የኢትዮጵያ አርሶአደሮች የመጤ ተምች መንጋን እንዴት እንደሚቆጣጠሩ መጤ ተምቹ

ግብርና

Notes to broadcasters

 

ለአዘጋጁ ማስታወሻ

መጤ ተምች በበቆሎ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ የነፍሳት ዝርያ ተባይ ነው፡፡ ተባዩ ሩዝ፣ ማሽላ፣ አጃ፣ ሸንኮራ አገዳ፣ አትክልቶችን እና ጥጥን፣ እንዲሁም ሌሎች ሰብሎችን ያጠቃል፡፡ መጤ ተምቹ የተነሳው ሞቃታማና ከፊል ሞቃታማ ከሆኑት የደቡብ እና የሰሜን አሜሪካ ክፍሎች ነው፡፡ ነገርግን ወደ ሌሎች የዓለም ክፍሎች በፍጥነት እየተዛመተ ነው፡፡

ይህ ፅሁፍ መጤ ተምች ከፍተኛ ጉዳት የማድረስ አቅም ቢኖረውም ባህላዊና ዘመናዊ የሆኑ ውጤታማ የመጤ ተምች መቆጣጠሪያ መንገዶች እንዳሉና የሚያደርሰውን ጉዳት መቀነስ እንደሚቻል ያሳያል፡፡

ይህ ፅሁፍ በዕውን የተደረጉ ቃለ-መጠይቆችን መሰረት በማድረግ እና በመቀየር የተዘጋጀ ነው፡፡ አዘጋጁ ይህን ፅሁፍ እንደ ጥናት ወረቀት ሊጠቀምበት አሊያም መጤ ተምችን ወይም ሌሎች ተባዮችን በሚመለከት ለሚሰራው ፕሮግራም እንደ መነሻ ሊጠቀምበት ይችላል፡፡

ወይም ተናጋሪዎቹን የሚወክሉ የድምፅ ተዋናዮችን በመጠቀም የመደበኛው የአርሶአደሮች ፕሮግራም አካል በማድረግ ሊዘጋጅ ይችላል፡፡ ይህ ከሆነ በፕሮግራሙ መጀመሪያ ላይ ድምፆቹ የተዋናዮች ድምፆች እንጂ ቃለ-መጠይቁ የተደረገላቸው የዋናዎቹ ሰዎች ድምፆች እንዳልሆኑ ለአድማጮች መንገርህን ማረጋጥ አለብህ፡፡

በአካባቢው ያሉትን ገበሬዎች፣ የግብርና ኃላፊዎች፣ እና ሌሎች ባለሙያዎችን አናግር፡፡ የሚከተሉትን ልትጠይቃቸው ይትችላለህ፡-

  • የመጤ ተምች መንጋን ለመቆጣጠር ምን ምን ዘዴዎችን ተጠቅመዋል?
  • ሰብላቸውን በተባይ እንዳይበላሽ እንዴት ይከላከላሉ?
  • ውጤታማ የሆኑ የተባይ መቆጣጠሪያ መንገዶችን በተመለከተ ያላቸው ምክር?

አርሶአደሮችን እና ባለሙያዎችን በቀጥታ ከማናገር በተጨማሪ እነዚህን ጥያቄዎች ለቀጥታ የስልክ ውይይት ወይም በቀጥታ የሚቀረብ ፅሁፍ መነሻ ሊያደርጓቸው ይችላሉ፡፡

ይህን ዝግጅት ለማሰራጨት የሚወስደው ጊዜ በግምት 20 ደቂቃ ሲሆን ይህም የፕሮግራሙ ስያሜ እና ማስተዋወቂያ፣ የፕሮግራም መግቢያ፣ እና ማጠቃለያ ጊዜን ይጨምራል፡፡

Script

ኒዮ ብራውን፡-
እንደምን አደራችሁ (ዋላችሁ/አመሻችሁ)! ዛሬ የኢትዮጵያ አርሶአደሮች የመጤ ተምች መንጋን ለመከላከል እንዴት እየጣሩ እንደሆነ እና ማሳቸው ላይ ትልቅ ጉዳት ከማድረሱ በፊት እንዴት እየተከላከሉት እንደሆነ እናወራለን፡፡
የድምፅ ግብአት፡-

ኒዮ ብራውን፡-
በኢትዮጵያ በልግ አየተባለ የሚጠራው ደረቅ ወቅት ነው፡፡ በኢትዮጵያ የሰሜን ምዕራብ እና ሰሜን መካከለኛ ክፍል ወደሚገኘው የአማራ ክልል ተጓዝኩ፡፡ በአማራ ክልል ከ85 ከመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ በግብርና የተሰማራ ነው፡፡ የመጤ ተምች መንጋን እንዴት እንደሚቆጣጠሩ ለማወቅ በክልሉ ያሉ አርሶአደሮችን እና ባለሙያዎችን ጠየቅኳቸው፡፡ ገብስ፣ ስንዴ፣ የቅባት እህሎች፣ ማሽላ፣ በቆሎ፣ አጃ፣ ባቄላ እና ሽንብራ በአማራ ክልል በብዛት የሚመረቱ ሰብሎች ናቸው፡፡ ነገርግን በአርሶአደሮቹ ምርታማነት ላይ አደጋ የሚጥሉ የመጤ ተምች መንጋን ጨምሮ ብዙ ተባዮች አሉ፡፡ ወደ ክልሉ የተጓዝኩት አርሶአደሮች የመጤ ተምች መንጋን እንዴት እየተቆጣጠሩና ሰብላቸውን እንዳያወድምባቸው እንዴት እየተከላከሉ እንደሆነ ለማወቅ ነው፡፡
የድምፅ ግብአት፡-

ኒዮ ብራውን፡-
በጉዞዬ ወቅት ካናገርኳቸው አርሶአደሮች መካከል ነጋ አሰፋ አንዱ ነው፡፡ ባህርዳር ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው ይነሴ ወረዳ ነው የሚኖረው፡፡ የ32 ዓመቱ አርሶአደር አራት ልጆች አሉት፤ ሁለት ወንዶችና ሁለት ሴቶች፡፡ ከእርሱ ጋር ያደረግኩትን ቆይታ እነሆ፡-
እንደምን አደርክ ነጋ!
ነጋ አሰፋ፡-
እንደምን አደርክ!
ኒዮ ብራውን፡-
ምን ምን አይነት ሰብሎችን ነው የምትዘራው?
ነጋ አሰፋ፡-
በዋናነት ለቤተሰቤ ቀለብ የሚሆን በቆሎ እና ዘንጋዳ ነው የምዘራው፡፡
ኒዮ ብራውን፡-
ስለ መጤ ተምች ልጠይቅህ እፈልጋለሁ፡፡ መጀመሪያ በማሳህ ላይ መጤ ተምች መኖሩን ወይም አለመኖሩን የምታየው ስንት ሰዓት ላይ ነው? መኖሩን ለማወቅ ምንድን ነው የምታየው?
ነጋ አሰፋ፡-
ማሳዬን የምቃኘው በጠዋት ነው፡፡ ይህንን ቅኝት የማደርገው ከዘራሁ ከ15 ቀናት በኋላ ሲሆን ምክንያቱም በእነዚህ ቀናት ውስጥ በቆሎ ማቆጥቆጥ ስለሚጀምር ነው፡፡ በቅኝቴ ወቅት የማየው ሰብሉ በእንስሳት መበላት አለመበላቱን እና በመጤ ተምች መበላቱን የሚያሳዩ ምልክቶች መኖር አለመኖራቸውን ነው፡፡ የመጤ ተምቹን (ትሉን) ምልክት ካገኘሁ ወዲያው ለሚመለከተው አካል አሳውቄ ፀረ-ተባይ ኬሚካል እንዲያቀርቡልኝ አድርጌ ማሳው ላይ እረጨዋለሁ፡፡
ኒዮ ብራውን፡-
መጤ ተምቹ ሰብልህን እያጠቃ መሆን አለመሆኑን እንዴት ነው የምታውቀው?
ነጋ አሰፋ፡-
በበቆሎው ላይ የደረሰውን ጉዳት በማየት መጤ ተምች ማሳዬን መውረር አለመውረሩን ማወቅ እችላለሁ፡፡ መጤ ተምቹ ቅጠሎቹን ከላይ ጀምሮ እየተመገበ ወደ ታች ወደ ስሩ ይወርዳል፡፡ ሰብሉም ሙሉ በሙሉ ይደርቃል፡፡
ኒዮ ብራውን፡-
መጤ ተምቹን ለማጥፋት የፀረ-ተባይ ማጥፊያ ኬሚካል አጠቃቀም ልምድህ ምን ይመስላል? ስትጠቀም ምን ምን ቅደም-ተከተሎችን ነው የምትከተለው?
ነጋ አሰፋ፡-
ለሚመለከተው አካል ካሳወቅኩ በኋላ የግብርና ባለሙያዎች ፀረ-ተባይ ኬሚካሉን ይሰጡናል፡፡ በማሳችን ልክ ምን ያክል ፀረ-ተባይ ኬሚካል እንደሚያስፈልግ ይወስናሉ፡፡ እንደየኬሚካሉ አይነት የሚመከረውን የኬሚካል መጠን ከትክክለኛው የውሃ መጠን ጋር ቀላቅለን ባለሙያዎቹ በነገሩን መሰረት ማሳው ላይ እንረጨዋለን፡፡ በእርግጥ ስንረጭ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እናደርጋለን፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ መጠቀም ካለብን በላይ እንዳንጠቀም የግብርና ባለሙያዎቹ ይከታተሉናል፡፡
ኒዮ ብራውን፡-
ለሰጠኸኝ ጊዜ አመሰግናለሁ፣ ነጋ!
ነጋ አሰፋ፡-
ምንም አይደል!
ኒዮ ብራውን፡-
በአማራ ክልል ባህርዳር ከተማ ዙሪያ ወዳለችው ይጎዲ ወረዳም ተጉዤ ነበር፡፡ በዛም ከስድስት ልጆቹና ሚስቱ ጋር የሚኖር ገብሬ አበባው የተባለ አርሶአደር አግኝቻለሁ፡፡ የ66 ዓመቱ አርሶ አደር በማሳው ላይ መጤ ተምችን እንዴት እንደሚከላከልና እንደሚቆጣጠር አብራቶልኛል፡፡
ከእኔ ጋር ለማውራት ጊዜህን ስለሰጠኸኝ አመሰግናለሁ፡፡
ገብሬ አበባው፡-
ምንም አይደል!
ኒዮ ብራውን፡-
ዋነኛው የገቢ ምንጭህ ምንድን ነው?
ገብሬ አበባው፡-
እንደ በቆሎ፣ ዘንጋዳ እና አልፎ አልፎ ደግሞ በርበሬ ያሉ ሰብሎችን እያመረትኩ እሸጣለሁ፡፡ ከማመርተው ውስጥ ሁለት ሶስተኛውን ወደገበያ አወጣዋለሁ፣ የቀረውን ደግሞ ለቤተሰቤ ቀለብ አደርገዋለሁ፡፡
ኒዮ ብራውን፡-
ማሳህ ላይ መጤ ተምችን እንዴት ነው የምትቆጣጠረው?
ገብሬ አበባው፡-
ማሳዬን በየቀኑ ጠዋት ከአንድ ሰዓት እስከ ሁለት ሰዓት እቃኛለሁ፡፡
ኒዮ ብራውን፡-
መጤ ተምች ሰብልህን እያጠቃ እደሆነ ካወቅክ በኋላ የምትጠቀማቸው ዘዴዎች ምን ምን ነው?
ገብሬ አበባው፡-
በፊት የወረዳው የግብርና ባለሙያዎች መጤ ተምቹ ማሳችንን እንዳይወር እንዴት እንደምንከላከል የተለያዩ ስልጠናዎችን ሰጥተውናል፡፡ ካለኝ ልምድ ግን ፀረ-ተባይ ኬሚካል መርጨት መጤ ተምችን ለመቆጣጠር ውጤታማው ዘዴ ነው፡፡ እኔ ራሴ በያዝነው የምርት ወቅት ከባለፈው ወቅት የበለጠ ምርት እንዳገኘሁ መናገር እችላለሁ፡፡
ኒዮ ብራውን፡-
መጤ ተምቹን ለመቆጣጠር መጤ ተምቹን በእጅ ማንሳትን ወይም ትሉን የሚቋቋሙ ተክሎች መትከልን የመሳሰሉ ዘዴዎችን ልትጠቀም ትችላለህ?
ገብሬ አበባው፡-
በእጅ መልቀም በጣም ጊዜ የሚፈጅ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ በየእለቱ ትሉን በእጅ ለመልቀም ቆራጥና ታታሪ አርሶአደር መሆን ያስፈልጋል፡፡ ትሉን ሳትቆጣጠርና ሳትለቅም አንድ ቀን ከዘለልክ ልፋትህ ሁሉ ከንቱ ይሆናል፡፡ ከፍተኛ የሆነ የመጤ ተምች ወረራ በሌለበት ጊዜ ቢሆን በእጅ የመልቀምን ዘዴ እተገብር ነበር፡፡ አሁን ግን የበለጠ ውጤታማ ስለሆነ ፀረ-ተባይ ኬሚካልን መጠቀም እመርጣለሁ፡፡
ኒዮ ብራውን፡-
ከእኔ ጋር ለማውራት ጊዜህን ስለሰጠኸኝ አመሰግናለሁ፡፡
ገብሬ አበባው፡-
ምንም አይደል!
ኒዮ ብራውን፡-
ወደ ደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ተጉዤ በዛ ያሉ አርሶአደሮች ተባይን እንዴት እንደሚቆጣጠሩ ለማወቅ ሞክሬያለሁ፡፡ ሀርቤ ታፈሰ የምትባል በዋናነት በቆሎ የምታመርት አርሶአደር አናግሬያለሁ፡፡ የ37 ዓመቷ አርሶአደር ሰባት ልጆች ያሏት ስትሆን በግብርና መንደር ባለችው ዶሬ ባፈኖ ቀበሌ ነው የምትኖረው፡፡ መጤ ተምችን ስለመቆጣጠር ስትናገር እንስማት፡-
ኒዮ ብራውን፡-
ሰላም ሀርቤ! እንደምን አለሽ?
ሀርቤ ታፈሰ፡-
ደህና ነኝ!
ኒዮ ብራውን፡-
በበቆሎ ማሳሽ ላይ መጤ ተምችን ለመቆጣጠር ስለምትከተዪው ዘዴ ንገሪኝ፡፡
ሀርቤ ታፈሰ፡-
በ2009 አገዳ ቆርቁር በቆሎዬን እንዳያወድመው ለማስቆም ስደክም ነበር፡፡ ያን ጊዜ ነው ተባዩን ለመቋቋም እና ለማገት በመሳብና-መግፋት ዘዴ ልዩ ተክሎችን መትከል እንደሚቻል ስልጠና የወሰድኩት፡፡ ይህ ዘዴ መጤ ተምችንም ለመከላከል ውጤታማ ሲሆን እስካሁን ድረስ በቆሎዬን ለመከላከል እየተጠቀምኩት ነው፡፡ ሰብሎቼ በመጤ ተምች እንዳይወድሙ መጠበቅ የቻልኩ ሲሆን ይህን ዘዴ ከመጠቀሜ በፊት እና ተባዮች በሚያጠቁ ጊዜ አገኝ ከነበረው ምርት የተሻለ አግኝቻለሁ፡፡
ኒዮ ብራውን፡-
የመሳብና-መግፋት ዘዴ ምን እንደሆነ እና በማሳሽ ላይ እንዴት እንደምትተገብሪው እባክሽ አብራሪ፡፡
ሀርቤ ታፈሰ፡-
የሁለት አይነት ተክሎችን ዘር ከአለምአቀፍ የነፍሳት አካል እና ስነ-ምህዳር ማዕከል ተቀበልኩ፡፡ በወሰድኩት ስልጠና መሰረት ተምቾቹን ለመግፋት ዴዝሞዲየም የተባለውን ተክል ዘር በበቆሎው ዘር መሐል መሐል ላይ በመስመር ዘራሁት፡፡ ቀጥሎ የብራቺያራ ዘርን በበቆሎው ዙሪያ ተምቾቹን ለመሳብና የሚጥሉትን እንቁላል ለማስቀረት እንዲጠቅም ዘራሁት፡፡ በነገራችን ላይ እነዚህን ተክሎች ለከብቶቼ መኖነት እጠቀማቸዋለሁ፤ ይህም ለማድለብና ብዙ ወተት እንዲሰጡ ለማድረግ ጠቃሚ እንደሆነ አውቄያለሁ፡፡
ኒዮ ብራውን፡-
ተምቾቹን ለመቆጣጠር ውጤማ ሆነው ያገኘሻቸው ሌሎች ዘዴዎች አሉ?
ሀርቤ ታፈሰ፡-
ባለኝ ልምድ የመሳብና-መግፋት ዘዴ በጣም ውጤታማ ዘዴ ነው፡፡ ፀረ-ተባይ ኬሚካሎችን ከመርጨት የበለጠ ውጤታማ ሀኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ በእርግጥ ፀረ-ተባይ ኬሚካሉ በጤና እና አካባቢ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል፤ በበቂ ሁኔታ ተባዮችን ላያስወግድም ይችላል፡፡ እነዚህ ልዩ ተክሎች ግን ለከብቶች መኖነት በመዋል ተጨማሪ ጥቅም ያላቸው ሲሆን ጤናም ላይ ሆነ አካባቢ ላይ ምንም ጉዳት አያደርሱም፡፡ ስለዚህ ይህን ዘዴ ነው የምመርጠው፡፡
ኒዮ ብራውን፡-
የግብርና ልምድሽን ስላጋራሽን አመሰግለሁ፡፡
ሀርቤ ታፈሰ፡-
ስላወራን ደስ ብሎኛል፡፡
ኒዮ ብራውን፡-
ውድ አድማጮቻችን በሰብል ምርትና አስተዳደር ለይ ከአንድ ባለሙያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጌ ነበር፡፡ መጤ ተምችን ለመቆጣጠር እየተሰራ ስላለው ነገር ያጫወተኝን እነሆ፡-
ኒዮ ብራውን፡-
ልታጫውተኝ ስለፈቀድክ አመሰግናለሁ፡፡
ባለሙያው፡-
ስራችንን ለማየት ስለመጣህ አመሰግናለሁ፡፡
ኒዮ ብራውን፡-
መጤ ተምችን እንዴት መቆጣጠር እንደሚቻል የአርሶአደሮችን ግንዛቤ ለማሳደግ ምን አይነት ስራዎችን እየሰራችሁ ነው?
ባለሙያው፡-
አርሶአደሮቹን ስናሰለጥን በመከላከል ላይ ልዩ ትኩረት እያደረግን ነው፡፡ ሰብል ከሰበሰቡ በኋላ ማረስ ሙሽሬውን ወደ አፈሩ ያስገባዋል፣ ከዚያም ሙሽው ከሽፋኑ እንደወጣ ይደርቃል፡፡ ለመጤ ተምች የማይጋለጡ ሰብሎችን አፈራርቆ መዝራት ማሳው ለተባይ አመቺ እዳይሆን ያደርገዋል፡፡ ማሳቸውን በቋሚነት መከታተል እንዳለባቸውም እናስተምራቸዋለን፡፡
በእርግጥ እነዚህን ዘዴዎች ቢጠቀሙም መጤ ተምቹ አሁንም ማሳቸው ላይ ሊታይ ይችላል፡፡ ስለሆነም አርሶአደሮቹን መጤ ተምቹን በዕጃቸው እየለቀሙ እንዲያወድሙት እናስተምራቸዋለን፡፡ አርሶአደሮቹ ማሳቸውን በሳምንት ሁለት ጊዜ እንዲከታሉ እንመክራቸዋለን፡፡ ይህ አይነቱ ቋሚ ክትትል መጤ ተምቹ ሰብላቸውን የትኛው ቦታ ላይ እያጠቃው እንደሆነ እንዲያውቁና ከቁጥጥር ውጪ ከመሆኑ በፊት መፍትሔ እንዲያፈላልጉ ዋስትና ይሰጣል፡፡ በበቆሎ ማሳቸው ላይ መጤ ተምቹ አንድ ጊዜ ከተስፋፋ በኋላ ፀረ-ተባይ ኬሚካል መርጨት ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ ዘዴ መጤ ተምቹን በማስወገድ ረገድ እጅግ ውጤታማ ቢሆንም ውድ ስለሆነ በብዛት አይቀርብም፡፡ ስለሆነም መጤ ተምቹ እስኪስፋፋ አለመጠበቅ የተሻለ ነው፣ አርሶአደሮቹ እነዚህን ባህላዊ የመከላከያ ዘዴዎች እንዲጠቀሙ የምንመክረውም ለዚህ ነው፡፡
መጤ ተምቹ በፍጥነት የሚስፋፋበት ጊዜ ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ ከአርሶአደሮቹ ጋር ሆነን ፀረ-ተባይ ኬሚካል በመጠቀም ተምቾቹን በመግደል ስርጭታቸውን ተቆጣጥረን ነበር፡፡
ኒዮ ብራውን፡-
ለአርሶአደሮቹ የትኛውን የመጤ ተምች መቆጣጠሪያ ዘዴ ትመክራለህ?
ባለሙያው፡-
የመጀመሪያው እርምጃ አርሶአደሮቹ መጤ ተምች በማሳቸው ላይ ሲያጋጥማቸው ባህላዊ መንገዶችን መተግበር ነው፡፡ ይህ የሚመከረውም ገንዘብ ስለሚቆጥብ እና በቤት ውስጥ ያለ ጉልበት ስለሚበቃው ነው፡፡ የአንድ አርሶአደር ቤተሰብ ማሳውን መከታል እና መጤ ተምቹ ሰብሉን ሳያጠፋው ቀድሞ ማስወገድ ይችላል፡፡ አንዳንድ አርሶአደሮች የዘሩት ሰብል ማጎንቆል ከጀመረ ሶስትና አራት ቀን በኋላ የከብቶችን ሽንት ይረጩበታል፡፡ ይህ ዘዴ ውጤታማ መሆን አለመሆኑን ለመፈተሽ የተደረገ ጥናት ግን የለም፡፡
ኒዮ ብራውን፡-
መጤ ተምችን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ሌሎች ባህላዊ ዘዴዎች አሉ?
ባለሙያው፡-
አዎ! አርሶአደሮች ትሉ የሚመገበው ምግብ ላይ እንደ ኒም፣ አሸዋ፣ አመድ፣ ማዳበሪያ፣ እና ባህላዊ አልኮል መጠጦችን የመሳሰሉ ነገሮች በመጨመር መጤ ተምችን ይቆጣጠራሉ፡፡ መጤ ተምቹ የተገኘው በአነስተኛ የማሳው ክፍል ላይ ከሆነና ሁሉንም የማሳው ክፍል መርጨት የማያስፈልግ ከሆነ ይህ ዘዴ የበለጠ ውጤታማ ዘዴ ይሆናል፡፡ መጤ ተምችን ለመቆጣጠር የሚደረጉ አካባቢያዊ ፈጠራዎችን ማበረታታት የኢትዮጵያ መንግስት ዋና ምክረ-ሀሳብ ነው፡፡
ፀረ-ተባይ ኬሚካሎችን በተመለከተ አርሶአደሮች በቂ ግንዛቤ ስለሌላቸው ትክክለኛውን መጠን ላይጠቀሙ የሚችሉበት እድል አለ፡፡ ይህም በአርሶአደሩም ሆነ በሰብሉ ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያመጣል፤ በተለይ ለረጅም ጊዜ ጥቅም ላይ ከዋለ፡፡ ሰብሎቻቸው ላይ የሚረጩት ኬሚካል አየር ሲስቡ ወደአፋቸው በመግባቱ የጉሮሮ ህመም ያለባቸው እንዲሁም የእይታ ችግር ያለባቸውን አርሶአደሮች አግኝተናል፡፡
ኒዮ ብራውን፡-
እነዚህ ባህላዊ መንገዶች ፀረ-ተባይ ኬሚካል ከመርጨት አንፃር ጊዜ የሚወስዱና ብዙ ጉልበት የሚፈልጉ ናቸው ብለው ስለሚያምኑ ከባህላዊ መንገዶች ይልቅ ፀረ-ተባይ ኬሚካሎችን መጠቀም የሚፈልጉ አርሶአደሮች አሉ፡፡ ሆኖም ፀረ-ተባይ ኬሚካሎችን ሲጠቀሙ ሁልጊዜም አስፈላጊውን ጥንቃቄ ይከተሉ አይከተሉ ማረጋጋጫ የለም፡፡ ስለዚህ ችግር ምን ትላለህ?
ባለሙያው፡-
እያጋጠመን ያለው ችግር የግንዛቤ እጥረት ነው፡፡ አንዳንድ አርሶአደሮች ማሳቸውን በየጊዜው ሳይከታተሉ ቀርተው ፀረ-ተባይ ኬሚካል ከመጠቀም ውጪ ሌላ አማራጭ እስከማይኖራቸው ጊዜ ድረስ ይጠብቃሉ፡፡ አስፈላጊውን ክትትል የማያደርጉባቸው የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡- አርሶአደሮች በሀይማኖታዊ ክብረ-በዓላት ወቅት አይሰሩም፣ አንዳንድ ጊዜም እንደ ጤፍ እና ማሽላ ያሉ ሎሎች ምርቶችን በመሰብሰብ ባተሌ ይሆናሉ፡፡ የመጤ ተምቹን በፍጥነት የመስፋፋት ባህሪን ለመቆጣጠር ፀረ-ተባይ ኬሚካሎችን ወደመጠቀም ያዘነብላሉ፡፡ ኬሚካሉ ውጤታማ ቢሆንም እንኳን ጤናቸውን አደጋ ላይ እንደሚጥል ግን ግንዛቤው የላቸውም፡፡
የጤና አደጋዎችን ለመቀነስ ለአርሶአደሮቹ በሚረጩበት ወቅት ስለሚያደርጉት መከላከያ እና የንፋስ አቅጣጫን ስለመለየት ስልጠና እየሰጠን ነው፡፡ በኬሚካል አጠቃቀም ወቅት ማድረግ ያለባቸውን እና የሌለባቸውን ነገር እንነግራቸዋለን፡፡ ነገርግን አሁንም እንደ ጓንት እና ፊት መከለያ ያሉ መከላከያዎችን የመግዛት አቅም ስለሌላቸው የአርሶአደሮች ጤና እየታወከ እንደሆነ የሚያሳዩ ክስተቶች አሉ፡፡ የተወሰኑትም መከላከያዎቹን ማድረግ ያለውን ጥቅም በመናቅ የማይጠቀሙ አሉ፡፡ ስለዚህ የአርሶአደሮችን ግንዛቤ በማሳደግ ረገድ በጣም ረጅም መንገድ ይቀረናል፡፡
ኒዮ ብራውን፡-
አመሰግናለሁ! የምትጨምረው ነገር አለህ?
ባለሙያው፡-
መጤ ተምችን በአግባቡ ለመቆጣጠር ጥሩ የግብርና ልምዶችን መተግበር እጅግ አስፈላጊ ቅድመሁኔታ መሆኑን መግለፅ እፈልጋለሀ፡፡ ጥሩ የግብርና ልምዶች ጤናማና መጤ ተምች የሚያደርሰውን ጉዳት የሚቋቋሙ ሰብሎችን ለማምረት ያስችላሉ፡፡ ለምሳሌ፡- መሬቱ በአግባቡ ካልተዘጋጀ ሰብሉ በተመሳሳይ መልኩ አይበቅልም አፈሩም ረግረግ ይሆናል፡፡ መጤ ተምችን ለመቆጣጠር ተፈጥሯዊና ሰው-ሰራሽ ማዳበሪያዎችን በመጠቀም ለሰብሉ የተመጣጠነ ምግብ ማቅረብና የተቀናጀ የመጤ ተምች መቆጣጠሪ መንገድን መጠቀም አስፈላጊ ነው፡፡ ለአርሶአደሮች የምንሰጠው ጥሩ ምክር ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ ሰብል እስከሚሰበሰብ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ጥሩ የግብርና ልምዶችን መተግበር እንዳለባቸው ነው፡፡
ኒዮ ብራውን፡-
ስታዳምጡት የነበረው የአርሶአደሮችን ፕሮግራም ነው፡፡ ዛሬ በአማራ ክልል እና በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች ህዝቦች ክልል ያሉ አርሶአደሮች መጤ ተምችን ለመቆጣጠር እና መጤ ተምቹ ሰብሎቻቸውን እንዳያጠቃ ለመከላከል እያደረጉት ስላለው ጥረት ታሪኮችን ነግረናችኋል፡፡ ስላዳመጣችሁን እናመሰግናለን፡፡ በሚቀጥለው ሳምንት በተመሳሳይ ሰዓት ሌላ ዝግጅት ይዘን ስለምንቀርብ እንድታዳምጡን እንጋዛለን፡፡ እስከዛው መልካም ሳምንት!

Acknowledgements

ምስጋና

አዘጋጅ፡- ኒዮ ብራውን (በአፍሮኤፍኤም 105.3 ከፍተኛ አዘጋጅ፣ አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ)

አርታኢ፡- አመንቲ ጫሊ (በፊድ ዘ ፊውቸር ኢትዮጵያ ቫልዩ ቼይን አክቲቪቲ የብሔራዊ ሰብል ምርት ባለሙያ፣ አዲስ አበባ ኢትዮጵያ)

የመረጃ ምጮች፡-

ገብሬ አበባው፣ አርሶአደር፣ ይጎዲ ቀበሌ፣ ባህርዳር አካባቢ፣ አማራ ክልል፣ ጥር 10፣ 2011 ዓ.ም

ነጋ አሰፋ፣ አርሶአደር፣ ይነሴ ቀበሌ፣ ባህርዳር አካባቢ፣ አማራ ክልል፣ ጥር 10፣ 2011 ዓ.ም

ሀርቤ ታፈሰ፣ አርሶአደር፣ ዶሬ ባፈኖ ቀበሌ፣ ሀዋሳ፣ ደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች ህዝቦች ክልል  ጥር 10፣ 2011 ዓ.ም

መለሰ አሻግሬ፣ የሰብል ምርት እና አስተዳደር ባለሙያ፣ በባህርዳር አካባቢ የግብርና ቢሮ፣ አማራ ክልል፣ ጥር 10፣ 2011 ዓ.ም

ይህ ፅሁፍ የዩኤስኤድ የፊድ ዘ ፊውቸር ኢትዮጵያ ቫልዩ ቼይን አክቲቪቲ በሆነው በአይሲቲ የተደገፈ መጤ ተምች ላይ ያተኮረ የሬድዮ ፕሮግራም ፕሮጀክት ድጋፍ የተሰራ ነው፡፡