስት)፣ ሚያዚያ 30፣ 2006 የሺ ቤኛ፣ አርሶ አደር፣ እና ልጇ ደያሳ ጅሩ፣ ግንቦት 18፣ 2006፡፡
መልካ ኮሬ፣ አርሶ አደር፣ ግንቦት 19፣ 2006፡፡

gac-logoበውጭ ጉዳይ፣ ንግድ እና ልማት ዲፓርትመንት በኩል ከካናዳ መንግስት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የተካሄደ ፕሮጀክት