Notes to broadcasters

ማስታወሻ ለጋዜጠኛው

በብዙ የአፍሪካ ክፍሎች የአየር ንብረት ለውጥ ለአርሶ አደሮች ተግዳሮት እየፈጠረባቸው ነው፡፡ በምስራቅ ኬንያ ያሉ አርሶ አደሮችም ረጃጅም የድርቅ ወቅቶች እጋጠሟቸው ነው፡፡

በኬንያ ያሉ ብዙ የቁም እንስሳት አርቢዎች ከብት ማርባት ይመርጣሉ፡፡ የአየር ንብረቱ እየተለወጠ ሲመጣ ግን አንዳንድ አነስተኛ አርሶ አደሮች ፍየል ማርባት አዋጭ እና ላም ከማርባት ይልቅ የተሻለ አማራጭ ሆኖ አግኝተውታል፡፡

በተለይ ደረቅ በሆኑ አካባቢዎች ፍየሎች ብርቱ እንስሳት ናቸው፡፡ ብዙ መኖ አይመገቡም፣ ምግባቸው ባለው ውሃ ብቻ እየተጠቀሙ ለቀናት ውሃ ሳይጠጡ መቆየት ይችላሉ፣ ብዙ መሬት አያስፈልጋቸውም፣ በደንብ ከተያዙ ደግሞ በስድስት ወራት ውስጥ ለመሸጥ የሚያስችል ክብደት ይኖራቸዋል፡፡

ይህ ስክሪፕት አንድ አነስተኛ አርሶ አደር ከፍየሎቹ ወተት እና ቀልዝ እንዴት ማግኘት እንደሚችል እና በመጨረሻም ፍየሎቹን በመሸጥ እንዴት ገንዘብ እንደሚያገኝ ያሳያል፡፡
ስክሪፕቱ በትክክለኛ ቃለ መጠይቆች መሰረት ተዘጋጅቷል፡፡ ስክሪፕቱን በእናንተ አካባቢ በተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ጥናት አድርጋችሁ ስክሪፕት ለማዘጋጀት ሃሳብ እንዲሰጣችሁ ልትጠቀሙበት ትችላለችሁ፡፡ ወይንም ይህንን ስክሪፕት ራሱን ተናጋሪዎቹን የሚወክል የድምጽ ተዋንያን በመጠቀም በጣቢያችሁ አዘጋጅታችሁ ልታቀርቡት ትችልላላችሁ፡፡ ራሱን የምትጠቀሙበት ከሆነ ፕሮግራሙ መጀመርያ ላይ ለአድማጮቻችሁ ድምጻቸው የሚሰማው ሰዎች ቃለ መጠይቁ ላይ ያሉት ትክክለኛ ሰዎች ሳይሆኑ ተዋንያን መሆናቸውን ግለጹ፡፡

ይህንን ስክሪፕት ተናጋሪዎቹን የሚወክሉ የድምጽ ተዋያንን በመጠቀም የመደበኛ ግብርና ፕሮግራማችሁ አካል አድርጋችሁ ልታቀርቡት ትችላላችሁ፡፡ እንዲህ የምታደርጉ ከሆነ ፕሮግራሙ መጀመርያ ላይ ለአድማጮቻችሁ ድምጻቸው የሚሰማው ሰዎች ቃለ መጠይቁ ላይ ያሉት ትክክለኛ ሰዎች ሳይሆኑ ተዋንያን መሆናቸውን ግለጹ፡፡

ይህንን ስክሪፕት በሃገራችሁ የወተት ፍየል ስለማርባት ጥናት ለማድረግ ማስረጃ አድርጋችሁ ወይም ፕሮግራም ለመፍጠር እንደ ፍንጭ ልትጠቀሙበት ትችላላችሁ፡፡

የወተት ፍየል የሚያረቡ አርሶ አደሮችን አነጋግሩ፡፡ የሚከተሉትን ዓይነት ጥያቄዎች ልትጠይቋቸው ትችላላችሁ፡-
የወተት ፍየል ማርባት ምን ጥቅም አለው?
ተግዳሮቶቹስ ምንድን ናቸው? ተግዳሮቶቹን እንዴት ተወጣችኋቸው?
በዚህ አካባቢ አርሶ አደሮች ፍየል በማርባት ገንዘብ ማግኘት የሚችሉ ይመስላችኋል?

የስልክ ፕሮግራም በማዘጋጀት አርሶ አደሮች ስለኒዚህ ጉዳዮች እንዲያወሩ ማድረግ ትችላላችሁ፡፡ አንድ ባለሙያ በመጋበዝ ለአርሶ አደሮቹ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ምላሽ እንዲሰጥ ማድረግ ትችላላችሁ፡፡

ስክሪፕቱ የሚወስደው ሰዓት ግምት፡- 25 ደቂቃ፣ መግቢያ እና መውጫ ሙዚቃን ጨምሮ፡፡

Script

የመግቢያ ሙዚቃ ከፍ ብሎ ከዚያ ዝቅ ይላል

አቅራቢዋ:
እንደምን አደራችሁ፤ ወደ አርሰ አደር ለአርሶ አደር ፕሮግራማችን እንኳን በሰላም መጣችሁ፡፡ በዛሬው ፕሮግራማችን የድርቅን ተጽእኖ እና አርሶ አደሮች እንዴት እየተቋቋሙት እንደሆነ እንነጋራን፡፡ በምስራቃዊ ኬንያ በምትገኘው በምዊንጊ ያሉ አንዳንድ አርሶ አደሮችን ጎብኝቻለሁ፤ እነዚህ አርሶ አደሮች በተሳካ ሁኔታ ከከብት አርቢነት ወደ ወተት ፍየል አርቢነት ተቀይረዋል፡፡ በመጀመርያም የአርሶ አደሮች አስተባባሪ ከሆነው ከማክዶናድ ምኑቬ ጋር ተነጋግሪያለሁ፡፡
አቅራቢዋ:
ድርቅ የሰዉን መተዳደርያ በምን መልክ ቀይሮታል?
ማክዶናድ ምኑቬ:
በምስራቃዊ ኬንያ ዋነኛው መተዳርያ የዝናብ ግብርና ነበር፤ አብዛኛዎቹ ሰዎች በግብርና ይተዳደሩ ነበር፡፡ ግብርናን ግን ረጃጅም ደረቅ ወቅቶች ተገዳድረውታል፡፡ ይሄ አካባቢ በከፍተኛ ደረጃ ከተጎዱት አካባቢዎች አንዱ ነው – ኑኢን ምዊንጊ የሚኖሩ ሰዎች ምግብ አጥተው ውሻ ይበሉ እንደነበር ዜናውን ሳትሰሚ አትቀሪም!
አቅራቢዋ:
ድርቁ አርሶ አደሮች ላይ ምን ምን ዓይነት ተጽእኖዎች ፈጥሮባቸው ነበር?
ማክዶናድ ምኑቬ:
ዘር አልበቅል እያለ፣ የሰብል ምርትም እየቀነሰ እና ወቅታዊ ወንዞች በመድረቃቸው ብዙ የቁም እንስሳት እየደከሙና በመጨረሻም እየሞቱ እንዲሁም ዝናብ ባለመኖሩ በነዚህ በነዚህ ጉዳዮች አርሶ አደሮች ያማርሩ ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ አርሶ አደሮችን በመንግስት እርዳት ላይ ጥገኛ እንዲሆኑ አስገድዷቸው ነበር፡፡
አቅራቢዋ:
የደረቅ ወቅቶችን እንዴት ማለፍ ቻሉ?
ማክዶናድ ምኑቬ:
አርሶ አደሮች ሌሎች መተዳደርያ መንገዶችን መፈለግ ጀመሩ፤ በሕገ ወጥ መንገድ ዛፍ ይቆርጡ፣ ከሰል ያከስሉ እና ከደረቁ ወንዞችም አሸዋ ያመርቱ ነበር፡፡ ይህም መሬታችንን ለግብርና እንዳይሆን የበለጠ አጎሳቁሎት ነበር፡፡

ወንዶች ወደ ከተማ እየሄዱ የግንባታ ቦታዎች ላይ ጥቂት ገንዘብ ለማግኘት በጉልበት ሠራተኛነት መቀጠር ጀመሩ፡፡ ልጆችም ክፍል ውስጥ በረሃብ መቀመጥ ስለማይችሉ ወደዚሁ ሥራ ተሰማርተው ነበር፡፡ ገበታ ላይ ምግብ ለማቅረብ ሁሉም አስተዋጽኦ ማድረግ ነበረበት፡፡

አሁን ግን አርሶ አደሮች ድርቁን የሚቋቋሙበት መንገድ አግኝተዋል፡፡ አሁን ድርቅ የሚቋቋሙ ሰብሎችን እያበቀልን፣ ድርቅ የመቋቋም ችሎታ ያላቸው የፍየል ዝርያዎችን እያረባን ጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ያለን፡፡

አቅራቢዋ:
ድርቁን ለመቋቋም ወደዚህ ዓየንት አሠራር መቀየራቸው የአርሶ አደሮችን ሕይወት አሻሽሎታል?
ማክዶናድ ምኑቬ:
እንዴታ፡፡ ፍየል ማርባት ለጀመሩት የምዊንጊ አርሶ አደሮች ዝናቡ ትንሽ እንኳን ቢሆን ወተት ያገናኛሉ፤ ፍየሎችን ሽጠው ገንዘብ ያገኛሉ፤ ድርቅ ለሚቋቋሙ ሰብሎቻቸውም ፍግ ያገኛሉ፡፡ ከአምስትና 10 ዓመት በፊት ይሆን እንደነበረው አሁን ቤተሰቦቻው አይራቡም፡፡ ሕጻናቱ ጤነኞች ናቸው፣ ትምሕርታቸውምንም አያቋርጡም፡፡ እንዲያውም አርሶ አደሮቹ አልፎ አልፎ ለትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር የሚሆን ጥቂት እህል ያቀርባሉ፡፡

አርሶ አደሮች ብዙ ፍየሎች ሲኖሯቸው እና አንድ ፍየል ሸጠው ጥሩ ብር ካገኙ ጥሩ የውሃ ማጠራቀሚያ በርሜሎች እንዲገዙ እናበረታታለን፡፡ በነዚህ በርሜሎች የሚይዙት ውሃ ለረጅም ጊዜ ያገለግላቸዋል፤ ዝናብ በተጠበቀበት ጊዜ ሳይመጣ ሲቀርም ይጠቀሙበታል፡፡ ዝናብ ሲመጣ ደግሞ ው እንዲያቁሩ እናበረታታቸዋለን፡፡ ይሄ በርግጥ የአርሶ አደሮቹን ህይወት ቀይሮላቸዋል፡፡

የመግቢያ ሙዚቃ ከፍ ብሎ ዝቅ ይልና ይጠፋል

አቅራቢዋ፡
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የኬንያ አነስተኛ አርሶ አደሮች ብዙም ፍየል አያረቡም ነበር፡፡ የፍየል ወተትም እምብዛም አይጠጡም ነበር፡፡ ያ ግን አሁን ተቀይሯል፡፡ በአርሶ አደሮች ቤት ፍየል የሚገኝበት አንድ የምስራቃዊ ኬንያ አነስተኛ መንደር ጎብኝቼ ነበር – በዚያ መንደር የፍየል ወተት በጣም ተወዳጅ መጠጥ ነው፡፡

ከጥቂት አመታት በፊት በዚህ አካባቢ ለሚኖሩ አብዛኞቹ አርሶ አደሮች ተመራጩ እንስሳ ላም ነበር፡፡ ላሞች ግን የተራዘመ ድርቅ መቋቋም አይችሉም፡፡ የአካባቢው አርሶ አደሮች ወደ ፍየል መቀየራቸው አስደስቷቸዋል፡፡ ከነዚህ አርሶ አደሮች አንዷ ቴሬሲያ ናት፡፡ ስለፍየሎቿ ስታወራ ደስታዋን መቆጣጠር ያቅታታል፡፡ በቅርቡ ወደ ምስራቃዊ ኬንያዋ ምዊንጊ የሄድኩኝ ጊዜ አግኝቻት ነበር፡፡

የእርሻ ድምጾች፡፡ የሰው ኮቴ ድምጽ፡፡ ድምጹ ይቀንስና ይቀጥላል

አቅራቢዋ፡
አሁን የምንገኘው በቴሬሲያ እርሻ ነው፤ እርሻው ከሁለት ቀርጥ ትንሽ ዝቅ ይላል፡፡ ከመኖርያ ቤቷ ጎን የፍየል ጎረኖ አለ፡፡ ቴሬሲያ ስንት ፍየሎች አሉሽ?
ቴሬሲያ:
አሁን አስር ፍየሎቸ አሉኝ፡- ሁለት ወንድ እና ስምንት ሴቶች፡፡ ስጀምር ሦስት ነው የነበረኝ፡፡
አቅራቢዋ፡
በጣም በዝተውልሻል፡፡ ምን ዓይነት ፍየሎች ነው ያሉሽ?
ቴሬሲያ:
ከወንድ ቶገንበርግ ፍየል እና ከአካባቢያችን ሴት ፍየሎች የተዳቀሉ ናቸው፡፡
አቅራቢዋ፡
ፍየል ማርባት የጀመርሽው እንዴት ነው?
ቴሬሲያ:
በፋርም አፍሪካ የወተት ፍየሎች ማሻሻያ ፕሮጀክት አማካኝነት የቶገንበርግ ወንድ ፍየል ያገኙ አርሶ አደሮች ነበሩ፡፡ በጊዜው በጣም ጥቂት ሰዎች የዚሀ አካባቢ ፍየሎች ነበሩን፤ ስለ ቶገንበርግ ግን ሰምተን አናውቅም ነበር፡፡ ግን የተዳቀሉት ፍየሎች በተለይ እንደኛ ላለ ደረቅ አካባቢ እንዴት እንደሚጠቅሙ አወቅን፡፡

ከወንድ ቶገንበርግ ፍየል ጋር ለማዳቀል ፕሮጀክቱ የአካባቢው ዝርያ ፍየል ገዝተን እንድንመጣ ይፈልግ ነበር፡፡ ጥርጣሬ ነበረኝ፤ ቢሆንም ሦስት ሴት ፍየሎች ገዝቼ በወንድ ቶገንበርግ ፍየል እንዲጠቁልኝ ወሰድኩ፡፡

ሦስቱም ሁለት ሁለት ግልገል ወለዱና ተገረምኩኝ፡፡ ከአካባቢያችን ዝርያዎች ይልቅ እነዚህ ትልቅ እና ጠንካራ ነበሩ፡፡ ከስድስት ወር በኋላ ጥቂቶቹን ሸጬ ሴቶቹን እንደገና ወስጄ አስጠቃሁ፡፡ ድጋሚ የተወለዱት ከመጀመርያዎቹ ይልቅ ጠንካራ ነበሩ! እንዲህ እያደረኩ አበዛኋቸው፡፡

አቅራቢዋ:
እንዴት ትመግቢያቸዋለሽ?
ቴሬሲያ:
ጭድ እና የቁጥቋጦ ቅጠሎች እመግባቸዋለሁ፤ አልፎ አልፎ ደሞ ከግብርና ሱቅ የእንስሳ መኖ እየገዛሁ እሰጣቸዋለሁ፡፡ የማዕድን ጨውም እሰጣቸዋለሁ፡፡ ተጨማሪ ምግቡ ወተታቸውን ያበዛዋል፡፡ ሦስት ወር ሲሞላቸው የሆድ ትላትል መዳኒት እሰጣቸዋለሁ፡፡ ሲያማቸው የእንስሳ ሐኪም ጠርቼ አሳክማለሁ፡፡
አቅራቢዋ:
ፍየሎች ጥሩ ጎረኖ እንደሚፈልጉ ይገባኛል፡፡ ፍየሎች ጤነኛ እንዲሆኑ ምን ዓይነት ጎረኖ ያስፈልጋቸዋል?
ቴሬሲያ:
መጀመርያ የፍየሎቹን ጎረኖ ከበጠጣቸው በላይ ከፍ የሚል እርብራብ ወለል አድርገሽ መሥራት አለብሽ፡፡ ፍየሎቹ በጠጣቸው ላይ ከተኙ ትላትል እና ሌሎች ጥገኛ ነፍሳት በመንጋው መካከል በቀላሉ በመሰራጨት ሊያሳምሟቸው ይችላሉ፡፡ በተጨማሪ ጎረኖውን በየቀኑ አጸዳለሁ፡፡
አቅራቢዋ:
ሁል ጊዜ ልክ እንዲዚህ ተዘግቶባቸው ነው የሚኖሩት?
ቴሬሲያ:
ሁል ጊዜ አይደለም፡፡ አልፎ አልፎ ከግቢ ውጭ ያሉ የዱር ዛፎች እና ቁጥቋጦዎችን ይቀነጣጥባሉ፡፡ ግን በሽታ እንዳይተላለፍባቸው ወይም ከዚህ አካባቢ ዝርያዎች ጋር እንዳይዳቀሉበኝ ስል ውጭ ካሉ ፍየሎች ጋር እንዳይቀላቀሉ አደርጋለሁ፡፡
አቅራቢዋ:
ከሌሎች የቤት እንስሳት አንጻር በዚህ አካባቢ ፍየል ማርባት ምን ይጠቅማል?
ቴሬሲያ:
ላም አድጋ ለመሸጥ እስከምትደርስ ድረስ ረዘም ያለ ጊዜ ትወስዳለች፡፡ የቶገንበርግ ዲቃላ በስድስት ወር አድጎ 6,000 ብር ይሸጣል፡፡ ላም ዓመት ሞልቷት እንኳን አትሸጥም – ብትሸጫትም የረባ ብር አታገኝባትም፡፡

አገር በቀል ፍየሎች በስድስት ወር በደንብ ስለማያድጉ ለመሸጥ አይደርሱም፡፡ አመት ከሞላቸው በኋላ እንኳን 850 ብር ቢሸጡ ነው፡፡ ዲቃላው ደግሞ ከተንከባከብሽው እስከ ስድስት ዓመት ሊኖር ይችላል፡፡

አቅራቢዋ:
የዲቃላዎቹ ወተት ምርት ብዙ ነው?
ቴሬሲያ:
አዎ፡፡ ሲዎልዱ ደግሞ ዲቃላዎቹ በቀን ሁለት ሊትር ወተት ይሰጣሉ – ጧት አንድ ሊትር ማታ አንድ ሊትር፡፡ ከአንድ ወይም ከሁለት ወር በኋላ ይቀንስና ለእንድ ሊትር እሩብ የጎደለው በቀን ሁለት ጊዜ ይሰጣሉ፡፡ በዚህ ልክ ለረጅም ጊዜ ወተት ይሰጣሉ፤ ኋላ ግን በቀን ወደ ግማሽ ሊትር ይወርዳል፡፡ ያን ጊዜ ለመጠቃት ደርሰዋል ማለት ነው፡፡ አንድ ፍየል ባንድ ጊዜ አንድ ግልገል ትወልዳለች፤ አንዳንዶቹ ግን ሁለትም ይወልዳሉ፡፡ ሁለት ከሚወልድት ፍየሎች ዘር ካስቀረሽ ባንድ ጊዜ ሁለት ሁለት የሚወልዱ መንጋዎች ይኖሩሻል፡፡
አቅራቢዋ:
የፍየል ወተት በዚህ አካባቢ ተቀባይነት አለው?
ቴሬሲያ:
ከጥቂት ኣመት በፊት ከነበረው አሁን ይሻላል፤ ብዙ ሰዎች ግን የፍየል ወተት ሽታው ደስ አይልም ይላሉ፡ ፡ ግን ወንዱን ፍየል ወተት በሚታለብበት ጊዜ እና ከወተቱም እንዳይደርስ ካደረግሽው ያንን ጠረን መከላከል ይቻላል፡፡

ሃቁ ግን ፍየሎችሽን እንደተንከባከብሻቸው ልክ ጥሩ ወተት ታገኛለሽ፡፡ የፍየል ወተት ላይ ያለው ጠረን የሚመጣው የሚታለቡትን ፍየሎች ከወንዶች ፍየሎች ጋር ስታኖሪያቸው ነው፡፡ እዚህ አካባቢ የፍየል ወተት መሸጥ የጀምርኩኝ ጊዜ የፍየል ወተት በፍጹም የማይጠጡ ሰዎች ነበሩ፡፡ አሁን ግን ይጠጡታል፡፡ ሽታ ስለሌለው ያንቺን ወተት እንወዳለን ይሉኛል፡፡

አቅራቢዋ:
ፍየሎችሽ ሰብል ለማምረት ረድተውሻል?
ቴሬሲያ:
አዎ በብዙ መልኩ፡፡ ፍየሎች ሸጬ የማገኘው ገንዘብ እርሻዬን ለሚያርሱልኝ ሠራተኞች ለመክፈል እና ዘር ለመግዛት ይረዳኛል፡፡ ከፍየሎቹም ፍግ ስለማገኝ መግዛት አያስፈልገኝም፡፡
አቅራቢዋ:
ከፍየሎችሽ በቂ ፍግ ታገኛለሽ?
ቴሬሲያ:
መዝሪያ ቦታዬ ትልቅ ስላልሆነ ይበቃኛል፡፡
አቅራቢዋ:
ይሄ ሥራ ግን ለሴቶች የሚከብድ ይመስላል፡፡ ለምን ወደ ሥራው ለመግባት ወሰንሽ?
ቴሬሲያ:
በጣም አትራፊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ትርፉ ነው አተኩሬ እንድሠራ እና እንድወደው ደረገኝ፡፡

ፍየሎቹ ጥሩ ሆነውልኛል፡፡ ወተቱን በቤታችን ጠጥተን የተረፈንን እሸጠዋለሁ፡፡ ሸጬ በማገኘው ብር ለቤት የሚያስፈልገንን እገዛለሁ፡፡ ገንዘብ በጣም ሲያስፈልገኝ አንድ ወይም ሁለት ፍየል ሸጬ ለትምህርት ቤት ክፍያ ወይም ለሐኪም እጠቀማለሁ፡፡

ከፍየሎቹ ባገኘሁት ብር የእህል መሸጫ ሱቅ ከፍቻለሁ፡፡ ብድርም ወስጃለሁ፤ በአርሶ አደር ቡድናችንም ፍየሎቼን ሸጬ ያገኘሁትን ገንዘብ ቆጥቤያለሁ፡፡ መኪና ገዝቻለሁ፤ አሁን ፍየሎቼን እና እህሌን ወደ ገበያ ለመሸጥ አመላልስበታለሁ፡፡

ዋናው ግን በነዚህ ፍየሎች የተነሳ ሦስቱ ልጆቼ ትምህርት ቤት መግባታቸው ነው፡፡ ሁለቱ ሴቶች ዩኒቨርሲቲ ጨርሰዋል፤ አንድ ልጅ በኮሌጅ አለኝ፡፡ የልጅ ልጆቼ የፍየል ወተት ይወዳሉ፤ በጣም ጤነኛ ናቸው!

አቅራቢዋ:
አድማጮቻችን ስትከታተሉት የነበረው ከቶገንበርግ ወንድ ፍየሎች እና ከአካባቢው ሴት ፍየሎች የተገኙ ዲቃላ ፍየሎችን ከምታረባው አርሶ አደር ቴሬሲያ ጋር ያደረግነውን ቀይታ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በቴሬሲያ መንደር የሚኖር ፍየል አዳቃይ ጋር እንገናኝ፡፡

መሸጋገርያ ሙዚቃ ወደ እርሻ ድምጽ እየተቀየረ ይሄዳል፡፡ ድምጹ ቀንሶ ከንግግሩ ስር ይቀጥላል፡፡

ቴሬሲያ:
ይሄው የጆሴፍ ግቢ ደርሰናል፡፡ ዛሬ በጣም ይሞቃል፣ እንግዲህ ዮሴፍ ተኝቶ ሊሆን ይችላል፡፡ እስኪ ልፈልገው፡፡ (ትጣራለች) ዮሴፍ፣ ዮሴፍ፣ እንግዶች መጥተዋል፡፡
ዮሴፍ:
(ከማይክ ውጭ) መጣሁ ትንሽ ጠብቁኝ፡፡

የእግር ኮቴ ድምጽ ይሰማል

ዮሴፍ:
(እያዛጋ) ይቅርታ አርጉልኝ፡፡ (ይስቃል) ሽማግሌ ነኝ እንግዲህ ጸሃዩ ሲያቃጥል እንቅልፍ ይጥለኛል፡፡ እንኳን ወደ ግቢዬ በደና መጣችሁ፡፡ እንደምታዩት ትንሽ ቦታ ናት – የኔ ቤት እና የፍየሎቹ ጎረኖ ነው ያለው ሁሉም አንድ ቀርጥ በማይሞላ መሬት ላይ፡፡
ቴሪሲያ:
ዮሴፍ፣ ዊኒን ተዋወቃት፡፡ ስለፍየሎች ለማውራት ዛሬ ትመጣለች ያልኩህ እሷን ነበር፡፡
ዮሴፍ:
እንዴት ዋልሽ፡፡ ዮሴፍ እባላለሁ፡፡ የቶገንበርግ ፍየል ከአገር በቀል ፍየሎች ጋር አዳቅላለሁ፡፡ አሁን ንጹህ የቶገንበርግ ዝርያ የሆነ ፍየል እና ሁለተ ዲቃላዎች አሉኝ፡፡
አቅራቢዋ:
ጤነኛ ይመስላሉ፡፡ ቶገንበርጉን ስንት ትሸጠዋለህ?
ዮሴፍ:
አሁን በየቀኑ ገንዘብ እያገኘሁበት ስለሆነ አልሸጠውም፡፡ ሁለቱን ዲቃላዎች ለግብርና ኤግዚበሽን ለማቅረብ እያደለብኳቸው ነው፡፡ እያንዳንዳቸው 6,000 ብር ሊሸጡ ይችላሉ፡፡ ለስድስት ወር ፍየል ጥሩ ዋጋ ነው፡፡

ፍየሎችሽን ከተንከባከብሻቸው ቤተሰብሽን ይንከባከቡልሻል፡፡ ከሰድስቱ ልጆቼ ሁለቱን ያስተማሩልኝ እነዚህ ፍየሎች ናቸው፡፡ ፍየሎቹ የናይሮቢው የንግድ ትርኢት ላይ ሽልማት አሸንፈው ነበር፡፡ በሚታለቡ ጊዜ ተጨማሪ ምግብ ካገኙ ብዙ ወተት ይሰጣሉ፡፡ አንድ ጤነኛ ዲቃላ ፍየል በቀን ሦስት ጊዜ ትታለባለች፡፡ አንዳንድ ገበሬዎች ከላም ይልቅ በነዚህ ፍየሎች የተሸለ ትርፍ ያገኛሉ፡፡ እኔ እነሱን እመርጣለሁ፡፡

አቅራቢዋ:
ቶገንበርግ ፍየልህ በቀን ስንት ሴት ፍየሎችን ያጠቃል?
ዮሴፍ:
በደንብ ከተቀለበ በቀን አምስት ወይም ከዚያ በላይ ሴት ፍየሎችን ያስተናግዳል፡፡
አቅራቢዋ:
ምን ትመግበዋለሁ?
Joseph:
ብዙ ምግብ ነው የሚበላው፡፡ ሳር እና ቅጠላ ቅጠል ቆርጬ አደርቅለታሁ፡፡ አንዳንዴ ሜዳ ላይ እንዲግጥ እለቀዋለሁ፡፡ ደረቅ ሳር ሲበላ ብዙ ውሃ ይጠጣል – አሳ በይው፡፡ አርጥብ ቅጠል ከበላ ግን ብዙም ውሃ አይፈልግም፡፡ በጣም ሞቃት በሚሆንበት ጊዜ ጥላ አደርግለታሁ፡፡ ጥላ ካላገኘ አየሩ ሞቃት ሲሆን በጣም ትንሽ ነው የሚበላው፡፡
አቅራቢዋ:
ቶገንበርጉ ፍየል ከመቼ ጀምሮ ነው ያለህ?
ዮሴፍ:
ጡሮታ ስወጣ ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ፡፡ ፍየሎቹን ከማግኘቴ በፊት መሰረታዊ የእንስሳት አያያዝ፣ ጥሩ መጠለያ አሠራር እና ጭድ አዘገጃት ስልጠና ወሰድኩኝ፡፡
አቅራቢዋ:
ሌሎች አርሶ አደሮች ሴት ፍየሎች ይዘው ሲመጡ ስንት ታስከፍላቸዋለህ?
ዮሴፍ:
የአርሶ አደሮች ቡድን አባል ለሆኑ 17 ብር ያህል እናስከፍላለን፤ አሁን ግን እነዚህን ፍየሎች መንከባከብ ውድ ስለሆነ 34 ብር ልናደርገው ነው፡፡ አባል ያልሆኑት እጥፍ ይከፍላሉ፡፡
አቅራቢዋ:
ላም ማርባት ታስባለህ?
ዮሴፍ:
እንዴት እቀልባቸዋለሁ? ከከብቶች አንጻር ፍየሎች ትንሽ ጉልበት እና ጊዜ ይበቃቸዋል፡፡ የሚበሉትም አነስ ይላል፤ ከላሞች ይልቅም እነሱ ከአካባቢው ጋር በቀላሉ ይለማመዳሉ፡፡ በቀላሉ አይታመሙም፤ በበጋው ወቅት አንዳንድ ጊዜ ከባድ ዝናብ ስለሚጥል ፍየሎቹን ብይዝ ይሻለኛል፡፡ እነዚህን ፍየሎች ማራባት በጣም ደስ ብሎኛል!

መሸጋገርያ ሙዚቃ

አቅራቢዋ:
ተመልሰናል አድማጮቻችን፡፡ የወተት ፍየሎን ስለማርባት እየተማርን ነው፡፡ የወተት ፍየል የምታረባዋን እና ፍየል የሚያዳቅለውን አርሶ አደር አዳምጠናል፡፡

ስለዚህ ከወተት ፍየሎቻችሁ ከፍተኛ ጥቅም ለማግኘት እንዴት ልትንከባከቧቸው ይገባል? የእንስሳት እርቢ እና ዘረ መል ባለሙያ የሆኑትን ፕሮፌሰር አይዛክ ሳንጋ ኮስጌይን አነጋግሬያቸዋሁ፡፡ በመጀመርያ በአፍሪካ ስላሉ የፍየል ዝርያዎች ጠየኳቸው፡፡

ኮስጌይ:
ፍየሎች በሦስት ምድብ ይከፈላሉ፡፡ የመጀመርያዎቹ አገር በቀል ፍየሎች ናቸው፤ እነዚህ ፍየሎች በአርሶ አደሮቻችን እጅ የሚገኙ ሲሆኑ ብዙውን ጊዜ ለስጋ ምርት ይውላሉ፡፡ ወተትም ስጋም የሚሰጡ መንታ ጥቅም ያላቸው ፍየሎችም አሉን፡፡ በመጨረሻም ቶገንበርግ፣ ሳነን እና አልፓይን የተባሉ ከውጭ የመጡ ዝርያዎች አሉ፡፡
አቅራቢዋ:
ቶገንበርግን ጠቀሱ፡፡ የኬንያን የአየር ንብረት እንዲቋቋም የሚያስችሉት ምን ነገሮች አሉት?
ኮስግይ:
ቶገንበርግ ምንጩ ስዊዘርላንድ ነው፡፡ ኃይለኛ ነው፤ ምግቡንም ፈልጎ መብላት ጎበዝ ነው፡፡ ይህ ዝርያ የሚስማማው ቀዝቃዛ አካባቢ ነው፤ በደንብ ከተያዘ ግን ኬንያም ጥሩ ይኖራል፡፡
አቅራቢዋ:
ቶገንበርግ ከአገር በቀል ፍየሎች የተለየ አያያዝ ይፈልጋል?
ኮስጌይ:
ሁሉም ፍየሎች በተለይ ደግሞ የወተት ፍየሎች ከአመጋብ፣ እርቢ፣ በሽታና ተባይ ቁጥጥር፣ የውጭ ጥገኛ አካላት ቁጥጥር እና ከመኖርያ ቦታ እና ደህንነታቸው አንጻር እንክብካቤ ይፈልጋሉ፡፡

ቶገንበርጎች በደንብ ካተመገቡ ወተት አይሰጡም፡፡ ከበሽታ ነጻ መሆንም አለባቸው፤ ለረጅም ጊዜ ጸሃይ ላይ መቆየት የለባቸውም፡፡ ከአገር በቀል ፍየሎች አንጻርም በቀላሉ በሳንባ ምጭ ይጠቃሉ፡፡

ለቶገንበርጎች ኃይል ሰጭ ምግብ፣ ገንቢ ምግብ እና ማዕድንን አመጣጥኖ የያዘ ምግብ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ገምቢ ምግብ እንዲያገኙ ከአሳ ተረፈ ምርት የተዘጋጀ መኖ ወይም ጥራጥሬ ልትጠቀሙ ትችላላችሁ፡፡ በተጨማሪም በቂ ሳር ለምሳሌ ሙጃ ወይም የስኳር ድንች ቅጠልና ግንድ ማቅረብ ያስፈልጋችኋል፡፡

አቅራቢዋ:
ቶገንበርግን እና ዲቃላዎቹን የሚያጠቁ የተለመዱ በሽታዎች ምንድን ናቸው?
ኮስጌይ:
ፍየሎችን በጣም በተደጋጋሚ የሚጠያቃቸው ተላላፊ የፍየሎች የሳምባ በሽታ ነው፡፡ በወሊድ ጊዜ ወይም መስክ ላይ በሚቆዩበት ጊዜም ለመንጋጋ ቆልፍ ይጋለጣሉ፡፡

አቅራቢዋ:
እነዚህ በሽታዎች እንዴት ይታከማሉ?
ኮስጌይ:
እንደ ሳንባ ምች ላሉ በሽታዎች ህክምናው አስቀድሞ በክትባት መከላከል ነው፡፡ የእንስሳት ሐኪም ፍየሉ ቆስሎ በባክቴሪያ ቢመረቅዝ አንቲባዮቲክ (የፀረ-ተህዋሲያን መድሃኒት) ሊሰጠው ይችላል፡፡

ሌላው መታየት ያለበት ጉዳይ ደግሞ የፍየሎቹ ጎረኖ ነው፡፡ ጥሩ ጎረኖ አያያዝ ወሳኝ ነው፡፡ በፍየሎቹ ማደርያ ውስጥ ነፋስ መንፈስ የለበትም፡፡

አቅራቢዋ:
ሌላስ ስለፍየሎች ጎረኖ መታሰብ ያለበት ምን ጉዳይ ይኖራል?
ኮስጌይ:
ዋናው ነገር የሳንባ ምች እና ትላትልን ለመካላከል ፍየሎች አርጥብ ወለል ላይ እንዳይተኙ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡

የፍየሎቹ ጎረኖ ከጉልበት ትንሽ ዝቅ ያለ ከፍታ ከመሬት ሊኖረው ይገባል፡፡ ይሄ ፍየሎቹ በጠጣቸው እና ሽንታቸው ላይ እንዳይተኙ ያደርጋል፡፡ የጎረኖውን ወለል በጣውላ ርብራብ ሥሩ፣ የፍየሎቹ በጠጥ እና ሽንት ወደ መሬት እንዲወርድ በጣውላዎቹ መካከል የ1.3 ሳንቲሜትር ያክል ክፍተት መተዉ ያስፈልጋል፡፡

ጎረኖው ሁል ገዜ ንጹህ እና ደረቅ፣ አየርም የሚገባበት መሆኑን አረጋግጡ፡፡ ጣራው እንዳያፈስ እና መመገቢያ ገንዳቸውም ንጹህ እንዲሆን ተከታተሉ፡፡ በትላልቆቹ ፍየሎች እንዳይረጋገጡ ግልገሎችን ከትልቆቹ ለዩዋቸው፡፡

የሆድ ትላትል ሕክምና ያስፈልጋል፡፡ ሁሉም እናስሳት ከስርያ በፊት ከሆድ ትላትል ነጻ እንዲሆኑ ማድረግ ጥሩ ነው፤ ክበድ ፍየሎም ከመውለዳቸው በፊት የትላትል መድሃኒት ይሰጣቸው፡፡ ግልገሎች በሦስተኛ ወራቸው ጡት ጥለው ሌላ ምግብ መውሰድ ሲጀምሩ የትላትል መድሃኒት ይሰጣቸዋል፡፡ ክረምት ከመጀመሩ በፊትም የትላትል መድሃኒት መስጠት ጥሩ ነው፡፡

አቅራቢዋ:
አንድ አርሶ አደር ከፍየሎቹ ከፍተኛ ጥራት ያለው ወተት ለማግኘት ምን ማድረግ አለበት?
ኮስጌይ:
ተጨማሪ ወተት ለማግኘት አርሶ አደሮቹ ግልገሎቹን አንዳንድ ቀን እያዘለሉ ከምትታለበው ፍየል መለየት አለባቸው፡፡ ፍየሏ ወተት የምታዘጋጀው ለልጆቿ ስለሆነ እንደዚህ በማድረግ ወተት ማዘጋጀት እንዳታቆም ማድረግ ይቻላል፡፡

በተጨማሪ ወተቱ ፍየል ፍየል እንዳይሸት ወንዶቹን እና ሴቶቹን እንለያቸዋለን፡፡ ጠረኑ የሚመጣው ከወንዶቹ ነው፤ ወንዶቹ በተለይ በስርያ ወቅት ከባድ ጠረን ስላላቸው ያ ጠረን ወደ ወተቱ ይገባል፡፡ ጠረኑ በቀላሉ ተሰራጭቶ ወተቱ በቀላሉ ያነሳዋል፣ በዚያ የተነሳ ያን ወተት ሰዎች ላይፈልጉት ይችላሉ፡፡

አቅራቢው:
ለአነስተኛ ፍየል አርቢዎች የሚናገሩት የመጨረሻ ቃል ይኖረዋታል?
ኮስጌይ:
አሁን መሬት እንደልብ ስለማይገኝ እና መጠኑም እያነስ ስለሆነ ፍየል ማርባት በጣም እየታወቀ ነው፡፡ በከተማ አካባቢ የወተት ፍላጎት እያደገ ነው፣ ነገር ግን እንደ ላም ላሉ ትላልቅ እንስሳት የሚሆን በቂ ቦታ ግን የለም፡፡

ብዙ ሰዎችን ፍየል እንዲያረቡ እመክራሁለ፡፡ የቶገንበርግ ፍየል ለምሳሌ በቀን እስከ አምስት ሊትር ወተት ትሰጣለች፣ ወተቱም ጥሩ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ለእንስሶቻችሁ የሚገባውን እንክብካቤ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡

አቅራቢዋ:
በጣም አመሰግናለሁ፡፡ ፕሮፌሰር ኮስጌ በደረቅ አካባቢዎች ለሚኖሩ አርሶ አደሮች የወተት ፍየል ማርባት እንዴት ጥሩ ሃሳብ እንደሆነ እያስረዱን ነበር፡፡ አንድ ፍየል አርቢ እና ፍየል አዳቃይም አዳምጠናል፡፡

ዋና ዋና ነጥቦቹ የሚከተሉት ናቸው፡- እንስሶቻችሁን በደንብ መመገብ አለባችሁ፣ ጥሩ ጎረኖ መሥራት አለባችሁ፣ ጥሩ ንጽህና መጠበቅ አለባችሁ፣ ክትባት እና የትላትል መድሃኒት በየጊዜው በመጠቀም በሽታን እና ጥገኛ ሕዋሳትን መከላከል አለባችሁ፡፡ በተጨማሪም ጤነኛ ወንዶችን በመጠቀም ማዳቀል ያስፈልጋል፡፡ በመጨረሻም ጠቦቶቹን በሚገባ በጥንቃቄ አሳድጉ፡፡

Acknowledgements

Contributed by: Ms. Winnie Onyimbo, Trans World Radio, Nairobi, Kenya
Reviewed by: Julie Ojango, Scientist, Animal Breeding Strategies, International Livestock Research Institute, Nairobi, Kenya, and John G. Fitzsimons, Associate Professor, School of Environmental Design and Rural Development, Ontario Agricultural College, University of Guelph, Canada

Project undertaken with the financial support of the Government of Canada through the Department of Foreign Affairs, Trade and Development (DFATD)

Adapted to the Ethiopian context by Dereje Fekadu, Senior Researcher in Animal Nutrition
Holetta Agricultural Research Center, Ethiopian Institute of Agricultural Research, Hoiletta, Ethiopia

The translation of this resource was supported by the International Finance Corporation

Information sources

Interviews:
Teresia Kyalo, Dairy goat farmer in Mwingi, eastern Kenya
Joseph Mwangangi Mkonzo, Dairy breeder in Mwingi, eastern Kenya
McDonald Mnuve, Farmer’s coordinator in Mwingi.

Interviews conducted on February 9 and March 12, 2015

Further information:
• Ukilima Smart, undated. Dairy goat farming. http://www.ukulimasmart.co.ke/index.php/animal-husbandry/dairy-farming/241-dairy-goat-farming
• J.M.K. Ojango, C. Ahuya, A.M. Okeyo and J.E.O. Rege, 2010. The FARM-Africa dairy goat improvement project in Kenya: A case study. International Livestock Research Institute. http://agtr.ilri.cgiar.org/index.php?option=com_content&view=article&id=202&Itemid=239
• Carl Jansen and Kees van den Burg, 2004. Goat keeping in the tropics. Agromisa Foundation, fourth edition. http://publications.cta.int/media/publications/downloads/371_PDF.pdf (619 KB)
• Dr. Boniface K. Kaberia, Mr. Patrick Mutia and Mr. Camillus Ahuya, undated. Farmers dairy goat production handbook. FARM Africa. Downloadable at http://r4d.dfid.gov.uk/PDF/Outputs/Livestock/DairyGoat.pdf (18 KB)